Friday, 21 November 2014

መምጫውን የማያውቅ መድረሻውን ያጣል


ታሪክ ለሰው ልጅ ስሩና መሠረቱ ነው።ታሪኩንና መምጫውን የማያውቅ ህዝብ መድርሻውን የማያውቅና ራሱንም ለባርነት አሳልፎ የሰጠ ይሆናል፡፡ ለክብሩ ለእርሱነቱ ለህብረቱና ለነፃነቱ ፀንቶ መቆየት እና የጥንካሬውና ተሳስሮ የመዝለቂያው ሰንሰለት ታሪኩ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የአሜሪካ ባርያ ፈንጋዮች ትናንት በገፍ ከአፍሪካ በባርነት ያመጡዋቸው አፍሪካውያን አንድ ቀን በአንድ ቆመውና በህብረታቸው ጠንክረው ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት እንዳይነሱ ሀ ብለው የነጠቋቸው ማንነታቸውን፤ ታሪካቸውንና መገኛቸውን ነበር፡፡ እንደ እቅዳቸውም እነሆ ዛሬ አብዛኛው ጥቁር አሜሪካዊ እኔ ማን ነኝ? መምጫዬስ ከወደየት ነው? በሚሉና በመሳሰሉ ጥያቄዎች ተተብትቦ ለምላሹ ሲውተረተር መገኘቱ፤ እንዲሁም ዛሬም ከተገዢነት መንፈስ ራሱን አላቆ በሁለት እግሩ ለመቆም ሲታትር ይገኛል፡፡
ሌላው የኢጣልያ ወራሪን ሀይል ቅስም የሰበረውና በአለም አቀፍ ደረጃ ቅሌት ያከናነበው የአድዋ ጦርነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ቅሌት በደም አጥቦ ሀያልነቱን ለአለም ለማሳየት በሞከረበት ሁለተኛው ወረራ ወቅት ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ የአድዋ ጦርነት የመሩት የአፄ ሚንሊክ ሀውልትን ከጥልቅ ጉድጓድ መቅበር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ባጠቃላይ አንድ ህዝብ እንደ ህዝብና ሀገር ጠንክሮና በነፃነት ኮርቶ ለመኖር ብሎም ከትውልድ ትውልድ መሸጋገር መቻል ከማረጋገጫው አንዱ የትናንት ማንነቱና የመገኛ ታሪኩ መሆኑን ከላይ በምሳሌነት ያነሳናቸው ነጥቦች ያረጋግጣሉ፡፡
ታሪክ ለአንድ ህዝብ የማንነቱ መገኛ፤ የመገኛው ምንጩና መምጫውን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን የነገ መዳረሻውን የመመልከቻ መነፅርና ጠንክሮ የመንቀሳቀሻው ጉልበቱ ሆኖ የሚያገለግል ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አንድ ህዝብ ታሪኩ ከጠፋ ሊገጥመው የሚችለው ችግርና ፈተና እንዲህ በቀላሉ የሚገመት ያለመሆኑንና እንደ ህዝብ እንደ ሀገር ቀጣይነቱን በቀላሉ መፍትሄ ከማይገኝለት ፈተና ውስጥ ይከተዋል ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያችን ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ህልውናዋ አደጋ ላይ የወደቀበት መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ባለፉት 23 አመታት በዘረኞቹ የወያኔ ጉጅሌዎች እጅ ከወደቀችበት እለት ጀምሮ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆኑ የታሪካችንና የባህልችን ዋና ዋና እሴቶች ዋነኛ ኢላማ ሆነዋል፡፡ ይህንንም በተደጋጋሚና በግልፅ ከወያኔው መሪ እስከ ተራ ደጋፊው የሚወረወረው በትር ያረጋግጣል፡፡ ጉጅሌዎቹ የነፃነት ምልክት የሆነውንና በዕልፍ አዕላፋት ደም መሥዋዕትነት ፀንቶ የቆየውን ሰንደቅ ዓላማ በሶ መጠቅለያ ጨርቅ ከማድረግ ጀምረው ዛሬ በምሁራን ጥረትና በእያንዳንዱ ዜጋ ድጋፍ የተሰባሰቡት የታሪኮቻችን መዛግብት በጥንቃቄ ከተቀመጡበት (ቤተ-መዛግብት) እያወጡ ከማውደምና ለስኳር መጠቅለያነት እስከ መሸጥ ደርሰዋል፡፡
ታሪካዊ ገዳማት ፈርሰዋል፤ ታሪካዊ ቅርሶች ለባእዳን አልፈው ተሽጠዋል፤ የነፃነት ታሪካችን እየተደለዘ በወያኔያዊ ዘረኛ የፈጠራ ታሪክ መተካቱ ቀጥሏል፤ ታሪካዊ ጀግኖቻችንን ማዋረድና ማውገዝ የእለት ተእለት ስራቸው ሁኗል። ወ ያኔዎች ኢትዮጵያዊነት ቅዝት ሆኖባቸዋል፤ ስለዚህም ቀንደኛ ጠላታቸው አድርገው ፈርጀውታል፡፡ ይህ የዘረኝነትና የዘረፋ ስርዓታቸው ውሎ ማደር የሚረጋገጠው ኢትዮጵያዊነት መመታት ሲችል ብቻ ነው ብለውም በፅኑ ያምናሉ፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊነታችንን ሊያዳክም ብሎም ሊያጠፋ ይችላል ብለው የገመቱትን ሁሉ ከመፈፀም የማይመለሱት፡፡ ለዚህም ነው በስንት ጥረትና በብዙዎች ድካም ተሰባስቦና ተደራጅቶ የቆየውን የታሪክ መዛግብትና መፅሀፍት ከቤተ-መዘክር አውጥቶ በኪሎ ለመቸብቸብ የበቁት፡፡
ታዲያ ኢትዮጵዊ ነን የምንል ሁሉ ዘሬም እንደትናንቱ ይህን በማንነታችን ላይ የሚደረግ የጥፋት ዘመቻ ለማስቆም መነሳት ግድ ይለናል። እየተፈፀመ ያለው የታሪክ ማጥፋት ዘመቻ ለነፃነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ከምናደርገው ትግል እኩል ጎን ለጎን ለታሪካዊ ቅርሶቻችንና መዛግብቶቻችን ከጥፋት የመከላከልና የማዳን ስራ የመስራት የትውልድ ኃላፊነት አለብን፡፡ አለበለዚያ መምጫውን የማያውቅ መድረሻውን አያውቅምና የምናደርገው የነፃነት ትግል የተሟላ ውጤት ማስገኘቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡ ተገንዝበንም ወያኔን በቃህ ልንለው ይገባል፡፡
በመጨረሻም ጂኦርጅ ኦርዌል ‘The most effective way to destroy people is to deny and obliterate their understanding of their own history” ብሎ ጽፎ ነበር። ህወሃቶች የዚህ ፍልስፍና ተከታዮች መሆንን በመምረጥ ለራሳቸው ውረደትን ፤ለአገራቸውም ውደቀትን ተመኝተዋል። ኢትዮጵያችን መንግስት በጠላትነት ተሰልፎ ከአገራችን ከህዝብና ለአገሪቷ እሴቶች ጋር የሚዋጋበት አገር ሁናለች። ህወሃት በብዙ መልኩ ሲታይ የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት መሆንን የመረጠ ቡድን ነው። የህወሃት በኢትዮጵያ ላይ በጠላትነት መቆሙ ያስቆጣቸው ወጣቶች እምቢ ለአገሬ፤ እምቢ ለክብሬ ብለው ተነስተው ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ተሠማርተዋል።ግዜው ከእነዚህ ወጣቶች ጎን የምንቆምበትም ጭምር ነውና ተነሱና ለነፃነታችንና ለአገራችን ዝና ለህዝባችን ክብር አብረን ታግለን ጠላትን የመረጠውን ህወሃትን እናስወግድ እና ንፁህ አገር እንፍጠር።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

Sunday, 16 November 2014

እንግሊዝ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በተመለከተ ደብዳቤ መጻፏን ወያኔ አረጋገጠ


የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በተመለከተ ለወያኔዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ደብዳቤ መጻፋቸውንና ወያኔም አቋሙን ግልጽ ማድረጓን የወያኔዉ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን ተናገረ። ሬድዋን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባለፈዉ ማክሰኞ በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ዴቪድ ካሜሩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደብዳቤ መጻፋቸውን የተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች መዘገባቸውን ሰምቻለሁ ካለ በኋለ “ለምን ጻፉ ማለት አይቻልም፤ ጥያቄዉ መሆን ያለበት ምን መለሳችሁ ነው፤” በማለት የተለመደ የማጭበርበሪያ ቃላት ደርድሯል።
የተለያዩ የእንግሊዝ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ላይ ቀደም ሲል የተፈረደውን የሞት ቅጣት እንዳትተገብር እንዲሁም ኢትዮጵያ ለሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ አቶ አንዳርጋቸውን የመጐብኘት ቋሚ ፈቃድ እንዲሰጥ በደብዳቤያቸው መጠየቃቸውንም ሬድዋን ሁሴን ተናግሯል።
ለዴቪድ ካሜሮን ደብዳቤ መልስ መሰጠቱን ያረጋገጠዉ ሬድዋን፣ “በተጨባጭ የተፈረደበትን ግለሰብ ነው የያዝነው፤ እንዲህ ብታደርጉት ባታደርጉት ብሎ ማንሳት ይቻላል። ምክንያቱም እነሱም የሚመለከታቸው በመሆኑ። በዚህ ምክንያት ግን የእኛ መልስ በራሳችን ሕግ መሠረት ዓለም አቀፍ ሕጉም በሚለው መሠረት የምናደርገውን እናደርጋለን፤” ብሏል። ኢትዮጵያ የምትተገብረው የራሷን ሕግ መሆኑን የገለጹት አቶ ሬድዋን፣ “ከነጭም ከጥቁርም የሚመጣን ደብዳቤ ተንተርሰን ምንም አንተገብርም፤” ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ደብዳቤ ጽፈው፣ በኢትዮጵያ በኩልም መልስ ተስጥቷል ያለዉ ሬድዋን ሁሴን በደብዳቤው የቀረቡ ጥያቄዎች ቅሬታ እንዳላስነሱ ሁሉ መልሱም ቅሬታ አያስነሳም የሚል ተስፋ በኢትዮጵያ በኩል መኖሩን ተናግረዋል።
“እነሱ ዜጋዬ ነው ብለዋል፤ የእነሱ ዜጋ እንደ ቼ ጉቬራ ነፃ አውጣ ተብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተላከም። የእነሱ ዜጋ ከነበረ የእንግሊዝን ዴሞክራሲ ይበልጥ ለመጨመር መታገል ይችል ነበር። ነገር ግን በኢትዮጵያ በቅጥር ነብሰ ገዳይነት ካልተሰማራ በስተቀር ሌላ ሚና አልነበረውም፤” ብለዋል።

የሰንደቅ አላማችን ጠላት ወያኔና ወያኔ ብቻ ነዉ!



ሰንደቅ አላማ ለአንድ አገር ህዝብ የኩራት፤ የአልበገር ባይነት፤ የአንድነትና የታሪክ ተከታታይነት ምልክት ነዉ። ሰንደቅ አላማ በአንድ በኩል የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ ክወዲሁ እያሳየን እየዟችሁ የሚለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በምናብ ወደኋላ እየወሰደን የድልና የመስዋዕትነት ታሪላችንን የሚያስታዉሰን የነጻነት፤ የሠላምና የብሩህ ተስፋ ማህደር ነዉ። የአገራቸን የኢትዮጵያ አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ አላማ ትናንትናና ከትናንት ወዲያ በተስፋፊዎች አለመደፈራችንን ብቻ ሳይሆን ዛሬም ዘረኞች የጫኑብንን የመከራ ቀንበር በቆራጥነት ሰብረን ነገና ከነገ ወዲያ የነፃነት አየር እንድንተነፍስ አስረግጦ የሚነግረን የአንድነታችን፤ የተገጋድሏችንና የድላችን ልዩ ምልክት ነዉ። አንድን ኢትዮጵያዊ ሰንደቅ አላማ ላንተ ምንህ ነዉ ብለን ብንጠይቀዉ ጥያቄዉን ዕድሜህ ስንት ነዉ ተብሎ እንደሚጠየቅ አንድና ሁለት ቃል ብቻ ተናግሮ አይመልስም። ሰንደቅ አላማም በአንድና በሁለት ቃላት ምንነቱ የሚገለጽ ተራ ቃል አይደለም። ኢትዮጵያዉያን ተማሩ አልተማሩ፤ ደሃ ሆኑ ኃብታም ፤ወንጀለኛ ሆኑ ወይም ሠላማዊ ለአገራቸዉ ሰንደቅ አላማ የተለየ ቦታ አላቸዉ። ሰዎች የአገራቸዉን ሰንደቅ አላማ የሚወዱትና ለሰንደቅ አላማዉ በክብር መዉለብለብ የህይወት መስዋዕትነት የሚከፍሉት ስለታዘዙ ወይም ስለ ሰንደቅ አላማዉ ተነግሯቸዉ አይደለም። በእርግጥም የሰንደቅ አላማ ክብርና የአገር ፍቅር ለሰዎች ሰንደቅ አላማዉን አክብሩ፤ አገራችሁን አፍቅሩ እየተባለ የሚነገር ነገር አይደለም። አገርንና ወገንን ማክበርና መዉደድ ሰንደቅ አላማን ከማክበርና ከማፍቀር ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነዉ።የሰንደቅ አላማ ልዪ ክብርና የአገር ፍቅር ሰዎች ተወልደዉ ከሚያድጉበት ማህበረሰብ፤ ከቤተሰብ፤ ከጎረቤትና ከጓደኛ እንደ ምግብና እንደ ዉኃ እየበሉና እየጠጡ የሚያገኙት የሰዉነትና የዜግነት መገለጫ ታላቅ እሴት ነዉ።
ለዚህም ነዉ የማንም አገር ዜጋ አገሩ ዉስጥ ቢኖር ወይም ካገሩ ዉጭ፤ ቢታሰር ባይታሰር፤ ሀብታም ቢሆን ወይም ደሃ፤ የኔ ነዉ የሚለዉን የእናት አገሩን ሰንደቅ አላማ በፍጹም የማይረሳዉ። ከአገራቸዉ ዉጭ የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ በተለይም ኢትዮጵያዉያን በተለያዩ ምክንያቶች የሚኖሩባቸዉን አገር ዜግነት ቢወስዱ እንኳን ሰንደቅ አላማቸዉን ባዩና ባስታወሱ ቁጥር የሚሰማቸዉ አገራዊ ስሜት እጅግ በጣም ከፍተኛ ነዉ – እንዲያዉም ከአገራቸዉ ተሰድደዉም ሆነ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከአገራቸዉ ዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ሰንደቅ አላማቸዉን ባዩ ቁጥር የአገራቸዉ፤ የወንዛቸዉ ፤ ተወልደዉ ያደጉበት መንደርና የልጅነት ትዝታቸዉ ባአይናቸዉ ላይ እየመጣ ዕንባ በዕንባ ይተናነቃሉ። ሰንደቅ አላማ ለአንድ አገር ህዝብ አንድ ነገር ነዉ፤ ብዙ ነገር ነዉ፤ ሁሉም ነገር ነዉ። ሰንደቅ አላማ ህዝብን ያስተባብራል፤ ያከባብራል፤ ያዋድዳል፤ መስዋዕትነትን፤ ፍቅርንና ብልፅግናን ያመለክታል።
ዛሬ የሰንደቅ አላማችንን ጉዳይ አቢይ የመወያያ አርዕት አድርገን የወሰድነዉ አለምክንያት አይደለም። በአገር ጥላቻቸዉና በስንደቅ አላማ ንቀታቸዉ የሚታወቁት የወያኔ ዘረኞች “የአብዬን ወደ እምዩ” እንዲሉ ሰንደቅ አላማቸዉ ተዋርዶ ከሚያዪ የቁም ሞታቸዉን የሚመር ትን ዉድ የኢትዮጵያ ልጆች ባንዲራዉን አዋረዱበለዉ መናገራቸዉን ስለማን ነዉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ አገሮች ተስማምተዉ የሚያከብሩት አለም አቀፉ የሰንደቅ አላማ አያያዝ ፕሮቶኮል በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሁሉም አገሮች ሰንደቅ አላማ በእኩል ደረጃ መቀመጥና መሰቀል አለበት፤ አንድ ላይ መሰቀልና አንድ ላይ መዉረድ አለበት ይላል። ይህንን ፕሮቶኮል ረስቶና ሰንደቅ አላማችንን ንቆ በአለም አቀፍ መድረክ ላይ ከሌሎች አገሮች መሪዎች ጋር የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እንደ አለባሌ ዕቃ ዘቅዝቆ ይዞ ያዋረደዉ ወያኔዎች “ታላቁ መሪ” ብለዉ የሚጠሩት ነገር ግን የለየለት የአገርና የህዝብ ጠላት የሆነዉ ዘረኛዉ መለስ ዜናዊ ነዉ። የህወሓትን ባንዲራ በየቦታዉ እየሰቀሉ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ተራ ጨርቅ ነዉ ብለዉ የሸቀጥ መጠቅለያ ያደረጉትም መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ ናቸዉ። ዛሬ ደማቅ ሰንደቅ አላማዉን አስመልክቶ በወያኔና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ያለዉ ትልቅ ልዩነት ትክክለኛዉና ህዝብ የኔ ነዉ ብሎ የተቀበለዉ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የትኛዉ ነዉ የሚለዉ ጥያቄ ላይ ነዉ አንጂ ባንዲራዉን ማክበር አለማክበር ወይም ማዋረድ ላይ አይደለም።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የእናት አገራችንን የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ታሪካዊ ተከታታይነትና ዘለዓለማዊነት አጉልቶ የሚያሳየን ከሁላችንም በላይ የገዘፈ ግዙፍ አርማ ነዉ፤ ይህ ማለት ደግሞ ሰንደቅ አላማችን ያቻትና ብሎ እንደሚያሳየን አገር አንደ ኢትዮጵያ ሙሉ ህልዉና ያለዉ ህያዉ አካል ነዉ ማለት ነዉ። ሰንደቅ አላማችንን የምንወደዉና የምናከብረዉም ህያዉ አገራችንን የሚወክል ህያዉ አካል በመሆኑ ነዉ። መለስ ዜናዊንና ስብሀት ነጋን የመሳሰሉ በጣት የሚቆጠሩ የትዉልድ ጭንጋፎች ለራሳቸዉ አገር ሰንደቅ አላማ ደንታ ላይኖራቸዉ ይችላል። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳለ ግን የህልዉናዉና የአንድንቱ መገለጫ የሆነዉን ሰንደቅ አላማ አይንቅም ወይም አያዋርድም፤ አንድ ህዝብ ባንዲራዉን የማይቀበልና የማያከብር ከሆነ ባንዲራዉ አይወክለዉም ማለት ነዉ፡ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዛሬ ያለዉ እዉነታም ይሄዉ ነዉ፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔ ባዕድ አካል የለጠፈበትን ባንዲራ የኔ ነዉ ብሎ አልተቀበለዉም ወይም ባንዲራዉ ይወክለኛል ብሎ አያምንም።
ዘርዓይ ደረስ በ1937 ዓም ሮም ዉስጥ የፋሺስት ጣሊያኖችን ጭንቅላት በገዛ አገራቸዉ እንደ ቅጠል እየጨረገደ ከጣለ በኋላ በጣሊያኖች ጥይት ቆስሎ ሲያዝ የተናገዉ የመጨረሻ ቃል ይህ የጣሊያኖች ባንዲራ ይዉረድና የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ይሰቀል የሚል የጀግንነትና የአገር ፍቅር ቃል ነበር። ጀግናዉ አብዲሳ አጋ በጣሊያን በረሃዎች ጣሊያኖችን እያሳደደ ሲገድል የኢትዮጵያ ባንዲራ ከአጠገቡ አልተለየችም። በቀዳማዊ ኃ/ስላሤና በደርግ ዘመነ መንግስት ተማሪዎች ጧት ወደ ክፍል ከመግባታቸዉ በፊት ተሰልፈዉ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በክብር ይሰቅሉ ነበር፤ ማታም ወደ ቤታቸዉ ከመሄዳቸዉ በፊት ጧት በክብር የሰቀሉትን ባንዲራ በክብር አዉርደዉ ነበር ወደየቤታቸዉ የሚሄዱት። ዛሬ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ጨርቅ ነዉ ብለዉ የተሳደቡና በዚህ ሰንደቅ አላማ ከገበያ የገዙትን ሸቀጥ እየጠቀለሉ አስራ ሰባት አመት የከረሙ ምናምንቴዎች ናቸዉ በሰንደቅ አላማ ክብርና በአገር ፍቅር ታንጾ ያደገዉን ኢትዮጵያዊ ሰንደቅ አላማዉን አዋረደ እያሉ የአዞ እምባ የሚያነቡት።
ሰንደቅ አላማ በዜጎች ልብ ዉስጥ አንደ እሳት የሚቀጣጠል የአገር፤ የህዝብና የዜግነት መገለጫ የሆነ ታላቅ አርማ ነዉ። ይህ አርማ ደግሞ ከእኛነታችንና ከህልዉናችን ጋር የተጣበቀ አርማ ነዉና መንግስት በተለዋወጠ ቁጥር አይለዋወጥም። ዛሬ ወያኔ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የገባዉ የማይታረቅ ቅራኔም የሚመነጨዉ ከዚሁ ከወያኔ ግራ የተጋባ እዉነታ ነዉ። የዚህ ዘመን ትዉልድም ሆነ ለዚህ ዘመን ትዉልድ አገርና ሰንደቅ አላማ አስረክቦ ያለፈዉ የቀድሞዉ ትዉልድ ሰንደቅ አላማዬ ብሎ የሚጠራዉና ወያኔ የኢትዮጵያ ባንዲራ እያለ የሚጠራዉ ነገር የተለያዩ ናቸዉ።
ባለፉት 75 አመታት አራት ኪሎ ቤ/መንግስትን የተቆጣጠሩት ሦስት ኃይሎች ማለትም የቀኃስ፤ የደርግና የወያኔ አገዛዞች ሁሉም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከራሳቸዉ ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል። በንጉሡና በደርግ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የይሁዳ አንበሳና የወታደራዊዉ መንግስት አርማ ነበረበት፤ ሆኖም እነዚህ ሁለት አርማዎች ያረፈበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በቤተመንግስትና ንጉሡና ፕሬዚዳንቱ በሚጓዙባቸዉ ኦቶሞቢሎች ላይ እንጂ ሌላ ቦታ አይታዩም ነበር። በመላዉ አገሪቱ በየቀኑ ጧት እየወጣ ማታ ሲመሽ የሚወርደዉና በየግለሰቦች ቤት የሚገኛዉ ሌጣዉ አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀዩ ሰንደቅ አላማ ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብም ሰንደቅ አላማዬ ነዉ ብሎ የሚያምነዉና የሚቀበለዉ ይህንኑ ምንም አይነት ባዕድ አካላ የሌለበትን አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ አላማ ነዉ።
ወያኔዎች ጫካ ዉስጥ ሆነዉ የትጥቅ ትግል በሚያካሄዱበት ወቅት ያነገቡትና ነጻ አወጣን ባሉበት ቦታ ሁሉ የሰቀሉት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሳይሆን የህወሓትን ባንዲራ ነበር። ከብዙ መረጃዎች እንደተረዳነዉ ወያኔዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አንደ ተራ ጨርቅ ቆጥረዉ ዕቃ መጠቅለያ አድርገዉት ነበር፤ ይህ ደግሞ የለየለት የጥላቻና የንቀት ምልክት ነዉ።
በአርግጥም ዋና ዋናዎቹ የወያኔ መሪዎች እነ ነመለስ ዜናዊና እነ ስብሐት ነጋ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ህዝብ ይጠሉ ስለነበር ለነሱ ትልቁ ቁም ነገር ህወሐትና የዘረኝነት ምልክት የሆነዉ የህወሓት ባንዲራ ነዉ እንጂ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ አልነበረም። ይህ ፀረ ህዝብና ፀረ አገር ባህሪያቸዉ ደግሞ ጫካ ዉስጥ ብቻ ተወስኖ የቆየ ባህሪ ሳይሆን አዲስ አበባ ገብተዉ ክህዝብ ጋር ሲቀላቀሉም በግልጽ የታየና ምን ግዜም ሊደበቅ የማይችል ባህሪይ ነዉ። የወያኔዉ ቁንጮ መለስ ዜናዊ እኛ ኢትዮጵያዉያን የምናከብዉንና የምንወደዉን ሰንደቅ አላማ “ጨርቅ” ብሎ መጥራቱ አዲስ የጀመረዉ ነገር ሳይሆን ከጫካ ይዞት የመጣዉ የተለመደ አባባል ነዉ። መለስ ዜናዊ ይህንን ጸያፍ ድፍረቱንና ፀረ ሰንደቅ አላማነቱን ለማረሳሳት የባንዲራ ቀን ብሎ ቢያዉጅም የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ልጆቹ፤ አባቶቹ፤ አያቶቹና ቅድም አያቶቹ የተሰዉለት ሰንደቅ አላማ በአለባሌ ሰዉ አንደበት “ጨርቅ” ተብሎ የተጠራበትን ቀን ምን ግዜም አይረሳም።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ የወያኔ ዘረኞች ኢትዮጵያዉያንን በተለይም በዉጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ባንዲራቸዉን አያከብሩም ወይም ባንዲራዉን አዋረዱ እያሉ መክስስ ጀምረዋል። በነገራችን ላይ ከወያኔዎችና ከጥቂት ሆዳም ተከታዮቻቸዉ ዉጭ የኢትዮጵያ ህዝብ አገር ዉስጥም በዉጭ አገሮችም በሰንደቅ አላማዉ ላይ ያለዉ አቋም ተመሳሳይ ነዉ። ወያኔ ሰንደቅ አላማዉ ላይ ባዕድ አካል ለጥፎ ከዛሬ ጀምሮ ሰንደቅ አላማችሁ ይህ ነዉ ብሎ አዋጅ ሲያወጣ አዋጁን የሰማለት አንድም ሰዉ አልነበረም። እንዲያዉም ህዘብ ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጣ፤ ሰርግ ሲደግስ፤ ኳስ ጨዋታ ሲሄድና በተለያዪ ቦታዎች ደስታዉንና ኃዘኑን ሲገልጽ አንግቦ የሚወጣዉ የወያኔን ባንዲራ ሳይሆን አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀዩን ሰንደቅ አላማ ነበር። ወያኔ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ የቀየረዉ በጠመንጃ ሀይል እንደሆነ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን የማይወደዉንና በሀይል የተጫነበትን ባንዲራ ተቀብሎ እንዲኖር ያደረገዉም በጠመንጃ ሀይል ነዉ።
ለመሆኑ እነሱ እራሳቸዉ የለየላቸዉ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ጠላት የሆኑት የወያኔ መሪዎች በዉጭ አገሮች የሚኖሩና አክርረዉ የሚቃወሟቸዉን የኢትዮጵያ ልጆች ባንዲራዉን አዋረዱ እያሉ ተደጋጋሚ ክስ የሚያሰሙት ለምንድነዉ? አንዳንድ ከህልዉናቸዉ ይልቅ ለማይጠረቃዉ ሆዳቸዉ ያደሩ ደካማ ግለሰቦችስ ይህንን የወያኔ መሠረተ ቢስ ክስ እየሰሙ አንደ ገደል ማሚቶ ደግመዉ ደጋግመዉ የሚያስተጋቡት ለምንድነዉ? አገራችን ኢትዮጵያ ሁለት የተለያዩ ባንዲራዎች ሊኖራት እንደማይችል ሁላችንም እናዉቃለን። ለመሆኑ ይህ እኛ ሰንደቅ አላማ እነሱ ባንዲራ እያልን የምንጠራዉ ነገር አንድና ተመሳሳይ ነዉ? ወያኔና በየቦታዉ ያስቀመጣቸዉ የገደል ማሚቶዎች ከሁሉም ነገር አስቀድመዉ መመለስ ያለባቸዉ ይህንን ጥያቄ ነዉ። እኛ ኢትዮጵያዉያን ከህጻንነታችን ጀምሮ የኛ ነዉ እያልን ያሳደገንን፤ የመራንን፤ አቅጣጫ ያሳየንነና በተለይ በልጅነታችን ት/ቤት እያለን ጧት በክብር ሰቅለን ማታ ላይ በክብር እያወርድን በክብር እናስቀምጥ የነበረዉን አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ አላማችንን ማክበርና መዉደድ ብቻ ሳይሆን ለዚህ ሰንደቅ አላማ ዘለዓለማዊነት አንድ ህይወታችንን እንሰጣለን። ሰንደቅ አላማዉን የማያከብር ህዝብ የለም፤ እኛም ኢትዮጵያዉያን ሰንደቅ አላማችንን እንወዳለን፤ እናከብራለንም፤ የምንወደዉና የምናከብረዉ ሰንደቅ አላማ ግን ባዕድ አካል የተለጠፈበትን የወያኔን ባንዲራ ሳይሆን የነፃነታችን፤ የእንድነታችን፤ የሰላማችንና የመዋዕትነታችን ምልክት የሆነዉን አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀዩን ሰንደቅ አላማ ነዉ። ይህንን ሰንደቅ አላማ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳንሆን ይህንን የጥቁር ህዝብ የነጻነትና የመስዋዕትነት ታሪክ ምልክት የሆነ ደማቅ ሰንደቅ አላማ አያሌ አፍሪካዉያንም ያከብሩታል። ለምሳሌ የስምንት የአፍሪካ አገሮች ባንዲራ አቀማመጡ ይለያያል አንጂ ቀለሙ አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ነዉ፤ ከዚህ በተጨማሪ የሌሎች 23 አፍሪካ አገሮች ባንዲራ ደግሞ ቀዩና አረንጓዴዉ ቀለም አለበት። ይህ ሁሉ የሚያሳየን ሰንደቅ አላማችን የፓን አፍሪካ ባንዲራ እየተባለ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችም የሚከበርና የብዙ አፍሪካ አገሮች ሰንደቅ አላማ መሰረት መሆኑን ነዉ።
የወያኔ ዘረኞች ኢትዮጵያ ዉስጥ የነበሩትንና በዉጭ አገሮች የሚገኙ አማራጭ የመረጃ ምንጮች ሁሉ ጥርቅም አድርገዉ ዘግተዉ እንደቤት ዉስጥ ዕቃቸዉ በሚቆጣጠሩት ቴሌቪዥን፤ ሬዲዮና ጋዜጣ “በሬ ወለደ” አይነት ዉሸታቸዉን ጧትና ማታ በተደጋጋሚ አየተናገሩ ለግዜዉም ቢሆን ህዝብን ማደናገር ይችሉ ይሆናል። ሰንደቅ አላማዉን የሚወደዉንና የሚያከብረዉን ኢትዮጵያዊም እነሱን ስለተቃወመ ብቻ ባንዲራዉን አዋረደ እያሉ ህዝብን ሊያታልሉ አንዳንድ ወደ ገባዎችንና ጥቂት የዋሆችን ሊያሳምኑ ይችሉ ይሆናል። ሆኖም የኢትዮጵያን ህዝብ እንወዳለን ፤ ለኢትዮጵያ አንድነት እንቆማለን፤ የዚህ አንድነት ምልክት የሆነዉን ሰንደቅ አላማም እናከብራለን አያሉ ታቦት ተሸክመዉ ቢምሉም የሚያምናቸዉ ቀርቶ ከጉዳይ ቆጥሮ የሚሰማቸዉ አንድም ዜጋ የለም። የወያኔ ዘረኞችና ቡችሎቻቸዉ የሚባቸዉ ቢሆን ኖሮ ዉስጣችን ያለዉን ከፍተኛ የአገር፤ የወገን፤ የባንዲራና የሉዓላዊነት ስሜት ደግመን ደጋግመን እንነግራቸዉ ነበር፡ ሀኖም እነሱን ከማስወገድ ጀምሮ አገራችንን እስከማረጋጋት ድረስ ብዙ አስቸኳይ የሆነ አገራዊ አደራና አገራዊ ስራ ይጠብቀናልና ለዛሬዉ እዚህ ላይ እናብቃ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ያሸንፋል!

Saturday, 15 November 2014

ጊዜው የሕዝባዊ እምቢተኝነት ነው!!!



በአሁኑ ወቅት በአገራችን በከተሞችና በገጠሮች እየታዩ ያሉ ምልክቶችን በጥንቃቄ የመረመረ ማንኛውም ሰው የሚከተሉትን መታዘቡ አይቀርም።
በአንድ በኩል፣ ወያኔ የተወገደባት፣ ፍትህ የሰፈነባትና የበለፀገች ኢትዮጵያ እውን ሆና የማየት ተስፋችን እየለመለመ ነው። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ዉስጥ ለረጂም ዓመታት በሕዝብ ላይ ሰፍኖ የነበረው የፍርሀት ደመና እየገለጠ በመሆኑ ተዘግተው የቆዩ አንደበቶች መናገርና “ይኸ ሁሉ ግፍ ለምን?” ብለው መጠየቅ ጀምረዋል። ይህንን መነቃቃት በአስተሳሰብም፣ በተግባርም፣ በኪነጥበብም እያየነው ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች ለውጥ በአገራችን ሊመጣ እንደሚችል ከማመን አልፎ ራሳቸውን በለውጥ አምጭ ኃይልነት መመልከት ጀምረዋል። በርካታ ወጣቶች ወያኔን በትጥቅ ለመገዳደር የወሰኑ ወገኖቻችንን እየተቀላቀሉ በዚህም ምክንያት ጉልበታቸውን እያፈረጠሙ ነው። የለውጡ እርሾ ከሲቪሉ አልፎ በመከላከያ ሠራዊቱ እና በኢሕአዴግ ድርጅቶች ውስጥም እየተብሰለሰለ ነው። የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፣ ህወሓት ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚጠቀምበት ኃይል መሆኑ እያበቃ በአንፃሩ የትግሉ አጋር የሚሆንባቸው ሁኔታዎች እየታዩ ነው። በሁሉም የሠራዊቱ ክፍሎች ጉምጉምታው ወደ ጩኸት እየተቀየረ በመሆኑ ሠራዊቱ በአለቆቹ ላይ የሚነሳበት ጊዜ እሩቅ አይደለም። በተለያዩ ምክንያቶች ህወሓትን ወይም ህወሓት የፈጠራቸውን ድርጅቶች የተጠጉ በአጠቃላይ ኢሕአዴግ በሚባለው ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንም “ለመሆኑ ማንን ነው እያገለገልን ያለነው?” ብለው በመጠየቅ ላይ ናቸው። በዚህም ምክንያት ወያኔ ውስጡ እየተረበሸ ነው። ከኢትዮጵያም ውጭ በሚገኘው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ያለው ቁጣና ዝግጁነት ከወትሮው እጅግ የላቀ ነው። በአጭሩ፣ በሁሉም አቅጣጫ፣ ደረጃ በደረጃ የሕዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
በአንፃሩ ደግሞ፣ የጨለማ ንጉሥ የሆነው ወያኔ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ወደ ፍርሀት ቆፈን ለመመለስ እስሩን ከመቸውም በላይ ያጧጧፈበት ጊዜ ነው። በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአፋር በሶማሊ … በመላው ኢትዮጵያ ብሩህ ራዕይ የሰነቁ ወጣቶችና አዛውንት ታድነው እየታሰሩ ናቸው። የወያኔ እስር ቤቶች በአርቆ አስተዋይ ዜጎቻችን ተሞልተዋል። ወትሮም ከፍተኛ የነበረው ስደት ብሶበታል፤ ለእውነት በጽናት የቆሙ ጋዜጠኞች ወይ ታስረው፣ አልያም ተሰደው አልቀዋል። የወያኔ የግዴታ ስልጠና አገሩን እያመሰው ነው። የኢትዮጵያዊያን ኑሮ በእጦቶች የታጀበ ሆኗል። የነፃነት እጦት፣ የፍትህ እጦት፣ የመብራት እጦት፣ የስኳር እጦት፣ የዘይት እጦት፣ የታክሲ እጦት፣ የመኖሪያ ቤት እጦት፣ እጦት፣ …. እጦት።
እነዚህ ሁለት ተፃራሪ እውነታዎች ሁለት ተፃራሪ ኃይሎች ለወሳኝ ፍልሚያ ፊት ለፊት መፋጠጣቸዉን በግልጽ ያሳያሉ። ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃነትና ባርነት፣ ፍትህና ጭቆና፣ ደስታና ሀዘን፣ ተስፋና ተስፋ መቁረጥ፣ ብልጽግናና ድህነት፣ እውቀትና ድንቁርና፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ለወሳኝ ግጥሚያ ተፋጠዋል። ይህ ፍጥጫ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታን በመወሰን ረገድ አቢይ ሚና የሚኖረው ወሳኙ ግጥሚያ – ሕዝባዊ እምቢተኝነት – መጀመሩን አብሳሪ ነው። የነፃነት፣ የፍትህ፣ የተስፋ፣ የብልጽግና፣ የእውቀትና የብርሃን ወገኖች ነን የምንል ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ይህንን ፍልሚያ በድል መወጣት ግዴታችን ነው።
ወያኔ ታጋዮችን ቢያስር ትግሉን አያስርም። በእጦት ኑሮዓችን በማመሰቃቀል በድህነት ሊያንበረክከን ቢሻም፣ በፍጹም አንበረከክለትም። በተዘረፈ የድሆች ድካም ህንፃዎችን ቢገነቡም የራስ ባልሆነ ጌጥ አንኮራም። የወያኔ የሆነ የኛ አይደለም፤ የእነሱ መክበር የኛ መክበር አይደለም። ወያኔ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ገዢና ተገዢ፤ በዳይና ተበዳይ፣ ገፊና ተገፊ ናቸው።
ተበዳይና ተገፊ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረኞች፣ ሙሰኞችና ከፋፋዮች የህወሓት ባለሥልጣኖቻቸውና ሎሌዎቻቸው ላይ ይነሳሉ። የተጀመረው ሕዝባዊ እምቢተኝነት አመቺ በሆኑ መንገዶች ሁሉ ይጧጧፋል።
የወያኔ ትዕዛዛትን መሻር፤ በሥራ ላይ መለገም፤ ግብር አለመክፈል፤ አድማ መምታት፤ የወያኔ ካድሬዎችን ማግለልና ማዋረድ፤ የነፃነት ኃይሎችን መደገፍ፤ የፓሊስና የጦር ሠራዊት አባላትን ማቅረብ እና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እነሱም የትግሉ አካል እንዲሆኑ ማበረታታት፤ ህሊና ያላቸው የኢሕአዴግ አባላት የሕዝቡን ትግል እንዲያግዙ ማበረታታት … – እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ በርካታ የትግል ስልቶች ከአሁን ጀምሮ በተከታታይ በሥራ ላይ መዋል ይኖርባቸዋል። የወያኔን የጭቆና ምሽግ ከውስጥ መሸርሸር፤ ከውጭ መደርመስ ይኖርበታል። የመሸርሸርና የመደርመስ ሥራዎች ተደጋግፈው እንዲሄዱ ማድረግ ይገባል። ጊዜው የእምቢተኝነት ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የነፃነት ንቅናቄ የኢትዮጵያ ሕዝብ አጠገቡ ባሉት መሪዎቹ አስተባባሪነት በአንድነት እንዲነሳ ጥሪ ያቀርባል፤ በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ሁለገብ ትግል በጽናት እንዲደግፉ ያሳስባል። ይህንን ትግል በድል መወጣት ግዴታችን ነው፤ እንወጣዋለንም!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Monday, 10 November 2014

የህወሃቱን ፖለቲካ የአዋጁን በጀሮ!


ህወሃት በተፈጥሮው የፖለቲካ ብዙህነት ወይም ብዝሃነትን ማቻቻል የሚባል ነገር አያውቅም። ሌላው ቀርቶ በራሱ በድርጅቱ ውስጥ የሚነሱ የተለዩ ሃሳቦችን ሁሉ እንደጠላት ሃሳብ ፈርጆ ሰዎችን ደብዛቸውን ማጥፋት የተለመደ የህወሃት አሰራር ነው። ይህን የህወሃት ባህርይ በቅጡ ለመረዳት በቅርቡ የቀድሞው የህወሃት አመራር አባል የነበረው አቶ ገብሩ አስራት የጻፈው መጽሃፍ ጥቂት ገጾች በማየት መረዳት ይቻላል። ተቃዋሚ ፓርቲ ሰላማዊም ሆነ አልሆነ በህወሃት እንደጠላት ነው የሚቆጠረው።
ሰሞኑን ከትግራይ የህዝብና የመንግስት ግንኙነት ቢሮ ከሚባለው መስሪያ ቤት በትግረኛ ተጽፎ ለአባለት በሚስጥር የተሰራጨ ደብዳቤ ማንኛውምንም ተቃዋሚና ከህወሃት ውጭ የሚያስብና ህወሃትን የማይከተል ሁሉ “ፀላኢቲ” ጠላቶች ሲል ይፈርጃል። በዚህ ባለ 5 ገጽ ደብዳቤ ውስጥ እነዚህን “ፀላኢቲ” እንዴት እንደሚያሳድዱ፣ እንዴት እንደሚያዋክቡና እንደሚያጠፉ የሚመክር መመሪያ የሚሰጡ ሃሳቦች ተቀምጠዋል። በደብዳቤው ላይ ከአናቱ ሆነው የሚያስተዳደሩትን ወገናቸውን እንኳን አይለይም። በአጭሩ እኛ እንዳንመርጥ የሚፈልግ፣ የሚቀናቀንና ሌሎች ሰላማዊ ፓርቲወችን የሚመራና የሚደግፍ ሁሉ ፀላኢቲ ነው።
ይህ ለ2007 ዓ.ም የክትትል ስራ የተመደበው የህወሃት ቡድን ስራውን የሚያከናውነው ከታክስ ከፋዩ በሚገኝ የመንግስት ገንዘብ መሆኑ ይታወቃል።
ዘንድሮ የምርጫ አመት መሆኑን ተከትሎ የፀላኢቲ ክትትልና አፈና ከአሁን ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ መሆኑም እየታየ ነው። ጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ በየክልሉ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ሁሉ በመታፈንና ወህኒ በመውረድ ላይ ናቸው።
የህወሃት ኢህአዴግ መሪዎች በአለም ዙሪያ ነጻነቴን የሚል የህዝብ ድምጽ በሰሙ ቁጥር የሚሰማቸውን ድንጋጤ የሚቀንሱት ዜጎችን በማፈን፣ በመግደል፣ በማሰቃየትና በማሰር ብቻ ነው።
ለህወሃት ምርጫና መድብለ ፓርቲ መልክን አሳምሮ ተቀባይነት ወደ ምእራባውያን ለልመና ለመውጫ እምጅ ዴሞክራሲያዊ ምርጫና የህዝብ ልእልና የሚባል ነገር ባጠገባቸው እንዲያልፍ ስለሚፈልጉ የሚያደርጉት አለመሆኑን በብዙ መንገዶች አሳይተውናል።
ከህወሃት ውጭ ያልህ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ አንተ ለወያኔ/ህወሃት ፀላኢቲ ጠላት ነህ። ወገኖቼ ብለህ የምታስብ ሁሉ ይህን የሚስጥር ደብዳቤያቸውን በማየት ብቻ ሳይሆን በተግባር አይተሃልና።
ያለህ ምርጫ እንደአባቶችህ፡-
እልም እንጅ ውሃ አይላመጥም፣
ጠላት ወዳጅ ላይሆን አልለማመጥም።
ብለህ መነሳይ ይኖርብሃል።
ትእግስት፣ አስተዋይነትና የፍቅር መንገድ መመኘት ከህወሃት ፀላኢቲነት አያላቅቅም። ህወሃትን ማስወገድ በጠላትነት ፈርጆ ሊውጥህ የመጣ ጠላትን ማስወገድ ማለት ነው።
ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ከዚህ በጠላትነት ከፈረጀህ የዘርፎ አደሮች ቡድን እንድትላቀቅ አቅሙን በመገንባት ለወሳኝ ፍልሚያ እተዘጋጀ ነው። መላው ወገናችን ወያኔ የፈጠረልህን የክፍፍልና የልዩነት አጥር እያፈራረስክ አንድነትን አጠንክር። በያለህበት ለነጻነትህ ተነሳ። ኑሮን ለማሸነፍም ሆነ መረጃ በማጣት በወያኔ ስር ተደራጅተህ በሎሌነት እንድታገለግል የተፈረደብህ ወገን ሁሉ ወያኔ ጠላት ብሎ እንደሚቆጥርህ አትዘንጋ። የነፃነታችን ቀን ቅርብ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

የፈርዖኖች ድንኳን እየፈረሰ ነው


“ዓረብ ስፕሪንግ” እየተባለ ስለሚነገረው ህዝባዊ አብዮት ብዙ ተብሏል። ያ ህዝባዊ አመፅ ለውጥ አምጥቷል።ማን ይነካኛል ብሎ ዜጎቹን መከራ ሲያበላ የነበረው የቱኒዚያው ቤኒ ዓሊ ዛሬ የተረሳ ግለሰብ ሁኗል። እኔ ከሌለው ይህች አገር ትጠፋለች ሲል የነበረው ጋዳፊ ከተደበቀበት የአይጥ ጉድጓድ ውስጥ ተጎትቶ ወጥቶ እንደ ውሻ ተቀጥቅጦ ሙቷል። ሆስኒ ሙባረክም እንዲሁ ተርስቶ ቀርቷል። የየመንም አምባገነን አገር ጥሎ ሂዷል።በሶሪያም አምባገነኖች ከእንግዲህ ተረጋግተው ህዝባቸው ላይ የሚያላግጡበት ዘመን አብቅቷል።
በቱኒዚያዊው ሙሃመድ ቦዛዚ መስዋዕትነት የተጀመረው ህዝባዊ ዓመፅ ብዙ የዓረብ አገራትን አዳርሷል። ይህ ህዝባዊ አመፅ ከዓረቡ ዓለም ባሻገር ወደ ጥቁር ህዝቦች ተሽጋግሯል። ቡርኪና ፋሶዎች ለ27 ዓመት ስልጣኑን ሙጥኝ ብሎ የኖረውን ብሌስ ኮምፓዖሬን ከተቆናጠጠው የስልጣን ወንበር ላይ አባረውታል።
ብሌስ ኮምፓዖሬ የገዛ ወገኑን ሠላም እያሳጣ በጎሬቤት አገሮች ዋና አስታራቂ፤ የሠላም ሰው መስሎ ለመታየት ይኳትን ነበር። አሜርካኖች ቁልፍ ወዳጃችን ይሉትም ነበር። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በጎረቤት አገሮች መረጋጋት ዋና ተዋኒያኒ እያለ ያሞጋግሰው ነበር። ብሌስ ኮምፓዖሬ የራሱ እያረረበት፤ የጎሬበቱን እያማሰለ የአሜሪካኖችንና የአውሮፓዊያንን ቀልብ ይዞ ድፍን ሃያ ሰባት ዓመት በስልጣን ተንጠላጥሎ ኑሯል።
የቡርኪናው ብሌስ ኮምፓዖሬ 27 ዓመት ስልጣን ላይ ሲቆይ እንደ ህወሃት ከገዛ ህዝቡ ድምፅ ይልቅ የሌሎችን ድምፅ መስማት ይመርጥ ነበር። ህዝቡ ነፃ ምርጫ ይደረግ፤ ዜጎች በመረጡት መሪ ይመሩ፤ አገር አይታመስ ቢሉት ሊሠማ አልወደደም። ከዚህ ከወገኑ ድምፅ ይልቅ ከባህር ማዶ “ቁልፍ ወዳጃችን” ለሚለው ድምፅ ይገዛ ነበር። በጎረቤት አገሮች ውስጥ አስታራቂ እና ሽማግሌ እኔ ነኝ ብሎ ራሱን በመሾም ላይ ታች እያለ ሌሎችን ለማስደሰት ይንከላወስ ነበር።ይህ ግን ክብር አልሆነለትም።
አልቃይዳና ቦኩ ሃራምን የመሰሉ አሸባሪ ኃይሎች በተነሱ ግዜ ለብሌስ ኮምፓዖሬ ሰርግና ምላሽ ሆነለት። አሸባሪነትን ለመዋጋት የአሜሪካኖች ምርጥ ወዳጅ ለመሆን በቃ። የአየር ክልሉንም ለአሜሪካን የስለላ አውሮፕላኖች እንደልብ ፈቀደ።አሜሪካኖችም በወቅቱ ወዳጅ ብለው የጠሩትን ግለሰብ የሚፈፀመውን ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ እና የሚፈፀመውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት አይተው እንዳላዩ ሆነው ልክ ለህወሃት እንደሚያደርጉት የገንዘብና ሌሎች እርዳታዎችን መለገሳቸውን ቀጥለው ነበር። አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ኃይሎች በየቦታው የመፈጠራቸው ሁኔታ ለህወሃቶችም የተመቻቸ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የሚካድ አይደለም።
ኮምፓዖሬ በመፈንቀለ መንግስት ስልጣን ከጨበጠ በኋላ ምርጫ በተካሄደ ቁጥር እርሱና ፓርቲው ምርጫ አካሂደን አሸንፈናል እያሉ ለ27 ዓመት በስልጣን ቆይተዋል። በሌላ መልኩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫው የተጭበረበረ እንደሆነ ቢናገሩም ሰሚ ሳያገኙ ኑረው ነበር። ግዜው ደርሶ የህዝብ ቁጣ ገንፍሎ ከፍርሃት በላይ ሆነና ኮምፓዖሬ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ከተዘባነነበት ቤተ-መንግስት ሾልኮ ለሰደት ተዳረገ።
ህወሃቶች ይሄንና ከዚህ ቀደም የታየውን የህዝብ ቁጣ አይተዋል። ከዚህ ዓይነቱ የህዝብ ቁጣ የሚቀስሙት ትምህርት ይኖራል ብለን አንጠብቅም። በፈርዖን ትዕቢት ድንኳን ተጠልለው የሚኖሩ ኃይሎች የህዝብ ቁጣ ገንፍሎ መቃብር እስከ ሚጨምራቸው ድረስ ይማራሉ ብሎ መጠበቅ ከንቱ ምኞት ነው።ዛሬ ሁሉ በእጃቸው፤ ሁሉ በደጃቸው ፤ሚድያው የእነርሱ፤ የመረጃ መረቡ ከአገር ደህንነት ይልቅ የእነርሱን እድሜ ለማራዘም የሚሰራ ሆኖ እንደሚቀጥል አምነዋል። የአገሪቷ አጠቃላይ ሃብትም በእጃቸን ነው። መከላከያ ኃይሉም እኛን ከመጠበቅ ውጪ ሌላ ተልዕኮ የለውም ብለዋል።ይሄን ሁሉ በእጃችን ይዘን ማነው የሚነካን? የትኛውስ ህዝብ ነው የሚነሳብን ብለው ልባቸውን እንደ አለት ማደንደንን መርጠዋል። የህዝብ አመፅ ተነስቶ አገር ከመታመሱ በፊት ለሁሉም በእኩል ደረጃ ሊጠቅም የሚችል ምን በጎ ነገር እንሥራ ብለው ለማሰብ ምንም ፍላጎት የላቸውም። እንዲያውም የህዝብ አመፅ ቢነሳ ውጤቱን ስለማታውቁት “ከማታውቁት መላክ፤የምታውቁት ሴይጣን ይሻላችኋል” ለማለት እየዳዳቸው እንደሆነ እያየን ነው።
ህወሃቶች ትውልድ፤ ወገን፤ አገር የሚባል ቋንቋ እንደማያውቁ በተግባር አሳይተውናል።የህወሃቶች አገራቸው ድርጅታቸው እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም።እነርሱ አገር ሲሉ እነርሱን እንጂ ሌላውን እንደማይጨመር መልሰው መላልሰው ነግረውናል። ”እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትበተናለች” የሚለው መፈክር ምንጩ ህወሃቶች አገርና ትውልድ የሚል ቋንቋ በውስጣቸው የሌለ መሆኑን ይገልጥልናል። ይሄ መፈክራችሁ ቅዥት ነው፤ ተው ከዚህ ቅዥታችሁ ወጥታችሁ ወደ ገሃዱ ዓለም ተመለሱ፤ በገሃዱ ዓለም አገር እና የተቆጣ ትልቅ ህዝብ አለ። ይህ አገርና ህዝብ ከእናንተ በላይ ነው ብሎ ሊመክራቸው የሚሞክር ከተገኘ አሸባሪነት ተለጥፎበት ጠላት ይባላል።
ለብሌስ ኮምፓዖሬ የአልቃይድና የቦኩ ሃራም መፈጠር ሰርግና ምላሽ የሆነውን ያህል አሸባሪነት ለህወሃቶች የመኖሪያቸው ድንኳን ሁኗቸዋል። አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚል ኮምፓዖሬ ለአሜሪካኖች ብርቱ ወዳጅ እንደ ነበረው ሁሉ ህወሃቶችም አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚል ሽፋን ለአሜሪካኖች ወዳጅ ለመሆን በቅተዋል። አሜሪካኖችም የህወሃትን ሥም ከአሸባሪነት መዝገብ ሳይፍቁ፤ ህወሃቶች የሚፈፅሙትን ወንጀል እያወቁ እንዳላወቁ፤ አይተው እንዳላዩ ሁነው እርዳታቸውን ሳያቋርጡ እሰከ ዛሬ አሉ። ይህ ለህወሃቶች ባዶ ድፍረት እና የትዕቢታቸውም ምንጭ ሁኗቸው የተሻለ ሃሳብ አለኝ የሚለውን ሁሉ አሸባሪ እያሉ ነው። ህወሃቶችን የሚያሸብራቸው ብዙ ነው። የነፃነት ጥያቄ ያነሳ ያሸብራቸዋል። እኛ ከህወሃት አናንስም፤ህወሃትም ከእኛ አይበልጥም የሚል ከተነሳም ያሸብራቸዋል። እኔ ህወሃትን አልመርጥም የሚል ድምፅ ከተሰማም አሸባሪ ነው። ይሄ የሚያሳየን ህወሃት ኃጢአቱ የሚያሳድደው እና ጥላው የሚያስበረግገው ድርጅት ወደ መሆን መሸጋገሩን ነው። ህወሃቶች በሰሙት ድምፅ ሁሉ እየበረገጉ አገሪቷን እያመሱ እንደማይዘልቋት እኛ ልናስታውሳቸው እንወዳለን።
ህወሃቶች ከህዝቡ ድምፅ ይልቅ የሌሎችን ድምፅ መስማት ከነ ልጅ ልጆቻችን አገሪቷን ለመበዝበዝ ይረዳናል የሚል የደንቆሮ ዕምነት አላቸው። በየጎረቤት አገር ውስጥ ዘው ብለው እየገቡ ራሳቸውን የሠላም መለእክተኛ አድርገው ለዓለም ህዝብ ለማሳየት ይኳትናሉ። እኛ ከሌለን ምስራቅ አፍሪካ በአክራሪ ኃይማኖተኞች ትጠለቀለቃለች፤የአሸባሪዎችም መናኽሪያ ትሆናለች ኢትዮጵያም ትበተናለች እያሉም የሌሎችን ቀልብ ለመያዝ ደጅ ይጠናሉ።ከአሜሪካንና ከአውሮፓዊያን እጅ ለሚወረወርላቸው ምናምን ሲሉ ሳይላኩ ይሄዳሉ፤ ሳይጠሩ ከተፍ ይላሉ። ህወሃቶች ይህን ተላላኪነትንና አደር ባይነት እንደ ሥራ ይቆጥሩታል።ሥራ በመሆኑም ሶማሊያ ዘው ብለው ገብተው የእኛን ልጆች አስከሬን በመቋዲሾ ጎዳና ላይ አስጎትተው መሳለቂያ እንዲሆን አድርገዋል። ህወሃቶች ሶማሊያ ዘው ብለው በመግባታቸው ኢትዮጵያ እንደ አገር ስትጎዳ በግል ደረጃ ግን የህወሃት ጄኔራሎችና ባለሟሎቻቸው በተገኘው የደም ገንዘብ ስም አጠራሩን እንኳ የማያውቁትን አልኮሆል እየተጎነጩ ተዘባነውበታል። ባለ ሃብትም ለመሆን በቅተዋል።
እነዚህ ቡድኖች በህዝቡ እና በአጠቃላይ አገሪቷ ላይ የሚፈፅሙት ክህደት በየትም አገር ታይቶ የሚታወቅ አይደለም።ብሌስ ኮምፓዖሬና ፓርቲው ከህወሃቶች ጋር ሲነፃፀሩ እንደ መልዓክና ሴይጣን ናቸው። ህወሃቶች ከሰው አብራክ የተፈጠሩ አይመስሉም። የስግብግብነታቸው ወሰን ማጣት፤ ምንም አገራዊ ራዕይ የሌላቸው መሆን፤ ርህራሄ የሌላቸው ፍፁም ጨካኞች መሆናቸው፤ ከእውነት ጋር የማይተዋወቁ ውሸትን የኑሯቸው ድንኳን ማደረጋቸው ሲታይ ህወሃትን የሚመስል ክፉ በየትም ዓለም አለ ለማለት ይቸግራል። የኢትዮጵያ ህዝብ በህወሃቶች የደረሰበትን ብዙ መከራ ተሸክሞ ለብዙ ዘመን ኑሯል። ብዙ ዜጎች አገር አልባ ሁነው ተንክራታች ሁነው ቀርተዋል። ብዙ እናቶች እንባቸውን በመዳፋቸው የሚያፍሱ ሁነው ቀርተዋል። ይህ ግን የሚያበቃበት ግዜ እሩቅ አይደለም።
ህወሃቶች ሆይ ስሙ !
ነገ እንደ ዛሬ አይሆንላችሁም። አንድ የዋህ አምባ ገነን ገዢ ሊፈፀመው የሚችለውን ድርጊት ለፈፀመው ለብሌስ ኮምፓዖሬ ዛሬ እንደ ትላንትና እንዳልሆነለት ተመልከቱ። እናንተ እያደረሳችሁ ያላችሁት በደል እና እየፈፀማችሁ ያላችሁት የአገር ክህደት ምሳሌ የማይገኝለት ነው። የእናንተ ምርጫ ከሰላም ይልቅ ደም መፋሰስ፤ አብሮ ከመኖር ይልቅ መለየት፤ ለወገንና ለአገር ከማሰብ ይልቅ ለግል ጥቅም ብቻ መሯሯጥ ሁኗል። በዚህ ምርጫችሁ የተቆጣ ህዝብ እንደ ተደፋነ እሳት ውስጥ ውስጡን እየጨሰ መሆኑን ለማስተዋል ትዕቢታችሁ ሂሊናችሁን ጋርዶታል። ትዕቢታችሁ ወሰን ከማጣቱ የተነሳ እዚህም እዚያም እየተነሱ ያሉትን ብዙ የብሶት ድምፆችን ለማፈን ብዙ ንፁሃን ዜጎችን ትገድላላችሁ፤ታስራላችሁ፤ ታንገላታላችሁ፤ ታዋርዳላችሁ። እናንተን ሸሽቶ ወደ ጎሬቤት አገር የሚሰደደውን ሳይቀር በቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች ታስገድላላችሁ፤ እያሳፈናችሁ ትወስዳላችሁ።የምትፈፅሙት ግፉ ፅዋውን ሞልቷል።
እኩይ ዲርጊታችሁ እያሳደዳችሁ የገዛ ጥላችሁ እንኳ እያሸበራችሁ ለአገራቸው በጎ ራዕይ ያላቸውን ጥሩ ዜጎች በሙሉ አሸባሪ እያላችሁ እንደምትከሱ ዓለም ሁሉ ዓይኑን ከፍቶ እየታዘበ ነው። በእኩይ ዲሪጊቶቻችሁ ምክንያት ከመሸበራችሁ የተነሳ ሁሉንም ድምፅ ለማፈን የምታጠፉት የአገር ሃብት ነፃነትን፤ እኩልነትን፤ ፍትህንና በእውነት ሊሠራ የሚችል ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ቢውል ኑሮ በእውነት ሠላም አግኝታችሁ መኖር በቻላችሁ ነበር። እናንተ ግን የጨለማውን መንገድ መርጣችኋልና እርሱን እንደምታገኙ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አይግባችሁ።
አዎን በምርጫችሁ መሠረት በሚገባችሁ ቋንቋ የሚያናግራችሁ ትውልድ የአያቶቹን የነፃነት ጋሻና ጦር አንስቶ ተሠማርቷል። አይናችሁ እያየ፤ጆሯችሁም እየሰማ ወጣቶች ከመላዋ ኢትዮጵያ ተሰባስበው አያቶቻቸው በኩራት በቆሙበት ተራራ ላይ አንገታቸውን ቀና አድርገው እየተመላለሱበት ነው። ህወሃትን የመሠለ ዘረኛ፤ ሌባ እና አደረ ባይ ቡድን ኢትዮጵያን የመሰለች ትልቅ አገር ሲያዋርድ አይተን ዝም ብንል እርግማን ይሁንብን ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች ዝናራቸውን ታጥቀው ተነስተዋል። እናቶችም ወገባቸውን በገመድ ታጥቀው ወጣቶቹን እየመረቁ ወደ ጀግኖቹ መንደር እየሸኙ ነው። የተቀሩትም ሳያቅማሙ የኃላ ደጀን ሁነው ቁመዋል። እንግዲህ ኢትዮጵያን የሚያዋርዱ፤ አገሪቷን የሚዘርፉ፤ ንፁሃን ዜጎችን የሚያሰቃዩ ወየውላቸው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

Monday, 3 November 2014

አማራ! አማራ! አማራ! ብቸኛዉ የወያኔ ዘፈን



“ሞኝና ወረቀት የያዙትን አይለቁም” የሚለዉ ቆየት ያለ ያለ የአገራችን ተረት ትርጉም ያልገባዉ ሰዉ ካለ የቅኔ አዋቂ መፈለግ ወይም መጽሐፍ ማገላበጥ የለበትም። ማድረግ ያለበት ቀላል ነገር ቢኖር ወያኔንና የወያኔን ስራ ትኩር ብሎ መመልከት ብቻ ነዉ። በመሠረቱ ወረቀት የያዘዉን አለመልቀቁ ወያኔን ጨምሮ ሁላችንም የምንፈልገዉ ነገር ነዉና ወረቀት ሊመሰገን ይገባል። ሞኝ የያዘዉን አለመልቀቁና ከግዑዙ ወረቀት ጋር መነጻጸሩ ግን ሞኝ አማራጭ የሚባል ነገር የማያዉቅና ግዜና ሁኔታ ሲለዋወጡ ያቺኑ በልጅነቱ የያዛትን አቋም ሙጭጭ አድርጎ እንደያዘ እድሜ ልኩን የሚኖር የሀሳብ ደሃ መሆኑን ያመለክታል። ሞኝን ሞኝ እያለን የምንጠራዉም በዚህ ደካማና ግትር አቋሙ የተነሳ ነዉ። ወያኔ ጫካ ዉስጥ እያለ ለአስራ ሰባት አመት፤ ከጫካዉ ወጥቶ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ደግሞ ለሃያ ሦስት አመታት የያዛቸዉን አቋሞችና የወሰዳቸዉን እርምጃዎች ረጋ ብሎ የተመለከተ ሰዉ ወያኔ፤ ወረቀትና ሞኝ ያላቸዉን የቅርብ ግኑኝነት በቀላሉ መመልከት ይችላል። ሦስቱም አንድ ነገር ከያዙ ሌላ የመያዝ ፍላጎትም ችሎታም የላቸዉም። አዎ! በእርግጥም ሞኝ በሞኝነቱ፤ ወረቀት የተፈጥሮ ጠባዩ በመሆኑ ወያኔ ደግሞ የወረቀትም የሞኝም ጠባይ ስላለዉ ሦስቱም የያዙትን አይለቁም።
የወያኔ መሪዎች ምን ለትግል አነሳሳችሁ ተብለዉ ሲጠየቁ በወጣትነታችን ጠመንጃ ተሸክመን ጫካ እንድንገባ ያስገደደን በወቅቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስር ሰድዶ የነበረዉ የብሄር ብሄረሰቦች ጭቆና ነዉ ብለዉ ነዉ አፋቸዉን ሞልተዉ የሚመልሱት። ዉሸታቸዉን ነዉ። የወያኔ መሪዎች በተለይ ሁለቱ በፀረ ኢትዮጵያ አቋማቸዉ የሚታወቁት መለስ ዜናዊና ስብሀት ነጋ ለትግል ያነሳሳቸዉ የብሄር ብሄረሰቦች ጭቆና ሳይሆን በአማራ ብሄረሰብ ላይ ያላቸዉ ከፍተኛ ጥላቻ ነዉ። ዛሬም አነዚህ ሁለት ፀረ አማራ ግለሰቦች የፈጠሩት ህወሓት የሚባል ዘረኛ ድርጅት ፀረ አማራ ከመሆኑ የተነሳ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች በተለየ መንገድ የገባበት ቦታ ሁሉ እየተከታተለ የሚያጠቃዉ ይህንኑ መከረኛ የአማራ ብሄረሰብ ነዉ። ወያኔዎች ለአማራ ብሄረሰብ ያላቸዉን ጥላቻ ላለፉት 34 አመታት በስድብ፤ በንቀትና አማራዉን በጅምላ በማንኳሰስ አሳይተዋል። ባለፉት አስር አመታት ደግሞ ኦሮሚያ፤ ቤንች ማጂና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዉስጥ የአማራ ተወላጆችን ይህ የእናንተ አገር አይደለምና ወጡ እያሉ አማሮችን ከዉሃ ዉስጥ የወጣ አሳ አድርገዋቸዋል።
ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት በግልጽ እንዳየናቸዉ የወያኔ መሪዎች አማራዉን በመዝለፍና በማፈናቀል ብቻ አልተገቱም፤ ይልቁንም አማራዉን ኢትዮጵያ ዉስጥ ለተከሰቱ ችግሮች ሁሉ ብቸኛ ተጠያቂ በማድረግ ይህንን በህዝብ ቁጥሩም ሆነ በታሪክ ስፋቱ አንጋፋ የሆነዉን ብሄረሰብ በሌሎቹ የአገራችን ብሄረሰቦች እንዲጠላና በአይነ ቁራኛ እንዲጠበቅ አድርገዋል። በዚህ የተነሳ ወያኔ ባለፉት ሃያ አራት አመታት ጠፍጥፎ የፈጠሯቸዉ በየክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ምስለኔዎች ምንም አይነት ችግር ባጋጠማቸዉ ቁጥር የችግራቸዉ መንስኤ አድርገዉ የሚወስዱት የአማራዉን ብሄረሰብ ነዉ። ዛሬ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች፤ ቤንች ማጂና ቤኒሻንጉል ዉስጥ አማራዉን አገርህ አይደለምና ዉጣ የሚባለዉ የዘረኝነት አባዜም ቢሆን የዚሁ ወያኔ ለረጂም አመታት በህዝብ መካከል ሆን ብሎ የዘራዉ ጥላቻ ዉጤት ነዉ።
ወያኔ እራሱን የኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዐት አባት አድርጎ በማቅረብ ብዙ ምዕራባዉያን መንግስታትንና ዋና ዋና ለጋሽ አገሮችን ከጎኑ ማሰለፍ ችሏል። ይህ የማጭበርበር ልምዱ ደግሞ የምርጫ ኮሮጆ እየሰረቀ ተመረጥኩ ያለባቸዉንና ድምጼ ይከበር ብሎ የጠየቀዉን ህዝብ በጥይት የጨፈጨፈበትን ምርጫ አንደ ትክክለኛ ምርጫ አድርጎ ለምዕራባዉያን በመሸጥ ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ አግኝቶበታል። ዘንድሮም ለሚደረገዉ ምርጫ እነዚሁ ምዕራባዉያን አጎሮች በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በኩል 15 ሚሊዮን ዶላር ወያኔን ለማስታቀፍ ሽርጉድ እያሉ ነዉ።
ኢትዮጵያ ዉስጥ የወያኔ ጥላቻና ዘረኝነት በከፍተኛ ደረጃ ከተንጸባረቀባቸዉ ቦታዎች አንዱና ዋነኛዉ ወያኔ ፈጠርኩት ወይም ጀመርኩት ብሎ የሚነግረን የመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ስርዐት ነዉ። በዚህ የወያኔ መድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ስርዐት ዉስጥ በአንድ በኩል ወያኔና ወያኔ በአምሳሉ የፈጠራቸዉ ድርጅቶች አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ በህጋዊ መንገድ የፓለቲካ ፓርቲ ብሎ የመዘገባቸዉ ነገር ግን በጠላትነት ፈርጆ የሚዋጋቸዉ ድርጅቶች አሉ። እነዚህ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በስም፤ በስትራቴጂና በአንዳንድ የፖለቲካ አቅጣጫዎች የሚለያዩ ቢሆንም ወያኔ ሁሉንም ትምክተኞች፤ ሽብርተኞች፤ የቀድሞ ስርዐት ናፋቂዎች ወይም የአማራ ልህቃን ፓርቲ እያለ ነዉ የሚጠራቸዉ። በወያኔ ቤት የህወሓትን ዘረኛ አምባገነን ስርዐት አጥብቆ የሚቃወምና ኢትዮጵያዊነትን ደጋግሞ የሚሰብክ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ከየትም ይምጣ ከየት የአማራ ልህቃን ፓርቲ ወይም ትምክህተኛ አማራ ተብሎ ነዉ የሚፈረጀዉ።
ይህ ርካሽና ጎታች የወያኔ ፓለቲካ ወያኔ በአማራ ብሄረሰብ ላይ ያለዉን ስር የሰደደ ጥላቻ ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ያለዉን ከፍተኛ ንቀት ያሳያል። ወያኔ የአገሩ አንድነት መደፈርና የሰብዓዊ መብቱ መረገጥ አንገብግቦት “ኢትዮጵያ” “ኢትዮጵያ” እያለ ድምጹን ከፍ አድርጎ የሚያሰማዉን ሁሉ ትምክህተኛ አማራ እያለ በተጣራ ቁጥር ሌሎቹን የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች አናንተ ኢትዮጵያዉያን አይደላችሁም ወይም ኢትዮጵያዊነት እናንተ ላይ የተጫነ ዕዳ ነዉ ብሎ እየነገራቸዉ ነዉ። ይህ ክፉና መዘዘኛ የሆነ ፀረ ኢትዮጵያ አባባል ደግሞ በሌላ መልኩ ህገ መንግስቱ ዉሰጥም የተቀመጠ አባባል ነዉ። የወያኔን ህገ መንግስት አንቀጽ 39 በትክክል ከተመለከትነዉ አንቀጹ የሚለዉ ኢትዮጵያዊነትን የማይፈልግ ሁሉ መገንጠልና የራሱን መንግስት መመስረት ይችላል ነዉ ። ወያኔ ሺ ግዜ ቢነግሩት ፍጹም የማይገባዉ የዉኃ ዉስጥ ድንጋይ ስለሆነ ነዉ እንጂ ቢገባዉማ ኖሮ እሱ በነጋ በጠባ ፀረ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስተምራቸዉ ደቡብ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች ይጠቅመናል፤ ያግባባናል ወይም የኤኮኖሚ ግኑኝነታችንን ያጠናክርልናል ብለዉ የክልላቸዉ የስራ ቋንቋ አድርገዉ የመረጡት አገራችን ዉስጥ የስራና የመግባቢያ ቋንቋ የሆነዉን አማርኛን ነዉ።
ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በወጣትነታቸዉ የተጠናወታቸዉን ፀረ አማራ በሽታ ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ ለእያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ ለማስተላለፍ ያላደረጉት ነገር የለም። ደግነቱ ግን አንዳንድ እንደነሱ በዘር በሽታ ከተለከፉ ጥቂት ህሙማን ዉጭ የወያኔን ፀረ ህዝብና ፀረ አገር ሃሳብ ተቀብሎ ያስተናገደ ማንም የለም። ሆኖም ወያኔዎች የአገሪቱን የሜድያ ተቋሞች ሙሉ በሙሉ ስለሚቆጣጠሩ ይህንን ፀረ አማራ ፕሮፓጋንደዳቸዉን ለኢትዮጵያ ህዝብ ማስታለፈቸዉን እንደቀጠሉበት ነዉ። ባለፉት ጥቂት አመታት በግልጽ እንዳየነዉ ደግሞ ወያኔ ይህንን ፀረ አማራ ዘመቻዉን እስከዛሬ ካስተናገደበት ከአገር አቀፍ መድረክ ወደ አለም አቀፍ መድረክ ይዞት እየሄደ ነዉ። በቅርቡ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ይፋ የሆኑ ሪፖርቶች በግልጽ እንዳሳዩን አንዳንድ ታሪክን አገላብጠዉ ማየት የተሳናቸዉና በተለይም የኢትዮጵያን ማህበረሰባዊ አደረጃጀት በሚገባ ያላጤኑ ሀላፊነት የጎደላቸዉ አለም አቀፍ ተቋሞች ይህንን ወያኔ በግርድፉ የሚያቀርብላቸዉን ፀረ ህዝብ ፕሮፓጋንዳ እንደትክክለኛ መረጃ በመዉሰድ የወያኔ ወጥመድ ዉስጥ ሰተት ብለዉ ሲገቡ ተስተዉሏል።
በያዝነዉ ወር በተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ስር የሶማሊያንና የኤርትራን ጉዳዮች የሚከታተለዉ ቡድን ለንባብ ባበቃዉ ሪፖርት ዉስጥ የወያኔን መዝገብ እያገላበጠ ያገኛቸዉን ፍጹም መሠረተ ቢስ የሆኑ መረጃዎች በመጠቀም የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን ስም ሲያጎድፍ ታይቷል። ይህ አለምአቃፋዊ ተቋም ገለልተኝነቱንና አለምአቀፋዊነቱን ዘንግቶ የአንድ ዘረኛ አምበገነን አገዛዝ ቃል አቀባይ በመሆን ከዘረኝነትና ከአምባገነንነት ለመላቀቅ ከወያኔ ጋር ትንቅንቅ ዉስጥ የገባዉን የኢትዮጵያ ህዝብ አሳዝኗል።
ይህ ተጠሪነቱ ለጸጥታዉ ምክር ቤት የሆነዉ ቡድን የተሰጠዉ ሃላፊነት የኤርትራንና የሶማሊያን ጉዳዮች መከታተል ሆኖ ሳለ በሪፓርቱ ላይ በግልጽ እንደታየዉ ግን በወያኔ ትዕዛዝ ግንቦት ሰባትንና በጸባየ ብልሹነታቸዉ ከግንቦት ሰባት የተሰናበቱ ግለሰቦችን ጉዳይ የሪፖርቱ ማዕከል አድርጎ አዉጥቷል።የዚህ ሃላፊነት የጎደለዉ ቡደን ሪፖርት የሚጀምረዉ ግንቦት 7 የታገደ ወይም የተከለከለ ድርጅት ነዉ እያለ ነዉ፤ ሆኖም ማን እንዳገደዉና የት አገር እንደታገደ ምንም ያለዉ ነገር የለም። ከዚህ በተጨማሪ እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር በግንቦት 2008 ዓም ከአራቱም ማዕዘናት የነጻነት፤ የፍትህና የእኩልነት ጥማት ባሰባሰባቸዉ ኢትዮጵያዉያን የተመሰረተዉን ግንቦት 7 ንቅናቄ በ2009 ዓም በአማራ ልህቃን የተመሰረተ ድርጅት ነዉ በማለት ወያኔ የሰጠዉን መረጃ ቅንጣት ታክል የማጣራት ስራ ሳይሰራ እንዳለ በሪፖርቱ ዉስጥ አጠቃልሏል። ኤርትራን አስመልክቶ ሪፖርቱ ዉስጥ የተጠቃለለዉን ዘገባ ለማረጋገጥ ሪፓርቱን ለኤርትራ መንግስትና በተመድ ለኤርትራ አምባሳደር ሌኬ ነበር የሚለዉ ይህ አሳፋሪ ቡድን ግንቦት 7ን በተመለከተ ወያኔ ያሳቀፈዉን የዉሸት መረጃ እንዳለ በማቅረብ ተጠሪነቱ ለተመድ የጸጥታዉ ምክር ቤት ሳይሆን ለወያኔ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
ለመሆኑ አንድ የተመድ አካል የሆነ ቡድን በአገሮችና በፓለቲካ ድርጅቶች ጉዳይ ምን አግብቶት ነዉ አንድን ድርጅት የዚህ ወይም የዚያ ብሄረሰብ ድርጅት ነዉ ብሎ ሪፖርት የሚያወጣዉ? ምክንያቱ ሰንካላና መሰረተ ቢስ ቢሆንም ወያኔ ግንቦት 7ን የአማራ ድርጅት ነዉ የሚልበት የራሱ የሆነ ምክንያት አለዉ፤ የተመድ አካል የሆነ ድርጅት ግን ምን አይነት ምክንያት ቢኖረዉ ነዉ እሱ እራሱ በዘር የተደራጀዉ ወያኔ የአያሌ ኢትዮጵያዉያን መሰባሰቢያ የሆነዉን ግንቦት ሰባትን የአማራ ልህቃን ድርጅት ነዉ ብለህ ዘግብ ሲለዉ አሜን ብሎና ሪፖርት ጽፎ ለአለም ህዝብ ያቀረበዉ?
ወያኔ ግንቦት 7ን ብቻ ሳይሆን አጥብቀዉ የሚቃወሙትንና የዘረኝነት ፖሊሲዉን የሚያጋልጡ ኃይሎችን ሁሉ ሽብርተኛ፤ ትምክህተኛ ወይም ስልጣን ናፋቂ አማራ እያለ ነዉ የሚጠራቸዉ። በወያኔ ቤት የኢትዮጵያን አንድነት የሚሰብክ ሁሉ ትምክተኛ አማራ፤ የመብት፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ የሚያነሳ የድሮዉን ስርዐት ናፋቂ፤ እኩልነትንና ፍትሃዊነትን እየዳሰሰ የሚጽፍ ጋዜጠኛና ጦማሪ ደግሞ ሽብርተኛ ነዉ። አማራንና የአማራን ባህል ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳዉ ወያኔ የእያንዳንዱ ችግር መንስኤ አማራ ነዉ ብሎ ቢናገር ብዙ አይገርመንም። ከጄኔራል ሳሞራ የኑስ እስከ ጄኔራል ታደሰ ወረደ፤ ከስዩም መስፍን እስከ አባይ ፀሐዬ፤ ከሟቹ መለስ ዜናዊ ጃጅቶ የባጥ የቆጡን እስከሚቀባጥረዉ ስብሃት ነጋ ድረስ ሌላ ዘር ሳይደባለቅበት በትግራይ ልጆች ብቻ የተሞላዉ ህወሓት የዘረኝነት ካባ ተከናንቦ አንድ አገር ህዝብ ሲያስርና ሲገድል በአይናቸዉ የሚያዩ ሰዎች ኢትዮጵያዉያንን በዘርና በቋንቋ ሳይሆን በፖለቲካ አስተሳሰባቸዉና በአገር ወዳድነታቸዉ ብቻ ያሰባሰበዉን ግንቦት ሰባትን ወያኔ በሉ ስላላቸዉ ብቻ የአማራ ልህቃን ፓርቲ ነዉ ማለታቸዉ ግን እጅግ በጣም ይገርማልም ያሳዝናልም።
የወያኔን ዘረኛ ስርዐት ለማጥፋት የምንታገል ኢትዮጵያዉያን በሙሉ ይህንን ወያኔ “የአማራ ልህቃን” በሚል ቅኝት ቃኝቶ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ የለቀቀዉን ነጠላ ዜማ በሚገባ ልንቃኘዉና ማርከሻዉን ልናዘጋጅለት ይገባል። ወያኔ አገር ቤት ዉስጥ እስከዛሬ ካጋጠመዉ መዐት ሁሉ ጋር በማያያዝ ያሰራጨዉ ፀረ አማራ ፕሮፓጋንዳ አገራችን ኢትዮጵያን ምን ያክል እንደጎዳት አይተናል። ዘንድሮ ወያኔ ጭራሽ ብሶበት አማራንና ሽብርተኝነትና ከስልጣን ጥማት ጋር በማያያዝ አለም አቀፉን ህብረተሰብ አማራን አንድ በሉልኝ እያለ ነዉ። “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ ይህንን ለጆሮ የሚቀፍ የወያኔ ነጠላ ዜማ ገበያ ላይ ከመዋሉ በፊት አሁኑኑ ማጥፋት አለብን። የወያኔን ፀረ አማራ ዘመቻ እንደ ፀረ ኦሮሞ፤ ፀረ ሶማሌ፤ ፀረ ትግራይ ፀረ ሲዳማና ባጠቃላይ እንደ ፀረ ኢትዮጵያ ዘመቻ አድርገን በማየት ሁላችንም እንደ አንድ ሰዉ ቆመን መዋጋትና ማክሸፍ አለብን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!