አባቶቻችን አገራቸውን ከባዕድ ወረራ ለመከላከል ደማቸውን ያፈሰሱትና አጥንታቸውን የከሰከሱ መጪው ትውልድ በአገሪቱ አንገት ማስገቢያ ጎጆ እንዲኖረው በማሰብ እንጅ፣ በደምና በአጥንት የተገዛው መሬት ለውጭ አገር ዜጎች እንዲቸበቸብ ወይም በመንግስት ስም የተደራጁ ሽፍቶች እንዲዘርፉት አልነበረም።
ሌላው አስገራሚና አሳዛኙ ነገር እንዲህ አይነት ሰቆቃ የተፈጸመባቸውና በዚህ ክረምት ወቅት ቤቶቻቸው ፈርሶና ንብረቶቻቸው ወድሞ ወደ ፍጹም ድህነት እንዲገቡ በተደረጉት ዜጎች መሬት ላይ፣ ህወሃት ኮንዶሚኒዬሞችን ገንብቶ ለዲያስፖራ ለመቸብቸብ ዕቅድ ያለው መሆኑ ነው። ዲያስፖራው አገዛዙ በወገኖቹ ላይ የሚፈጽማቸውን ሰቆቃና ግድያ በማጋለጥ ሥራ ላይ በመጠመዱ የህወሃት መሪዎች እረፍት አጥተዋል። በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ አጋዚ የተባለው ሃይል በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል የቀን ጉዳይ ካልሆነ በቀር በአለም አቀፍ ወንጀል እንደሚያስጠይቅ ወያኔ ይረዳል። ይህንን ስጋት ለማስቆም የዲያስፖራን እንቅስቃሴ ማዳከም እንደስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ የጀመረው የነ ቴዎድሮስ አድሃኖም አገዛዝ፣ ዲያስፖራውን በጥቅም በመከፋፈል ስጋቱ ይቀነሳል ብሎ ያምናል። ከዚህም በተጨማሪ አገር ውስጥ የሚደረገውን አልገዛም ባይነት ትግል ለማጠናከር የዲያስፖራው እምቅ ሃይል የሚፈጥረውን ተአምር ህወሃት አውቆታል። ላፍቶ ክፈለ ከተማ 40 በ 60 በተባለው ፕሮጄክት የኮንዶሚኒዬም ባለቤት በመሆን የአገራቸውንና የወገኖቻቸውን ስቃይ ለማራዘም ላኮበኮቡ የዲያስፖራ አባላት እየተመቻቸች ያለ ሰፈር ነው። ከውስጧ እየተሰማ ያለው ለቅሶና ዋይታ የማይቆረቁራቸው ፤ ኮንዶሚኒዬም ቤት የሚያማልላቸው ዲያስፖራዎች አይኖሩም አይባልም።
አርበኞች ግንቦት 7 የህወሃት አገዛዝ ዜጎችን በመግደልና በማሰር ከቀያቸውና ከመኖሪያቤታቸው በሚያፈናቅለው የከተማም ሆነ የገጠር መሬት ላይ ማንም ሰው በህግ ፊት በዘላቂነት የሚጸና መብት ሊያገኝ ይችላል ብሎ አያምንም። ህወሃት በሚወረውርላቸው የጥቅም ፍርፋሪ የወጎኖቻቸውን ስቃይና መከራ ዕድሜ እያራዘሙ ያሉ ከየማህበረሰቡ የተገዙ ስላሉ በተለመደው ርካሽ ዋጋ በንጽጽር ደህና መኖር እየቻለ ካለው የዲያስፖራ ማህበረሰብ ሰዎችን መሸመት እችላለሁ ብሎ ህወሃት እየተንቀሳቀሰ ነው። በቴዎድሮስ አድሃኖም ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ በተግባር እንዲተረጎም በውጪ አገር ባሉ የወያኔ ኤምባሲ ሁሉ የተበተነው የዲያስፖራ ፖሊሲ አላማ ይሄ ነው። ቀርሳና ኮንቶማ በእንዲህ አይነት ርካሽ ጥቅም የሚሸመቱ የዲያስፖራ አባላትን ለማሰባሰብ እየተዘጋጀ ያለ ሰፈር ነው። አርበኞች ግንቦት 7 የሶስት ቀን አራስ በተገደለችበት፤ በርካታ እናቶች፤ አቅመደካማ አዛውንቶችና ታዳጊ ህጻናት ተፈናቅለው ለጎዳና ተዳዳሪነት በተዳረጉበት ቦታ ላይ የሚገነባውን ኮንዶሚኒዬም፤ ለተለያዩ አገልግሎት የሚሆኑ ህንጻዎች ወይም ሌላ ኢንቬስትመንት ባለቤት ለመሆን በየዋህነት ያሰፈሰፉ ካሉ ውሳኔያቸውን ቆም ብለው እንዲያጠኑት ይመክራል። ከቤታቸው ተፈናቅለው እንባቸውን እያፈሰሱና በየሜዳው ተበትነው የሚንከራተቱ ወገኖቻችን እንባ ሳይደርቅ ህወሃት ወደ መጨረሻው ከርሰመቃብር ይወርዳል። ይህ ምኞት ሳይሆን የቆምንለትና እየሞትንለት ያለው ትግል ውጤት ነው።
ወያኔ ሃብት ለማካበት በሚያጧጡፈው የመሬት ንግድ የሚፈናቀሉ ወገኖቻችን ህይወት ሁላችንንም ይመለከታል። የአገሪቱን ዜጎች ለጎዳና ተዳዳሪነት በመዳረግ የሚገነቡ አዳዲስ ህንጻዎችና መንገዶች ልማት ሳይሆን ማህበራዊ ቀውስ በመፍጠር ህብረተሰቡን ለከፍተኛ ችግር የሚዳርግ አደጋውም ለአገር የሚተርፍ ነው። አልጠግብ ባይ ጥቂት የህወሃት አመራሮች ህዝባችንን ሲያፈናቅሉትና አገር አልባ ሲያደርጉ ዝም ብሎ መመልከት ችግሩ እንዲባባስና እያንዳንዳችን የጥቃቱ ሰለባ እንዲንሆን መጋበዝ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ይህንን የህወሃት ዜጎችን የማፈናቀል እርምጃ ለማስቆምና በግፍ ለተገደሉ ወገኖቻችን በህግ ለመፋረድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በያለበት ጸረ ወያኔ ትግሉን እንዲያፏፉምና ትግሉን እንዲቀላቀል ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
No comments:
Post a Comment