Tuesday, 9 August 2016

አንዳርጋቸው ጽጌ የታገተበትን ሁለተኛ አመት ስናስታውስ ለነጻነት ትግሉ ያለንን ቁርጠኝነት በማደስ ነው!! –


June 23, 2016
def-thumbየአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ
የወያኔ አገዛዝ በአቡደራቡህ መንሱር ሃዲ ይመራ ከነበረው የየመን መንግሥት ጸጥታ ሃይል ጋር በመመሳጠር አንጋፋውን መሪያችንንና የትግል ጓዳችንን አንዳርጋቸው ጽጌን ከሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ አግቶ በቁጥጥሩ ስር ካስገባ እነሆ ዛሬ ሁለት አመት ሞላው።
የአለም አቀፉን ህግ በመተላለፍ ህወሃት ድንበር ተሻግሮና ባህር አቁርጦ አንዳርጋቸው ጽጌን ከየመን ሲያግት ቢያንስ ሁለት ውጤቶችን ለማግኘት አሰፍስፎ እንደነበር መገመት አያስቸግርም። አንደኛው ሥልጣን ላይ ተደላድሎ ለብዙ አመታት የመቆየት ምኞቱን አደጋ ላይ የጣለበትን የአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ አከርካሪ በመምታት ትግሉን አሽመደምደዋለሁ የሚል የተሳሳተ ስሌት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ህወሃትን የሚግደራደር ሃይል የትም ቢሆን ሊያመልጥ እንደማይችል በማሳየት የኢትዮጵያን ህዝብ አንገት ለማስደፋትና በፍርሃት አንቀጥቅጦ ለመግዛት የታለመ የእብሪት ውሳኔ ነው።
በዚህም ስሌት ህወሃት አንዳርጋቸው ጽጌን በእጁ ለማስገባት በአፈናው ተግባር ተባባሪ ለሆነው ለመንሱር ሃዲ መንግሥት ዘጠኝ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደከፈለ በራሱ አንደበት ሳይደብቅ ለደህንነት አባላቶቹ ሲናገር ተደምጧል። ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ከድህነት ወለል በታች ላለቺው አገራችንና የዕለት ህይወቱን ከአለም አቀፍ ህብረተሰብ በሚለገስ የምግብ ዕርዳታ ለሚገፋው ህዝባችን ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። በግዜያዊ ጥቅም አይናቸው የታወረዉ የየመን መንግሥት ባለስልጣኖችም ቢሆኑ ለፍትህ፥ ለእኩልነትና ለነጻነት የሚታገልን አንድ ኢትዮጵያዊ በአገሩ አየር መንገድ ሲጓዝ አግተዉ ለወያኔ ሲያስረክቡ ለረጅም አመታት በዘለቀዉና ለወደፊትም ጸንቶ በሚቆየዉ የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት ላይ ጥሎት የሚያልፈዉ መጥፎ ጠባሳ የታያቸዉ አይመስልም። የሰነዓውን ኦፕሬሽን በህወሃት በኩል የመራውና አንዳርጋቸዉ ጽጌ እጆች ላይ ካቴና አጥልቆ ለወያኔ ያስረከበው አብረሃም መንጁስም ቢሆን በስልጣን ሽኩቻ ከነበረበት ሃላፊነት ተፈንግሎ ዛሬ የት እንዳለ ከሱ ከራሱ ዉጭ ሌላ ሰዉ የሚያዉቅ አይመስለንም።
የህወሃት አፈናና ጭቆና የመረረው ህዝባችን አንዳርጋቸው ጽጌን ለማገት የተሄደበት ርቀትና የተከፈለው ዋጋ በነጻነቱ ላይ የተቃጣ ድፍረት መሆኑን ያሳየው “እኔም አንዳርጋቸው ነኝ” በሚል ቁጣ ሆ ብሎ በመነሳት ነው። አገር ውስጥና ከአገር ውጪ የተቀጣጠለው ይህ ህዝባዊ ቁጣ በአንድ አንዳርጋቸው መታገት እልፍ አእላፍ አንዳርጋቸውን ከማፍራቱም በላይ የህወሃት መሪዎችንና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው እንደለመዱት ደረታቸውን ነፍተው በሠላም እንዳይወጡና እንዳይገቡ ወደ ሚያሸማቅቃቸው የተግባር እርምጃ ተሸጋግሯል።
አርበኞች ግንቦት 7 ከአንዳርጋቸው መታገት በኋላ የተቀጣጠለው ህዝባዊ ቁጣ የአንዳርጋቸዉ የረጅም ጊዜ ምኞትና ትግል ላይ በነበረባቸዉ አመታት በከፍተኛ ደረጃ የደከመበት የልፋቱ ዉጤት ነው ብሎ ያምናል። አርበኞች ግንቦት 7 ይህንን ህዝባዊ ቁጣና ህዝባዊ መነቃቃት አስተባብሮና የሚያስፈልገውን አመራር ሰጥቶ ትግሉን ከዳር ለማድረስ በሙሉ ሃይሉና ጉልበቱ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለወዳጅም ለጠላትም ይገልጻል።
የምንወደውና የምናፈቅረው የትግል ጓዳችን አንዳርጋቸው ጽጌ የታገተበትን ሁለተኛ አመት ስናስታውስ ይህ ጀግና ሰዉ የጀመረውን ትግል ከዳር ለማድረስ ያለንን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ነው። ለፍትህ ለእኩልነትና ለነጻነት ሲታገሉ የወያኔ ሠለባ የሆኑ ወገኖቻችንን በፍጹም እንደማንረሳቸዉና በየዕስር ቤቱ በዘረኞች እብሪት እየተሰቃዩ ያሉ ወገኖቻችን ሁሉ ነጻ እስኪወጡ ድረስ እነሱ አንግበው የተነሱትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ቆራጥነት ትግሉን እንደምንቀጥል ቃል እንገባለን።
የትግል ጓዳችን አንዳርጋቸዉ ሆይ ! ያንተና እንዳንተ በወያኔ ሰቆቃ የሚፈጸምባቸው ጓዶቻችን ሁሉ የመከራ ዘመን የሚያበቃው የወያኔ የሥልጣን ዕድሜ ለማሳጠር የጀመርከውን ትግል ከዳር ስናደርስ መሆኑን አንተም ታውቀዋለህና እንደምንታደግህ አትጠራጠር።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

No comments:

Post a Comment