Monday, 3 November 2014

አማራ! አማራ! አማራ! ብቸኛዉ የወያኔ ዘፈን



“ሞኝና ወረቀት የያዙትን አይለቁም” የሚለዉ ቆየት ያለ ያለ የአገራችን ተረት ትርጉም ያልገባዉ ሰዉ ካለ የቅኔ አዋቂ መፈለግ ወይም መጽሐፍ ማገላበጥ የለበትም። ማድረግ ያለበት ቀላል ነገር ቢኖር ወያኔንና የወያኔን ስራ ትኩር ብሎ መመልከት ብቻ ነዉ። በመሠረቱ ወረቀት የያዘዉን አለመልቀቁ ወያኔን ጨምሮ ሁላችንም የምንፈልገዉ ነገር ነዉና ወረቀት ሊመሰገን ይገባል። ሞኝ የያዘዉን አለመልቀቁና ከግዑዙ ወረቀት ጋር መነጻጸሩ ግን ሞኝ አማራጭ የሚባል ነገር የማያዉቅና ግዜና ሁኔታ ሲለዋወጡ ያቺኑ በልጅነቱ የያዛትን አቋም ሙጭጭ አድርጎ እንደያዘ እድሜ ልኩን የሚኖር የሀሳብ ደሃ መሆኑን ያመለክታል። ሞኝን ሞኝ እያለን የምንጠራዉም በዚህ ደካማና ግትር አቋሙ የተነሳ ነዉ። ወያኔ ጫካ ዉስጥ እያለ ለአስራ ሰባት አመት፤ ከጫካዉ ወጥቶ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ደግሞ ለሃያ ሦስት አመታት የያዛቸዉን አቋሞችና የወሰዳቸዉን እርምጃዎች ረጋ ብሎ የተመለከተ ሰዉ ወያኔ፤ ወረቀትና ሞኝ ያላቸዉን የቅርብ ግኑኝነት በቀላሉ መመልከት ይችላል። ሦስቱም አንድ ነገር ከያዙ ሌላ የመያዝ ፍላጎትም ችሎታም የላቸዉም። አዎ! በእርግጥም ሞኝ በሞኝነቱ፤ ወረቀት የተፈጥሮ ጠባዩ በመሆኑ ወያኔ ደግሞ የወረቀትም የሞኝም ጠባይ ስላለዉ ሦስቱም የያዙትን አይለቁም።
የወያኔ መሪዎች ምን ለትግል አነሳሳችሁ ተብለዉ ሲጠየቁ በወጣትነታችን ጠመንጃ ተሸክመን ጫካ እንድንገባ ያስገደደን በወቅቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስር ሰድዶ የነበረዉ የብሄር ብሄረሰቦች ጭቆና ነዉ ብለዉ ነዉ አፋቸዉን ሞልተዉ የሚመልሱት። ዉሸታቸዉን ነዉ። የወያኔ መሪዎች በተለይ ሁለቱ በፀረ ኢትዮጵያ አቋማቸዉ የሚታወቁት መለስ ዜናዊና ስብሀት ነጋ ለትግል ያነሳሳቸዉ የብሄር ብሄረሰቦች ጭቆና ሳይሆን በአማራ ብሄረሰብ ላይ ያላቸዉ ከፍተኛ ጥላቻ ነዉ። ዛሬም አነዚህ ሁለት ፀረ አማራ ግለሰቦች የፈጠሩት ህወሓት የሚባል ዘረኛ ድርጅት ፀረ አማራ ከመሆኑ የተነሳ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች በተለየ መንገድ የገባበት ቦታ ሁሉ እየተከታተለ የሚያጠቃዉ ይህንኑ መከረኛ የአማራ ብሄረሰብ ነዉ። ወያኔዎች ለአማራ ብሄረሰብ ያላቸዉን ጥላቻ ላለፉት 34 አመታት በስድብ፤ በንቀትና አማራዉን በጅምላ በማንኳሰስ አሳይተዋል። ባለፉት አስር አመታት ደግሞ ኦሮሚያ፤ ቤንች ማጂና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዉስጥ የአማራ ተወላጆችን ይህ የእናንተ አገር አይደለምና ወጡ እያሉ አማሮችን ከዉሃ ዉስጥ የወጣ አሳ አድርገዋቸዋል።
ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት በግልጽ እንዳየናቸዉ የወያኔ መሪዎች አማራዉን በመዝለፍና በማፈናቀል ብቻ አልተገቱም፤ ይልቁንም አማራዉን ኢትዮጵያ ዉስጥ ለተከሰቱ ችግሮች ሁሉ ብቸኛ ተጠያቂ በማድረግ ይህንን በህዝብ ቁጥሩም ሆነ በታሪክ ስፋቱ አንጋፋ የሆነዉን ብሄረሰብ በሌሎቹ የአገራችን ብሄረሰቦች እንዲጠላና በአይነ ቁራኛ እንዲጠበቅ አድርገዋል። በዚህ የተነሳ ወያኔ ባለፉት ሃያ አራት አመታት ጠፍጥፎ የፈጠሯቸዉ በየክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ምስለኔዎች ምንም አይነት ችግር ባጋጠማቸዉ ቁጥር የችግራቸዉ መንስኤ አድርገዉ የሚወስዱት የአማራዉን ብሄረሰብ ነዉ። ዛሬ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች፤ ቤንች ማጂና ቤኒሻንጉል ዉስጥ አማራዉን አገርህ አይደለምና ዉጣ የሚባለዉ የዘረኝነት አባዜም ቢሆን የዚሁ ወያኔ ለረጂም አመታት በህዝብ መካከል ሆን ብሎ የዘራዉ ጥላቻ ዉጤት ነዉ።
ወያኔ እራሱን የኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዐት አባት አድርጎ በማቅረብ ብዙ ምዕራባዉያን መንግስታትንና ዋና ዋና ለጋሽ አገሮችን ከጎኑ ማሰለፍ ችሏል። ይህ የማጭበርበር ልምዱ ደግሞ የምርጫ ኮሮጆ እየሰረቀ ተመረጥኩ ያለባቸዉንና ድምጼ ይከበር ብሎ የጠየቀዉን ህዝብ በጥይት የጨፈጨፈበትን ምርጫ አንደ ትክክለኛ ምርጫ አድርጎ ለምዕራባዉያን በመሸጥ ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ አግኝቶበታል። ዘንድሮም ለሚደረገዉ ምርጫ እነዚሁ ምዕራባዉያን አጎሮች በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በኩል 15 ሚሊዮን ዶላር ወያኔን ለማስታቀፍ ሽርጉድ እያሉ ነዉ።
ኢትዮጵያ ዉስጥ የወያኔ ጥላቻና ዘረኝነት በከፍተኛ ደረጃ ከተንጸባረቀባቸዉ ቦታዎች አንዱና ዋነኛዉ ወያኔ ፈጠርኩት ወይም ጀመርኩት ብሎ የሚነግረን የመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ስርዐት ነዉ። በዚህ የወያኔ መድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ስርዐት ዉስጥ በአንድ በኩል ወያኔና ወያኔ በአምሳሉ የፈጠራቸዉ ድርጅቶች አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ በህጋዊ መንገድ የፓለቲካ ፓርቲ ብሎ የመዘገባቸዉ ነገር ግን በጠላትነት ፈርጆ የሚዋጋቸዉ ድርጅቶች አሉ። እነዚህ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በስም፤ በስትራቴጂና በአንዳንድ የፖለቲካ አቅጣጫዎች የሚለያዩ ቢሆንም ወያኔ ሁሉንም ትምክተኞች፤ ሽብርተኞች፤ የቀድሞ ስርዐት ናፋቂዎች ወይም የአማራ ልህቃን ፓርቲ እያለ ነዉ የሚጠራቸዉ። በወያኔ ቤት የህወሓትን ዘረኛ አምባገነን ስርዐት አጥብቆ የሚቃወምና ኢትዮጵያዊነትን ደጋግሞ የሚሰብክ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ከየትም ይምጣ ከየት የአማራ ልህቃን ፓርቲ ወይም ትምክህተኛ አማራ ተብሎ ነዉ የሚፈረጀዉ።
ይህ ርካሽና ጎታች የወያኔ ፓለቲካ ወያኔ በአማራ ብሄረሰብ ላይ ያለዉን ስር የሰደደ ጥላቻ ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ያለዉን ከፍተኛ ንቀት ያሳያል። ወያኔ የአገሩ አንድነት መደፈርና የሰብዓዊ መብቱ መረገጥ አንገብግቦት “ኢትዮጵያ” “ኢትዮጵያ” እያለ ድምጹን ከፍ አድርጎ የሚያሰማዉን ሁሉ ትምክህተኛ አማራ እያለ በተጣራ ቁጥር ሌሎቹን የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች አናንተ ኢትዮጵያዉያን አይደላችሁም ወይም ኢትዮጵያዊነት እናንተ ላይ የተጫነ ዕዳ ነዉ ብሎ እየነገራቸዉ ነዉ። ይህ ክፉና መዘዘኛ የሆነ ፀረ ኢትዮጵያ አባባል ደግሞ በሌላ መልኩ ህገ መንግስቱ ዉሰጥም የተቀመጠ አባባል ነዉ። የወያኔን ህገ መንግስት አንቀጽ 39 በትክክል ከተመለከትነዉ አንቀጹ የሚለዉ ኢትዮጵያዊነትን የማይፈልግ ሁሉ መገንጠልና የራሱን መንግስት መመስረት ይችላል ነዉ ። ወያኔ ሺ ግዜ ቢነግሩት ፍጹም የማይገባዉ የዉኃ ዉስጥ ድንጋይ ስለሆነ ነዉ እንጂ ቢገባዉማ ኖሮ እሱ በነጋ በጠባ ፀረ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስተምራቸዉ ደቡብ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች ይጠቅመናል፤ ያግባባናል ወይም የኤኮኖሚ ግኑኝነታችንን ያጠናክርልናል ብለዉ የክልላቸዉ የስራ ቋንቋ አድርገዉ የመረጡት አገራችን ዉስጥ የስራና የመግባቢያ ቋንቋ የሆነዉን አማርኛን ነዉ።
ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በወጣትነታቸዉ የተጠናወታቸዉን ፀረ አማራ በሽታ ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ ለእያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ ለማስተላለፍ ያላደረጉት ነገር የለም። ደግነቱ ግን አንዳንድ እንደነሱ በዘር በሽታ ከተለከፉ ጥቂት ህሙማን ዉጭ የወያኔን ፀረ ህዝብና ፀረ አገር ሃሳብ ተቀብሎ ያስተናገደ ማንም የለም። ሆኖም ወያኔዎች የአገሪቱን የሜድያ ተቋሞች ሙሉ በሙሉ ስለሚቆጣጠሩ ይህንን ፀረ አማራ ፕሮፓጋንደዳቸዉን ለኢትዮጵያ ህዝብ ማስታለፈቸዉን እንደቀጠሉበት ነዉ። ባለፉት ጥቂት አመታት በግልጽ እንዳየነዉ ደግሞ ወያኔ ይህንን ፀረ አማራ ዘመቻዉን እስከዛሬ ካስተናገደበት ከአገር አቀፍ መድረክ ወደ አለም አቀፍ መድረክ ይዞት እየሄደ ነዉ። በቅርቡ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ይፋ የሆኑ ሪፖርቶች በግልጽ እንዳሳዩን አንዳንድ ታሪክን አገላብጠዉ ማየት የተሳናቸዉና በተለይም የኢትዮጵያን ማህበረሰባዊ አደረጃጀት በሚገባ ያላጤኑ ሀላፊነት የጎደላቸዉ አለም አቀፍ ተቋሞች ይህንን ወያኔ በግርድፉ የሚያቀርብላቸዉን ፀረ ህዝብ ፕሮፓጋንዳ እንደትክክለኛ መረጃ በመዉሰድ የወያኔ ወጥመድ ዉስጥ ሰተት ብለዉ ሲገቡ ተስተዉሏል።
በያዝነዉ ወር በተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ስር የሶማሊያንና የኤርትራን ጉዳዮች የሚከታተለዉ ቡድን ለንባብ ባበቃዉ ሪፖርት ዉስጥ የወያኔን መዝገብ እያገላበጠ ያገኛቸዉን ፍጹም መሠረተ ቢስ የሆኑ መረጃዎች በመጠቀም የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን ስም ሲያጎድፍ ታይቷል። ይህ አለምአቃፋዊ ተቋም ገለልተኝነቱንና አለምአቀፋዊነቱን ዘንግቶ የአንድ ዘረኛ አምበገነን አገዛዝ ቃል አቀባይ በመሆን ከዘረኝነትና ከአምባገነንነት ለመላቀቅ ከወያኔ ጋር ትንቅንቅ ዉስጥ የገባዉን የኢትዮጵያ ህዝብ አሳዝኗል።
ይህ ተጠሪነቱ ለጸጥታዉ ምክር ቤት የሆነዉ ቡድን የተሰጠዉ ሃላፊነት የኤርትራንና የሶማሊያን ጉዳዮች መከታተል ሆኖ ሳለ በሪፓርቱ ላይ በግልጽ እንደታየዉ ግን በወያኔ ትዕዛዝ ግንቦት ሰባትንና በጸባየ ብልሹነታቸዉ ከግንቦት ሰባት የተሰናበቱ ግለሰቦችን ጉዳይ የሪፖርቱ ማዕከል አድርጎ አዉጥቷል።የዚህ ሃላፊነት የጎደለዉ ቡደን ሪፖርት የሚጀምረዉ ግንቦት 7 የታገደ ወይም የተከለከለ ድርጅት ነዉ እያለ ነዉ፤ ሆኖም ማን እንዳገደዉና የት አገር እንደታገደ ምንም ያለዉ ነገር የለም። ከዚህ በተጨማሪ እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር በግንቦት 2008 ዓም ከአራቱም ማዕዘናት የነጻነት፤ የፍትህና የእኩልነት ጥማት ባሰባሰባቸዉ ኢትዮጵያዉያን የተመሰረተዉን ግንቦት 7 ንቅናቄ በ2009 ዓም በአማራ ልህቃን የተመሰረተ ድርጅት ነዉ በማለት ወያኔ የሰጠዉን መረጃ ቅንጣት ታክል የማጣራት ስራ ሳይሰራ እንዳለ በሪፖርቱ ዉስጥ አጠቃልሏል። ኤርትራን አስመልክቶ ሪፖርቱ ዉስጥ የተጠቃለለዉን ዘገባ ለማረጋገጥ ሪፓርቱን ለኤርትራ መንግስትና በተመድ ለኤርትራ አምባሳደር ሌኬ ነበር የሚለዉ ይህ አሳፋሪ ቡድን ግንቦት 7ን በተመለከተ ወያኔ ያሳቀፈዉን የዉሸት መረጃ እንዳለ በማቅረብ ተጠሪነቱ ለተመድ የጸጥታዉ ምክር ቤት ሳይሆን ለወያኔ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
ለመሆኑ አንድ የተመድ አካል የሆነ ቡድን በአገሮችና በፓለቲካ ድርጅቶች ጉዳይ ምን አግብቶት ነዉ አንድን ድርጅት የዚህ ወይም የዚያ ብሄረሰብ ድርጅት ነዉ ብሎ ሪፖርት የሚያወጣዉ? ምክንያቱ ሰንካላና መሰረተ ቢስ ቢሆንም ወያኔ ግንቦት 7ን የአማራ ድርጅት ነዉ የሚልበት የራሱ የሆነ ምክንያት አለዉ፤ የተመድ አካል የሆነ ድርጅት ግን ምን አይነት ምክንያት ቢኖረዉ ነዉ እሱ እራሱ በዘር የተደራጀዉ ወያኔ የአያሌ ኢትዮጵያዉያን መሰባሰቢያ የሆነዉን ግንቦት ሰባትን የአማራ ልህቃን ድርጅት ነዉ ብለህ ዘግብ ሲለዉ አሜን ብሎና ሪፖርት ጽፎ ለአለም ህዝብ ያቀረበዉ?
ወያኔ ግንቦት 7ን ብቻ ሳይሆን አጥብቀዉ የሚቃወሙትንና የዘረኝነት ፖሊሲዉን የሚያጋልጡ ኃይሎችን ሁሉ ሽብርተኛ፤ ትምክህተኛ ወይም ስልጣን ናፋቂ አማራ እያለ ነዉ የሚጠራቸዉ። በወያኔ ቤት የኢትዮጵያን አንድነት የሚሰብክ ሁሉ ትምክተኛ አማራ፤ የመብት፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ የሚያነሳ የድሮዉን ስርዐት ናፋቂ፤ እኩልነትንና ፍትሃዊነትን እየዳሰሰ የሚጽፍ ጋዜጠኛና ጦማሪ ደግሞ ሽብርተኛ ነዉ። አማራንና የአማራን ባህል ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳዉ ወያኔ የእያንዳንዱ ችግር መንስኤ አማራ ነዉ ብሎ ቢናገር ብዙ አይገርመንም። ከጄኔራል ሳሞራ የኑስ እስከ ጄኔራል ታደሰ ወረደ፤ ከስዩም መስፍን እስከ አባይ ፀሐዬ፤ ከሟቹ መለስ ዜናዊ ጃጅቶ የባጥ የቆጡን እስከሚቀባጥረዉ ስብሃት ነጋ ድረስ ሌላ ዘር ሳይደባለቅበት በትግራይ ልጆች ብቻ የተሞላዉ ህወሓት የዘረኝነት ካባ ተከናንቦ አንድ አገር ህዝብ ሲያስርና ሲገድል በአይናቸዉ የሚያዩ ሰዎች ኢትዮጵያዉያንን በዘርና በቋንቋ ሳይሆን በፖለቲካ አስተሳሰባቸዉና በአገር ወዳድነታቸዉ ብቻ ያሰባሰበዉን ግንቦት ሰባትን ወያኔ በሉ ስላላቸዉ ብቻ የአማራ ልህቃን ፓርቲ ነዉ ማለታቸዉ ግን እጅግ በጣም ይገርማልም ያሳዝናልም።
የወያኔን ዘረኛ ስርዐት ለማጥፋት የምንታገል ኢትዮጵያዉያን በሙሉ ይህንን ወያኔ “የአማራ ልህቃን” በሚል ቅኝት ቃኝቶ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ የለቀቀዉን ነጠላ ዜማ በሚገባ ልንቃኘዉና ማርከሻዉን ልናዘጋጅለት ይገባል። ወያኔ አገር ቤት ዉስጥ እስከዛሬ ካጋጠመዉ መዐት ሁሉ ጋር በማያያዝ ያሰራጨዉ ፀረ አማራ ፕሮፓጋንዳ አገራችን ኢትዮጵያን ምን ያክል እንደጎዳት አይተናል። ዘንድሮ ወያኔ ጭራሽ ብሶበት አማራንና ሽብርተኝነትና ከስልጣን ጥማት ጋር በማያያዝ አለም አቀፉን ህብረተሰብ አማራን አንድ በሉልኝ እያለ ነዉ። “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ ይህንን ለጆሮ የሚቀፍ የወያኔ ነጠላ ዜማ ገበያ ላይ ከመዋሉ በፊት አሁኑኑ ማጥፋት አለብን። የወያኔን ፀረ አማራ ዘመቻ እንደ ፀረ ኦሮሞ፤ ፀረ ሶማሌ፤ ፀረ ትግራይ ፀረ ሲዳማና ባጠቃላይ እንደ ፀረ ኢትዮጵያ ዘመቻ አድርገን በማየት ሁላችንም እንደ አንድ ሰዉ ቆመን መዋጋትና ማክሸፍ አለብን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments:

Post a Comment