Sunday, 16 November 2014

የሰንደቅ አላማችን ጠላት ወያኔና ወያኔ ብቻ ነዉ!



ሰንደቅ አላማ ለአንድ አገር ህዝብ የኩራት፤ የአልበገር ባይነት፤ የአንድነትና የታሪክ ተከታታይነት ምልክት ነዉ። ሰንደቅ አላማ በአንድ በኩል የወደፊቱን ብሩህ ተስፋ ክወዲሁ እያሳየን እየዟችሁ የሚለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በምናብ ወደኋላ እየወሰደን የድልና የመስዋዕትነት ታሪላችንን የሚያስታዉሰን የነጻነት፤ የሠላምና የብሩህ ተስፋ ማህደር ነዉ። የአገራቸን የኢትዮጵያ አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ አላማ ትናንትናና ከትናንት ወዲያ በተስፋፊዎች አለመደፈራችንን ብቻ ሳይሆን ዛሬም ዘረኞች የጫኑብንን የመከራ ቀንበር በቆራጥነት ሰብረን ነገና ከነገ ወዲያ የነፃነት አየር እንድንተነፍስ አስረግጦ የሚነግረን የአንድነታችን፤ የተገጋድሏችንና የድላችን ልዩ ምልክት ነዉ። አንድን ኢትዮጵያዊ ሰንደቅ አላማ ላንተ ምንህ ነዉ ብለን ብንጠይቀዉ ጥያቄዉን ዕድሜህ ስንት ነዉ ተብሎ እንደሚጠየቅ አንድና ሁለት ቃል ብቻ ተናግሮ አይመልስም። ሰንደቅ አላማም በአንድና በሁለት ቃላት ምንነቱ የሚገለጽ ተራ ቃል አይደለም። ኢትዮጵያዉያን ተማሩ አልተማሩ፤ ደሃ ሆኑ ኃብታም ፤ወንጀለኛ ሆኑ ወይም ሠላማዊ ለአገራቸዉ ሰንደቅ አላማ የተለየ ቦታ አላቸዉ። ሰዎች የአገራቸዉን ሰንደቅ አላማ የሚወዱትና ለሰንደቅ አላማዉ በክብር መዉለብለብ የህይወት መስዋዕትነት የሚከፍሉት ስለታዘዙ ወይም ስለ ሰንደቅ አላማዉ ተነግሯቸዉ አይደለም። በእርግጥም የሰንደቅ አላማ ክብርና የአገር ፍቅር ለሰዎች ሰንደቅ አላማዉን አክብሩ፤ አገራችሁን አፍቅሩ እየተባለ የሚነገር ነገር አይደለም። አገርንና ወገንን ማክበርና መዉደድ ሰንደቅ አላማን ከማክበርና ከማፍቀር ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነዉ።የሰንደቅ አላማ ልዪ ክብርና የአገር ፍቅር ሰዎች ተወልደዉ ከሚያድጉበት ማህበረሰብ፤ ከቤተሰብ፤ ከጎረቤትና ከጓደኛ እንደ ምግብና እንደ ዉኃ እየበሉና እየጠጡ የሚያገኙት የሰዉነትና የዜግነት መገለጫ ታላቅ እሴት ነዉ።
ለዚህም ነዉ የማንም አገር ዜጋ አገሩ ዉስጥ ቢኖር ወይም ካገሩ ዉጭ፤ ቢታሰር ባይታሰር፤ ሀብታም ቢሆን ወይም ደሃ፤ የኔ ነዉ የሚለዉን የእናት አገሩን ሰንደቅ አላማ በፍጹም የማይረሳዉ። ከአገራቸዉ ዉጭ የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ በተለይም ኢትዮጵያዉያን በተለያዩ ምክንያቶች የሚኖሩባቸዉን አገር ዜግነት ቢወስዱ እንኳን ሰንደቅ አላማቸዉን ባዩና ባስታወሱ ቁጥር የሚሰማቸዉ አገራዊ ስሜት እጅግ በጣም ከፍተኛ ነዉ – እንዲያዉም ከአገራቸዉ ተሰድደዉም ሆነ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከአገራቸዉ ዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ሰንደቅ አላማቸዉን ባዩ ቁጥር የአገራቸዉ፤ የወንዛቸዉ ፤ ተወልደዉ ያደጉበት መንደርና የልጅነት ትዝታቸዉ ባአይናቸዉ ላይ እየመጣ ዕንባ በዕንባ ይተናነቃሉ። ሰንደቅ አላማ ለአንድ አገር ህዝብ አንድ ነገር ነዉ፤ ብዙ ነገር ነዉ፤ ሁሉም ነገር ነዉ። ሰንደቅ አላማ ህዝብን ያስተባብራል፤ ያከባብራል፤ ያዋድዳል፤ መስዋዕትነትን፤ ፍቅርንና ብልፅግናን ያመለክታል።
ዛሬ የሰንደቅ አላማችንን ጉዳይ አቢይ የመወያያ አርዕት አድርገን የወሰድነዉ አለምክንያት አይደለም። በአገር ጥላቻቸዉና በስንደቅ አላማ ንቀታቸዉ የሚታወቁት የወያኔ ዘረኞች “የአብዬን ወደ እምዩ” እንዲሉ ሰንደቅ አላማቸዉ ተዋርዶ ከሚያዪ የቁም ሞታቸዉን የሚመር ትን ዉድ የኢትዮጵያ ልጆች ባንዲራዉን አዋረዱበለዉ መናገራቸዉን ስለማን ነዉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ አገሮች ተስማምተዉ የሚያከብሩት አለም አቀፉ የሰንደቅ አላማ አያያዝ ፕሮቶኮል በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሁሉም አገሮች ሰንደቅ አላማ በእኩል ደረጃ መቀመጥና መሰቀል አለበት፤ አንድ ላይ መሰቀልና አንድ ላይ መዉረድ አለበት ይላል። ይህንን ፕሮቶኮል ረስቶና ሰንደቅ አላማችንን ንቆ በአለም አቀፍ መድረክ ላይ ከሌሎች አገሮች መሪዎች ጋር የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እንደ አለባሌ ዕቃ ዘቅዝቆ ይዞ ያዋረደዉ ወያኔዎች “ታላቁ መሪ” ብለዉ የሚጠሩት ነገር ግን የለየለት የአገርና የህዝብ ጠላት የሆነዉ ዘረኛዉ መለስ ዜናዊ ነዉ። የህወሓትን ባንዲራ በየቦታዉ እየሰቀሉ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ተራ ጨርቅ ነዉ ብለዉ የሸቀጥ መጠቅለያ ያደረጉትም መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ ናቸዉ። ዛሬ ደማቅ ሰንደቅ አላማዉን አስመልክቶ በወያኔና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ያለዉ ትልቅ ልዩነት ትክክለኛዉና ህዝብ የኔ ነዉ ብሎ የተቀበለዉ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የትኛዉ ነዉ የሚለዉ ጥያቄ ላይ ነዉ አንጂ ባንዲራዉን ማክበር አለማክበር ወይም ማዋረድ ላይ አይደለም።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የእናት አገራችንን የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ታሪካዊ ተከታታይነትና ዘለዓለማዊነት አጉልቶ የሚያሳየን ከሁላችንም በላይ የገዘፈ ግዙፍ አርማ ነዉ፤ ይህ ማለት ደግሞ ሰንደቅ አላማችን ያቻትና ብሎ እንደሚያሳየን አገር አንደ ኢትዮጵያ ሙሉ ህልዉና ያለዉ ህያዉ አካል ነዉ ማለት ነዉ። ሰንደቅ አላማችንን የምንወደዉና የምናከብረዉም ህያዉ አገራችንን የሚወክል ህያዉ አካል በመሆኑ ነዉ። መለስ ዜናዊንና ስብሀት ነጋን የመሳሰሉ በጣት የሚቆጠሩ የትዉልድ ጭንጋፎች ለራሳቸዉ አገር ሰንደቅ አላማ ደንታ ላይኖራቸዉ ይችላል። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳለ ግን የህልዉናዉና የአንድንቱ መገለጫ የሆነዉን ሰንደቅ አላማ አይንቅም ወይም አያዋርድም፤ አንድ ህዝብ ባንዲራዉን የማይቀበልና የማያከብር ከሆነ ባንዲራዉ አይወክለዉም ማለት ነዉ፡ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዛሬ ያለዉ እዉነታም ይሄዉ ነዉ፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔ ባዕድ አካል የለጠፈበትን ባንዲራ የኔ ነዉ ብሎ አልተቀበለዉም ወይም ባንዲራዉ ይወክለኛል ብሎ አያምንም።
ዘርዓይ ደረስ በ1937 ዓም ሮም ዉስጥ የፋሺስት ጣሊያኖችን ጭንቅላት በገዛ አገራቸዉ እንደ ቅጠል እየጨረገደ ከጣለ በኋላ በጣሊያኖች ጥይት ቆስሎ ሲያዝ የተናገዉ የመጨረሻ ቃል ይህ የጣሊያኖች ባንዲራ ይዉረድና የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ይሰቀል የሚል የጀግንነትና የአገር ፍቅር ቃል ነበር። ጀግናዉ አብዲሳ አጋ በጣሊያን በረሃዎች ጣሊያኖችን እያሳደደ ሲገድል የኢትዮጵያ ባንዲራ ከአጠገቡ አልተለየችም። በቀዳማዊ ኃ/ስላሤና በደርግ ዘመነ መንግስት ተማሪዎች ጧት ወደ ክፍል ከመግባታቸዉ በፊት ተሰልፈዉ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በክብር ይሰቅሉ ነበር፤ ማታም ወደ ቤታቸዉ ከመሄዳቸዉ በፊት ጧት በክብር የሰቀሉትን ባንዲራ በክብር አዉርደዉ ነበር ወደየቤታቸዉ የሚሄዱት። ዛሬ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ጨርቅ ነዉ ብለዉ የተሳደቡና በዚህ ሰንደቅ አላማ ከገበያ የገዙትን ሸቀጥ እየጠቀለሉ አስራ ሰባት አመት የከረሙ ምናምንቴዎች ናቸዉ በሰንደቅ አላማ ክብርና በአገር ፍቅር ታንጾ ያደገዉን ኢትዮጵያዊ ሰንደቅ አላማዉን አዋረደ እያሉ የአዞ እምባ የሚያነቡት።
ሰንደቅ አላማ በዜጎች ልብ ዉስጥ አንደ እሳት የሚቀጣጠል የአገር፤ የህዝብና የዜግነት መገለጫ የሆነ ታላቅ አርማ ነዉ። ይህ አርማ ደግሞ ከእኛነታችንና ከህልዉናችን ጋር የተጣበቀ አርማ ነዉና መንግስት በተለዋወጠ ቁጥር አይለዋወጥም። ዛሬ ወያኔ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የገባዉ የማይታረቅ ቅራኔም የሚመነጨዉ ከዚሁ ከወያኔ ግራ የተጋባ እዉነታ ነዉ። የዚህ ዘመን ትዉልድም ሆነ ለዚህ ዘመን ትዉልድ አገርና ሰንደቅ አላማ አስረክቦ ያለፈዉ የቀድሞዉ ትዉልድ ሰንደቅ አላማዬ ብሎ የሚጠራዉና ወያኔ የኢትዮጵያ ባንዲራ እያለ የሚጠራዉ ነገር የተለያዩ ናቸዉ።
ባለፉት 75 አመታት አራት ኪሎ ቤ/መንግስትን የተቆጣጠሩት ሦስት ኃይሎች ማለትም የቀኃስ፤ የደርግና የወያኔ አገዛዞች ሁሉም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከራሳቸዉ ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል። በንጉሡና በደርግ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የይሁዳ አንበሳና የወታደራዊዉ መንግስት አርማ ነበረበት፤ ሆኖም እነዚህ ሁለት አርማዎች ያረፈበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በቤተመንግስትና ንጉሡና ፕሬዚዳንቱ በሚጓዙባቸዉ ኦቶሞቢሎች ላይ እንጂ ሌላ ቦታ አይታዩም ነበር። በመላዉ አገሪቱ በየቀኑ ጧት እየወጣ ማታ ሲመሽ የሚወርደዉና በየግለሰቦች ቤት የሚገኛዉ ሌጣዉ አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀዩ ሰንደቅ አላማ ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብም ሰንደቅ አላማዬ ነዉ ብሎ የሚያምነዉና የሚቀበለዉ ይህንኑ ምንም አይነት ባዕድ አካላ የሌለበትን አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ አላማ ነዉ።
ወያኔዎች ጫካ ዉስጥ ሆነዉ የትጥቅ ትግል በሚያካሄዱበት ወቅት ያነገቡትና ነጻ አወጣን ባሉበት ቦታ ሁሉ የሰቀሉት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሳይሆን የህወሓትን ባንዲራ ነበር። ከብዙ መረጃዎች እንደተረዳነዉ ወያኔዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አንደ ተራ ጨርቅ ቆጥረዉ ዕቃ መጠቅለያ አድርገዉት ነበር፤ ይህ ደግሞ የለየለት የጥላቻና የንቀት ምልክት ነዉ።
በአርግጥም ዋና ዋናዎቹ የወያኔ መሪዎች እነ ነመለስ ዜናዊና እነ ስብሐት ነጋ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ህዝብ ይጠሉ ስለነበር ለነሱ ትልቁ ቁም ነገር ህወሐትና የዘረኝነት ምልክት የሆነዉ የህወሓት ባንዲራ ነዉ እንጂ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ አልነበረም። ይህ ፀረ ህዝብና ፀረ አገር ባህሪያቸዉ ደግሞ ጫካ ዉስጥ ብቻ ተወስኖ የቆየ ባህሪ ሳይሆን አዲስ አበባ ገብተዉ ክህዝብ ጋር ሲቀላቀሉም በግልጽ የታየና ምን ግዜም ሊደበቅ የማይችል ባህሪይ ነዉ። የወያኔዉ ቁንጮ መለስ ዜናዊ እኛ ኢትዮጵያዉያን የምናከብዉንና የምንወደዉን ሰንደቅ አላማ “ጨርቅ” ብሎ መጥራቱ አዲስ የጀመረዉ ነገር ሳይሆን ከጫካ ይዞት የመጣዉ የተለመደ አባባል ነዉ። መለስ ዜናዊ ይህንን ጸያፍ ድፍረቱንና ፀረ ሰንደቅ አላማነቱን ለማረሳሳት የባንዲራ ቀን ብሎ ቢያዉጅም የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ልጆቹ፤ አባቶቹ፤ አያቶቹና ቅድም አያቶቹ የተሰዉለት ሰንደቅ አላማ በአለባሌ ሰዉ አንደበት “ጨርቅ” ተብሎ የተጠራበትን ቀን ምን ግዜም አይረሳም።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ የወያኔ ዘረኞች ኢትዮጵያዉያንን በተለይም በዉጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ባንዲራቸዉን አያከብሩም ወይም ባንዲራዉን አዋረዱ እያሉ መክስስ ጀምረዋል። በነገራችን ላይ ከወያኔዎችና ከጥቂት ሆዳም ተከታዮቻቸዉ ዉጭ የኢትዮጵያ ህዝብ አገር ዉስጥም በዉጭ አገሮችም በሰንደቅ አላማዉ ላይ ያለዉ አቋም ተመሳሳይ ነዉ። ወያኔ ሰንደቅ አላማዉ ላይ ባዕድ አካል ለጥፎ ከዛሬ ጀምሮ ሰንደቅ አላማችሁ ይህ ነዉ ብሎ አዋጅ ሲያወጣ አዋጁን የሰማለት አንድም ሰዉ አልነበረም። እንዲያዉም ህዘብ ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጣ፤ ሰርግ ሲደግስ፤ ኳስ ጨዋታ ሲሄድና በተለያዪ ቦታዎች ደስታዉንና ኃዘኑን ሲገልጽ አንግቦ የሚወጣዉ የወያኔን ባንዲራ ሳይሆን አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀዩን ሰንደቅ አላማ ነበር። ወያኔ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ የቀየረዉ በጠመንጃ ሀይል እንደሆነ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን የማይወደዉንና በሀይል የተጫነበትን ባንዲራ ተቀብሎ እንዲኖር ያደረገዉም በጠመንጃ ሀይል ነዉ።
ለመሆኑ እነሱ እራሳቸዉ የለየላቸዉ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ጠላት የሆኑት የወያኔ መሪዎች በዉጭ አገሮች የሚኖሩና አክርረዉ የሚቃወሟቸዉን የኢትዮጵያ ልጆች ባንዲራዉን አዋረዱ እያሉ ተደጋጋሚ ክስ የሚያሰሙት ለምንድነዉ? አንዳንድ ከህልዉናቸዉ ይልቅ ለማይጠረቃዉ ሆዳቸዉ ያደሩ ደካማ ግለሰቦችስ ይህንን የወያኔ መሠረተ ቢስ ክስ እየሰሙ አንደ ገደል ማሚቶ ደግመዉ ደጋግመዉ የሚያስተጋቡት ለምንድነዉ? አገራችን ኢትዮጵያ ሁለት የተለያዩ ባንዲራዎች ሊኖራት እንደማይችል ሁላችንም እናዉቃለን። ለመሆኑ ይህ እኛ ሰንደቅ አላማ እነሱ ባንዲራ እያልን የምንጠራዉ ነገር አንድና ተመሳሳይ ነዉ? ወያኔና በየቦታዉ ያስቀመጣቸዉ የገደል ማሚቶዎች ከሁሉም ነገር አስቀድመዉ መመለስ ያለባቸዉ ይህንን ጥያቄ ነዉ። እኛ ኢትዮጵያዉያን ከህጻንነታችን ጀምሮ የኛ ነዉ እያልን ያሳደገንን፤ የመራንን፤ አቅጣጫ ያሳየንነና በተለይ በልጅነታችን ት/ቤት እያለን ጧት በክብር ሰቅለን ማታ ላይ በክብር እያወርድን በክብር እናስቀምጥ የነበረዉን አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ አላማችንን ማክበርና መዉደድ ብቻ ሳይሆን ለዚህ ሰንደቅ አላማ ዘለዓለማዊነት አንድ ህይወታችንን እንሰጣለን። ሰንደቅ አላማዉን የማያከብር ህዝብ የለም፤ እኛም ኢትዮጵያዉያን ሰንደቅ አላማችንን እንወዳለን፤ እናከብራለንም፤ የምንወደዉና የምናከብረዉ ሰንደቅ አላማ ግን ባዕድ አካል የተለጠፈበትን የወያኔን ባንዲራ ሳይሆን የነፃነታችን፤ የእንድነታችን፤ የሰላማችንና የመዋዕትነታችን ምልክት የሆነዉን አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀዩን ሰንደቅ አላማ ነዉ። ይህንን ሰንደቅ አላማ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳንሆን ይህንን የጥቁር ህዝብ የነጻነትና የመስዋዕትነት ታሪክ ምልክት የሆነ ደማቅ ሰንደቅ አላማ አያሌ አፍሪካዉያንም ያከብሩታል። ለምሳሌ የስምንት የአፍሪካ አገሮች ባንዲራ አቀማመጡ ይለያያል አንጂ ቀለሙ አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ነዉ፤ ከዚህ በተጨማሪ የሌሎች 23 አፍሪካ አገሮች ባንዲራ ደግሞ ቀዩና አረንጓዴዉ ቀለም አለበት። ይህ ሁሉ የሚያሳየን ሰንደቅ አላማችን የፓን አፍሪካ ባንዲራ እየተባለ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችም የሚከበርና የብዙ አፍሪካ አገሮች ሰንደቅ አላማ መሰረት መሆኑን ነዉ።
የወያኔ ዘረኞች ኢትዮጵያ ዉስጥ የነበሩትንና በዉጭ አገሮች የሚገኙ አማራጭ የመረጃ ምንጮች ሁሉ ጥርቅም አድርገዉ ዘግተዉ እንደቤት ዉስጥ ዕቃቸዉ በሚቆጣጠሩት ቴሌቪዥን፤ ሬዲዮና ጋዜጣ “በሬ ወለደ” አይነት ዉሸታቸዉን ጧትና ማታ በተደጋጋሚ አየተናገሩ ለግዜዉም ቢሆን ህዝብን ማደናገር ይችሉ ይሆናል። ሰንደቅ አላማዉን የሚወደዉንና የሚያከብረዉን ኢትዮጵያዊም እነሱን ስለተቃወመ ብቻ ባንዲራዉን አዋረደ እያሉ ህዝብን ሊያታልሉ አንዳንድ ወደ ገባዎችንና ጥቂት የዋሆችን ሊያሳምኑ ይችሉ ይሆናል። ሆኖም የኢትዮጵያን ህዝብ እንወዳለን ፤ ለኢትዮጵያ አንድነት እንቆማለን፤ የዚህ አንድነት ምልክት የሆነዉን ሰንደቅ አላማም እናከብራለን አያሉ ታቦት ተሸክመዉ ቢምሉም የሚያምናቸዉ ቀርቶ ከጉዳይ ቆጥሮ የሚሰማቸዉ አንድም ዜጋ የለም። የወያኔ ዘረኞችና ቡችሎቻቸዉ የሚባቸዉ ቢሆን ኖሮ ዉስጣችን ያለዉን ከፍተኛ የአገር፤ የወገን፤ የባንዲራና የሉዓላዊነት ስሜት ደግመን ደጋግመን እንነግራቸዉ ነበር፡ ሀኖም እነሱን ከማስወገድ ጀምሮ አገራችንን እስከማረጋጋት ድረስ ብዙ አስቸኳይ የሆነ አገራዊ አደራና አገራዊ ስራ ይጠብቀናልና ለዛሬዉ እዚህ ላይ እናብቃ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ያሸንፋል!

No comments:

Post a Comment