Monday, 21 September 2015

ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ የተሰጠ መግለጫ


September 15, 2015
መስከረም 3 ቀን 2008 ዓ.ም
def-thumbበኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ባጠቃላይና በተለይ ደግሞ ህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ስልጣኑን በተቆጣጠረባቸው ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ውስጥ ህወሓት/ኢህአዴግን እንቃወማለን በሚለው ወገን ገንነው የመጡ ሁለት አፍራሽና ኋላቀር የፖለቲካ አዝማሚያዎች (trends ) አሉ። ከነኝህ ውስጥ አንደኛው ራስን በፖለቲካ አመለካከት ዙሪያ ከማሰባሰብ ይልቅ በጎጥና በዘውግ ደረጃ የመመልከትና ሀገራዊ ፖለቲካን በደም ቆጠራ የመመንዘር አባዜ ነው። ሁለተኛውና ከዚሁ ያልተናነሰው ችግር የፖለቲካ ድርጅት በመሰረታዊ ያመለካከት መርሆች ዙሪያ ሰፋ ያለ የማህበረሰብ ክፍልን የማሰባሰቢያ ድንኳን መሆኑ ቀርቶ፤ በስራ ሳይሆን ድንገተኛ አጋጣሚን በመጠበቅ ትርፍ ለማጋበስ በሚቋምጡ ሰነፍ “ነጋዴዎች“ የተቋቋሙ ሩቅ የማይሄዱ የንግድ ድርጅቶች ይመስል በተግባር ምንም የማይፈይዱ ”የፖለቲካ ድርጅቶች“ እንደ አሸን የመፍላታቸው ፈሊጥ ነው። እነኝህ ሁለቱም አዝማሚያዎች የህወሓት/ኢህአዴግን ህይወት ከማራዘም አልፈዉ ማህበረሰቡን ወደሚመኘው እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አንድ ጋት እንኳን ፈቀቅ አላደረጉትም። ይልቁንም ዴሞክራሲን የሚናፍቁ ታጋዮች ተሰባስበውና ተጠናክረው ስርዓቱን ከመግፋት ይልቅ በግለሰብ ደረጃ ወይንም በትናንሽ ቡድኖች በመሰባሰብ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በስርዓቱ በቀላሉ እየተመቱ ብዙ ታጋዮች ለሞት፤ ለስቃይና ለእስር ተዳርገዋል። አሁንም እየተዳረጉ ነው።
የዚህ አይነት የትግል አካሄድ ሩቅ እንደማያስኬድ የኢትዮጵያ ህዝብ ከተገነዘበው ቆይቷል። ይህ አካሄድ እንዲቀየርና የፖለቲካ ሀይሎች ተሰባስበው ይህንን በስልጣን ላይ ከሚገባው በላይ የቆየና አገሪቱን ለውርደት የዳረገ የጥቂት ዘራፊዎች ቡድን ከጫንቃው ላይ እንዲያነሱለት ሲማጠን ቆይቷል። ምንም እንኳን በመሪዎች ድክመት የሚመኘውን ዳር መድረስ ባይችልም ባጭር ጊዜ ልምዱ በትንሹም ቢሆን የተባበረ ትግል ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም በመጠኑም ቢሆን አይቶታል።
ይህ የህዝብ ፍላጎት መኖር ግን በራሱ ይህንን የተባበረ ሰፊ ማህበራዊ እንቅስቃሴ መፍጠርን ቀላል ያደርገዋል ማለት አይደለም። በብዙ ስራ፤ በብዙ ድካምና ያላሰለሰ ጥረት የሚፈጠር እልህ አስጨራሽ ሂደት ነው። ባንድ በኩል እንዲህ አይነት ሰፊ የህዝብ እንቅስቃሴ በስልጣኑ ለመቆየት የሚፈጥርበትን ችግር የሚረዳው በስልጣን ላይ ያለው የዘራፊዎች ቡድን ይህን እንቅስቃሴ ከወዲሁ ለማምከን ያለ የሌለ የገንዘብ፤ የስለላና የተንኮል ሀይሉን ይጠቀማል። በተቃዋሚ ድርጅቶች ውስጥ ሰርጎ በመግባትና ደካማ ሀይሎችን በገንዘብ በመግዛት ወይንም በማስፈራራት እንዲህ አይነት ትብብሮች እንዳይፈጠሩ ከውስጥ ለመቦርቦር ተግቶ ይሰራል። በሌላ በኩል ደግሞ የትም የማያደርሳቸውን “የራሳቸውን ድርጅት” የሙጢኝ ብለው ለትልቅና አገራዊ አላማ እራሳቸውን ላለማስገዛት የቆረጡ ደካማ “የድርጅት መሪዎች” እንዲህ አይነቱን የጋራ እንቅስቃሴ በራሳቸው ግብዝነትና ስግብግብነት ምክንያት ብቻ ሊያሰናክሉት መሞከራቸው አይቀርም።
ይህ ግን ጊዜው ያለፈበት አዝማሚያ ነውና የሚሳካ ሙከራ አይሆንም። የተናጠል ትግል ሂደት ማብቂያው ጊዜ ተቃርቧል። የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚታገሉ ኃይሎች እንዲህ አይነቱን ፋይዳ ቢስ ሂደት የመቀበል ትዕግስታቸው ተሟጧል። በቅርብ ጊዜ የሞላ አስገዶምን መክዳት በማስመልከት የትህዴን አመራር ባወጣው መግለጫ “ኢትዮጵያን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለማድረግ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር አብሮ መስራት የድርጅታችን መሰረታዊ መርሆ ነው” እንዳለው ይህ መሰረታዊ መርሆ በሀገራችን የጸረ ህወሓት/ኢህአዴግ ትግል የበላይነት ይዞ እየመጣ ያለ እጅግ አስፈላጊና ለድሉም ወሳኝ የሆነ የጊዜው የፖለቲካ አዝማሚያ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ይህን መሰረታዊ መርሆ ከምር ወስዶ የሚንቀሳቀስ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነው።
ይህ አዲስ የፖለቲካ አዝማሚያ ምቾት የማይሰጣቸው የፖለቲካ ኃይሎች መኖራቸው የሚጠበቅ ነው። የህወሓት/ኢህአዴግ የስለላ ድርጅት ከሰሞኑ ሞላ አስገዶምን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ በግልጽ እንዳስቀመጠው ኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲ ኃይሎች ተሰባስበው እንዳይታገሉና ስርዓቱን እንዳይፈታተኑ የማያደርገው ጥረት የለም። በዚህ በህወሓት/ኢህአዴግ መሰሪ እንቅስቃሴ ደግሞ በቀላሉ መጠቀሚያ የሚሆኑት በጋራ የሚደረግ ትግል በግለሰብ ደረጃ ያሳጣናል ብለው የሚፈሩት “የግል ጎጆና” ጥቅም የሚያስጨነቃቸው ደካማ የፖለቲካ መሪዎች ነን ባዮችን ነው። ባንጻሩ በየድርጅቶቹ ውስጥ በሚገኙት ብዙሀኑ ሩቅ አሳቢ መሪዎች ጥረትና በተለይም ደግሞ ይህን ትግል ለአላማ እንጂ ለሌላ ምንም አይነት የግል ጥቅም ያልተቀላቀሉና በትግሉ ሂደትም ትልቁን ሚና በሚጫወቱት ብዙሀን ታጋዮች አልበገር ባይነት እንዲህ አይነት ደካማ መሪዎች ተከታይ በማጣት ሲዳከሙና በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በድርጅታቸው ውስጥ የሚነሳባቸውን ተቃውሞ መቋቋም ባለመቻላቸው በቀላሉ እየተፍሸለሸሉ ከመራገፍ በስተቀር በድርጅቶቹ ላይ ከባድ ጉዳት ሳያደርሱ ይከስማሉ።
በህወሓት/ኢህአዴግ “የስለላ ድርጅት አቀናባሪነት” በሞላ አስገዶም መሪነት ከሰሞኑ የተሞከረው የማፍረስ ንቅናቄ ከሽፎ ወደ ተስፋ መቁረጥ የክህደት እንቅስቃሴ የተቀየረው የሰሞኑ ሙከራም የዚህ አጠቃላይ ሂደት አካል ነው። በዚህ የከሸፈ ሙከራ ውስጥ እጅግ የሚገርመውና የትህዴንን ብዙሀን አመራሮች ብስለት፤ የድርጅቱን መዋቅራዊና ድርጅታዊ ጥንካሬ፤ እንዲሁም ብዙሀኑ ታጋይ ለጋራ ትግል ያለውን ቆራጥ አቋም ያስመሰከረው፤ ይህንን የማፍረስ ሙከራ የመራውና ሳያሳካለት በመጨረሻም በጣም ጥቂት ተከታዮቹን ብቻ ይዞ የከዳው ለረጅም ጊዜ የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበረው ሞላ አስገዶም መሆኑ ነው። እንዲህ አይነት የመክዳት ሂደት ባጭር ጊዜ በማህበረሰባችን ላይ የሚፈጥረውን አስጨናቂ ስሜት የምንረዳው ቢሆንም ከዚያ በላይ ልንረዳው የሚገባው ግን በእንዲህ አይነት ከፍተኛ ያመራር ቦታ የነበረ ሰው ሙከራ አለመሳካት በእርግጥም የሀገራችን ፖለቲካ እየበሰለ፤ ከግለሰብ አመራሮች ተጽእኖ እየተላቀቀ፤ አዲስ የተባብሮ መታገል አቅጣጫን እያበሰረ እየሄደ መሆኑንና በትናንሽ ሰዎች መግተርተር ይህ ሂደት የማይቀለበስ መሆኑን የሚያመለክት የረጅም ጊዜ ግኝት መሆኑን ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 በዚህ አጋጣሚ ለትህዴን ብዙሀን አመራርና ለሰፊው ታጋይ በመርህ ላይ ለተመሰረተው አቋማቸውና መርሃቸውን ለማስጠበቅ ለሚያደርጉት ቆራጥ ትግል ያለውን ጓዳዊ አክብሮት ይገልጻል። በመግለጫቸው ላይ በግልጽ ያስቀመጡት መርሆአቸው የኛም መርሆ መሆኑን ስንገልጽላቸው በታላቅ ኩራት ነው። ድርጅታቸውን እያጸዱ የተመሰረቱበትን መርሆ ጠብቀው ለመጓዝ ባሳዩት ቁርጠኝነትና ወደፊትም በሚያደርጉት ትግል ምንጊዜም ከጎናቸው መሆናችንንና ጓዳዊ ድጋፋችን ምንጊዜም እንደማይለያቸው በዚህ አጋጣሚ ደግመን ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን። በመግለጫቸው ላይ እንዳሉትም ይህ ትግል ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሳያደርግ የማይቆምና እንዲያውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለኢትዮጵያ ህዝብም በየጊዜው በሚፈጠሩ እንቅፋቶች ላይ ሳያተኩር ትግሉን በሙሉ ልብ እንዲደግፍ ያደረጉት ጥሪ የኛም ጥሪ ነው።
አንድነት ኃይል ነው!!!
አርበኞች ግንቦት 7: ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ

መልካም አዲስ ዓመት – ድጋፍ ለአገር አድን ንቅናቄ


September 12, 2015
def-thumb“የኢትዮጵያ አገር አድን በዲሞክራሲ የጋራ ንቅናቄ” ምስረታ ዜና በአዲስ ዓመት መባቻ መሰማቱ ትልቅ የምሥራች ነው። ይህንን ንቅናቄ ለመመስረት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምስጋና ይገባቸዋል።
የኢትዮጵያ አገር አድን በዲሞክራሲ የጋራ ንቅናቄ መመስረት የህወሓት አገዛዝን ተጋግዞ ለመጣል ከማስቻሉም በላይ ድሉ የአንድ ወይም የጥቂት ድርጅቶች ድል ከመሆን ይልቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ድል እንዲሆን ያስችላል። ከዚህም በተጨማሪ ከህወሓት አገዛዝ በኋላ የተባበረች ኢትዮጵያ እንደምትኖረን ማስተማመኛ ከሚሰጡን ነገሮች ዋነኛው ዛሬ የምናደርጋቸው ትብብሮች ናቸው። የአገር አድን ንቅናቄ ዛሬ የምናደርገውን ትብብር መዋቅራዊ ገጽታ የሚሰጠው እና ዘለቄታነት እንዲኖረው የሚያግዝ በመሆኑ ለአገራችን ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ የሚሰጠው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው።
የአንድን ድርጅት ጥንካሬ ከሚወስኑ ነገሮች ዋነኛው የአባላቱና ደጋፊዎቹ ጥንካሬ ነው። የአገር አድን ንቅናቄም ጥንካሬ ከሚወስኑት ነገሮች ዋነኛው አባላትና ደጋፊው ናቸው። የአገር አድን ንቅናቄ እንዲጎለብት የምንመኝ ሁሉ ለንቅናቄው መጠናከር የምናበረክተው አስተዋጽኦ አለ። ከሁሉ አስቀድሞ ኢትዮጵያ አገራችን ከግዛቷ ውስጥ የሚገኙ ማኅበረሰቦች ሁሉ አገር መሆኗን እና እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ከሌላው ጋር እኩል መብት ያለው መሆኑን መቀበልና በተግባርም ማሳየት ይገባል። እያንዳንዱ ዜጋ እና እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ከሌሎች ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር በጋራ አገራችን የማዳን እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። በምናደርጋቸው ፓለቲካዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የዜጎችና የማኅበረሰቦች በእኩልነት መሳተፍ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ተረድተን መንቀሳቀስ ይኖርብናል። ለህወሓት “ከፋፍለህ ግዛ” ፓሊሲ መመቸት የለብንም። በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በእድሜም ሆነ በቋንቋ ሳንከፋፈል የጋራ ትኩረታችንን የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያን ማዳን ላይ እናድርግ።
በኢትዮጵያ፣ በዳር አገር እና በውጭ አገራት የሚገኙ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች ከሕይወት መስዋትነት ጀምሮ በጊዜዓቸው፣ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ንቅናቄዓቸውን ሲረዱ ቆይተዋል። በአሁኑ ሰዓት በበርካታ የዓለም ከተሞች እየተደረጉ ያሉት የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻዎች የሚያመለክቱት የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች ምን ያህል የነፃነት ትግሉ የጀርባ አጥንት መሆናቸው ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 ይህ ድርጅታዊ ፍቅርና ተነሳሽነት ወደ አገር አድን ንቅናቄውም እንዲሸጋገር ይሻል።ከአሁን በኋላ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት እና ደጋፊዎች የአገር አድን ንቅናቄውን የማጠናከር ኃላፊነት አለባቸው። በዚህም ምክንያት የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች በሚያደርጓቸው የትግል እንቅስቃሴዎች ሁሉ የሌሎች ዲሞክራሲያዊ የኢትዮጵያ ኃይሎች ተሳትፎ እንዲኖርበት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሕዝብን የማስተባበር ሥራ በሁሉም ቦታዎችና በሁሉም እርከኖች መሠራት ይኖርበታል። ይህ የሁለገብ የትግል ስትራቴጂዓችን አንዱ አካል በመሆኑ አባላት ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ያሳስባል።
አርበኞች ግንቦት 7 ለአባላቱና ደጋፊዎቹ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ “እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰን፤ አዲሱ ዓመት የድል ዓመት እንዲሆንልን በጽናት እንታገል” ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Thursday, 10 September 2015

ረሀብን ለማጥፋት ህወሓትን ማስወ


September 3, 2015
def-thumbረሀብ በአገራችን ላይ እያንዣንበበ ነው። በአፋርና በሱማሌ ከከብቶች አልፎ ሕፃናት እየሞቱ ነው። የረሀቡ አደጋ ወደ ኦሮሚያና ሌሎች የደቡብ ገጠሮች እየተዛመተ ነው፤ ሰሜን ኢትዮጵያም ከአደጋ ውጭ አይደለም።
“ከአስር ዓመታት በላይ በተከታታይ በየዓመቱ ከአስር በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት አሳይተናል” የሚለው ዓይን ያወጣ ውሸት፤ “ድህነትን ተረት እናደርጋለን” የሚለው ጉረኛ መፈክር፤ “መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ እንደርሳለን” የሚለው ባዶ ተስፋ፤ የወያኔዎችና ጀሌዎቻቸው በፎቅና ቪላዎች መንበሽበሽ፤ የድግሶችና የስብሰባዎች መብዛት ለሕዝባችን ቁርስ፣ ምሳና እራት አልሆኑም።
አገዛዙ ጉራውና ባዶ ተስፋ መስጠቱ እንዳለ ሆኖ የረሀቡን ምክንያት በተፈጥሮ ላይ ማላከኩን ተያይዞታል። ለመሆኑ ተፈጥሮ ብቻውን እየተደጋገመ ለሚመጣ ችጋርና ቸነፈር በቂ ምክንያት ሆኖ ያውቃልን? አስከፊ የረሀብ ዜናዎች የሚሰማባቸው አገሮች በሙሉ ነፃነት የታፈነባቸው አገሮች መሆናቸው የአጋጣሚ ጉዳይ ነውን? ለምንድነው አንድ ዓይነት ችግር እየተደጋገመብን መላ መፈለግ ያቃተን? መልሱ አጭርና ቀጥተኛ ነው። “ችግር የመሳካት እናት” የምትሆነው በነፃነት ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ሲኖር ነው። በባርነት ጨለማ ውስጥ ያለ ጭንቅላት ለችግሮች መፍትሄ የማፍለቅ አቅም የለውም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ድኩም ጭንቅላት ችግሮችን ማሸነፍ ሳይሆን ተሸናፊነትን ተቀብሎ ከችግሮች ጋር ተስማምቶና ተወዳጅቶ መኖርን ይመርጣል። ነፃነት ያለው ሕዝብ ረሀብን እንደሚያሸነፍ ተደጋግሞ የታየ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ረሀብን የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ውጤት ብቻ አድርጎ ማቅረብ እውነትን መሸፈጥ የሚሆነው። ረሀብ የብልሹ አስተዳደር ውጤት ነው።
አገራችንን የረሀብ ቀጠና ካደረጉ የ24 ዓመታት የህወሓት “ድሃን ዘርፈህ ብላ” የኢኮኖሚ ፓሊሲ ውጤቶች መካከል አንዳንዱን ለአብነት ያህል መዘርዘር ይቻላል።
1. ገበሬና መሬት ተለያይተዋል። ለም መሬቶች በኢንቨስትመንት ስም በዘመኑ የህወሓት ጉልተኞች በመያዛቸውና እነሱ ደግሞ በተራቸው ለባዕዳን እየሸጡ በመሆኑ ባለሀገሩ ጭሰኝነት እንኳን አጥቶ ለቀን ሠራተኝነትና ልመና ተዳርጓል። አዳዲሶቹ ባለሃብቶች ለፈጣን ኪስ መሙላት እንጂ ለዘለቄታ የአፈር ልማት ፍላጎቱም እውቀቱም የላቸውም። በዚህም ምክንያት ገበሬው ትንሽ የዝናብ ዝንፈት እንኳን መቋቋም እስከማይችልበት ደረጃ ተዳክሟል።
2. በዘር ላይ በተመሰረተ ክልላዊ ድንበር ሳቢያ ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች በአገራቸው ውስጥ ተዘዋውረው መሥራት አልቻሉም። ከሰሜን ወደ ደቡብ ከተሰደደ የአገራችን አርሶ አደር ይልቅ ለቻይና ገበሬ መሬት ማግኘት ይቀለዋል። እንዲያውም ኢትዮጵያዊው ድሀ ገበሬ በዱላ ሲባረር፤ ከውጭ አገር የመጣው ቱጃር ገበሬ ብድርና ማበረታቻዎች ይሰጠዋል።
3. ደኖቻችን ተጨፍጭፈው፣ ለም መሬታችን ተሸርሽሮ በማለቁ የግብርናችን ምርታማነት በእጅጉ ቀንሷል። በዘመነ ወያኔ የደን ጭፍጨፋና የመሬት መሸርሸር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል። አገሪቷ በፍጥነት ወደ ምድረበዳነት እየተቀየረች ነው።
4. ፋይዳ ያለው የስነ ሕዝብ ፖሊሲ ባለመኖሩ የሕዝብ ብዛት አሻቅቧል። እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዛት ሊቆጣጠር የሚሞክረው ቢሮ ውስጥ ቁጭ ተብሎ በሚደረግ የቁጥር ጨዋታ ነው። የስታተስቲክሱ ባለሥልጣን ቁጥራችንን በትክክል ሊነግረን ባይፈልግም እንኳን ረሀብ መብዛታችንን እየነገረን ነው።
5. የህወሓት ባለሥልጣኖችና በየክልሉ ያደራጇቸው ምስለኔዎች ራሳቸውን ባለሚሊዮኖች አድርገዋል። እነዚህ በአንድ ጀምበር የበቀሉ ቱጃሮች ከገንዘብ በተጨማሪም የጄኔራልነት፣ የሚኒስቴርነት፣ የክልል ገዢነት፣ እጅግ ቢያንስ የቢሮ ኃላፊነት ሥልጣንን ኪሳቸው ውሰጥ ከተዋል፤ ልባቸው የተመኘውን ዲግሪ ሸምተዋል። የመንግሥት ሥልጣንና ሃብት ይኸን ያህል የተቆራኙበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ኖሮ አያውቅም። የጥቂቶች ያለአገባብና ያለቅጥ መክበር በአንፃሩ ደግሞ የብሃኑን ሕዝብ መደህየት ድህነትን መዋቅራዊ አድርጎታል።
6. በአቋራጭና በፍጥነት ለመክበር አስተማማኙ መንገድ የገዛ ራስ ጥረትና ታታሪነት ሳይሆን ቅጥፈት፣ አጭበርባሪነትና ሎሌነት መሆኑን የወያኔ ካድሬዎች በተግባር እያሳዩ ጥሮ ማደርን “ኋላ−ቀር አሠራር” አድርገውታል። በህወሓት የኢኮኖሚ ፓሊሲ የተበረታቱት አድርባይነት፣ ስንፍናና እና ልመና ችግርን የመጋፈጥ አቅማችንን ሰልበውታል።
እነዚህና የመሳሰሉት ጭብጦችን በማንሳት የረሀቡ መሠረታዊ ምክንያት የህወሓት አገዛዝ እንጂ ተፈጥሮ አለመሆኑን አስረግጠን እንናገራለን። ሕዝባችን በነፃነት ማሰብ፣ መመራመር፣ መፈተሽ ቢችል ኖሮ ረሀብን ማጥፊያ ብልሃት ማግኘት ባላቃተውም ነበር። ወደፊትም ቢሆን ተፈጥሮ እኛ እንደፈለግናት አትሆንም፤ መተማመኛችን የሰው ልጅ ወሰን የለሽ የፈጠራ ችሎታና ችግሮችን የመፍታት አቅም ነው። ለዚህ ደግሞ ችግሮችን በልጦ መገኘት ያስፈልጋል። ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከችግሮች በታች ሆኖ መፍትሄ ከአገዛዙ የሚጠብቅ ደካማ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህም ምክንያት ነው የችግሮቻችን ቁንጮ ራሱ ወያኔ ነው የምንለው።
ህወሓትን ከመንግሥት ሥልጣን ሳናስወግድ ድህነትንና ረሀብ እናስወግዳለን ማለት ዘበት ነው:: ድህነት የህወሃት ዋነኛ የገቢ ምንጭ በመሆኑ ህወሓት ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ በወሬ ካልሆነ በስተቀር ድህነት በተግባር ሊቀጭጭ አይችልም። ችጋርና ህወሓት እጅና ጓንት ናቸው። ረሀብ የህወሓት ባለውለታ ነው። ረሀብ የህወሓት የቁርጥ ቀን አጋሩ ነው። ህወሓት በረሃ እያለ በአሸዋ የተሞሉ ጆንያዎችን እህል አስመስሎ በመሸጥ ለእርዳታ በመጣ ገንዘብ ራሱን አደራጅቷል። ስልጣን ከያዘም በኋላ “ረሀብን እየተዋጋሁ ነው” በማለት የምዕራባዊያንን ድጋፍ ለማግኘት ጠቅሞታል። ረሀብና ችጋር የወያኔ “ጪስ አልባ” እንዱስትሪዎች ናቸው። ሕዝባችን ተራበ ማለት የወያኔ ኩባንያዎች ሥራ አገኙ ማለት ነው። ህወሓት ረሀብን ለመቀነስ ቅንጣት ታህል ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ በዚህ ወር ውስጥ በተደረጉ ስብሰባዎች በወጣው ወጪ ብቻ በአገራችን ላይ ያንዣበበውን ረሀብ በቁጥጥር ማዋል በተቻለ ነበር።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ለወገኖቻቸን መራብ ተጠያቂው የህወሓት ዘረኛ አገዛዝ ነው ይላል። ረሀብን ከኢትዮጵያ ምድር ለዘለቄታው ለማስወገድ የህወሓት አገዛዝን አስወግደን በምትኩ ለሕዝብ ደህንነት የቆመ፣ በሕዝብ የተመረጠ እና ከሕዝብ አብራክ የወጣ መንግሥት እንዲኖረን እንታገል ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Wednesday, 2 September 2015

መልዕክት በድሆች ድህነት ለመክበር መሯሯጥ ላይ ላሉ የዲያስፓራ ማኅበረሰብ አባላት !


August 27, 2015
def-thumbየግል ኑሮን ለማደላደል ሲባል የወያኔ አባል መሆን “ወይን ለመኖር” የሚል ስያሜ ከተሰጠው ዓመታት ተቆጥሯል። “ወይን ለመኖር” ዜጎች ነፃነታቸውን ለጥቅም አሳልፈው የሚሸጡበት፤ የሰው ልጅ ክብር የሚዋረድበት ገበያ ነው። በወይን ለመኖር “የገበያ ህግ” መሠረት እያንዳንዱ ዜጋ ሊያገኘው መብቱ የሆነውን አገልግሎት እንዲያገኝ የህወሓት፣ የብአዴን፣ የኦህዴግ፣ የደህዴግ፣ የአብዴፓ፣ የቤጉህዴፓ፣ የጋህአዴን፣ የሀብሊ ወይም የኢሶዴፓ አባል መሆን፤ አልያም መደገፍ ግዴታ ነው። እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች የህወሓት ተቀጽላ ወያኔዎች ናቸው። የእነዚህ ድርጅቶች አባል ወይም ደጋፊ ያልሆነ እንኳስ የመንግሥት አገልግሎት ሊያገኝ ጥሮ ግሮ ያፈራውንም ይነጠቃል።
በዚህም ምክንያት፣ በገጠር ያለው አርሶ አደር ቁራጭ የእርሻ መሬት፣ የግብርና ባለሙያዎች የምክር እገዛ፣ የማዳበሪያና ዘር ግዢ፣ ብድር ወይም እርዳታ ለማግኘት በአካባቢው ባለ የወያኔ ድርጅት አባልነት መመዝገብ፤ አንድ ለአምስት መደራጀት እና የወያኔን የስልጣን እድሜ የሚያራዝሙ ነገሮችን መሥራት ይጠበቅበታል። በከተሞች ውስጥም ሥራ ለመቀጠር፣ ለደረጃ እድገት፣ የመኖሪያ ቤት (ኮንዶሚንየም) ለመግዛት ሲባል መወየን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ሆኗል:: በንግዱም ዘርፍ የንግድ ፈቃድ፣ የሥራ ቦታ እና የባንክ ብድር ለማግኝት፣ የመንግሥት ጨረታዎችን ለማሸነፍ፣ ከጉምሩክ እቃ ለማስለቀቅ፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት መወየን ግዴታ ነው።
“ወይን ለመኖር” የኢትዮጵያን ሕዝብ ያዋረደ፤ ለትውልድ የሚተርፍ የማኅበራዊ ስነልቦና ኪሳራ ያደረሰ እና ደካማውን ወያኔን ጠንካራ በማስመሰል በሕዝብ የትግል መንፈስ ውስጥ ፍርሃትን የረጨ መሆኑ ግንዛቤ እየዳበረ በመጣ መጠን እየቀነሰ የመጣ ክስተት ነው። በአሁኑ ሰዓት ከቀድሞው እጅግ በተሻለ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ራሳችንን ከህወሓት ባርነት እያላቀቅን ምሬታችንን በግልጽ መናገር የጀመርንበት ወቅት ነው፤ ከዚያም አልፎ የህቡዕ ተግባራዊ የትግል እንቅስቃዎችን ማድረግ ደረጃ ላይ ደርሰናል።
አገር ውስጥ እየተዋረደ የመጣው “ወይን ለመኖር” በአገዛዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን (ዲያስፓራ) መካከል ነፃነታቸውን በጥቅም የሚለውጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ፍለጋ ተሠማርቷል። አገዛዙ ተስፋ ያደረገው ያህል ባይሆንም ጥረቱ የተወሰነ ውጤት እያስገኘለት ነው። በጥቅማ ጥቅም እየደለለ ካመጣቸው ውስጥ በስርዓቱ ብልሹነት ያዘኑና የተሰማቸውን በግልጽ የተናገሩ መኖራቸው የሚያስደስትና የሚያበረታታ ቢሆንም ከመንደር ካድሬዎች ባነሰ ተለማማጮችና አጎብዳጆች በማየታችን ተሸማቀናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካለነው አብዛኛው ሕዝብ አንፃር ሲታይ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ዲያስፓራዎች መካከልም ነፃነታቸውን በጥቅም ለመለወጥ የሚፈቅዱ መገኘታቸው አሳዛኝ ነው። እነዚህ ክብራቸውን በጥቅም የለወጡ ዲያስፓራዎች ዓለም ባንክንና የዓለም የገንዘብ ድርጅትን (IMF) ተክተው ህወሓት ስላስገኘው ፈጣን እድገት በአገዛዙ ራድዮ እና ቴሌቪዥን ሲነግሩን መስማት ያሳፍራል። የህወሓት አገዛዝ “ፍትህን፣ መልካም አስተዳርንና ዲሞክራሲን አስፍኗል፤ ይህንንም መጥተን በዓይኖቻችን ተመልክተናል” እያሉ የግፉን ገፈት እየቀመስን ላለነው ሲነግሩን መስማት ያማል።
እነዚህ ወገኖቻችን ህወሓትን በማሞካሸት የሚያገኙት መሬት ብዙ ድሆች የተፈናቀለቡት፤ ለእነሱ በብላሽ የተሰጠው ብድር በረሃብ ለሚጠቃ ወገን የተላከ እርዳታ መሆኑ ማሳሰብ ይገባል። ከህወሓትና አጫፋሪዎቹ ጋር ተስማምተው ባገኙት ገንዘብ የሚቆርሱት እያንዳንዱ እንጀራ የብዙ ወገኖቻችን ደምና እንባ የፈሰሰበት መሆኑ ማስገንዘብ ያሻል። ከህወሓት ጋር በማበር በወገኖቻችን ድህነትና ችጋር እየከበሩ ያሉ የዲያስፓራ ማኅበረሰብ አባላት ከዚህ እኩይ ሥራቸው እንዲታቀቡ ማስጠንቀቅ ይገባል። እኚህ ወገኖች የራሳቸው ክብር ማጉዳፋቸውን ብቻ ሳይሆን የልጅ ልጆቻቸውም የሚያፍሩባቸው መሆኑን ማስታወስ ይገባል። ከዚህም አልፎ የዛሬ ተግባራቸው ነገ በህግ የሚያስጠይቃቸው መሆኑን ሊያውቁ ይገባል።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የአገዛዙን እድሜ በማራዘም ላይ የተሰማሩ፤ በድሆች ድህነት ለመክበር በመሯሯጥ ላይ ያሉ፤ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ለአገዛዙ ጥብቅና የቆሙ የዲያስፓራ አባላት ከዚህ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ያሳስባል።
አርበኞች ግንቦት 7 “ከህወሓት ውድቀት በኋላ ያለው ጊዜ ለእናንተም ከዛሬው የተሻለ ይሆናል። ዛሬ ከህወሓት ጋር ያላችሁን ሽርክና አቋርጡ። ለነፃነት የሚደረገውን ትግል እርዱ፤ መርዳት ባትችሉ እንቅፋት አትሁኑ፤ አለበለዚያ ግን ከተጠያቂነት የማታመልጡ መሆኑን እወቁ” ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!! !

Thursday, 13 August 2015

አለቃዎ ሳይሆን ቅን ህሊናዎ የሚያዝዎትን በመፈፀም መልካም ዜጋ ይሁኑ!


def-thumbመልካም ዜጋ ማለት ምን ማለት ነው?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ በርካታ መጻሕፍት መፃፍ ይቻላል፤ መሠረተ ሀሳቡን ግን በጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ማቅረብ ይቻላል።
መልካም ዜጋ ኢፍትሃዊ ተግባር ሲፈፀም “እኔ ምናገባኝ?” አይልም። መልካም ዜጋ “ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ”፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶም አይብቀል”፤ “እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም” እና በርካታ መሰል ምሳሌዎችን አይሰማም። መልካም ዜጋ በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ከነፃና ቅን ህሊናው ጋር ታርቆ ይኖራል።
የህወሓት አገዛዝ፣ መልካም ዜጋ ማለት የመንግሥት ሥልጣን የያዘን ማንኛውም አካል ማክበርና በታማኝነት ማገልገል ተደርጎ እንዲተረጎምለት ይሻል። ፍትህ የሚያዛባ መንግሥትን መቃወም የመልካም ዜጋ አቢይ ተግባር መሆኑ የዘመናችን ወጣት እንዳይገነዘብ ያደርጋል። በተለይ ባለሙያዎች የሚያገለግሉትን አገዛዝ ባህርይ እግምት ውስጥ ሳያስገቡ የተቀጠሩበትን ሥርዓት በታማኝነት ማገልገል የዜግነት ግዴታቸው አድርገው እንዲወስዱት ይወተውታል።
ኦስካር ግሮኒንግ ( Oskar Groening)የዘጠና አራት ዓመት ሽማግሌ ጀርመናዊ ነው። በጀርመን የሂትለር አገዛዝ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንፁሃን የተፈጁበት አሽዊትስ ካምፕ ውስጥ የሂሳብና ጽህፈት ሠራተኛ ነበር። ኦስካር ግሮኒንግ አንድም ሰው አልገደለም፤ አንድም ሰው አልገረፈም። እሱ ሂሳብ ነው የሠራው። ሆኖም በደል ሲፈፀም አይቶ “ምናገባኝ” ብሎ አልፏልና ከብዙ ዓመታት በኋላ ተከሶ በቅርቡ የ4 ዓመታት እስር ተፈርዶበት በሁለት እግሮቹ መቆም በማይችልበት በ 94 ዓመቱ በእርጅናውና በመጦሪያው ዘመን ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ፊት ተዋርዶ እስር ቤት ወርዷል።
በአንፃሩ ኦስካር ሽንድለር (Oskar Schindler) በጀርመን ናዚ ወቅት ሂትለር ይመራው የነበረው የናዚ ፓርቲ አባልና ሰላይ ነበር። ሆኖም ግን የሥርዓቱን ኢሰብዓዊነት ሲረዳ እዚያው የናዚ ፓርቲ ውስጥ ሆኖ አለቆቹ ያዘዙትን ሳይሆን ቅን ህሊናው ያዘዘውን በምስጢር መሥራት ጀመረ፤ በዚህም የ 1200 ሰዎችን ሕይወት ታደገ። ከጦርነቱ በኋላ ኦስካር ተከብሮ የኖረ በርካታ የክብር ስሞችና ሽልማቶች የተሰጠው በመልካም አርዓያነቱ የሚጠቀስ ሰው ሆነ።
በአገራችንም በአምስት ዓመታቱ የፋሽስት ወረራ ወቅት ስመ ጥር የውስጥ አርበኞች ነበሩ። ከነፃነት በኋላ ባንዶች እንኳን በውስጥ አርበኝነት ለመጠራት ያደርጉት የነበረውን እሽቅድድም ልብ በሉ።
በህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴግ፣ ደህዴግ እንዲሁም አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ ያላችሁ ወገኞች ኦስካር ግሮኒንግን ወይንስ ኦስካር ሽንድለርን መምሰል ትፈልጋላችሁ? በህወሓት ፋሽስታዊ አገዛዝ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት ውስጥ ያላችሁ ወገኖቻችን ነገ የምትዋረዱበትን ሥራ መሥራት ነው የሚበጃችሁ ወይስ ዛሬ ከህሊናችሁ ጋር ታርቃችሁ እየኖራችሁ ነገ ደግሞ ልጆቻችሁና የልጅ ልጆቻችሁ የሚኮሩበትን ተግባር መፈፀም ትፈልጋላችሁ? በአገዛዙ የስለላ ድርጅቶች ውስጥ ያላችሁ ወገኖች ስማችሁን በመልካም ማስጠራት አትሹምን?
ልቦና ያላችሁ ወገኖቻችን ሆይ! መልካም ዜግነት ሎሌነት አይደለም። መልካም ዜግነት ለቅን ህሊና ታማኝ መሆን ነው። መልካም ዜግነት ሲመች በገሀድ፤ ሳይመች በምስጢር ኢፍትሃዊነትን መዋጋት ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በማናቸውም መንገድ በአገዛዙ የፓለቲካ፣ የጦርና የፓሊስ ተቋማት፤ በስለላም ይሁን በሌላ የሲቪል ሙያ የተሰማራችሁ ወገኖቻችን የታዘዛችሁትን ሳይሆን ቅን ህሊናችሁ የሚጠይቃችሁን በመሥራት ኢፍትሃዊ፣ ፋሽስታዊና ዘረኛ የሆነውን የህወሓት አገዛዝን እንድታዳክሙ ጥሪ ያቀርብላችኋል። በአገዛዙ ውስጥ ሆናችሁ እያለም የምትሠሩት ለሀገርና ለትውልድ የሚጠቅም በርካታ ሥራ አለ። የአገዛዙን ምስጢራዊ ሰነዶች ለአርበኞች ግንቦት 7 እንዲደርስ ማድረግ፤ አሊያም በማኅበራዊ ሚዲያዎች (ለምሳሌ ፌስ ቡክና ቱተር) ማሰራጨት ትልቅ ዋጋ ያለ ሥራ ነው። የህወሓት ፀረ-አገር እና ፀረ-ሕዝብ ፕሮጀክቶችን ማሰናከል ሌላ ትልቅ ሥራ ነው። በነፃነት ታጋዮች ላይ የሚደረጉ ዱለታዎችን ማክሸፍ ሕይወት አድን ሥራ ነው። ድርጅቶቹ ውስጥ ሆኖ ድርጅቶቹን ማዳከም የመልካም ዜግነት ግዴታ መወጣት ነው።
በሥርዓቱ ውስጥ ሆነው ኢፍትሃዊነትን ለማጋለጥ እና ሥርዓቱን ለማዳከም ለሚጥሩ ወገኞች አርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ ክብር አለው፤ ደህንነታቸው እንዲጠበቅም የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ፀረ ኢትዮጵያ እና ፀረ ሰው የሆነውን የህወሓትን ሥርዓት ለመጣል እና በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነትና የሀገር አንድነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ለማጽናት ከሥርዓቱ ውስጥም ውጭም የሚደረገውን ትግል እናፋፍም።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
CategoryEditorial

Friday, 7 August 2015

የፕሬዚዳንት ኦባማ የአፍሪካ ኅብረት ንግግርና እንደምታው


August 7, 2015
def-thumbየዩ ኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓም አዲስ አበባ ውስጥ በአፍሪካ ኅብረት ጽ/ቤት ያደረጉት ንግግር በርካታ ቁምነገሮችን የያዘ በመሆኑ አንጽዖት ሊሰጠው እንደሚገባ አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ያምናል።
ፕሬዚዳንቱ በዚህ ንግግራቸው የአፍሪቃን በተለይም ደግሞ የአገራችንን ችግሮች ነቅሰው አሳይተዋል። ሰብዓዊ መብቶች ሰው በመሆናችን ያገኘናቸው በመሆኑ በቆዳችን ቀለም፣ በተወለድንበት አካባቢ፣ በምንናገረው ቋንቋ ወይም በሌላ ማናቸውም ምክንያቶች ሊሸራረፉ የማይገቡ መሆኑን በመግለጽ “ሁላችንም እኩል ተወልደናል” በማለት ዘረኞችን አፍ የሚያዘጋ ኃይለቃል ተናግረዋል። “ሁላችንም ከአንድ ግንድ የበቀልን ነን፤ ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን፤ ሁላችንም አንድ ጎሳ ነን” ካሉ በኋላ በዓለም ያለው አብዛኛው ችግር ይህንን መረዳት አለመቻላችን፤ ራሳችንን በእያንዳንዳችን ውስጥ ማየት አለመቻላችን ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ በብዙ የአፍሪቃ አገሮች፣ ዜጎች ነፃነታቸው የተገፈፈ መሆኑን፤ ምርጫ መኖሩ ብቻ ዲሞክራሲ ሰፈነ ማለት አለመሆኑ አብራርተዋል። ጋዜጠኞች፣ የተቃውሞ ፓለቲካ መሪዎችና ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች፣ የሲቪክ እንቅስቃሴዎች መሪዎችን በእስር ቤት እያጎሩ ወይም በነፃነት እንዳይቀሳቀሱ እያደረጉ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አደረግን የሚሉ አገሮች መኖራቸው ለመግለጽ ኢትዮጵያን በዋቢነት ጠርተዋል።
ፕሬዚዳንት ኦባማ የሰላምና የደህንነት ጉዳይ ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን በሰፊው ከገለጹ በኋላ ለሰላም ሲባል ነፃነትን መንፈግ ሁለቱንም ሊያሳጣ የሚችል መሆኑም አስገንዝበዋል።
እድገትን በማፋጠን ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት አዲስ አስተሳብ ያሻል፤ ለአዲስ አስተሳሰብ ደግሞ በነፃነት ማሰብ፤ ድምፃቸው የሚሰማ ዜጎች መኖር እና የሰብዓዊ መብቶች መከበር ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል። የአፍሪቃ መሪዎች ሥልጣን ላለመልቀቅ የሚሄዱትን ርቀት በማንሳት ተሳልቀውበታል፤ ሙስናም የልማትና የመልካም አስተዳደር ፀር መሆኑን አስምረውበታል።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ ይኸ ቀራቸው በማይባል ሁኔታ በአህጉራችን በአፍሪቃ በተለይ በኢትዮጵያ የሰፈነው ክፉ አገዛዝ መተቸታቸው፤ ይህንን እዚያው የአፍሪቃ መዲና በሆነችሁ አዲስ አበባ ተገኝተው መናገራቸው በበጎ ይመለከተዋል። እሳቸው ያነሷቸውን ቁም ነገሮችን አድምጠው ማስተካከያዎችን የሚያደርጉ ገዢዎች ኑረውን ቢሆን ኖሮ የኛ ትግል ባላስፈለገ ነበር። ችግሩ መስማት እንጂ ማዳመጥና መተግበር የማያውቁ ገዢዎች የሰፈኑብን መሆኑን ነው።
ስለሆነም፣ አርበኞች ግንቦት 7: ፕሬዚዳንት ኦባማ በአፍሪቃ ኅብረት ንግግራቸው ሀቁን አብጠርጥረው በመናገራቸው የተሰማውን አድናቆት ይገልፃል፤ በዚሁ አጋጣሚ ደግሞ በንግግራቸው ያነሷቸው ቁምነገሮችን መደመጣቸውና በተግባር መተረጎማቸውን እንዲከታተሉ አበክሮ ይጠይቃል።
የፕሬዚዳንት ኦባማ ንግግር በሀቅ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ የህወሓት ሽማምንት የተከፉ ቢሆንም የኢትዮጵያን ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እውነታ የመቀየር ኃላፊነት የእኛው የኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት መሆኑን በመረዳት፤ ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲና ለአገር አንድነት ግድ ያለን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ተባብረን አገራችን ከዘረኛውና ፋሽስታዊ ህወሓት አገዛዝ ነፃ የማውጣት ተጋድሎዓችን አጠናክረን እንድንቀጥል አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
CategoryEditorial

በሙስሊም እንቅስቃሴ መሪዎች ላይ የተሰጠውን ፍርደገምድል ፍርድን እናወግዛለን!


August 4, 2015
def-thumbየህወሓት አገዛዝ የሚዘውረው የይስሙላ ፍርድ ቤት ዛሬ ሀምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በሙስሊም ወገኖቻችን መሪዎች ላይ ፍርደገምድል ውሳኔ ሰጥቷል። በዚህ ውሳኔ መሠረትም የእምነት መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው በሰላማዊ በሆነ መንገድ የጠየቁ ወገኖቻችን መሪዎች እስከ 22 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
ሙስሊም ወገኖቻችን ጥያቄዎቻቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ሥርዓቱ ያደረገውን ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን ተቋቁመው “ድምፃችን ይሰማ!” የሚል አቤቱታ ከማቅረብ የዘለለ አንዳችም የኃይል እርምጃ ወስደው አያውቁም። ሆኖም “በደል ደርሶብኛልና ልሰማ” ብሎ አቤቱታ ያቀረበ ሕዝብ መሪዎችን እስከ ሃያ ሁለት ዓመታት በእስር መቅጣት የአገዛዙ እብሪትና ማናለብኝነት አጉልቶ የሚያሳይ ተግባር ነው።
አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህን ፍርደገምድል ውሳኔ አጥብቆ ያወግዛል።ይህ ፍርደገምድል ውሳኔ የተሰጠው ፕሬዚዳንት ኦባማ በአገራችን መዲና ተገኝተው “ለሰላም ሲባል ነፃነትን ማፈን ሁለቱንም ያሳጣል” ባሉ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑ አገዛዙ የሚሰማ ጆሮ የሌለው መሆኑ የሚያረጋግጥ ሆኗል።
የሙስሊም መሪዎች በእስር ላይ በነበሩት ጊዜ በምርመራ ስም ተደብድበዋል፤ ክብራቸው ተደፍሯል፤ የተለያዩ ዘግናኝ ሰቆቃዎች ተፈጽሞባቸዋል፤ የሀሰት ዶክመንታሪ ፊልሞች እንዲሰራጩ ተደርገው ስማቸውን ለማጥፋት ሙከራ ተደርጓል።
በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ የደረሰው በደል ሃይማኖት ሳይለይ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰ በደል ነው፤ መፍትሄ የምናገኘውም በጋራ በምናደርገው ትግል ህወሓትን አስወግደን በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና የአገር አንድነት የሚጠብቅ የመንግሥት ሥርዓት ስናቆም ነው። ከዚህ በመለስ የሚገኝ መፍትሄ የለም። የእምነት መብቶች የሚከበሩት ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ ሲከበሩ እንደሆኑ “በድምፃችን ይሰማ” ሥር የተሰባሰቡ ወገኖቻችን ይረዳሉ ብለን እናምናለን።
አርበኞች ግንቦት 7 ሙስሊም ወገኖቻችን ለዓመታት ያለመታከት ያካሄዱትን ትግል ያደንቃል። ከእንግዲህ ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዘን፤ ተደጋግፈን በመታገል ህወሓትን አስወግደን በምትኩ ለሁላችንም የምትመች አገር እንድንገነባ ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ
CategoryAmharic