Monday, 21 September 2015

መልካም አዲስ ዓመት – ድጋፍ ለአገር አድን ንቅናቄ


September 12, 2015
def-thumb“የኢትዮጵያ አገር አድን በዲሞክራሲ የጋራ ንቅናቄ” ምስረታ ዜና በአዲስ ዓመት መባቻ መሰማቱ ትልቅ የምሥራች ነው። ይህንን ንቅናቄ ለመመስረት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምስጋና ይገባቸዋል።
የኢትዮጵያ አገር አድን በዲሞክራሲ የጋራ ንቅናቄ መመስረት የህወሓት አገዛዝን ተጋግዞ ለመጣል ከማስቻሉም በላይ ድሉ የአንድ ወይም የጥቂት ድርጅቶች ድል ከመሆን ይልቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ድል እንዲሆን ያስችላል። ከዚህም በተጨማሪ ከህወሓት አገዛዝ በኋላ የተባበረች ኢትዮጵያ እንደምትኖረን ማስተማመኛ ከሚሰጡን ነገሮች ዋነኛው ዛሬ የምናደርጋቸው ትብብሮች ናቸው። የአገር አድን ንቅናቄ ዛሬ የምናደርገውን ትብብር መዋቅራዊ ገጽታ የሚሰጠው እና ዘለቄታነት እንዲኖረው የሚያግዝ በመሆኑ ለአገራችን ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ የሚሰጠው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው።
የአንድን ድርጅት ጥንካሬ ከሚወስኑ ነገሮች ዋነኛው የአባላቱና ደጋፊዎቹ ጥንካሬ ነው። የአገር አድን ንቅናቄም ጥንካሬ ከሚወስኑት ነገሮች ዋነኛው አባላትና ደጋፊው ናቸው። የአገር አድን ንቅናቄ እንዲጎለብት የምንመኝ ሁሉ ለንቅናቄው መጠናከር የምናበረክተው አስተዋጽኦ አለ። ከሁሉ አስቀድሞ ኢትዮጵያ አገራችን ከግዛቷ ውስጥ የሚገኙ ማኅበረሰቦች ሁሉ አገር መሆኗን እና እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ከሌላው ጋር እኩል መብት ያለው መሆኑን መቀበልና በተግባርም ማሳየት ይገባል። እያንዳንዱ ዜጋ እና እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ከሌሎች ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር በጋራ አገራችን የማዳን እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። በምናደርጋቸው ፓለቲካዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የዜጎችና የማኅበረሰቦች በእኩልነት መሳተፍ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ተረድተን መንቀሳቀስ ይኖርብናል። ለህወሓት “ከፋፍለህ ግዛ” ፓሊሲ መመቸት የለብንም። በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በእድሜም ሆነ በቋንቋ ሳንከፋፈል የጋራ ትኩረታችንን የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያን ማዳን ላይ እናድርግ።
በኢትዮጵያ፣ በዳር አገር እና በውጭ አገራት የሚገኙ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች ከሕይወት መስዋትነት ጀምሮ በጊዜዓቸው፣ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ንቅናቄዓቸውን ሲረዱ ቆይተዋል። በአሁኑ ሰዓት በበርካታ የዓለም ከተሞች እየተደረጉ ያሉት የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻዎች የሚያመለክቱት የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች ምን ያህል የነፃነት ትግሉ የጀርባ አጥንት መሆናቸው ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 ይህ ድርጅታዊ ፍቅርና ተነሳሽነት ወደ አገር አድን ንቅናቄውም እንዲሸጋገር ይሻል።ከአሁን በኋላ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት እና ደጋፊዎች የአገር አድን ንቅናቄውን የማጠናከር ኃላፊነት አለባቸው። በዚህም ምክንያት የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች በሚያደርጓቸው የትግል እንቅስቃሴዎች ሁሉ የሌሎች ዲሞክራሲያዊ የኢትዮጵያ ኃይሎች ተሳትፎ እንዲኖርበት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሕዝብን የማስተባበር ሥራ በሁሉም ቦታዎችና በሁሉም እርከኖች መሠራት ይኖርበታል። ይህ የሁለገብ የትግል ስትራቴጂዓችን አንዱ አካል በመሆኑ አባላት ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ያሳስባል።
አርበኞች ግንቦት 7 ለአባላቱና ደጋፊዎቹ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ “እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰን፤ አዲሱ ዓመት የድል ዓመት እንዲሆንልን በጽናት እንታገል” ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

No comments:

Post a Comment