ዘረኛውና አምባገነኑ የህወሓት አገዛዝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከካድሬ ማሰልጠኛ ማዕከላትነት ለይቶ የማያይ ስለመሆኑ በተቋማቱ ውስጥ የሚደረጉ ተግባራት ማረጋገጫዎች ናቸው። ለዚህ ተግባሩ በሰነድ ደረጃ መቅረብ ከሚችሉት የቅርብ ጊዜ ማስረጃዎች ዋነኛው በህዳር 2007 ዓ.ም. በሥራ ላይ የዋለው “የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኢህአዴግ የምርጫ ድል ልማት ሰራዊት ግንባታ አደረጃጀት ማንዋል” የተሰኘው በትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተላለፈው ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ፣ የህወሓት አሳፋሪ የትምህርት ፓሊሲ ባፈጠጠ መልኩ የተገለፀበት፤ የኢፌዴሪ መንግሥት ተብሎ በሚጠራው የህወሓት አገዛዝ ተቋም እና በህወሓት/ኢህአዴግ ፓርቲ መካከል ለይምሰል እንኳን ልዩነት አለመኖሩ በግላጭ የሚታይበት ሰነድ በመሆኑ በዚህ ርዕሰ አንቀሳችን በስፋት ልንዳስሰው ወስነናል።
ሰነዱ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ መርዙን መርጨት የሚጀምረው ገና በመግቢያው ስለማንዋሉ አስፈላጊነት ሲገልጽ ነው። ማንዋሉ “ከምንም በላይየብጥብጥና የሁከት መንስኤ የሆነውን ተማሪ በኢህአዴግ አመራር አባላት እየታገዙ ለመያዝ የሚያስችል ነው” በማለት ህወሓት ተማሪውን የሚመለከተው “ከምንም በላይ በብጥብጥ መንስኤነት” መሆኑ፤ ለዚህ መድሀኒቱ ደግሞ ተማሪውን በኢህአዴግ አመራር አባላት “መያዝ” መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ይገልፃል። ቀጥሎም “በምርጫው ሊፈጠር የሚችለውን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁከትና ብጥብጥ ለማስቆም በማደራጀት መረጃ ለመጥለፍ አመችነቱ የላቀ እንደሚሆን ታምኖበታል” በማለት መረጃ መጥለፍ የዩኒቨርስቲዎችና የትምህርት ሚኒስቴር ሥራ እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል።
የማንዋሉን ዓላማዎች በሚገልፀው ክፍል ደግም “… የከፍተኛ ትምህርት የትምህርት የልማት ሰራዊት ግንባታን ወይም የፓለቲካ ሰራዊት ግንባታ በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተደራጀና በተናቀጀ ሁኔታ በማቀጣጠልና በማስቀጠል … ምርጫ 2007 ውጤታማ ለማድረግ እና የኢህአዴግን አሸናፊነት ለማረጋገጥ ነው” በማለት ተቋማቱን የኢህአዴግ የምርጫ መሣሪያ መሆናቸውን፤ ግባቸውም የኢህአዴግ አሸናፊነትን ማረጋገጥ መሆኑ ይገልፃል።
በገጽ 3 ላይ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች “በኢህአዴግ ላይ ያላቸው አቋም የወረደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በማንኛውም ተቃውሞ ድምፅ ከተጠሩ፤ ሰልፍ የሚያደምቁ፤ ተቃውሞን ከግብ ለማድረስ ሁነኛ መሳሪያ ናቸው። ተማሪዎች በየትኛውም ሐገር እንደታየው አደባባይን የመያዝ ህዝብን አስተባብረው ለተቃውሞ የማሳደም እድላቸው የሰፋ በመሆኑ ከዚህም ሲያልፍ፤ የኢህአዴግ ምከታን በመቃወም ለጠላት ጎራ ተሰልፈው የመታጠቅ እድላቸው ከፍተኛ ነው” ሲል “በወጣቱ እጠላለሁ” የሚለው የህወሓት/ኢህአዴግን ስጋት አፍረጥርጦ ያወጣል። ትንሽ ወረድ ብሎ ደግሞ “በተለይ በአሁኑ ሰዓት ፈተና ላይ የጣለን የምርጫ ጉዳይ እንደምናሸንፍ ቃል የተያዘለት ቢሆንም፤ ፈተናዎች የሚፈጠሩት በህዝብ እና በራሱ ታማኝ ባልሆኑ ሃይሎች ማለትም በመንግስት ክንፍ አይቀለበስም ብሎ ማሰብ አይቻልም። በዚህም ቀድሞ መዘጋጀት ያለበት እና ለሁከት እና ለብጥብጥ መሳሪያ ሊሆን የሚችለው የህዝብ ክንፍ የተማረው ሃይል ሊሆን ስለሚችል ሊታሰብበት ይገባል” ሲል በተማረው ወጣትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሠራተኞች ላይ ያለው ጥርጣሬና ፍርሃት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ይገልፃል።
የ2007 ምርጫ በህወሓት ሹማምንት ላይ የፈጠረውን ጭንቀት በዚህ ሰነድ ላይ በገሀድ የሚታይ በመሆኑ እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር በጥንቃቄ ሊነበብና ሊተነተን የሚገባው ነው። ለምሳሌ በገጽ 6 ላይ ስለዩኒቨርስቲ ተማሪ ሲገልጽ “የአመፅ እና የብጥብጥ መነሻ ሊሆን የሚችል ሀይል መሆኑን በአክራሪዎች ሲጠለፍ፤ ከመንግስት ሃይማኖቱን እየመረጠ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ፤ በጅማ ዩኒቨርስቲ፤ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ እና በሌሎችም ትምህርቱን ትቶ ሲኮበልል ተመልክተናል” ይላል። ለተማሪዎች፣ ከመንግሥት እና ከሃይማኖት አንዱን እንዲመርጡ ተደርጎ ሃይማኖታቸውን የመረጡ መኖራቸውን እና ይህ ደግሞ አደገኛ ነገር መሆኑን ነው ይህ ዓረፍተ ነገር የሚነግረን። ለመሆኑ ይህ ምን የሚሉት ምርጫ ነው? በእንዴት ያለ ሥርዓት ነው ዜጎች ከመንግስትና ከሃይማኖት አንዱን ምረጡ የሚባለው? እንዲህ ዓይነት ምርጫ ቀርቦ ሃይማኖትን መምረጥ እንዲህ ክፉ ነገር የሆነው ለምንድነው? ይህ ጉዳይ ብቻውን ብዙ የሚያነጋገር ነገር አለው።
በገጽ 8 ላይ ደግሞ “ከፍተኛ አመራሩ ተቋማዊ ለውጥ እንዲሁም የትምህርት ልማት ሰራዊት ግንባታ ቴክኒካዊ ሳይሆን ፓለቲካዊ ጉዳይ መሆኑን ተገንዝቦ ካለእርሱ ባለቤትነትና ቀጥተኛ ተሳትፎ ሰራዊት መገንባት እንደማይቻል በመገንዘብ የመሪነት ሚናውን ካለምንም ማወላዳት መወጣት ይጠበቅበታል” በማለት እየተሠራ ያለው የፓርቲ ወገንተኛ የሆነ ፓለቲካ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የትምህርት ተቋማት መሪዎች ዋና ተልዕኮ ትምህርት ማስተማር ሳይሆን የወያኔ ፖለቲካን ማስፈጸም መሆኑን ምንም ሳይጎረብጠው ፍርጥርጡን ያወጣዋል። ትንሽ ወረድ ብሎም “የጋራ መግባባት የምንለካው በመጀመሪያ ለምርጫው የኢህአዴግ የድጋፍ የድል ሰራዊት ብዛት ነው” በማለት ከላይ ያለውን በማጠናከር ወገንተኛነቱም ለኢህአዴግ መሆኑ ያውጃል። በመጨረሻም “ … ሁሉም የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች ውጤታቸው የሚሞላላቸው ለምርጫው በሚያዘጋጁት የድጋፍ ሃይል ይወሰናል” በማለት የአካዳሚ ነፃነት ብቻ ሳይሆን የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓትን ለቀብር ያዘጋጃል።
ይህ ነው የህወሓት የትምህርት ፓሊሲ! የዩኒቨስቲዎች ቁጥር ለማመን በሚቸግር መጠን ቢጨምር፤ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ቅበላ በብዙ መቶኛዎች ቢያድግ ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ፓሊሲ ከተገነባ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ይገኛል የምንለው ፋይዳ ምንድነው?
ህወሓት በገሀድ በጠላትነት የፈረጃቸው የአገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በአጽንኦት እንዲመለከቱ ግንቦት 7፣ የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ያሳስባል። ትውልድንም የትምህርት ሥርዓቱንም የማዳን ግንባር ቀደም ኃላፊነት በተማሪዎችና በመምህራን የወደቀ ሸክም ነው ብሎ ግንቦት 7 ያምናል። መላው የትምህርት ሥርዓት ለአንድ ፓርቲ የምርጫ ውድድር መሣሪያነት ሲውል ማየት እና የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች የሥራ አፈፃፀም የሚወሰነው ለገዢው ፓርቲ ባስገኙት ድምጽ ብዛት ነው መባሉ፤ እነሱም ይኸንን ተቀብለው መሥራት መቀጠላቸውን የመሰለ አሳፋሪ ነገር በአካዳሚያ ውስጥ የለም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ይህን ውርደት መቀበል የለባቸውም። ሰነዱ ህወሓት ከፍተኛ ትምህርትን የሚመለከትበት ዕይታ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነውና ለምርጫ ወቅት ብቻ የተዘጋጀ የአጭር ጊዜ መመሪያ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ይህ ሰነድ ህወሓት፣ ተማሪዎችንና መምህራንን እንደጠላት፤ ተቋማቱን ደግሞ ጠላትን እንደመቆጣጠሪያ መሣሪያ እንደሚመለከት፤ ይህ ዕይታው ደግሞ ቋሚ መሆኑ በግልጽ ያሳያል። በህወሓት ዕይታ ከተገነቡ ተቋማት ምን ዓይነት ትምህርት ይገኛል?
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የትምህርት ኃላፊዎችና ፕሬዚዳንቶች ሆይ! ለገዛ ራሳችሁ ክብር፣ ለአካዳሚ ነፃነት፣ ለትውልድ ስትሉ በዚህ መመሪያ ላይ አምጹ! “እንቢ፣ አሻፈረን፣ በዚህ መመሪያ አንገዛም” በሉ! የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችሁ ይቆማል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!