Tuesday, 23 September 2014

የኦጋዴን ኡኡታ



ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በወጣትነታችን ብረት አንስተን ጫካ እንድንገባ አደረገን ብለዉ የሚናገሩት በወቅቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተንሰራፍቶ ይታይ የነበረዉ በብሄር ብሄረሰቦች ጭቆና ነበር። ወያኔዎች በለስ ቀንቷቸዉ አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ በኋላም ቢሆን ለእነሱ ለራሳቸዉ የሚመች ህገ መንግስት ጽፈዉ ትልቁን የኢትዮጵያ ችግር ፈታን ብለዉ የሚናገሩት ይህንኑ ዛሬም ድረስ እናት አገራችንን ኢትዮጵያን እንደ ነቀርሳ በሽታ ቀስፎ ይዞ የሚቆጠቁጣትን የብሄር ብሄረሰቦች ችግር ነዉ። ወያኔ በ1994 ዓም ህገመንግስቱን አጽድቆ የፌዴራል ስርዐት ከመሰረተ በኋላ ድምጹን ከፍ አድርጎ የጮኸዉ ማንም መፍታት ቀርቶ ሞክሮት አንኳን የማያዉቀዉን የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ችግር እኔ ፈታሁት የሚል ለሱና ለደጋፊዎቹ ብቻ የሚሰማ ጩኸት ነበር። ወያኔ የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ከታሰሩበት ሰንሰለት ፈትቼ “ነፃ” አወጥቼ እራሳቸዉን በራሳቸዉ እንዲመሩ መንገድ ከፈትኩላቸዉ ብሎ ከተናገረ ከሃያ አመታት በኋላ ዛሬም ኢትዮጵያ ዉስጥ የትኛዉም ብሄረሰብ እራሱን በራሱ ማስተዳደር ቀርቶ የአገሪቱ ዜጎች ባሰኛቸዉ ቦታ መኖር እንኳን አይችሉም። የሚገርመዉ ነጻነትና እኩልነት የሠላም ጠላቶች የሆኑ ይመስል ዛሬ ወያኔ ነጻ ወጡ የሚላቸዉ ብሄረሰቦች በሚኖሩበት አካባቢ ሁሉ የሚታየዉ የአገራችንን አንድነት ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ብጥብጥ፤ ግጭትና ክልሌን ለቅቀህ ዉጣ የሚል ወያኔ ይዞብን የመጣዉ መፈክር ነዉ።
ወያኔ ጫካ ዉስጥ እያለ ደርግን በተደጋጋሚ በዘር ማጥፋት ወንጀል ይከሰስ እንደነበር ያኔ ወያኔ ምን ይዞልን ወይም ይዞብን ይመጣ ይሆን እያልን እንከታተለዉ ለነበርን ኢትዮጵያዊያን የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነዉ። ከወያኔ ዉንጀላዎቹ አንዱና ዋነኛዉ ደግሞ ወያኔ እራሱ አቀነባብሮና አዘጋጅቶ ሐዉዜን ዉስጥ በቪድዮ እየተቀረጸ የተካሄደዉ ዉጊያ ነበር። በዚህ ዉጊያ ላይ ደርግ በአዉሮፕላንና በታንክ እየታገዘ መንደሮችን በመደምሰስ ብዙ ሰላማዊ ዜጎችን እንደጨረሰ ወያኔ ዛሬም ድረስ የሚነግረን ዉንጀላ ነዉ። የወያኔ መሪዎች የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያዉቀዉ የማይፈልጉትና እነሱም በፍጹም የማይነግሩን እዉነት ቢኖር ደርግን አሸንፈዉ አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ ከደርግ የወረሱት እነሱ እንደሚሉት ባዶ ካዝና ብቻ ሳይሆን የደርግን ክፋት፤ ጭካኔና ጭፍጨፋ ጭምር መሆኑን ነዉ።
ዘረኞቹኦ የወያኔ መሪዎች ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸሙትን ወንጀል መዘርዘር እራሱን የቻለ ትልቅ ፕሮጀክት ነዉና ዛሬ ወደዚያ አንሄድም፤ ሆኖም ይህ ዘረኛ ቡድን ነኝ ብሎ የሚናገረዉን አለመሆኑን ለማሳየት ስንል ብቻ ሁለቱን ትላልቅ የወያኔ የሰዉ ዘር ማጥፋት ወንጀሎች መናገሩ ፍሃዊ ይመስለናል። የወያኔ ዘረኞች በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፈጸሟቸዉ ወንጀሎች አንዱና ትልቁ በታህሳስ ወር 1996 ዓም በአኝዋክ ህዝብ ላይ የፈጸሙት የሰዉ ዘር ማጥፋት ወንጀል ሲሆን ሌላዉ ደግሞ አሁንም ድረስ እልባት ያላገኘዉና ምስራቅ ኢትዮጵያ ዉስጥ በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ የሚፈጽሙት አይን ያወጣ ጭፍጨፋ ነዉ። ፋሺስቱ ደርግ በአዉሮፕላንና በጦር ሂሊኮፕተሮች እየታገዘ ህፃን፤ አዋቂ፤ ሴትና ወንድ ሳይለይ ህዝብ ይጨፈጭፋል እያለ ሲከስ የነበረዉ ወያኔ ዛሬ እሱ እራሱ ከደርግ በከፋ ሁኔታ ኦጋዴን ዉስጥ እንዲህ ነዉ ተብሎ በቃላት ለመናገር የሚያዳግት ሰቆቃ በኦጋዴን ህዝብ ላይ እየፈጸመ ነዉ። ደርግን – ደርግ ለመሬቱ እንጂ መሬቱ ላይ ስለሚኖረዉ ህዝብ ደንታ የለዉም እያለ አምርሮ ይኮንን የነበረዉ ወያኔ የሱም ጉዳይ አጋዴን ዉስጥ አገኛለሁ ብሎ ከሚተማመነዉ የነዳጅ ኃብት ጋር እንጂ ከኦጋዴን ህዝብ ጋር እንዳልሆነ በተደጋጋሚ በዚህ ህዝብ ላይ በፈጸማቸዉና ዛሬም ድረስ በሚፈጽማቸዉ አረመኔያዊ የጭካኔ እርምጃዎች በተግባር አረጋግጧል። የሰላም፤ የፍህና የነጻነት ጠላት የሆነዉ ወያኔ ኦብነግን ከኦጋዴን ምድር አጠፋለሁ በሚል ሰበብ በክልሉ በየቀኑ በሚወስዳቸዉ ፀረ ህዝብ እርምጃዎች የብዙ ሠላማዊ ዜጎችን ደም እያፈሰሰ ነዉ።
በ1983 ዓም የሽግግሩ መንግስት ሲቋቋም የጀመረዉን የትጥቅ ትግል አቋርጦና የታጠቀዉን መሳሪያ አዉርዶ የሽግግሩን መንግስት ከተቀላቀሉት አማጽያን ዉስጥ አንዱ ኦብነግ በሚል ምህጻረ ቃል የሚታወቀዉ የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር ነበር። ይህ ግንባር በታህሳስ ወር 1984 ዓም ኦጋዴን ዉስጥ በተካሄደዉ የአካባቢ ምርጫ ከ80 በመቶ በላይ ድምጽ በማግኘት የክልሉን መንግስት መስርቶ የሽግግሩ መንግስት የስራ ዘመን እስካበቃበት ግዜ ድረስ ኦጋዴንን አስተዳድሯል፤ ሆኖም ክልሎች እራሳቸዉን ችለዉ በራሳቸዉ መርህና የፖለቲካ ፕሮግራም ሲመሩ ማየትና መስማት የማይወደዉ ወያኔ የኢትዮጵያ ሶማሌ ዲሞክራቲክ ሊግ የሚባል ተለጣፊ ድርጅት በመፍጠርና ይህ ተለጣፊ ድርጅት የ1987ቱን ምርጫ እንዲያሸንፍ በማድረግ ሰላም ፈልጎ የመጣዉን ኦብነግ ከጨዋታ ዉጭ በማድረግ ሌሎች አማራጮችን አንዲመለከት አስገድዶታል። በዚህ የወያኔ አሻጥርና የማግለል እርምጃ የተከፋዉና በሠላማዊ መንገድ ለኦጋዴን ችግሮች መፍትሄ ማግኘት ይቻላል በሚል እምነት ትጥቁን ፈትቶ የሽግግሩን መንግስት የተቀላቀለዉ ኦብነግ አንደገና ትጥቁን አንስቶ ጦርነት ዉስጥ ለመግባት ተገድዷል። የወያኔ መሪዎች ፍላጎትም ቢሆን በፌዴራሊዝም ስም በየክልሉ የራሳቸዉን አሻንጉሊቶች እያስቀመጡ በእጅ አዙር ክልሎችን በቁጥጥራቸዉ ዉስጥ ማድረግ ነዉ አንጂ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች እራሳቸዉን በራሳቸዉ እንዲያስተዳድሩ ማድረግ እንዳልሆነ በኦጋዴንና በሌሎችም ክልሎች የወሰዷቸዉ እርምጃዎች በግልጽ ያሳያሉ።
የደርግ ስርዐት በህዝባዊ አመጽ ተደምስሶ አዲስ አበባ ዉስጥ በ19983 ዓም የሽግግር መንግስት ሲቋቋም የኦብነግ መሪዎች ከመሳሪያ ትግል ይልቅ በሽግግር መንግስቱ ዉስጥ መሳተፍ ለመብቱና ለነጻነቱ እንታገላለን ለሚሉት የአጋዴን ህዝብም ሆነ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይበጃል ብለዉ ጫካዉን ጥለዉ ከተማ መምጣታቸዉ የሚያሳየን አንድ ትልቅ ሀቅ ቢኖር ለትግል ያነሳሳቸዉ የፍትህ፤ የነጻነትና የእኩልነት ጥማት መሆኑን ነዉ። ኦብነግ ገዢዎችም ሿሚዎችም እኛ ብቻ ነን በሚሉ ስግብግብ የወያኔ መሪዎች ተገፍቶ የሚያስተዳድረዉን ህዝብ ጥሎ ጫካ ባይገባ ኖሮ ዛሬ ኦጋዴን የሰላም ቀጠና ሆና ኦጋዴንን ለማዉደም የሚወጣዉ ከፍተኛ ወታደራዊ ወጪ ለዕድገትና ለልማት ስራዎች ይዉል ነበር።
የወያኔን መሪዎች ተንኮል፤ አሻጥርና ራስ ወዳድነት ከኦብነግ መሪዎች በላይ የሚያዉቅ ማንም የለም። ሆኖም የኦብነግ መሪዎች መሠረታዊ ፍላጎት የኦጋዴን ህዝብ መብቱና ነጻነቱ ተጠብቆ ፍትህ በሰፈነባት ኢትዮጵያ ዉስጥ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በእኩልነት እንዲኖር ማየት ስለሆነ በወያኔ ዘረኞች ዕብሪትና ተንኮል ተስፋ ሳይቆርጡ ይህ ፍላጎታቸዉ ሊሳካ የሚችልበትን መንገድ በሰላማዊ መንገድ ለማሳካት አሁንም እንደጣሩ ነዉ። ወያኔ ግን ይህንን የኦብነግ መሪዎች የሰላም ፍላጎት እንደ ፍርሃትና ሞኝነት በመቁጠር በጎረቤት አገር መሪዎች አማላጅነት ለድርድር የመጡ የኦብነግ መሪዎችን ለድርድር ከሄዱበት ከናይሮቢ ከተማ አፍኖ ወደ አዲስ አበባ ወስዷል። የወያኔ መሪዎች እንደነዚህ አይነቶቹን ጭፍንና ፀረ ሠላም የሆኑ እርምጃዎችን በኦብነግና በሌሎችም ብረት ባነሱ ኃይሎች ላይ በመዉስድ በአንድ በኩል በሠላማዊ መንገድ በዉይይትና ድርድር ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን አላስፈላጊ ወደ ሆኑ አዉዳሚ ጦርነቶች እንዲያመሩ ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ የህዝብን ልብ በማስሸፈት በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል። ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ ሃምሳ ኪሎሜትር በማይሞላ ርቀት እራሳቸዉን “ነፃ አዉጭ” ግንባር ብለዉ የሰየሙ አያሌ ድርጅቶች ይገኛሉ። እነዚህ የዚህ ወይም የዚያ ብሄረሰብ ነፃ አዉጭ ግንባር ነን ባዮች የተፈጠሩት የወያኔ ዘረኝንት፤ ዕብሪትና ንቀት ትዕግስታቸዉን ባስጨረሰ ሰዎች ነዉ እንጂ የነዚህ ድርጅቶች መሪዎች እንመራዋለን የሚሉት ህዝብ ችግር ከተቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ጋር አብሮ እንደሚፈታ ረስተዉት አይደለም።
የሰብዓዊ መብቶች ተንከባካቢ ወይም በፈረንጆቹ ቋንቋ ሂዩማን ራይትስ ዋች የተባለዉ አለም አቀፍ ተቋም እንደ ፈረንጆቹ አመን አቆጣጠር በሁለት ሺ ስምንት በመረጃ አስደግፎ ባወጣዉ ዘግናኝ ሪፖርት ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ በኦጋዴን ህዝብ ላይ የሚፈጽመዉን የጅምላ ቅጣት በግልጽ አሳይቶን ነበር። ሪፖርቱ ኦጋዴን ዉስጥ የመከላከያ ሠራዊት፤ ልዩ ፖሊስና የአካባቢዉ ሚሊሺያ ሠላማዊ ዜጎችን ከየመንደሩ እየጎተቱ የኦብነግ አባላት ናችሁ ብለዉ እንደሚረሽኑና ቤታቸዉን እንደሚያቃጥሉ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብና ለእኛ የጉዳዩ ባለቤት ለሆንነዉ ኢትኦጵያዉያን አሳዉቋል። ይህ በቪድዮ ተደግፎ የቀረበዉ ሪፖርት እናት ልጄ ፊቴ ላይ ተረሸነ፤ አባት የልጆቼ እናት አይኔ እያየ ተደፈረች፤ ህጻናት ደግሞ አይናችን እያየ ወላጆቻችንን ተቀማን ብለዉ እያለቀሱ ሲናገሩ ያሳየን ሪፖርት ነበር። በወቅቱ ይህንን እጅግ በጣም ዘግናኝ የሆነ ቪዲዮ አይቶ ልቡ ያልተነካ ኢትዮጵያዊ አልነበረም።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ይህንን ሪፖርት ይፋ ካደረገ ከስድስት አመታት በኋላ ዛሬም ወያኔ በኦጋዴን ወገኖቻችን ላይ የሚፈጽመዉን ለጆሮ የሚዘገንን ወንጀል ከመፈጸም ወደ ኋላ አላለም። እንዲያዉም ኦብነግን ከኦጋዴን ምድር ላይ ጠራርጌ አጠፋለሁ እያለ ግድያዉን፤ አፈናዉን ፤ ድብደባዉንና እስሩን በስፋት ቀጥሎበታል። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ዛሬም ኦጋዴን ዉስጥ ሠላማዊ ዜጎችን በዘፈቀደ ይገድላሉ፤ ወጣትና ህጻናት ሴቶችን ይደፍራሉ፤ መኖሪያ ቤቶችን ያቃጥላሉ። ባለፈዉ ማክሰኞ መስከረም አምስት ቀን የኢትዮጵያ ሳቴላይት ቴሌቪዥን በቪድዮ አስደግፎ ባቀረበዉ ዘገባ የወያኔ መሪዎች ምን አይነት ጨካኞች፤ አረመኔዎችና ለሰዉ ልጆች ምንም አይነት ክብር የሌላቸዉ አዉሬዎች መሆናቸዉን በግልጽ አሳይተዉናል። የዛሬ ስድስት አመት ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣዉ ሪፖርትና ከሰሞኑ ደግሞ ኢሳት ቴሌቪዥን ባቀረበዉ የግማሽ ሰዐት ሪፖርት ዉስጥ የኦጋዴን ዜጎቻችን አሁንም ለእርድ አንደሚጎተት እንስሳ ተጎትተዉ በጥይት እንደሚደበደቡ፤ የኦጋዴን ምድርም ካላይና ከታች በቦምብ አንደሚጋይ በአይናችን ተምልከተናል።በዚህ ሰዉ ሆኖ መፈጠርን በሚያስጠላ ቪዲዮ ዉስጥ የወያኔ አረመኔ መሪዎች ሠላማዊ ዜጎችን እንደ ቅጠል አርግፈዉ “ልቀመዉ” “አምጣና ደርድር” እያሉ የራሳቸዉን ዜጋ በጅምላ በገደሏቸዉ የራሳቸዉ ዜጎች አስከሬን ፊት ቆመዉ ደስታቸዉን ሲገልጹ ታይተዋል። ከዚህ በተጨማሪ አንደኛዉ ወያኔ የአስከሬኑን ጭንቅላት በቪድዮ ቅረጸዉ ሲል ሌላዉ ደግሞ ይሄኛዉ ጆሮዉ ተቆርጧል እያሉ በገደሏቸዉ ሰዎች ፊት ቆመዉ ሲሳለቁ ተሰምተዋል። በዚህም ወያኔዎች ከእነሱ ዉጭ የሆንዉን ኢትዮጵያዊያን በቁማችን ብቻ ሳይሆን ሞተንም እየሰደቡንና እያዋረዱን የሚደሰቱ አርዮሶች መሆናቸዉን በተግባር አረጋግጠዋል።
ይህ በኦጋዴን ወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰዉ በደልና የጅምላ ግድያ እኛን አይመለከትም የምንል ኢትዮጵያዊያን ካለን እጅግ ባጣም ተሳስተናል። ወያኔ አዲስ አበባ ዉስጥም ኦጋዴን ዉስጥ ሠላማዊ ዜጎችን ሲገድል ለእኛ ተራዉ እስኪደርሰን ድረስ በህይወት ላለነዉ ኢትዮጵያዉያን የግድያዊ ቦታና የሟቹ ማንነት ምንም ልዩነት የለዉም። አዲስ አበባም፤ ኦጋዴንም፤ አምቦም ወዘተ የምንገደለዉ እኛዉ ኢትዮጵያዉያን ነን: ይንን ግድያና ዉርደት በቃ ብለን በተባበረ ክንድ ወያኔንና ዘረኛ ስርዐቱን ማስወገድ ያለብንም እኛዉ ኢትዮጵያዉያን ነን።
ከኦጋዴን ክልል ዉጭ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ፍላጎት ሠላም፤ ፍትህ፤ ነጻነት’ እኩልነትና ብልጽግና ነዉ፤ አርግጠኞች ነን የኦጋዴን ወገኖቻችን ፍላጎትም ከዚህ የተለየ አይደለም። ወያኔ በዘር፤ በቋንቋና በሐይማኖት ከፋፍሎን እንዳሰኘዉ እያሰረን፤ እየደበደበንና እየገደለን ለሃያ ሦስት አመት በላይ የዘለቀዉ ስላልታገልነዉ ወይም አሜን ብለን አንገታችንን አቀርቅረን ስለተገዛንለት አይደለም፤ ሁላችንም ወያኔን ለማስወገድና የናፈቀንን የነጻነት አየር ለመተንፈስ አቅማችን የፈቀደዉን ሁሉ አድርገናል። ሆኖም ወያኔ ገመናችንን አንድ በአንድ የሚያዉቅ አገር በቀል ጠላት ነዉና ድካማችንና በሚገባ ያዉቃል። እስከዛሬ የሚያሰቃየብም ደካማ ጎናችንን ስለሚያዉቅና ይበልጥ ደካሞች ሊያደርገን ቀንና ማታ ስለሚሰራ ነዉ። ዛሬ ይህንን ወያኔ በግልጽ የሚያዉቀዉን ድካማችንን ለማስወደግድና እነዚህን ዘረኞች ለማንቀጥቀጥ ለወያኔና ለቅጥረኞቹ መለያየትን፤ጎራ ለይቶ እርስ በርስ መናከስንና አንዳችን ስንበደል ሌሎቻችን ቀመን መመልከትን እምቢ ማለት አለብን። እነዚህ ሦስት ነገሮች በፍጥነት ማድረግ ከቻልንና ፍትፍ፤ ነጻነትና እኩልነት አስተባብረዉን ወያኔን በአንድነት ከታገልነዉ ወያኔ ከአንድ ሳምንት ትገል የማያልፍ ደካማ ጠላት ነዉ።የወያኔ ጥንካሬ የኛ መለያየትና እርስ በርስ መበላላት ብቻ ነዉ። ወያኔን አንድ ሆነን በጋራ ከታገልነዉ የመሳሪያ ጋጋታ አያስፈልገንም፤ አንድነታችን ብቻ ገፍቶ ይጥለዋል፤ተለያይተን ሁላችነም በየፊናችን ከታገልነዉ ግን እስካፍንጫችን ብንታጠቅም እያቆሰልነዉ እኛም እንቆስላለን እንጂ አናሸንፈዉም። ስለዚህ ዛሬ የኦጋዴን እልቂት እንዲቆም፤ የጋምቤላ መሬት ሽያጭ እንዲያበቃ፤ የአማራ፤ የአፋርና የሙርሲ ሀዝብ መፈናቀል ባስቸኳይ እንዲቆምና አገራችን ኢትዮጵያን በማዕከል በጋራ እየመራን በክልል ደግሞ እራሳችንን በራሳችን ማስተዳደር እንድንችል ሁላችንም በአንድነት በወያኔ ላይ ክንዳችንን እናንሳ!!

No comments:

Post a Comment