እኔም አንዳርጋቸው ነኝ የሚል ድምፅ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ እያሰተጋባ ነው። ይሄን ድምፅ የሚያቆመው አንዳችም ምድራዊ ኃይል አልተገኘም። ኢትዮጵያዊ ባለበት ሥፍራ ሁሉ ይሄ ድምፅ ከፍ ብሎ እየተሰማ ነው። ይህንንም ተከትሎ “ላንቺ ነው ኢትዮጵያ፤ ላንቺ ነው ኢትዮጵያ” የሚለው መዝሙር በኢትዮጵያ ተራሮች እናት ላይ እየተዘመረ ነው። ፍትህ ተዋርዳለች፤እኩልነት ጠፍቷል፤ ነፃነት የለም ያሉ ምርጥ ኢትዮጵያዊያን ሳያቅማሙ አያቶቻቸው በተመላለሱበት ተራሮች ላይ ተሠማርተዋል። ሞትንም ንቀው ጋሻ አንስተዋል፤ ሰይፋቸውንም መዘዋል። ለፍትህ፤ ለዕኩልነት እና ለነፃነት የተመዘዘው ሰይፍ ከእንግዲህ ወደ ሰገባው እንደማይመለስ ህወሃቶች እንዲያውቁት እንፈልጋለን።
በኢትዮጵያችን ፍትህ ከጠፋ ብዙ ዘመን ሁኖታል። ከሁሉም ዘመን የህወሃቶች ዘመን ግን የተለየ ነው። ህወሃቶች ህግን ዜጎችን የማጥቂያ መሣሪያ አድርገው መጠቀማቸው ከሌሎች እንዲለዩ ያደርጋቸዋል። እነዚህ ቡድኖች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ቂም መወጣጪያ ህጎችን አውጥተዋል። እንዲህ በማድርጋቸውም ሠላም እናገኛለን ብለው ያስባሉ። የህወሃቶች አስተሳሰብ ደካማና እርባና ቢስ መሆኑን ከሚያሳዩ ተግባሮቻቸው መካከል አንዱ ይሄው በፍትህ ሳይሆን በህግ ብዛት ሠላም እናገኛለን ብለው ተስፋ ማድረጋቸው ነው። የህግ ብዛት ሠላምን አያስገኝም፤ ፍትህንም ማስፈን አይችልም። እንዲያውም ህግ በበዛ ቁጥር ፍትህ እየጎደለች እንደምትሄድ የህወሃቶች ድርጊት ደህና ምስክር ነው። እነርሱ ዜጎችን ለመበቀያ ብለው የሚያወጧቸው ጥቃቅን ህጎች እነርሱ “ህገ መንግስት” ብለው የሚጠሩትን የሚንዱ እና ፍትህን ዋጋ የሚያሳጡ ሁነው እያየናቸው ነው። የፀረ ሽብር ህጉ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን የዜጎችን የመናገር የመደራጀትና በሰላማዊ መንገድ የመንግስትን እኩይ ተግባራት የመቃወምን መብት የገፈፈ ነው። የፀረ ሙስና ህጉም ቢሆን እንዲሁ ነው። በፀረ ሙስና ህጉ የሚጠየቁ በህወሃት የተጠሉ ብቻ ስለመሆናቸው በሙስና የተጨማለቁት የህወሃት ሹማምንት ህያው ምስክሮች ናቸው። በህወሃቶች ህግ ሁሉም ዜጎች እኩል አይደሉም። ህወሃቶች ከሌሎች ይበልጣሉ። የህወሃቶች ምኞት እነርሱ ከህግ በላይ፤ ሌላው ህዝብ ከህግ በታች ሁነው ህወሃትን ተሸክመው እንዲኖሩ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ኢ-ፍትሃዊነት መታገል ግዜው የሚጠይቀው ታሪካዊ ግዴታ ነው። መሪያችን አንዳርጋቸው ፅጌ የተነሳውም ህወሃቶች መሣቂያ መሳለቂያ ያደረጓትን ፍትህ ወደ ሚገባት ክብር ለመመለስ ነው። በአገራችን የህግ የበላይነት ሠፍኖ ጥቂቱ ብዙሃኑን ሳይጫን፤ ማንም ማንንም ሳይሸከም ሁሉም በህግ እና በፍትህ እኩል ሁኖ የሚኖሩባት ሠላም የበዛላት ሥፍራ እንድትሆን የመሪያችን የአንዳርጋቸው ምኞት ነው። ይሄን ምኞት ሚሊየኖች አንግበው ተነስተዋል።
ህወሃቶች አገራችንን አደጋ ላይ ከጣሉባቸው አንኳር ድርጊቶቻቸው መካከል አንዱ በዜጎች መካከል እየፈጠሩ ያሉት ግልፅ ልዩነት ነው። ህወሃቶች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እኩል ነን የሚል እምነት የላቸውም። የህወሃቶች ዕምነት እነርሱ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ከፍ እንደሚሉና በዚያች አገር ውስጥ የተለየ መብት እንዳላቸው ነው። ለመገድልም፤ ለመዝረፍም፤ዜጎችን ለማሳቃየት እና ከአገር ለማባረርም መብቱ የእኛ ነው የሚል ጅላጅል እምነት አላቸው። ይህ የሞኝ እምነታቸው በዜጎች መካከል ቂመ በቀል ሊያተርፍ የሚችል አድሎዎ እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል። አድሎአቸውንም ይበልጥ የከፋ የሚያደርገው ህወሃቶች ሁሉን አድራጊ እኛ ነን ብለው ሲያበቁ የህወሃት የበላይነት የለም ብላችሁ እምኑ ብለው ዜጎችን መጫናቸው ነው። ይህ ድርጊታቸው ብዙ ዜጎችን አስቆጥቷል። ህወሃቶች ግን የዜጎችን ቁጣ የሚያይ ዓይን፤ የሚያስተውል ሂሊና ርቋቸዋል። በኢትዮጵያችን በህወሃቶች አማካኝነት እየተፈጠረ ያለው ግልፅ አድልዖ ለአገራችን ህልውና ከፍተኛ አደጋ ነው። በህዝብ መካከል አድልዖ መፈፀም እና ቂምና በቀልን መትከል የህወሃቶች የመኖሪያ ድንኳናቸው ሁኗል። መከፋፈልና አድልዖ ባለበት አገር ውስጥ ሠላም ይኖራል ማለት አይቻልም። አድልዎ የታላላቅ ግጭቶችና ለውጦች ጥሩ ምክንያት መሆኑን መርሳት አይገባንም።መሪያችን አንዳርጋቸውም ሆነ ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የተነሳው እንዲህ በዜጎች መካከል የሚፈፀመውን አድልዖ ለማስቆምና ዜጎች በገዛ አገራቸው በእኩልነት የሚኖሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው። ይህ የእኩልነት ጥያቄ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጎች ጥያቄ ሁኖ ከኢትዮጵያ እስከ ውጪ አገራት ድረስ እያሰተጋባ ነው።
ሌላው ህወሃቶች አገሪቷን እያዋረዱ ካሉበት ነገሮች መካከል አንዱ የነፃነት ጥያቄ ነው። እኛ ከመጣን በኋላ በኢትዮጵያ ነፃነት ሰፈነ እያሉ ያላዝናሉ። ህወሃቶች ከነፃነት ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችለውን ኃላፊነት ለመረዳትና ለመሸከም ከፍተኛ የሆነ የአስተሳሰብ ድክመት አለባቸው። ከነፃነት ጋር የሚመጣውን ኃላፊነት ለመሸከም ብቻ ሳይሆን የነፃነትንም ትርጉም ለመረዳት ከፍተኛ የሆነ የእውቀት ማነስ ችግር ያለባቸው መሆኑም ይታወቃል። ራሳቸውን ከታሰሩበት የድንቁርና ሰንሰለት ማስፈታት ሳይችሉ ከሰሞኑ የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎችን ሰብስብው የእኛን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ካልስተማርናችሁ ትምህርታችሁን አትቀጥሉም ሲሉ ማሰብ ማቆማቸውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን አንድ እውነት ሁኖ አግኝተነዋል። ማሰብ የሚችሉ ቢሆኑማ ኑሮ ነፃነት ማለት ‘የእናንተን አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስማት አልፈልግም ማለትን’ እንደሚጨምር ያውቁ ነበር። ነፃነትን የማያውቁት ነፃ አውጪዎች ነን ባዮቹ ህወሃቶች ግን ተማሪው መስማት የማይፈልገውን አብዮታዊ ዲሞክራሲ አስገድደው እየጋቱት ይገኛሉ። ለሚቀጥለውም አርባና ሃምሳ ዓመት ስልጣኑን ለማንም አሳልፈን የምንሰጥ አይደለንም ሲሉ በድፍረት ተናግረዋል። የዚህ ሁሉ ድፍረት ምንጭ ህወሃቶችን የተፀናወታቸው እኔ ብቻ ከሚል ከንቱ አስተሳሰብ የመነጨው ስግብግብነታቸው መሆኑን መገነዘብ ያስፈልጋል።
እንግዲህ ፍትህ መቀለጃ ሁናለች፤ እኩልነት ተጓድሏል፤ ነፃነት ጠፍቷል የሚሉ ዜጎች ከሁሉም አቅጣጫዎች ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። የህዝቡ ብሶትም ፅዋውን ሞልቶ እየፈሰሰ ነው፤ ቁጭቱም ከመቸውም ግዜ በላይ ግሏል። ከሰሞኑ በሃያ ስድስት ታላላቅ ከተሞች የተደረጉት ውይይቶችም ያሳዩን አንድ እውነት ህዝቡ ይበልጥ መቆጣቱን ነው። ቁጣውም የተገለፀበት መንገድም ሌላው አስደማሚ ጉዳይ ነው።“እኛም አንዳርጋቸው ነን” ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል። ከእንግዲህ ፍርሃት ሆይ መወጊያህ ወዴት አለ የሚሉ ኢትዮጵያዊያን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ላንቺ ነው ኢትዮጵያ፤ ላንቺ ነው ኢትዮጵያ እያሉ ዘምረዋል። ይሄ ለፍትህ፤ ለእኩልነትና ለነፃነት ለሚታገሉ ታጋዮች ተስፋ ሰጪ ምልክት ነው።
ህወሃቶች በሠላማዊ መንገድ ለሚደረገው ትግል መንገዱን ሲያደናቅፉ እሰከ ዛሬ ዘልቀዋል። አሁን ጭራሹን ገና ሃምሳ የመከራ ዘመን እየተመኙልን ነው። ይሄ ምኞታቸው ቅዥት ሁኖ እንደሚቀር እኛ ልናስታውሳቸው እንፈልጋለን። በዚያች አገር ለውጥ መምጣት አለበት። ለውጡ በዛፍ ላይ የተንጠለጠለ የጎመራ ፓፓያ አይደለም በራሱ ወደ ምድር የሚወርድ፤እኛ ራሳችን ልናወርደው የሚገባን እንጂ። ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት እያንዳንዱ ዜጋ በቻለው መሣሪያና ባለው አቅም ሁሉ ለልውጡ ሳያቅማማ መታገል ይኖርበታል። ህወሃቶች ነፃነታችንን አይሰጡንም፤ ፍትህም ከእነርሱ እጅ የምትገኝ አይደለችም፤ እኩልነትንም የሚያውቁ አይደሉም እነዚህ ወርቃማ እሴቶች በትግል የሚገኙ ናቸው። እነዚህን ክቡር ስጦታዎች አስነጥቆ ዝም ያለ ወደ መታረጃው ሥፍራ የሚነዳ ከብትን ይመስላል። ብዙ ኢትዮጵያዊያን እንዲህ መሆንን የሚምርጡ አይደሉም። በየከተሞቹ በተደረገው ውይይት ከተገነዘብናቸው እውነቶች መካከል አንዱ ዜጎች ለፍትህ፤ለእኩልነት እና ለነፃነት አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ነው።
በህወሃት ዘመነ መንግስት የመከራ እንባችሁን በመዳፋችሁ የምታፍሱ፤ ህወሃት በአገሪቷ ላይ እያደረሰ ያለው የጥፋት ድርጊት የሚያነገበግባችሁ እና ምን እናድርግ መሪ አጣን የምትሉ ስሙን! መሪ ካጣችሁ እንዲህ አድርጉ “ራሳችሁ ተነሱና መሪ ሁኑ!”። ከምታምኗቸው ጥቂት ወዳጆቻችሁ ጋር ሁናችሁ ተደራጁ፤ አንዳችሁ አንዳችሁን አድምጡ፤ ጥሩ ተመሪ መሆን ከቻላችሁ ጥሩ መሪ ወጥቷችኋል ማለት ነው። የአገራችን ፈርጀ ብዙ ችግር በጥቂት ዜጎች ብቻ የሚቀረፍ አይደለም።የሁሉንም ቁርጠኛ ዜጎች ትግል የሚጠይቅ ነውና በየመንደራችሁ ተደራጅታችሁ የጎበዝ አለቃ መርጣችሁ ዘረኞችን፤ ዘራፊዎችንና አድሎዋዊ ሥርዓት የዘረጉባችሁን ታገሏቸው። እንዲህ ካደረጋችሁ ከእኛ ጋር ለመገናኘት መንገዱ ቀላል ይሆናል።
የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጥያቄ አጭርና ግልፅ ነው። ፍትህ፤ ነፃነትና እኩልነት በኢትዮጵያችን ይሰፈን ነው። የህወሃትን ዘረኝነትና አምባገነንነት የሚፀየፍ ሁሉ የንቅናቄያችን ደጋፊ ነው። እነዚህን ነገሮች በኢትዮጵያ ለማስፈን በሚችለው ሁሉ ርምጃ መውሰድ የጀመረ የንቅናቄያችን አካል ነው። እኛም ከጎኑ አለን። እንዲህ በማድረግ የማይቀረውን ለውጥ አናመጣለን። ለውጡ ይመጣል አንድም የተፈጥሮ ህግ ስለሆነ፤ አንድም ደግሞ እኛ ሳናቅማማ የፈለግነውን ለውጥ ለማምጣት ስለተነሳን።
ህወሃቶች መስልጠን የማይችሉ፤ ከአዲስ አስተሳሰብ ጋር ራሳቸውን ማዋሃድ የማይሆንላቸው ፍፁም ግትሮች መሆናቸውን በተዳዳጋሚ አይተናል። ይሄን ግትርነታቸውን እንደ ጀግንነት ይቆጥሩታል። በአገራችን ደህና አባባል አለች እንዲህ የምትል “ሞኝ አሸነፈ ምን ብሎ? እምቢ ብሎ” ይባላል። ህወሃቶችን በዚህ አባባል መግለፅ ሞኝ ያስመስላቸዋል እነርሱ ግን ሞኞች አይደሉም ጨካኞች እንጂ። የጭካኔያቸው ምንጭ ደግሞ በራሳቸው የማይተማመኑ ደካሞች መሆናቸው ነው። እነርሱ ከዛሬ ሠላሳ ዓመት በፊት በመስታወት ውስጥ ያዩትን የራሳቸውን ምሥል ዛሬም መልሰው ያንኑ ምሥል እያዩት ነው። ከሠላሳ ዓመት በኋላም ሊቀየሩ አልቻሉም። ከዚያ ካረጀው ምሥላቸው ላይ ዓይናቸውን ነቅለው ግዜው እና ሁኔታው የፈጠረውን በአካባቢያቸው ያለውን አዲስ ምሥል ለማየት አቅቷቸውል። ስለዚህ ህወሃቶችን ማስወገድ ግድ ነውና ሁሉም በያለበት ለሚመጣው ለውጥ ራሱን ያዘጋጅ፤ የለውጡም አካል ይሁን እንላለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
No comments:
Post a Comment