Monday, 11 April 2016

ትግሉ ሰፊ የምሁራን ተሳትፎ ይሻል!


April 8, 2016
def-thumbኢትዮጵያ በበብዛትም ይሁን በጥራት በውጭው አለምም ይሁን በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ምሁራን ያፈራች ሀገር ነች። በጅጉ የሚያሳዝነው ግን በሀገሪቱና በሕዝቧ ችግር ላይ ሀሳብ ሲሰጡ ፣ ባደባባይ ሲከራከሩና ሲታገሉ የሚታዩት በጅጉ ጥቂቶች ናቸው። ርግጥ ነው ተከታታይ መንግስታት በምሁራን ላይ ያደረሱት ጥቃትና ማግለል ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ብዙዎች መከራን ከህዝብ ጋር ከመጋፈጥ ይልቅ አጎንብሶ ማሳለፈን የመረጡበት ሁኔታ አለ። ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆኑም ለግል ጥቅማቸው ቅድሚያ በመስጠት ከጨቋኝ ገዥዎች ጋር በመተባበር የሚሰሩ መኖራቸውም አይካደም። አብዛኛው ምሁራን በተለይም በብዙ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ጭምር ሀገሪቱን ከገባችበት ማጥ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ውስጥ እየተሳተፉ አይደለም። ይህ ዛሬ ባለው ችግርም ይሁን በታሪክ ፊት አሳዛኝ ነው።
ሀገራችን ዛሬ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። የተማሩ ልጆቿ መላ እንዲመቱ በመጠየቅ ላይ ትገኛለች። ይልቁንም በሀገራችን ያለው ችግርና ሀገሪቱ እየሄደች ያለችበት መንገድና አቅጣጫ በተለይ ምሁራንን እንቅልፍ ሊነሰ ይገባል። ዕውነታው ከዚህም አልፎ የሀገሪቱን አሳዛኝና አደገኛ ሁኔታ ለመቀየር በሚደረገው ትግል ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ግድ ይላል። የመንግስት ግፍና ሰቆቃ በበዛበትና የሀገራችን ሕልውና አደጋ ላይ በወደቀበት በአሁኑ ሰዓት ምሁራን ላለመሳተፍ ምክንያት ማቅረብ የማይችሉበት ወቅት ላይ ደርሰናል። እንደማንኛውም ሀገር ምሁራን የኢትዮጵያ ምሁራን በሀገራችን ውስጥ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና ፍትሕ የሰፈነበት ስርዓት እንዲመሰረት ሊሸሹት የማይገባ ትልቅ ሚና አላቸው።
ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎች መንግስት በልማትና በልማት እያመካኘ የሚያካሂደውን ሰፊ ዝርፊያ እንዲሁም ወያኔ ሩብ ምዕተ አመት ሙሉ በብሄረሰብ እኩልነት ስም እየማለ የሚያደርሰውን ያንድ ብሄረሰብ ጉጅሌ የበላይነት ማስፋፋት እምርረው በመታገል ላይ ናቸው። መስዋዕትነቱን እየከፈሉ የሚታገሉትና የሚወድቁ የሚነሱት ወጣቶችና ምስኪን ገበሬዎች ናቸው። እነዚህ ወገኖቻችን ሕይወታቸውን ሳይቀር ሲገብሩ በየቀኑ እየሰማንና እያየን ነው። ይህንን የህዝብ ጥያቄና ትግል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምሁር ተመልካች ሆኖ ሊቀመጥ አይገባም። ትግሉን ከመምራት ጀምሮ እስከ ተራ ታጋይነት ባሉት ረድፎች ሁሉ ምሁራን ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል። ሰለትግሉ እቅጣጫም ሆነ ስለሀገሪቱ መጻዔ ዕድል ሃሳብ ማመንጨትና ማሰራጨት ይኖርበታል። ሀገራችን የደለቡ ችግሮቿን ተቋቁማ ፍትሕ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ሀገር የሚያደርጋትን የምህንድስና ስራ አስቀድሞ ማሰብና ማመቻቸት ይኖርበታል። ርግጥ ነው ይህን መሰል ተሳትፎ የሚያደርጉ ምሁራን አሁንም አሉ። ቁጥራቸው ግን ሊሆን ከሚገባው ጋር ሲወዳደር በጅጉ አነስተኛ ነው።
ምሁርነት ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ መቀዳጀት ብቻ እንዳልሆነ የታወቀ ነገር ነው። ምሁርነት ምሉዕ የሚሆነው መላውን የተፈጥሮ ከባቢ ከህዝብ ማህበራዊ ሕይወት ጋር አጣምሮ የሚያስብ አዕምሮን በዕውነት ላይ ለተመሰረተ ሀሳብና ዕውቀት ክብር መስጠትን ለተግባራዊነቱ መሟገትን የጨመረ ሲሆን ነው ። በመሆኑም ሁሌ እንደሚባለው ምሁርነት የጋን መብራትነት አይደለም። ምሁርነት በጨለማ ውስጥ ችቦ ሆኖ ብርሃን መፈንጠቅን ይመለከታል። ምስዋዕትነትንም ይጠይቃል።
ያለንበት ወቅት ለኢትዮጵያ ምሁራን ከፍተኛ ፈተናም ዕድልም ይዞ ቀርቧል። ይህ ልሽሽህ ቢሉት የማይሸሽ ፈተና ከመሆኑ ባልተናነሰ በታሪካችን እንድ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የጎላ አሻራን ለማኖርም ትልቅ የታሪክ ዕድል ነው። ይህ ፈተና ከፍተኛ ያርበኝነት ስሜትንና ሀላፊነት መውሰድን ይጠይቃል። አገር በተወሳሰበ ችግር ምክንያት ወደ አረንቋ እየገባች ምንም ሳይሰሩ መቀመጥ ወይም ዝም ብሎ ከመመልከት የበለጠ ለምሁር ሂሊና የሚከብድ ነገር ሊኖር አይችልም:: በጣም ላስተዋለ ሰው እንዲህ አይነት ዝምታ ሐጢያትም ነው። በእንዲህ አይነት ፈታኝ ወቅት የኢትዮጵያ ምሁራን ሀገሪቱን ወደተሻለ አቅጣጫ እንድትሔድ ላለመታጋል ምንም ምክንያት ማቅረብ አይችሉም። ሀሳብ የሚሰራጭባቸው የሀሳብ ክርክር የሚካሔድባቸው መድረኮች ፣ አደባባዮች ፣ የመገናኛ መሳሪያ አይነቶች የፖለቲካና የሲቪክ ማህበሮች ባገር ውስጥም በውጭም ያሉት መሳተፊያ ናቸው።
ድርጅታችን አርበኞች ግንቦት 7 ምሁራን በሰፊውና እንደየፍላጎቶቻቸውና ችሎታቸው ሊሳተፉ የሚችሉባቸው በርካታ የትግል መስኮች አሉት። የሀገሪቱን ውስብስብ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ የጥናት ውጤቶች ፣ ሀሳቦች ፣ ምክሮችም ሆነ ቀጥተኛ የምሁራን ተሳትፎ ለማስተናገድ አመቺ ሁኔታ ያለበት ድርጅት ነን። ወደፊትም የምሁራን ተሳትፎ እንዲጎለብት ሁኔታዎችን ይበልጥ ለማመቻቸት እንሰራለን። ዽርጅታችን የሀገራችን ችግር የሚወገደውና ዲሞክራሲና የዜጎች እኩልነት የሚረጋገጠው በበሰለና ከተራ ዜጋ እስከ ብስል ምሁራን በሚያከሂዱት ክርክርና የበሰለ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ መሆኑን ያምናል። አሁን ያለው የሀገራችን ምሁራን ተሳትፎ ደረጃ ሁላችንም ከምንጠብቀው በታች በጅጉ ያነሰ መሆኑ ሁላችንንም ከማሳዘን አልፎ የሚያስቆጭና የሚያንገበግብ ሆኖአል:: አገርና ህዝብ ድረሱልኝ እያለ በሚጣራበት በዚህ የታሪክ አጋጣሚ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደሩ ማለፍ ይቻል ይሆናል። ይዋል ይደር እንጂ ለነጻነቱ ቀናዕ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበትን አፈናና ጭቆና እምቢኝ ብሎ ነጻነቱን ሲቀዳጅ ግን ከታሪክ ፍርድና ከህዝብ ትዝብት ማምለጥ አይቻለም።
አርበኞች ግንቦት 7 በአገር ውስጥም ሆነ በተለያየ ምክንያት በአለም ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ምሁር ለወገን ደራሽነቱንና አለኝታነቱን አሁኑኑ ይወጣ ዘንድ ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

Wednesday, 6 April 2016

ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ተጠናክሮ ይቀጥል!


March 12, 2016
def-thumbከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝባዊ እምቢተኝነት አድማሱን እያሰፋ በመሄድ ላይ ነው። የአዲስ አበባ የታክሲ አሽከርካሪዎች ያደረጉት አድማ፣ ወደ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ጋይንት፣ ደብረታቦር፣ አለምበር፣ ነቀምት፣ ወለጋ፣ ወሊሶና ሌሎችም አካባቢዎች ተዛምቷል። በተለይ በአዲስ አበባ በሙስና የተጨማለቁት የወያኔ ሹማምንት ፣ የሚይዙትና የሚጨብጡት አጥተው ሲባዝኑ ተመልክተናል። ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረው ድንፋታ ሁሉ ተንኖ፣ “ብቻ ስራ ጀምሩልን እንጅ እኛ ጥያቄውን በአፋጣኝ እንመልሳለን” በማለት ሾፈሮችን ሲማጸኑ አይተናል ።አድማው የወያኔን ትእቢት ያስተነፈሰ፣ የውስጡን ቀፎነት ገሃድ ያወጣና፣ እንደ ፊኛ ተነፍቶና ግዙፍ መስሎ የሚታየውን ሃይል በትንሽ ሃይል ማስተንፈስ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ክስተት ነው። የአለም በር አሽከርካሪዎች ደግሞ ” የምታደርጉትን አድርጉ እንጅ፣ በእኛ ላይ ቅጣት ልትጥሉ አትችሉም” በማለት ጠንካራ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ከመገናኛ ብዙሃን ሰምተናል። እንዲህ አይነት ህዝባዊ እምቢተኝነቶች፣ የነጻነት ታጋዮችን የትግል ወኔ የሚያነሳሱ ብቻ ሳይሆን፣ ወያኔ የማይቀረውን ሞት ሲሞት፣ በመቃብሩ ላይ አስተማማኝ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉ ናቸው። ወያኔ ተለጣፊ የሲቪክና የሙያ ማህበራትን በራሱ አምሳል ፈጥሮ፣ በአባሎቻቸው የተመረጡት ማህበራት እንዲኮላሹ በማደረግ ለአመታት የመብት ትግሎች እንዲቀዛቀዙ ቢያደርግም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በእነዚህ ማህበራት ተስፋ የቆረጡ ሰራተኞች ፣ የይስሙላ ማህበራቱን ወደ ጎን በመተውና ራሳቸውን ከወያኔ እይታ ውጭ በማደራጀት ያካሄዱት ትግል፣ በአርያነቱ የሚዘከርና በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ ነው። ከሰሞኑ የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል የተገኘው ትልቁ ትምህርትም ይህ ነው፤ ዜጎች ለመብታቸው ለመታገል እስከቆረጡ ድረስ፣ የወያኔን አንድ ለአምስት የጥርነፋ ስልት በዘዴ በማለፍ ራሳቸውን በራሳቸው አደራጅተው መብታቸውን ለማስከበር የሚያግዳቸው ሃይል አይኖርም። በኦሮምያ የሚካሄደው ህዝባዊ እምቢተኝነትም ሆነ የታክሲ አሽከርካሪዎች አመጽ፣ ዜጎች ለመብታቸው ለመታገል ሲቆርጡ የሚፈጥሩት አቅም፣ ከወያኔ የጥርነፋ አቅም በላይ መሆኑን ያሳዬና ሌሎቻችችንም ትልቅ ትምህርት የምንወስደበት ነው።
የአለማችን የነጻነት ትግሎች ታሪክ እንደሚነግረን በጭቆናና አፈና ቀንበር ውስጥ የሚገኙ ህዝቦች ትክክለኛ አላማና ራእይ አንግበው አንድ ጊዜ ቆርጠው ትግል ከጀመሩ፣ ትግላቸው እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ይሄዳል እንጅ፣ በገዢዎች የአፈና መሳሪያዎች አይቆምም። ከአራት አመታት በፊት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የለኮሱት የድምጻችን ይሰማ ትግል፣ ከ 2 ዓመታት በፊት በደቡብ የአገራችን ክፍል ለነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ እርሾ ሆኖ አገልግሏል፤ የደቡቡ ህዝብ ትግል ደግሞ ኦሮምያን ከጫፍ ጫፋ ላዳረሰው ህዝባዊ ትግል መነሻ ሆኖ አግልግሏል፤ በኦሮምያ የቀጠለው ትግልም እንዲሁ በአማራ ክልል ለሚታዩት ተቃውሞች እና በአዲስ አበባ እንዲሁም በሌሎች ከተሞች ለታዩት የታክሲ ሾፈሮች አድማ መነሻ ሆኗል። እነዚህ ተቃውሞች እስካሁን ተቃውሞውን ባልተቀላቀሉ ሌሎች ማህበረሰቦችም ዘንድ ተመሳሳይ መነቃቃት እንደሚፈጥሩና እኔም ለመብቴ መከበር መነሳት ይኖርብኛል የሚል እልህና ቁጭት እንደሚፈጥር አይጠረጠርም:: በዚህም ምክንያት መምህራን፣ የተለያዩ የፋብሪካ ሰራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ የተለያዩ የሙያ ማህበራት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ጡረተኞች፣ ፖሊሶች፣ የቀድሞ ወታደሮች፣ አርሶ አደሮች ወዘተ መብታቸውን ለማስከበር በአንድነት ወይም በየግላቸው እንደሚነሱ ይጠበቃል:: ህዝባዊ ትግል እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጣይ ነውና። ህዝባዊ አመጽ የሚቆመው ፣ በጥይት ወይም በዱላ ሳይሆን፣ ለአመጽ ምክንያት የሆነውን ጥያቄ በመመለስ ብቻ በመሆኑ፣ በአሁኑ ሰአት በአገራችን ዋነኛው የአመጽ መንስኤ የሆነው የመብት ጥያቄ ፣ ትክክለኛውን ምላሽ እስካላገኘ ድረስ ሊቆም አይችልም።
አርበኞች ግንቦት7 ህዝባዊ እምቢተኝነትን እንደ አንድ የትግል ስልት አድርጎ ሲያውጅ፣ የወያኔን አፋኝ ስርዓት በውጭም በውስጥም ለመከፋፋልና ለማዳከም ይጠቅማል ከሚል ስልት ብቻ ሳይሆን፣ የህዝባዊ እምቢተኝነት መጠናከርና ይህን ትግል የሚያካሂዱት የሲቪክም ሆነ የሙያ ማህበራትን ማጠናከር ፣ ከወያኔ ፍጻሜ በሁዋላ፣ በአገራችን ለሚጀመረው የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ከልብ በማመንም ጭምር ነው። ወያኔ ገና ወደ ስልጣን ሲመጣ፣ የሰራተኛ ፣ የመምህራን ፣ የጋዜጠኞች ወዘተ ማህበራትን ዳግም እንዳያንሰራሩ አድሮጎ የመታቸው፣ የማህበራቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንደልብ የሚዘርፍበትን ስልጣን እንደሚያሳጣው ስለሚያውቅ ነው፣ ለነገሩ ከመጀመሪየውም ለዝርፊያና ለቅሚያ የመጣ ሽፍታ፣ በአገራችን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲፈጠር ፍላጎት ሊኖረው ይችላል ብሎ ማሰብም የዋህነት ነበር። አስገራሚው ነገር ደግሞ ይህ የሽፍታ ስብስብ፣ ከ25 አመታት ዝርፊያ በሁዋላ፣ በቃኝ ብሎ ከዘረፋ ተግባሩ ለመታቀብ አለመቻሉና የዘረፈውን ህብት እንኳን ተመቻቸቶ ለመብላት የሚያስችለውን ስርዓት ለመገንባት አለመቻሉ ነው። ስብስቡ ላለፉት 25 ዓመታት ዘርን ከዘር እያጋጨ፣ እየገደለና እያሰረ፣ ያለከልካይ እንዲዘርፍ በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት የህዝባችን ነጻነትም በዛው ልክ እየተደፈጠጠ መጥቷል፣ ዛሬ እስከናካቴው ሰብሰብ ብሎ የግል ጉዳይን መጫወትም እንደሰላማዊ ሰልፍ እየተቆጠረ፣ የሚያስከስስበትና የሚያስደበድብት ደረጃ ተደርሷል ። የሙያና የሲቪክ ማህበራት እንዲኮላሹ መደረጋቸው፣ ወያኔ እንደልቡ እንዲዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ ለነጻነቱ የሚታገል፣ ወኔና የአገር ፍቅር ስሜት ያለው ትውልድ እንዳይፈጠር አድርጓል። ነገር ብዙ ጥፋቶች ከደረሰም በሁዋላም ቢሆን፣ ህዝባችን ቀስ በቀስ የወያኔን ማንነት ይበልጥ እያወቀ ሲመጣ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደምናየው ፣ ህዝባዊ ተቃውሞችና አልገዛም ባይነቱን እያሳደገ መጥቷል። ለዚህ ውጤት መገኘት ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፤ ህዝባችን ለመረጃዎች ቅርብ እየሆነ በሄደ ቁጥር የመብት ትግሎችም በዚያው ልክ እየተጠናከሩ የሚሄዱ በመሆኑ፣ መጪዎች አመታት የኢትዮጵያውያንን የነጻነት ትግል የሚያስተናግዱ ብቻ ሳይሆን የአገራችን መጻኢ እድል የሚወሰንባቸው ወሳኝ አመታት በመሆናቸው ሁላችንም ማንኛውንም እንቅስቃሴ በንቃት እየተከታተልን የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለብን።
አርበኞች ግንቦት7 በሃይል ትግሉም በህዝባዊ እምቢተኝነቱም በኩል ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ሌት ተቀን አቅም የፈቀደለትን ሁሉ እያደረገ ይገኛል። የንቅናቄያችን ሊቀመንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እንዳደረጉት ሁለቱም የትግል ስልቶች ተቀናጅተው የወያኔን ግብአተ መሬት እንዲያፋጥኑ ድርጅታችን ሁኔታዎች አመቺ ናቸው ብሎ በሚያምንበት ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኛ ነው። ፍትህ፤ እኩልነትና ነጻነት በአገራችን እንዲሰፍን የሚሻ ማንኛውም ዜጋ በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ንቅናቄያችን የቆመለትን አላማ ለማሳካት በያለበት ሆኖ ትግሉን እንዲቀላቀል ወገናዊ ጥሪያችንን መላልሰን እናቀርባለን:: በሥራ ዋስትና ሰበብ ከወያኔ አለቆቻቸው የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው በገዛ ወገኖቻቸው ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ በማካሄድ ላይ የሚገኙ የመከላከያ ፤ የፖሊስና የደህንነት ሃይሎችም ቆም ብለው በማሰብ ከህዝባቸው ጋር እንዲወግኑ አርበኞች ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪውን ያስተላልፋል::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
አርበኞች ግንቦት7

ዛሬም እንደ አድዋው ጊዜ አብረን እንነሳ

March 3, 2016
def-thumbበያዝነው ሳምንት አባቶቻችን የነበረውን የትጥቅ የበላይነት መከታ በማድረግ ሀገራችን ኢትዮጵያን ለመውረርና ህዝቧን በውርደትና በባርነት ለመግዛት የዘመተብንን የጣሊያን ጦር አለምን ማስደነቅ ብቻ ሳይሆን የታሪክን አቅጣጫ የቀየርውን ያድዋን ጦርነት ድል የመቱበት 120ኛ ዐመት ይከበራል። አድዋ ሲወሳ ፈጽሞ ልንረሳው የማንችለው ነገር በእግር በፈረስ ከሀገራችን ልዩ ልዩ ቦታዎች የብሔረሰብም ሆነ ሌላ ልዩነት ሳያግዳቸው እንደ አንድ ሰው የተነሱ አባቶቻችንን የህብረት ተጋድሏቸውን ነው።። የድላቸው ዋንኛ ምክንያትም ህብረትና አንድነታቸው እንደነበር ልንዘነጋው አይገባም። እድዋ የመላው ጥቁር ሕዝብ አንጸባራቂና አለም ያላሰበው ድል እንዲሆን ያደረገው አባቶቻችን ወርደትንና ባርነትን ከሞት በላይ ስለቆጠሩት ብቻ ሳይሆን በህብረትና ባንድነት መነሳታቸው እንደነበር ፈጽሞ ልንዘነጋው አይገባም። ተዋርዶና ተንበርክኮ መገዛትን ምንም ያህል ቢጠሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ባይነሱ ይህን እንጸባራቂ ድል ይቀዳጁ ነበር ብሎ ማሰብ ይከብዳል።
ዛሬ በተደጋጋሚ ሀገራችንን የወረሩ ጠላቶች ሁሉ ሊጠቀሙበት ሞክረው ያልቻሉትን የከፋፍለህ ግዛ ሴራ በመጠቀም እንደባዕድ ሊገዛን እየሞከረ ያለውና ሀገራችንን ካላንዳች ይሉኝታ በመዝረፍና ልጆቹዋን ካለርሕራሔ በመጨፍጨፍ ላይ የሚገኘውን የሁላችንም ጠላት የሆነውን ወያኔን ከላያችን ላይ አሽቀንጥረን የምንጥለውና ነጻነታችንን የምንቀዳጀው እንደ አድዋው ጊዜ እብረን የተነሳን እንደሆን ብቻ ነው። ወያኔ 25 ዓምት የፈነጨብንና ሀገራችንን ከባዕድ ባልተናነሰ ዛራፊነትና ጨፍጫፊነት ሊገዛ የቻለው የውበታችን ምልክት የሆነውን ብሔረሰባዊ ልዩነታችንን እየተጠቀመ ይሁን እንጂ ብዙዎቻችንም ተመሳሳይ ዓላማ ይዘን በህብረት ለመታገል ባለመወሰናችን ካባቶቻችን ያድዋ ትሪክ ባለመማራችን መሆኑን መካድ አይቻልም።
ብዙ ወገኖቻችን ሲሉ እንደሚሰማው የወያኔው ጉጅሌ ሀይል የራሱ ድርጅታዊ ጥንካሬ የፈጠረለት ሀይል ሳይሆን ከኛ መከፋፈል ያገኘው ነው። ዛሬ በኦሮሚያና ሌሎች አካባቢዎች የህዝቡን መሬት ካለይሉኝታ የሚዘርፈው ወያኔ፣ ሕጻን ሽማግሌ ሳይለይ በእብሪትና በድፍረት መደዳውን ኦሮሞ ወገኖቻችንን እየጨፈጭፈ ያለው ህዝቡ አይተባበርም በሚል ነው። የሀገራችንን ድንበር ቆርሶ ለመስጠት ከጀርባችን ሆኖ የሚደራደረው የተባበረና አንድ ድምጽ ያለው ህዝብ አይጠይቀኝም ከሚል በመነጨ ጥጋብ ነው። የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ማንነቴን ከናንተ ይበልጥ የማውቀው ራሴ ነኝ ስላላቸው እየነቀሱ የሚያፍኑትና ይስንቱን ቤት ለዘላለሙ እንዲዘጋ ያደረጉት የሚተባበር ሕዝብ የለም በሚል ተስፋ ነው።
ወያኔ የብሔረሰብ ልዩነታችንን ብቻ ሳይሆን በትግል ዘዴ አመራረጣችንና በተለያዩ በክርክር ሊቋጩ የሚችሉ የፖለቲካ ልዩነታችን መሀል በመግባት ወደ አንድነት እንዳንመጣ ከለመታከት ይሰራል። በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ይህ እንዲሆን የፈቀድንለት ራሳችን በመሆናችን ላለመተባበራችን ሁላችንም የተወሰነ ወቀሳ መውሰድ ይኖርብናል።
አሁን ጊዜ የለንም። ወገኖቻችን በገፍ አየተጨፈጨፉ መፈጠራቸውን ሊጠሉ በቻሉበት ደረጃ ደርሰዋል። በየቦታው አመጾች በመቀጣጠል ላይ ናቸው። ወያኔ በተወሰነ ደረጃ የህዝቡ ቁጣ ስላስደነገጠው የሚያውቀውን የመጨፍጨፍና የመቀጥቀጥ ፖለቲካ በስፋት ተያይዞታል።አርበኞች ገንቦት 7 በሀገርም ከሐገር ውጭም ካሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ያድዋውን አይነት ህብረት እንዲፈጠር ይፈልጋል። ያለን መስፈሪያ ሀገራችንን ሉዓላዊ ሆና መቀጠሉዋና ወደፊት የምንመሰርተው መንግስት ዲሞክራሲያዊ መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ነው። እኛ በሰላምም በሐይል አማራጭም ከወያኔ ጋር የሚተናነቁትን ማንኛውንም የፖለቲካ ሀይሎች እንደግፋለን። ሕዝባችን ወይ ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ እያለ ሲጮህ ብዙ ዘመን ሆነው። እናም እንተባበር።
አባቶቻችን የዛሬ መቶ ሀያ አመት የተጠቀሙበት ስልት ለኛ ለልጅ ልጆቻቸው የሚሳነን ሊሆን አይገባም። ሁል ጊዜ እንደሚባለው እንድነት ሀይል ነው። ወያኔ አንድ ላይ በቆምን ማግስት በኢትዮጵያ መሬት ላይ አይኖርም። አድዋ ላይ ጠላትን ተባብረው እንዳንበረከኩት አባቶቻችን፣ ራሳቸውንና እኛን ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን መላውን ጥቁር ህዝብ እንዳኮሩትና የአለም ታሪክን አቅጣጫ እንደቀየሩት አባቶቻቸን ተባብረን እንድንነሳ አርበኞች ግንቦት 7 የትግል ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

Friday, 26 February 2016

ጭፍጨፋውን ለማስቆም ሆ ብሎ መነሳት ብቸኛው መፍትሄ ነው !

 
February 26, 2016   
def-thumbየዛሬ 79 አመት ባህር አቋርጦ ድንበር ተሻግሮ የመጣው የጣሊያን ፋሽስት ሠራዊት በአዲስ አበባ ነዋሪ ወገኖቻችን ላይ ከፈጸመው ዘግናኝ የጭፍጨፋ እርምጃ የማይተናነስ እልቂት፣ ዛሬም በኦሮሞ ወገናችን ላይ በአገር በቀል የህወሃት አልሞ ተኳሽ የአጋዚ ጦር ሠራዊት እየተፈጸመ ይገኛል።
የካቲት 12 ቀን 1929፣ በሮዶልፎ ግራዚያኒ ትዕዛዝ የአዲስ አበባን ነዋሪ ሕዝብ በደም ጎርፍ ባጥለቀለቀው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ህጻናት፣ ጎልማሶች ፣ ሽማግሌዎች፣ አሮጊቶች፤ ነፍሰጡሮች፣ ለጋ ወጣቶች፣ በአጭሩ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሁሉ ዘራቸው ፣ ሃይማኖታቸውና ጾታቸው ሳይለይ በጅምላ በመታረዳቸው፣ ደማቸው በስድስት ኪሎ አደባባይ እንደ ወራጅ ወንዝ መፍሰሱን፣ ታሪክ ጊዜ በማያደበዝዘው ብዕሩ መዝግቦት ይገኛል። የግራዚያኒ ጦር በወገኖቻችን ላይ ያንን አሰቃቂ እልቂት የፈጸመው ለነጻነታቸው ቀናይ የሆኑት ሞገስ አስግዶምና አብረሃ ደቦጭን የመሳሰሉ ጀግኖች ኢትዮጵያኖች፣ የጣሊያንን ቅኝ አገዛዝ በመቃወም በጠላት ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ለመበቀልና በጠመንጃ ሃይል የአገሪቱን ህዝቦች በባርነት ቀንበር ሥር አውሎ ሃብትና ንብረት ለመዝረፍ በማለም ነበር።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነ የመጣው በፋሽስት ጣሊያንና ለጠባብ የቡድንና የግል ጥቅም የመንግሥትን ሥልጣን የሙጥኝ ባለው ህወሃት መካከል ያለው ልዩነት አንዱ ባዕድ ወራሪ ሌላኛው አገር በቀል ከመሆን ያለፈ አይደለም። ጣሊያን የኢትዮጵያን ማዕከላዊ ሥልጣን የፈለገው ለአገሩ ኢንዱስትሪ የሚሆን ጥሬ የተፈጥሮ ሃብት ፍለጋ ሲሆን፣ ህወሃት ደግሞ የአገሪቱን ለም መሬት በርካሽ ዋጋ ለባዕድ በመቸብቸብ ጭምር ባለሥልጣናቱና የጥቅም ተጋሪዎቹ ሃብት እንዲያካብቱ ከማድረግ የዘለለ ራዕይ ኖሮት እንዳልሆነ በበርካታ ተግባሮቹ አስመስክሯል።
ወያኔ አጋዚ የሚባል ልዩ ጦር አሰልጥኖና አስታጥቆ ከህዝብ የሚነሳን ተቃውሞና እሮሮ ለመጨፍለቅ የሚወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ፣ መነሻው ለዘረፋ መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀምበትን በትረ ስልጣን ለመከላከል እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ አካባቢ የተጀመረውን ህዝባዊ ተቃውሞ በሃይል ለመጨፍለቅ የህወሃት ልዩ ቅልብ ጦር በህዝባችን ላይ እየወሰደ ያለው ጭፍጨፋ የፋሺስት ግራዚያን ጦር አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ላይ የዛሬ 79 አመት ከፈጸመው የሚለየው በሟቹች ቁጥር እና በገዳዮቹ ማንነት ብቻ ነው። የአጋዚን ጦር አሰልጥኖና አስታጥቆ በገዛ ወገኑ ላይ ፣ እንደባዕድ ሠራዊት፣ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ እንዲፈጽም ያሰማራው ህወሃትም ሆነ ከአለቆቹ የተሰጠውን ትዕዛዝ በፍጹም ታማኝነት ተቀብሎ በገዛ ወገኖቹ ላይ ታሪክ ይቅር የማይል ወንጀል በመፈጸም ላይ የሚገኘው ይህ ሠራዊት፣ ላለፉት 25 አመታት ያልአግባብ ያፈሰሰው ደምና የቀጠፈው ወገኖቻችን ህይወት ቁጥር ለመቁጠር እያዳገተ መጥቷል።
በተለያዩ ጊዜዎች በኦጋዴን፤ በጋምቤላ፤ በቤኔሻንጉል፤ በአፋር፤ በአማራና ደቡብ አካባቢዎች ከደረሰው የግድያ ፍጅት በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመደፍጠጥ የአጋዚ ጦር ከአለቆቹ በተሰጠው ትዕዛዝ የጨፈጨፋቸው ዜጎች ቁጥር ከ300 በላይ ደርሷል:: ቁጥሩ ከዚህ በእጥፍ የሚበልጥ ቁስለኛና ከ8 ሺህ በላይ እስረኞችም እንዳሉ ገለልተኛ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየተናገሩ ነው። በአልሞ ተኳሾች ህይወታቸው ከተቀጠፉት መሃል ዕድሜያቸው ገና 8ና 9 አመት የልበለጣቸው ታዳጊዎች፤ አሮጊቶችና እርጉዝ ሴቶች ይገኛሉ። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአምቦ ከተማ በደረሰው ጥቃት የ9 አመት ታዳጊ ህጻንን ግንባር አነጣጥሮ የመታው የአጋዚ ጦር፣ ወንድሟን ከወደቀበት ለማንሳት ጎንበስ ያለቺውን እህቱን በሌላ ጥይት በመምታት ቤተሰቦቿንና የከተማውን ህዝብ የመረረ ሃዘን ውስጥ ጥሏል፤ ተመሳሳይ ግድያ በአሰላ ከተማ ውስጥ በምትኖር የ8 ዓመት ታዳጊ ላይም ተደግሟል።
በሴቶችና በህጻናት ላይ ጥይት የሚያስተኩስ የአውሬነት ባህሪ ከየትኛው ባህላችን የመጣ ነው? ይህንን አሰቃቂ ድርጊት የተመለከተ ወይም የሰማ ሰው እንዴት አድርጎ ነው ሠራዊቱንና አዛዦቹን ከአብራኩ የተገኘ የአገሩ ዜጋ አድርጎ ማሰብ የሚችለው? የዚህ አይነት አሰቃ ድርጊት ዛሬ የጀመረ ሳይሆን በድህረ ምርጫ 97 በአዲስ አበባና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥም ተፈጽሟል። በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ በወቅቱ ከተማዋን ወሮ የነበረው የአጋዚ ጦር ያገኘውን ሁሉ በጥይትና በቆመጥ ሲያዋክብ፣ ሠይድ የተባለ የ10 አመት ልጅ የጨርቅ ኳሱን ከመሬት አንስቶ ለመሮጥ ሲንደረደር አናቱን በጥይት ተመቶ እስከወዲያኛው አሸልቦአል። በስተርጅናቸው ይጦሩኛል ብለው መርካቶ ውስጥ ሽንኩርት በመቸረቸር ሁለት ልጆቻቸውን ተቸግረው ያሳደጉ የእነ ፍቃዱ እናት በአጋዚ ጥይት ሁለቱንም በአንድ ጀንበር ተነጥቀዋል:: ምንም ጥፋት እንዳላጠፋ እየመሰከሩ ባላቸውን ከእስር ለመታደግ የሞከሩ የልጆች እናት ወ/ሮ እቴነሽ ሴት ልጆቻቸው ፊት በጥይት ተገድለው ቤተሰብ የተገደሉበትን ጥይት ዋጋ ከፍሎ አስከሬን አንዲወስድ ተደርጓል። የ14 አመቱ ነብዩ አለማየሁም ባንክ ልትዘርፍ ነበር ተብሎ በግፍ ተገድሏል። ያ እሮሮ ያ ጩኸት ወያኔ ሥልጣን ላይ እስካለ ብቻ ሳይሆን እስከ ወዲያኛውም ከህሊናችን አይጠፋም። ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ የድህረ ምርጫ 97 አይነቱ ጭፍጨፋ አሁንም የኦሮሚያ ከተሞችንንና መንደሮችን እያዳረሰ ነው። “እናቴን ለምን ገደላችሁብኝ” ያለ ወጣት ደምቢዶሎ ውስጥ በጠራራ ጸሃይ ህዝብ ፊት ተረሽኗል፤ ምንም አይነት መሣሪያ ያልታጠቁ እናትና ልጅ በአንድ ቀን በአንድ ጀንበር በግፈኞች ጥይት ለህልፈት በቅተዋል፤ በደኖ ውስጥ ፍሮምሳ አብዲ የተባለ የ10 አመት ታዳጊና ወላጅ እናቱም እንዲሁ። ምስራቅ ሃራርጌ ውስጥ ደረታቸው ላይ በተተኮሰ ጥይት ህይወታቸውን ያጡት የ60 አመቷ አዛውንት አዴ ጁሃራ ሙሳንና የሌሎች ሰለባዎችን ፎቶግራፍ በማህበራዊ ድህረ ገጽ የተመለከትን ሁሉ ልባችን በሃዘን ተወግቶአል ፤ በቁጭትም በግኗል። በመቻራ፤ በነገሌ፤ በነቀምት፤ በኮፈሌ፤ በመንዲ፤ በሆሮ ጉዱሩ፡ በቦቆጂ፤ በአሰላ፤ በሮቤ፤ በጎባ፤ በመቱ ወዘተ በየቀኑ እየፈሰሰ ባለው ደም ምክንያት ተመሳሳይ ለቅሶ ተመሳሳይ ዋይታ የአገራችንን ምድር እያናወጠ ነው። ይህ አረሜኔያዊ ጭፍጨፋ የዕለት ተዕለት በሆነበት ሰሞን ባለፈው ሰኞ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የኦሮሚኛ ፕሮግራም ቃለመጠይቅ የሰጠው ጌታቸው ረዳ፡ በገዛ ወገኑ ላይ እንዲህ አይነት ዘግናኝ እርምጃ እየወሰደ ያለውን የአጋዚ ጦር “በመልካም ሥነምግባር የታነጸና ህዝባዊ ወገናዊነቱን ያረጋገጠ” በማለት ሲያሞካሸው ተሰምቷል። ከሶስት አራት ቀን ቆይታ ቦኋላ ደግሞ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በኦሮሚያ ያለው እንቅስቃሴ “የመንግሥትን ሥልጣን በሃይል ለመንጠቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ ስለሆነ የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል” ሲል በቴለቪዢን መስኮት ብቅ ብሎ ዝቷል። ታዳጊ ህጻናትንና እርጉዝ ሴቶችን ግንባር አልሞ የሚመታ ሃይል ከማሰማራትና ህዝብ ከማስጨፍጨፍ የበለጠ ምን አይነት የማይዳግም እርምጃ ለመውሰድ ህወሃት እንደተዘጋጀ ሃይለማሪያም ደሳለኝ እራሱ የሚያውቅ አይመስለንም። ህዝባዊ ተቃውሞ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ታንክና መትሬየስ እየተተራመሰ እየተመለከትን የማያዳግም እርምጃ የሚሉን እንደ ባህሪ አባታቸው ፋሽስት ጣሊያን የመርዝ ጭስ ከአየር የሚለቅ አይሮፕላን ለማሰማራት ፈልገው ይሆን ? ወቅቱ ፈቀደም አልፈቀደ ወያኔ ሥልጣኑን ለመከላከል ይጠቅማል ብሎ እስካመነ ድረስ የማይወስደው የጭካኔ እርምጃ ይኖራል ብሎ ማሰብ ቢያዳግትም፣ እንደ ሁለተኛው የአለም ጦርነት የመርዝ ጭስ በመጠቀም ሥልጣን ላይ ተደላድሎ መቀመጥ እንደማይቻል የመረዳት አቅም ያለው ወያኔ ውስጥ አለ ብሎ መዘናጋት አያስፈልግም።
በህዝብና በአገር ሃብት ጠንካራ ሠራዊት ገንብቶ ህዝብ እየገደለ፤ እያፈናቀለና እያሰደደ እስከወዲያኛው ሥልጣን መቆጣጠር የቻለ መንግሥት በታሪክ አይታወቅም። የወያኔም መንግስት የመጀመሪያው ሊሆን አይችልም:: የግራዚያኒ ቁራጭ የዛሬው ጥቁር ፋሽስት ወያኔ እራሱን የተለየ ጠንካራ አድርጎ የሚቆጥረው የአለም አምባገነኖችን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የአገራችንን የቀደምቶቹን አወዳደቅ ታሪክ እንኳ መለስ ብሎ ለመመልከት ባለመቻሉ ነው። በጠመንጃ ሃይል በአንድ ወቅት በአንድ ቦታ የሚነሳውን ወይም የተነሳውን ተቃውሞ ማዳከም ወይም መቆጣጠር ይቻል ይሆናል። አፍኖና ነጻነት ገፎ ሥልጣን ላይ ተደላድሎ ለረጅም ጊዜ መኖር ግን በፍጹም እንደማይቻል ወያኔ እራሱ ካካሄደው የጸረ ደርግ ትግል መማር ነበረበት:: ባለመማሩም የራሱን የወደፊት ዕጣ ከቀድሞው የዩጎዝላቪያ ፕሬዝደንት ስሎባዳን ሚሎሶቪችና የአይቬርኮስቱ ሎሬንት ባግቦ ተርታ እያሰለፈ ነው:: ሁለቱም በየአገራቸው ባደራጁትና በሚመሩት ሠራዊት ተማምነው በአገርና በህዝብ ላይ ለፈጸሙት ወንጀል በመጨረሻቸው አፍንጫቸውን ተሰንገው አለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተወረውረዋል:: የአገር መከላኪያ ጦር ዋና አላማና ተግባር የአገርን አንድነትና ሉአላዊነት ከባዕድ ወረራ መከላከል ነው። ወያኔ እየገዛት ባለችው አገራችን ግን እየሆነ ያለው በሠላም አስከባሪነት ሥም ለወያኔ መሪዎችና የጦር ጀነራሎች በውጪ ምንዛሪ ገቢ የሚያስገኝ ድንበር ዘለል ግዳጅ ተግባር ላይ መሠማራት ወይም የገዛ ወገንን መግደልና ማሠር ሆኗል:: ይህ አካሄድ በአስቸኳይ መቆም አለበት:: የወያኔን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ሲባል የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተቀብሎ ህዝብ መጨፍጨፍ፤ ማቁሰልና ማሰር የፍርድ ቀን ሲመጣ “ታዝዤ ነው” በሚል ከተጠያቂነት ነጻ የማያደርግ ወንጀል መሆኑን ሁሉም ሊያውቅ ይገባል:: አሁን በኦሮሚያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ ህዝብ በመፍጀት ለወያኔ ግዳይ ጥሎ የመሸለም አባዜ የተጠናወታቸው አዛዦች ካሉ ቆም ብለው
ማሰብና ከድርጊታቸው መታቀብ ያለባቸውም ከታሪክና ከህግ ፍርድ እራሳቸውን ለማዳን ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 በኦሮሚያ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ ለማስቆም ሁላችንም ሆ ብለን መነሳት፤ አምርረን በመታገል ይህን እጅግ ጨካኝ ዘረኛ ስርአት በማስወገድ ወንጀለኞቹን ለህግ ማቅረብ መቻል ይኖርብናል ብሎ ያምናል:: አባቶቻችን በፋሽስት ጣሊያን ጦር የተሰነዘረብንን ወረራና ጥቃት ለማክሸፍ ሆ ብለው በህብረት እንደዘመቱት ሁሉ፣ ይህ የኛ ትውልድም አገራችንንና ህዝባችንን ለከፋ መከራ የዳረገውን የወያኔ አገዛዝ ከላያችን አሽቀንጥሮ ለመጣል በህብረት መነሳትና መዝመት ያለብን ግዜው አሁን ነው።
በወያኔ ከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ምክንያት በፍርሃትና በጥርጣሬ መተያየታችን የአገዛዙን ጡንቻ አፈርጥሞታል። አንዱ ሲጠቃ ሌላው ዝም ማለቱን ከቀጠለ ሁላችንም በየተራ ተደቁሰን በባርነት ቀንበር ሥር ስንማቅቅ እንኖራለን። ይህ እንዳይሆን የፈለገ ሁሉ ዛሬውኑ በኦሮሚያ እየተቀጣጠለ ያለውን የነጻነት ትግል ይቀላቀል። ከአሁን ጀምሮ አንዱ ሲደማ የሌላው ከዳር ሆኖ ተመልካችነት ማብቃት ይኖርበታል። አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔን ጭፍጨፋ ለማስቆምና አገራችን ውስጥ ሠላም ፍትህና እኩልነት እንዲሰፍን የሚያካሂደውን ትግል ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለው ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲቀላቀሉት የትግል ጥሪውን በድጋሚ አጠናክሮ ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

Tuesday, 23 February 2016

የቆሰለው አውሬ አገራችንን ይበልጥ ሳያቆስል በጊዜ እንነሳ!

   
February 20, 2016 More
def-thumbየንቅናቄያችን ሊቀመንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ ተገኝተው ለኢትዮጵያውያን ባደረጉት ንግግር ወያኔ የቆሰለ አውሬ ሆኗል ብለው ነበር። ፕ/ር ብርሃኑ በንግግራቸው፣ የቆሰለ አውሬ በህይወት ለመቆየት ሲል ያለ የሌለውን ሃይል በመጠቀም ጥቃት በሰነዘረበት ግለሰብ ላይ የበቀል እርምጃ ከመውሰድ ወደ ሁዋላ የማይል በመሆኑ፣ ጥቃቱን ለመከላከል በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበው ነበር። አውሬነት የጭካኔ ደረጃንና ሁዋላቀርነትን የሚያሳይ ገላጭ ቃል ነው፤ አውሬነት ወያኔ በህዝባችን ላይ ለሚፈጽመው ግፍ ጥሩ ወካይ ቃል ነው፤ ነገር ግን ወያኔ ከአውሬ አልፎ የቆሰለ አውሬ ሆኗል፤ አደገኛነቱም ጨምሯል።
ፕ/ር ብርሃኑ በትክክል እንዳሉት የወያኔ የጥቃት ኢላማዎች ወያኔን የሚታገሉት የነጻነት ሃይሎች ብቻ አይሆኑም። መላው የአገራችን ህዝብ በቆሰለው አውሬ ከመጎዳት አያመልጥም። በነፍስ ግቢና ውጪ መካከል የሚገኘው የቆሰለው አውሬ አፈር ልሶ ከቁስለቱ አገግሞ እንዳይነሳ ጥፋቱን እየተከላከሉ፣ ሞቱ የሚፋጠንበትን መንገድ መቀየስ ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል። የቆሰለ አውሬ ወዳጅ ጠላት መለየት የማይችል፣ ፊት ለፊት ባገኘው ላይ ሁሉ እርምጃ ለመወሰድ የሚንደፋደፍ በመሆኑ፣ ሁሉም ዜጋ የጥቃት ጥፎሮቹ እሱም ላይ እንደሚያርፉ በመገንዘብ አውሬውን ለማጥፋት መረባረብ ይኖርበታል።
ሰሞኑን በኦሮሚያ አካባቢ እየተቀጣጠለ በመጣው ህዝባዊ እምቢተኝነት ወደ ከርሰ መቃብር እየተገፈተረ መሆኑ የገባውና የቆሰለ አውሬነት ባህሪውን በይፋ ማሳየት የጀመረው ይህ የወያኔ አገዛዝ አጥፍቶ ለመጥፋት አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት፡ አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር በማጋጨት የመፈራገጥ እርምጃውን ተያይዞታል:: ተጨማሪ ጊዜና እድል ከተሰጠውም ሌሎች ከዚህ የከፉ ድርጊቶችንም ሊፈጽም እንደሚችል ልብ ማለት ያሻል። ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ፍንዳታዎችን ሲያካሄድ የነበረ አገዛዝ ወደዚያ ልማዱ ተመልሶ ጉዳት ለማድረስ ወደኋላ የማይመለስ ብቻ ሳይሆን ተሰሚነት አላቸው የሚባሉትን ወይም ከሌላ ብሄረሰብ የሆኑትን በማስገደል በቀል ሊያስነሳ የሚችል ግጭት ሊቀሰቅስ እንደሚችል ይጠበቃል:: በኦሮምያና ተቃውሞ በሚያይልባቸው ሌሎች አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ህዝቡን በርሃብ ከመቅጣትም ወደ ኋላ የመለሳል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል:: ማምሻም እድሜ ነው እንደሚባለው ወያኔ ህዝባችንን በማጋጨት እስትንፋሱን ለአንድ ቀን የሚያረዝም እስከመሰለው ድረስ የሚችለውን ሰይጣናዊ መንገዶች ሁሉ ከመሞከር የማይታቀብ ፍጡር መሆኑ ጥርጣሬ ውስጥ የሚገባ አይደለም:: ይህ ሁሉ ሙከራ ከከሸፈበትና እንደማያዋጣው ከተረዳ በዘረፋና በሙስና የሰበሰበውን ሃብትና ንብረት ማሸሹን አጠናክሮ ይገፋበታል።
አርበኞች ግንቦት7 በ11ኛው ሰአት የሚገኘውን የቆሰለውን አውሬ ጥፋት ለመቀነስም ሆነ ግብዓተ መሬቱን ለማፋጠን ፣ በወታደራዊው እና በህዝባዊ እምቢተኝነቱ መስኮች ተግቶ እየሰራ ነው። ንቅናቄው ሁኔታዎችን ሁሉ አጥንቶ ተስማሚ ሆኖ ባገኘበት ሰዓት በቆሰለው አውሬ ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ ለኢትዮጵያ ህዝብ በተደጋጋሚ ገልጿል። ንቅናቄያችን አገራችንን ከቆሰለው አውሬ ቁጥጥር ሙሉ በሙሉ ካላቀቀ በሁዋላ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መክሮና ዘክሮ የሚገነባት የነጻነትና የእኩልነት አገር እንዲኖረን ለማስቻል አቅም የፈቀደለትን ሁሉ ከማድረግ ለአፍታም ቢሆን ወደ ኋላ እንደማይል ፣ የንቅናቄው ሊቀመንበር እና የመላው አባላቱ ተወካዮች በቅርቡ ባካሄዱዋቸው ጉባኤዎች በድጋሜ አረጋግጠዋል።
በአገር ቤትና በውጪ የሚኖረው ህዝባችንም በበኩሉ ይህ የቆሰለ አውሬ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ለማክሸፍ ከዚህ የሚከተሉትን እርምጃዎች እንደአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ መውሰድ ይኖርበታል።
1ኛ. በየቀኑ የሚካሄዱ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ትኩረት ሰጥቶ መከታተልና መረጃ መሰብሰብ:: ያገኛቸውንም መረጃዎች ወዲያውኑ ለመገናኛ ብዙሃን ማቀበል
2ኛ. የቆሰለው አውሬ አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት፣ አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር ለማጋጨት የሚያደርገውን ጥረት ማክሸፍንና ፣ ማጋለጥ።
3ኛ. ለዚህ እኩይ ስራ የሚሰለፉ ሃይሎችን ማስጠንቀቅ፣ ማጋለጥና እንደ አስፈላጊነቱ ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ።
4ኛ. በየአካባቢው የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ትንሽ ትልቅ ሳይባል መቀላቀል። በተለይ የወያኔ የነርቭ ማእከል ናቸው በሚባሉት ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰድ።
5ኛ. የወያኔን አገዛዝ ለመለወጥ በትግል ላይ ያሉ ድርጅቶችን በማቴሪያል፣ በገንዘብና በማንኛውም ነገር መርዳት።
6ኛ. በሁለገብ ትግሉ እየተሳተፉ ያሉ ሃይሎችን በአካል መቀላቀል፣ ካልተቻለም መረጃ በማቀበል ማገዝ።
7ኛ. ወያኔ በመካከላችን የዘረጋውን የልዩነት አጥር በማፍረስ ጥርጣሬና አለመተማመን እንዳይኖር ማድረግ፡ እያንዳንዱ ለሁሉም ሁሉም ለያንዳንዱ ወገናዊነቱን መግለጽ፤ የጎንዮሽ ሽኩቻዎችን ማቆምና የፖለቲካ መስመር ልዩነቶቻችንን ለማጥበብ ዝግጁ መሆን።
8ኛ. የእርስ በርስ ትብብርን ማጠናከር አንዱ ሲጎዳ ሌላው እያከመ፣ ሁሉም ተቃውሞውን በየአቅጣጫው መጀመር።
አርበኞች ግንቦት7 እንደቆሰለ አውሬ መፈራገጥ የጀመረው የወያኔ አገዛዝ በአገራችንና በህዝባችን ላይ ሊያደርስ የሚችለው አደጋ እንዲቀንስና ድህሬ ወያኔ የህዝቦቿን አንድነት በእኩልነት የምታረጋግጥ የተረጋጋች ፣ ሰላምና ብልጽግና የሰፈነባት አገር ለመመሥረት ከሚሹ የአገሪቱ ልጆች ሁሉ ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ የነጻነት ቀን እንደሚያቃርብ እርግጠኛ ነው ።
የወያኔን የሥልጣን እድሜ ለማሳጠር ሁላችንም ለተግባራዊ ትግል ዛሬውኑ ታጥቀን በቆራጥነት እንነሳ!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
አርበኞች ግንቦት7

በህወሓት አገዛዝ ቁጥጥር ስር የሚገኘው አየር ኃይል አብራሪ የነበረው አብዮት ማንጉዳይ ከ10 ዓመታት እስር በኋላ በረሃ ወርዶ አርበኞች ግንቦት 7ን ተቀላቀለ፡፡

February 1, 2016 
(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ)
በህወሓት አገዛዝ ቁጥጥር ስር የሚገኘው አየር ኃይል አብራሪ የነበረው አብዮት ማንጉዳይ ከ10 ዓመታት እስር በኋላ በረሃ ወርዶ አርበኞች ግንቦት 7ን ተቀላቀለ፡፡
በ1997 ዓ.ም የተደረገው ምርጫ ውጤት መጭበርበሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመፅ በኃይል ለመድፈቅ የህወሓት አገዛዝ አየር ኃይሉን ለመጠቀም በተጠንቀቅ እንዲቆም ማዘዙን በመቃወም ኤም.አይ-35 ተዋጊ ሄሊኮፕተር ይዞ ከአንድ ሌላ ጓደኛው ጋር ወደ ጅቡቲ የኮበለለው አብዮት ማንጉዳይ በጅቡቲ መንግስት አማካኝነት ተላልፎ በመሰጠቱ ነበር ለእስር የበቃው፡፡
አብዮት በህወሓት ደህንነቶች እጅ እንደወደቀ ክስ ተመስርቶበት ለፍርድ ሳይቀርብ በድሬ ደዋና በሌሎች ስውር ማሰቃያ ስፍራዎች እጅግ በጣም ዘግናኝና አስከፊ የሆነ ሰቆቃ ተፈፅሞበታል፡፡
አብዮት ማንጉዳይ በረሃ ወርዶ አርበኞች ግንቦት 7 እያፋፋመው የሚገኘውን የአርበኝነት ጎራ ነፍጥ ጨብጦ ለመቀላቀል አሁን በስልጠና ላይ ይገኛል፡፡

Tuesday, 9 February 2016

የህዝባችን እንባ ለማቆም ሁላችንም አምርረን እንታገል !


January 29, 2016  
def-thumbኢትዮጵያ አገራችን ከፍተኛ የሆነ የህልውና ስጋት ተደቅኖባታል። ልጆቿ በያቅጣጫው ዋይታቸውን እያሰሙ ነው። የወያኔ የተበላሸ ስርዓት እና የስግብግብነት ተፈጥሮ ተደማምረው ህዝባችንን በቃላት ሊገለጽ በማይቻል ሰቆቃ ውስጥ ከተውታል። ህሊና ይዘው መፈጠራቸው ጥያቄ ውስጥ እስከሚገባ ድረስ፣ ቅልብ የወያኔ ገዳይ ወታደሮች በኦሮሞ እናቶችና ህጻናት ላይ የፈጸሙት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በረጅሙ ታሪካችን ያላየነውና ያልሰማነው ነው። ባለፉት መንግስታት ለነጻነታቸው የጮሁ ወጣቶች በስርዓቱ የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው ታሪክ የመዘገበው ሃቅ ነው፣ ነገር ግን ህጻናትና ታዳጊዎች እጅግ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ግንባራቸውንና ደረታቸውን በጥይት እየተመቱ ሲወድቁ ስንመለከት ይህ በታሪካችን የመጀመሪያ ነው። አለም በፍጥነት እየተለወጠ ባለበት በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መወሰዱ ደግሞ የአገዛዙ ቁንጮዎችንና እነሱን ተከትለው ወደ ጥፋት አረንቋ የሚተሙትን ሁሉ ከሰው መፈጠራቸውን እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው። የኦሮሞ ህዝብ በአጋዚ ወታደሮችና በፌደራል ፖሊሶች በግፍ ለተነጠቀው ልጆቹ ድምጹን ከፍ አድርጎ አልቅሷል፤ ቁጭቱን በቻለው መንገድ ሁሉ ሊገልጸው ሞክሯል። ነገር ግን እስካሁኗ ሰአት ድረስ መገደሉ፣ መታሰሩ፣ መሰደዱ፣ መዋረዱ አለቆመም። አገዛዙ ለአንድ ቀን በስልጣን ላይ ውሎ እስካደረ ድረስ ይኸው ግፍ ይቀጥላል።
የወልቃይት ህዝብ እኛ እንደፈለግን እንጅ አንተ እንደፈለክ አትኖርም ተብሎ ተፈርዶበት ያለፉትን 25 ዓመታት በስቃይ አሳልፏል። አሁንም እንደገና ” እኛ እናውቅልሃለን እየተባለ” መከራውን እየበላ ነው። በአካባቢው ያንዣበበው የሞት ደመና እጅግ አደገኛ ነው። እየተረጨ ያለው መርዝ ካልቆመ፣ አካባቢው በአጭር ጊዜ የግጭት አውድማ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ዘራፊው የህወሃት ቡድን ግጭትን ከማባበስ በተረፈ ችግሩን የማስቆም ፍላጎት አላሳዬም።
በዚሁ አካባቢ የአንድ አገር ሎጆችን ቅማንትና አማራ እያሉ እርስ በርስ ለመከፋፈልና ለማጋጨት ወያኔ እየዘራው ያለው ይጥፋት ዘር እስካሁን ከደረሰው እልቂት በላይ ሌላ እልቂት ይዞ እየመጣ ነው። የአገር ሰላምና ጸጥታ እናስከብራለን ብለው መሳሪያ የታጠቁ ሃይሎች በሁለቱም ወገን ግጭት ለመቀስቀስ ሲዶልቱ፣ ሲያቅራሩና ሲሸልሉ ውለው እያደሩ ነው። ከዚህ ሁሉ የእልቂት ጀርባ ያሉት ዜጎችን ካላጋጩ ውለው ማደር የማይችሉት የወያኔ መሪዎችና ግብረአበሮቹ ናቸው።
የደቡብ ህዝብም ልጆቹን በሞት እየተነጠቀ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቹም በየእስር ቤቱ ታጉረዋል፡፡ ዛሬ ወደ ኮንሶ፣ አርባምንጭ፣ ቁጫ፣ ሃመር ወዘተ ብንሄድ የምንሰማው ዋይታና ለቅሶ ነው።
የሶማሌው ወገናችን በልዩ ሃይል አባላት የዘረ ፍጅት እየተፈጸመበት ነው፤ አፋሩ ፣ ጋምቤላውና ቤንሻንጉሉ ከቀየው እየተፈናቀለ፣ መሬቱን እየተነጠቀ ለሞትና ለዘላለማዊ ድህነት ተዳርጓል።
ይሄ ሁሉ መከራና ግፍ ሳያንስ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ህዝባችን በረሃብ እየተጠቃ መሆኑ በሰፊው እየተነገረ ነው። በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በተፈጥሮ በሚሳበብ የአየር መዛባት ችግር ምክንያት ባለፈው የምርት ዘመን የተዘራው ሰብል እንዳለ ወድሞአል:: በዚህም የተነሳ በህዝባችን ላይ ያንዣበበው የረሃብ አደጋ እስከዛሬ ካየነው ሁሉ የከፋ እንደሚሆን አለማቀፍ ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ነው። ላለፉት 10 አመታት በእጥፍ አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቤያለሁ እያለ ህዝብ ሲያደነቁርና የለጋሽ አገሮችን ቀልብ ለመሳብ ሲባዝን የኖረው ወያኔ ግን በፈጠራ ታሪክ የገነባው ገጽታ እንዳይበላሽበት ረሀቡን ለመደበቅና የጉዳት መጠኑን ለማሳነስ ብዙ ርቀት ተጉዟል። ያም ሆኖ የችግሩ ግዝፈት እያየለ ሲመጣና ተጎጂዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደየ አጎራባች ከተሞች መሸሽ ሲጀምሩ ሳይወድ በግድ ለማመን ተገዷል። ። በሰሜን ወሎ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በደቡብና በኦሮምያ በድርቁ ምክንያት በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ የሚገኙ እናቶችና ህጻናት ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም፣ ወያኔ ግን እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ እዚህም ላይ የቁጥር ጨዋታ በመያዙ አሁንም ተገቢው እርዳታ ለህዝባችን በጊዜ እንዳይደርስ እየተከላከለ ለህዝብ መከራ ደንትቢስነቱንና ጨካኝነቱን እያሳየ ይገኛል።
ወያኔ በህዝባችን ላይ የደገሰው የሞት ድግስ በዚህ ብቻ አያበቃም። የኑሮ ውድነቱ ጣሪያ በመንካቱ ህዝቡ እያንዳንዷን ቀን የሚያሳልፈው በጣርና በጭንቅ ነው፤ ከጥቂት የወያኔ ባለስልጣናትና ሸሪኮቻቸው ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ኑሮው ሲኦል ሆኖበታል። ችግሩና መከራው እየከፋ ሲሄድ እንጅ እየቀነሰ ሲሄድ አይታይም። በሚብለጨለጩና የህዝቡን መሰረታዊ የፍጆታ ችግር በማይቀርፉ ስራዎች ላይ በማትኮር ህዝብን በልማት ስም ለመሸንገል ሙከራ ቢደረግም፣ አልተሳካም። ከኑሮ ውድነት በተጨማሪ ስራ አጥነቱ፣ አፈናው ፣ ስደቱ እስርና እንግልቱ፤ ሙስናው፣ የፍትህ እጦቱ ወዘተ የአገራችን ህዝብ ኑሮውን በጉስቁል እንዲገፋ አድርጎታል።
አርበኞች ግንቦት 7 አገራችንና ህዝባችን ከዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ መውጣት የሚችለው አገዛዙ የዘረጋው የተበላሸ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎች ሲለወጡና ከህዝብ፡በህዝብ ለህዝብ የሚቆም የመንግሥት ሥርዓት በአገራችን እውን መሆን ሲችል ብቻ ነው ብሎ ያምናል:: የወያኔ የሥልጣን ዕድሜ በተራዘመ ቁጥር በህዝባችን ላይ የሚደርሰው በደልና ሰቆቃም እንዲሁ እየተራዘመ ይሄዳል:: ህዝባችን ከሚደርስበት ለቅሶና መከራ እንዲገላገል ሁላችንም በያለንበት አምርረን እንታገል::

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
አርበኞች ግንቦት7