Tuesday, 23 June 2015

የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የታፈኑበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከዓርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ


June 23, 2015
def-thumbአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በወያኔ ከሰነዓ አለም አቀፍ አውሮፓላን ጣቢያ ታፍነው ከተወሰዱ በዛሬው ዕለት ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ. ም፣ አንድ ዓመት ይሞላቸዋል። የወያኔ አረመኔዎች ይህን ዓይነት የውንብድና ተግባር ሲፈጽሙ በከፍተኛ ደረጃ ያሰሉት፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በማፈን፣ ንቅናቄው ብሎም ሕዝቡ፣ ለዕኩልነት፣ ለፍትህና ለነጻነት፣ የሚያደርገውን ትግል ለማዳከምና ከተቻለም ደግሞ ለማጥፋት እንደሆነ፣ ምንም የማያጠራጥር ጉዳይ ነው።
ለመሆኑ የወያኔዎች ስሌት በምን ያህል ትክክል ነበር ?
ባለፈው አንድ አመት ውስጥ፣ ወያኔ በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የፈጸመው የውንብድና አፈና ተግባር፣ ንቅናቄያችን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በሐገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባለው ሕዝብ ልብ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ሌላው ቀርቶ ከአፈናው በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ንቅናቄያችንን በጥርጣሬ የሚመለከቱ ወገኖች በአደባባይ ወጥተው፣ ” እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ” በማለት አቶ አንዳርጋቸውና ንቅናቄው ለሚታገሉለት ሕዝባዊና ሐገራዊ ዓላማ መቆማቸውን በግልጽ አሳይተዋል። እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በሐገር ውስጥ፣ በምድር ላይና በውጭ ሐገር የሚገኘውን የንቅናቄያችንን አካላት ተቀላቅለዋል። ቀደም ሲል በንቅናቄያችን በተለያዩ ደረጃዎች ይሰሩ የነበሩ ዓባላቶች ከአፈናው በኋላ ለትግሉ ያላቸውን ቁርጠኝነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምረዋል።
የአቶ አንዳርጋቸውን አፈና ተከትሎ፣ የንቅናቄው አመራር መሰረታዊ የትግል እንቅስቃሴዎቹን በስፋትና በጥልቀት በመፈተሽ አስፈላጊውን ማሻሻያዎችና ማስተካካያዎችን አድርጓል። ንቅናቄያችን አቶ አንዳርጋቸው ለረጅም ጊዜ የደከሙለትን ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ የመታገለን ጥረት አሳክቶ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዓርበኞች ግንባር ጋር ሙሉ ለሙሉ ተዋህዷል። ከዚህም በተጨማሪ የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን ጨምሮ፣ ከሌሎች አምስት በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋራ በጥምረት ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሷል።
በሌላ በኩል ያለፈው አንድ አመት የወያኔ የዘረኛ ዓምባገነን ቡድን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን የአፈና፣ የግድያ፣ የዕስርና የድብደባ ውንብድና ተግባር አጠናክሮ የቀጠለበት ዓመት ነበር ። ለዚህም ጸረ ሕዝብ ተግባሩ፣ በባህርዳር ከተማ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሰውን ግድያ፣ በሰላም እንታገላለን ብለው ይንቀሳቀሱ የነበሩትን የአንድነትና የመኢሀድ ድርጅቶች ማፍረስ ብቻ ሳይሆን፣ ዓባሎቻቸው ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ የድብደባና የዕስር ወንጀል መጥቀስ ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በኦሮምያ፤ በአፋር፤ በጋምቤላ፤ በኦጋዴን፤ በትግራይና በደቡብ ክልሎች ይህ ነው የማይባል አፈና፤ ግድያና የሕዝብ መፈናቀል በሰፊው አከናውኗል:: ከምርጫው ጋር ተያይዞም በአደረበት ስጋት የተነሳ በርካታ፣ በተለይ ወጣቶች ላይ፣ የመደብደብ፣የማዋከብ የዕስርና የግድያ ተግባር የፈጸመው በዚሁ አቶ አንዳርጋቸውን ከአፈነበት ቀን ጀምሮ በተቆጠረው የአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ነበር። በጣም የሚገርመው ለራሱ አመቻችቶ ያዘጋጅውን ምርጫ እንኳን ሙሉ በሙሉ አሸነፍኩ ብሎ ከአወጀም በኋላም፣ ከምርጫው በፊት በሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ወንጀል አጠናክሮ መቀጠሉ ያለበትን የስጋትና ጭንቀት ደረጃ የሚያሳይ መረጃ ነው ።
የወያኔ በራስ የመተማመን ደረጃ ከመቼውም ወቅት ይልቅ እጅግ አሽቆልቁሎ የታየውም ባለፈው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ነበር። በሐገር ውስጥ ይነሳብኛል ብሎ በሚያስበው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ስጋት ምክንያት ይህን ስጋት ለመቀነስ በአንድ መንገድም ይሁን በሌላ ይረዱኛል ብሎ ያሰባቸውን በአካባቢው የራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ያላቸውን ቀደም ሲል ወቀሳ ቢጤ እንደመሰንዘርም ዕልህም እንደመጋባትም ይዳዳቸው የነበሩትን መንግስታት ባለሥልጣኖች በመማጸንና ሐገር ውስጥ በመጋበዝ ማንነቱን አበጥሮ ለሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአደባባይ ወጥተው ወያኔ ያልሆነውን ነው ብለው ምስክርነት እንዲሰጡለት ማድረጉ የወያኔ ስጋት የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ የሚያሳይ ሌላው መረጃ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ንቅናቄያችን አቶ አንዳርጋቸውን አፍነው ለወያኔ የሸጡትን የየመን ባለሥልጣኖች ድርጊት በሚመለከት በጊዜው በሰጠው መግለጫ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ “ጊዚያዊ ጥቅምን በማየት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዕኩልነት፣ ለፍትህና ለነጻነት የሚያደርገውን ትግል ከወያኔ ጋር በቀጥታም ሆን በተዘዋዋሪ በመተባበር ለማፋን መሞከር፣ ታሪካዊ ስህተት መስራት ነው!” እንዳለው ሁሉ፣ ዛሬም የሌሎች መንግስታት ባለ ሥልጣኖች እንደ ትላንትናዎቹ የየመን ባለሥልጣኖች ጊዚያዊ ጥቅምን ብቻ በማየት ሌላ ታሪካዊ ስህተት እንዳይደግሙ ከወዲሁ ለማሳሰብ ይወዳል።
በንቅናቂያችን እምነት ከዚህ በላይ በጥቂቱም ቢሆን ለማሳየት እንደተሞከረው ያለፈው አንድ ዓመት ያሉት መረጃዎች በሙሉ የሚያሳዩት ወያኔ አቶ አንዳርጋቸውን በማፈን ለማዳከም ያሰበው ትግል ይበልጥ ተጠናክሮና ተቀጣጥሎ በርካታ አንዳርጋቸውዎችን ከማፍራቱም በላይ ብዙዎች ለነጻነታቸው መተኪያ የሌላትን ህይወታቸውን እስከመስጠት የሚያደርስ ዕልህ ውስጥ ገብተዋል። ወያኔ እንዳሰበውና እንዳሰላው ትግሉ መዳከም ሳይሆን መሬት እያያዘና እየተጠናከረ በመምጣቱ የወያኔ ስጋት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እየጨመረ ሄዷል። ይህም ሁኔታ የዛሬ አንድ ዓመት በፊት ወያኔ አቶ አንዳርጋቸውን ሲያፍን ያሰላው ስሌት እጅጉኑ የተሳሳተ እንደነበረ በግልጽ አረጋግጧል። የወያኔ የአፈና ተስፋ ገና በአፈናው ማግስት እንደ ጧዋት ጤዛ ተኗል። ከአለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በመላው ሀገሪቷ ተጠናክሮ የምናያቸው የወያኔ የጭካኔ እርምጃዎች የሚያመለክቱት ይህንኑ ስጋትና ጭንቀት ነው። የወያኔ የቅዥትና የስጋት የዛፍ ላይ እንቅልፍ፣ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ተሸጋግሮና ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ንቅናቄያችን፣ አርበኞች ግንቦት 7፣ ለዕኩልነት ለፍትህና ነጻነት የሚደረግ ትግል፣ በተለይ እንደወያኔ ባለ ዘረኛ አምባገነን ቡድን በበላይነት በሚዘወር ሐገራዊ ሁኔታ ውስጥ፣ ምን ያህል ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን አስቀድሞ ጠንቅቆ ያውቃል። ይህም ሆኖ ግን ባለፈው አንድ ዓመት፣ የትግል ጓዳችን የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው በወያኔ እጅ ከወደቁበት ጊዜ ጀምሮ እየደረሰባቸው ያለውን መከራና ስቃይ እንዲሁም ይህ ሁኔታ በቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ ያስጀመረውን የጭንቀት ዘመን፣ ለአንድ ሴኮንድም ቢሆን መዘንጋት አይችልም።
ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 በአቶ አንዳርጋቸው ላይ በአፈናው የተነሳ የደረሰው መከራና ስቃይ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ ለፍትህ ለዕኩልነትና ለነጻነት በመቆማቸው በወያኔ አረመኔዎች ቁም ስቅላቸውን የሚያዩት በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ሰቆቃ የሚያበቃው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ በሚያደርገው ሁለ ገብ ትግል በመሆኑ ማንኛችንም በአቶ አንዳርጋቸውም ሆነ በሌሎች ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እንደራሳችን ጥቃት አድርገን የሚሰማን ወገኖች በሙሉ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከታፈኑበት አንድ አመት ወዲህ የተጀመረውን ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ አጠናክረን ወደ ውጤት ደረጃ በማድረስ መጭው ዘመን የሕዝብ የፍትህ የእኩልነትና የነጻነት ተስፋ የሚለመልምበት ፣ የወያኔ አምባገነን ሥርዓት እድሜ የሚያጥርበት ዘመን እንዲሆን የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ንቅናቄያን ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል።
ክብር ለፍትህ ለእኩልነትና ነጻነት መስዋትዕነት ለከፈሉና እየከፈሉ ላሉ ታጋዮች!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
አርበኞች ግንቦት7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ
ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ.ም.
CategoryAmharic

Saturday, 20 June 2015

ለሰማዕታቱ አደራ የምንሰጠው ምላሽ ምንድነው?


June 18, 2015
def-thumbኢትዮጵያ አንድ ተጨማሪ ወጣት ልጇን አጣች። ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓም ማታ የደብረ ማርቆሱ የሰማያዊ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ ወጣት ሳሙኤል አወቀ ኢሰብዓዊ በሆነ ድብደባ ሕይወቱ አልፏል። ይህ ወጣት በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ በጽናት ታግሏል። ለኢትዮጵያ ይበጃል ብሎ ባመነበት መንገድ ተጉዞ ለትግሉ ሕይወቱን ሰጥቷል። ሳሙኤል በሕይወቱ ላይ ያንዣበበውን አደጋ በትክክል ያውቅ ነበር፤ ለህልፈት የዳረገው አደጋ በመድረሱ በፊት ተደጋጋሚ ጥቃቶች ደርሰውበታል፤ ሆኖም ግን ግንባሩን አላጠፈም። በሕይወቱ ላይ ያንዣንበበውን አደጋ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ በመገመቱ “ከታሠሩኩም ህሊናዬ አይታሰርም፤ ከገደሉኝም ትግሌን አደራ። በተለይ የኔ ትውልድ አደራ!”የሚል ኗሪውን እረፍት የሚነሳ ተማጽኖ በጽሁፍ አስቀምጦ የመጨረሻውን ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ለዚህ የሙት አደራ ምላሻችን ምንድነው?
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በወጣት ሳሙኤል አወቀ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል፤ ለቤተሰቦቹም መጽናናትን ይመኛል።
ዛሬን እየኖርን ያለነው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከሀቅ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጠናል። እንዴት ነው የሳሙኤል አወቀ እና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰማዕታት አደራ መወጣት የምንችለው? እንዴት ነው ይህንን የህወሓት ፋሽስታዊ ዘረኛ ሥርዓት ማስወገድና በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነበት፤ የአገር አንድነት የተረጋገጠበት ሥርዓት መገንባት የምንችለው? እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለዚህ ትግል የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ምንድነው? ማንን ነው የምንጠብቀው?
አርበኞች ግንቦት 7 መፍትሔው ሁለገብ ትግል ነው ብሎ ያምናል። ሁለገብ ትግል ደግሞ ሕዝባዊ አመጽንና ሕዝባዊ እምቢተኝነትን አቀናጅቶና አስማምቶ ማራመድን ይጠይቃል። በሁለገብ ትግል እያንዳንዱ ለውጥ ፈላጊ የሚያበረክተው ነገር አለ። ሁለገብ ትግልን የሆነ አካል የሆነ ቦታ እስኪጀምረው መጠበቅ አይገባም፤ እያንዳንዳንችን እንደሁኔታው በየአካባቢያችን ልንጀምረው የምንችለው የትግል ስትራቴጄ ነው። ሁለገብ ትግል በየአካባቢያችን በምስጢር በመደራጀት “እኔም ኃላፊነት አለብኝ” እንድንል የሚያደርግ አሳታፊ የሆነ የትግል ስትራቴጂ ነው። ሁለገብ ትግል ጥቂቶችን ሳይሆን በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሚያሳትፍ ሕዝባዊ ትግል ነው።
በየጊዜው በህወሓት ፋሽስቶች ለሚደርስብን በደል ምላሽ መስጠት የሚኖርብን በየአካባቢያችን በምስጢር በመደራጀት ለአምባገነን አገዛዝ ያለን ጥላቻ ስንገልጽ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከራሱ ይጀምር፤ ለህወሓት አምባገነን አገዛዝ ላለመንበርከክ ቃል ይግባ፤ ከሚመስለው ጋር ይቧደን፤ የትግሉን አቅም ይገንባ፤ በአቅሙ መጠን አምባገነኑን ሥርዓት ይገዳደር። ትግሉ እሆነ ቦታ እስኪጀመር መጠበቁን ትተን በሁሉም ከተሞችና በሁሉም የገጠር መንደሮች በአቅማችን መጠን ትግሉን እናፋፍም። እያንዳንችን ለነፃነታችን ኃላፊነት አለብን። የሰማዕታት አደራ የእያንዳንዳችን አዕምሮ እረፍት ሊነሳ ይገባል። ይህንን ስናደርግ ነው ለሰማዕታቱ አደራ ምላሽ ሰጠን ማለት የምንችለው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
CategoryEditorial

Thursday, 11 June 2015

ከቴፒ ወጣቶች የምንማራቸው ቁም ነገሮች


June 10, 2015
def-thumbበደቡብ ኢትዮጵያ ሸካ ዞን የሚገኙ የቴፒ ወጣቶች በህወሓት አገዛዝ የሚደርስባቸው በደል አንገሽግሿቸው ራሳቸውን አደራጅተው በአገዛዙ ላይ እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል። እነዚህ ወጣቶች ግንቦት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በአካባቢያቸው የሚገኝን አንድ የፓሊስ ጣቢያ ወረው እስረኞችን ማስፈታታቸው በመላው ኢትዮጵያ እንዲታወቁ ምክንያት ሆኗል፤ የአገዛዙ ሚዲያም ድርጊቱ መፈፀሙ በተዘዋዋሪም ቢሆን አምኗል።
ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲ፣ ለእኩልነት እና ለአገር አንድነት ግድ ያለን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከቴፒ ወጣቶች የምንማራቸው በርካታ ቁም ነገሮች ያሉ ቢሆንም የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለን እናምናለን።
1. “ጥቂቶች ነን፤ ምንም ማድረግ አንችልም” ብለው ተስፋ ቆርጠው በደልን ለመቀበል አልመረጡም፤
2. ዓላማቸው ትልቅና ሀገራዊ ቢሆንም እርጃዎቻቸው አካባቢ ተኮር አድርገዋል፤
3. የሚወስዷቸው እርምጃዎች በአቅማቸው መጠን እንዲሆኑ በማድረግ በራሳቸው ላይ ያለው መተማመን እንዲጎለብት ማድረግ ችለዋል፤
4. እንደሁኔታው በፍጥነት መሰባሰብና መበታተን የሚችል ቀልጣፋስብስብ ማደራደት ችለዋል፤ እና
5. በከፍተኛ ሥነሥርዓት በመታነጽ ከቴፒ ሕዝብ ጋር ያላቸውን ትስስር አጠናክረዋል።
ሁላችንም ከእነዚህ ወጣቶች ልንማር ይገባል። በአምባገነን አገዛዝ ጉያ ውስጥ የሚደራጅ የአመጽ ኃይል የተለያዩ አደረጃጀቶች ሊኖሩት ይችላል። አንዱ አደረጃጀት የቴፒ ወጣቶች በተግባር ያሳዩን ነው – ተንቀሳቃሽ፣ ለግዳጅ ተሰባስቦ በፍጥነት የሚበተን፤ መልሶ ደግሞ የሚሰባሰብ ቀልጣፋ ድርጅት።
በምርጫ 97 በሰላማዊ መንገድ የሰጡትን ድምጽ ይከበርን ያሉ ወገኖታችን በአዲስ አበባ ከተማ በግፍ የተጨፈጨፉበት ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓም 10ኛ ዓመት በሀዘን አስታውሰናል። ከዚያ ወዲህ በርካታ ወገኖቻችንን በሰላማዊና ህጋዊ ትግል አጥተናል፤ ብዙዎች ቆስለዋል፤ በሺዎች የሚገመቱ በእስር እየማቀቁ ነው። ሆኖም ግን ያ የትግል መስመር የትም አላደረሰንም። የህወሓት አገዛዝ እንዲያበቃ እና በምትኩም ሕዝብ በነፃነት የመረጠው አስተዳደር እንዲኖር የምንፈልግ ወገኖች ሁሉ ወደግባች የሚያደርሱንን አማራጮችን መፈለግ ግዴታችን ሆኗል።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “ሁለገብ ትግልን” እንደ ትግል ስትራቴጂ ሲመርጥ በውስጡ ብዙ አማራጭ ስልቶች መኖራቸውን እግንዛቤ በማስገባት ነው። የቴፒ ወጣቶች በተግባር ያሳዩን የተለያዩ የሁለገብ ትግል ስትራቴጂ አካል የሆኑ በርካታ የትግል ስልቶች መኖራቸውን ነው። ቴፔ የተደረገው እንዳለ ሌላ ቦታ ይደረጋል ማለት አይደለም። ከቴፒ የምንማረው ዋናው ቁምነገር በፈጠራ እና በአካባቢ እውቀት በታገዘ ስልት ወያኔ መፋለም ያለብን መሆኑ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 የቴፒ ወጣቶች ላሳዩት ተግባራዊ መነሳሳት አድናቆት እና ለከፈሉት መስዋዕትነት ያለውን ክብር እየገለፀ በሌላው የአገራችን ክፍሎች ያሉ ወጣቶችም ከቴፒ ወንድሞቻቸው ትምህርት እንዲቀስሙ ያበረታታል።
በዚህ አጋጣሚም በየቦታው በራስ አነሳሽነት የሚጀመሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች አካባቢ ተኮር ቢሆኑም እንኳን አገራዊ እይታ እንዲኖራቸው፤ ከሌሎች መሰል እንቅስቃሴዎች ጋር እንዲቀናጁና እንዲደጋገፉ ብሎም የሀገራዊ ትግሉ አካል እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ያስገነዝባል፤ ይህ ተግባራዊ እንዲሆንም ይሠራል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
CategoryEditorial