Sunday, 1 January 2017

የአፈናውና ሰቆቃው መጠናከር ለነጻነታችን ከምናደርገው ትግል አይገታንም።



December 24, 2016
የመንግሥትን በትረ ሥልጣን በጠመንጃ ሃይል ተቆጣጥረው ያሉት የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ላለፉት 25 አመታት በህዝባችን ላይ ተንሰራፍተው  የዘረፉት የአገር ሃብት ፤ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ  በየባንኩ ያከማቹት ጥሬ ገንዘብና በዘመድ አዝማዶቻቸው ሥም እዚህና እዚያ የዘረጉዋቸው የንግድ ድርጅቶች ብዛት እንዲሁም ያለዕውቀታቸውና ልምዳቸው ለሩብ አመታት ሲሿሿሙበት የኖሩት ሹመትና ማዕረግ  አሁንም ቢሆን በቃኝ ከሚሉበት ደረጃ እንዳላደረሳቸው ሥልጣንን በሰላማዊ መንገድ እንዲያስረክቡ የተቃውሞ ድምጻቸውን በሚያሰሙ ወገኖቻችን ላይ እየወሰዱት ካለው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መረዳት ይቻላል።
በአንድ ወቅት አገሪቱ ውስጥ ሰፍኖ የኖረው አስተዳደራዊ በደል የፈጠረው ህዝባዊ ብሶት ብረት እንዲያነሱ እንዳደረጋቸው በኩራት በመደስኮር ገድላቸውን በታሪክ መዝገብ ላይ ለማስፈር ደፋ ቀና እያሉ ያሉ እነዚህ ሃይሎች፡ አስመርሮናል ብለው መሳሪያ ካነሱበት ሥርዓት የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ ፤ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የአገር ሃብት ዘረፋ ተግባር ላይ በጅምላ ተሰማርተው ሃብት ሲያካብቱ ፤ በአገሪቱ ባህልና ወግ የገዘፈ ልዕልናና ክብር የነበረውን የህግ የበላይነት ባህል አጥፍተውና በራሳቸው ተጽፎ የጸደቀውን ህገ መንግሥት ተላልፈው በጠራራ ጸሃይ ብዙዎችን ጎዳና ላይ ሲጨፈጭፉ፤ ሲያስሩና ሲያንገላቱ ፤ ከአያት ቅድመ አያቱ ጀምሮ እትብቱ ከተቀበረበት ቀዬ ሺዎችን አፈናቅለው መሬቱን ሲቀራመቱና  ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ለባዕዳን በርካሽ ዋጋ በመቸብቸብ ለጎዳና ተዳዳሪነት ሲዳርጉት ከማየት የበለጠ ወንጀልና ህሊናን የሚያቆስል ኢፍትሃዊነት በዚህች ምድር አይኖርም።
ይህ ሁሉ ግፍና መከራ እየተፈራረቀበት ያለውን ህዝብ በትግላችን ውጤት ፍትህና ርትዕ አቀዳጅተንሃል፤ በብሄር ማንነትህና በምትናገረው ቋንቋ እንድትኮራ አድርገንሃል፤ ተገፍተህባት የኖርክባት አገር ባለቤት እንድትሆን አስችለንሃል ፤ዲሞክራሲን በአገራችን እውን በማድረግ በየ5 አመቱ በምትመርጠው መንግሥት የምትተዳደርበት ሥርዓት ዘርግተንልሃል ፤ ደሃውን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረገ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣት በምድራችን ፈጣን የሆነ ልማትና ዕድገት አስገኝተንልሃል፤ በዚህም የተነሳ ከኖርክበት ረሃብና እርዛት መላቀቅ ብቻ ሳይሆን በአጭር ግዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ልናሰልፍህ ነው ፤ ወዘተ እያሉ ሲያላግጡበትና ሲዘባበቱበት ማየት እጅግ የሚያሳምም ነው።
ላለፈው አንድ አመት አገሪቷ ውስጥ እጅግ ተጠናክሮ የቀጠለውና ወያኔ በፈረጠመ ክንዱ ለመጨፍለቅ ያለ የሌለ ሃይሉን ለመጠቀም ደፋ ቀና እያለ ያለው ህዝባዊ እምቢተኝነት መሠረቱ ይህ ለሩብ አመታት በአገራችንና በህዝባችን ላይ ተንሰራፍቶ የቆየውን ኢፍትሃዊነት፤ አፈናና ጭቆና ከህዝባችን ጫንቃ አሽቀንጥሮ ለመጣል የሚደረግ የነጻነት ትግል ነው።  ይህንን ትግል ለማፈን ህወሃት ከአለም አቀፍ ለጋሽ አገሮች በተሰበሰበ ገንዘብ ከምዕራባዊያን ወዳጆቹ፤ ከራሺያና ከቻይና የፈለገውን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ በግዢ ቢያግበሰብስ፤ የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም የተቀጠረ እልፍ አእላፍ  የአጋዚ ወታደርና ልዩ ጦር በየመንደሩ ተሰማርቶ የታዘዘውን ያህል አፈና፤ ግዲያና እስራቱን ቢያጧጡፍ የሚቻል አይሆንም። በገዛ አገራችን እንደሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠርን ከሥራ ፤ ከመኖሪያ ቀያችንና ከትውልድ መንደራችን መፈናቀል ሰልችቶናል። ልጆቻችን በገዛ አገራቸው ተስፋ ቆርጠው እንጀራ ፍለጋ  በረሃ ሲያቋርጡ በጨካኞች እጅ እየወደቁ በአክራሪዎች ሰይፍ እንደከብት መታረዳቸውን ማስቆም ከኛ ውጪ ለሌላ ለማንም የተሰጠ ሃላፊነት አይደለም። ከአሁን ቦኋላ የአገራችን የኢትዮጵያ ምድር የሚቆረቆሩላትን ልጆቿን እየቀበረች የጠላትን ህልም ለማሳካት ሊያጠፏት ሌት ተቀን የሚማስኑ ባንዳ ልጆቿን እሽሩሩ የምትልበት ዘመን ማብቃት ይኖርበታል።
አርበኞች ግንቦት 7 የህወሃት አገዛዝ ህዝባችንን በቋንቋና በዘር ከፋፍሎ እርስ በርሱ በማናከስ ለዘመናት የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ሲሰራው የነበረው የተንኮል ሴራ ሁሉ ከሽፎአል ብሎ ያምናል። የጎንደርና የባህርዳር ህዝብ ባሰማው ተቃውሞ በህወሃት አልሞ ተኳሾች ጥይት የሚሞተው ኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው ሲል በአርሲ፤ በቢሾፍቱ፤ በደምቢዶሎና በተለያየ የኦሮሚያ ክልል የሚኖረው ህዝብ አማራ ወገናችን ነው ከአሁን ቦኋላ እትለያዩንም፤ አንድ ነን ሲል ድምጹን ከፍ አድርጎ አሰምቷል። ይህ የወንድማማችነትና የአንድነት መንፈስ ህወሃትን ያሸብረዋል ብቻ ሳይሆን እንዳበደች ውሻ ያቁነጠንጠዋል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ የህወሃት ወታደራዊ መኮንኖች ሥልጣን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉበት የኮማንድ ፖስት የተቋቋመው ይህ የወንድማማችነትና የአንድነት መንፈስ ሊፈጥረው የሚችለውን ህብረት በጠመንጃ ሃይል ከወዲሁ ለመቅጨት ነው። በመላው አገሪቱ በተለይም በአማራ፤ በኦሮሚያና በኮንሶ በርካታ ሺዎችን ሰብስቦ በማጎር ፤ የታሠሩትን በጉልበት ወይም በጊዜያዊ ጥቅም በመደለል ቅስም መሥበር በስፋት የተያያዘውም የህብረትና የአንድነት ድምጽ ጎልቶ መሰማት ከጀመረ ወዲህ መሆኑ ግልጽ ነው። ከአንድ ወር የጅምላ  እስር ቦኋላ ሰሞኑን የተለቀቁ 9 ሺህ ለውጥ ፈላጊዎችን “አይደገምም” የሚል ጽሁፍ የተጻፈበት ነጭ ካናቴራ ማልበስ በህወሃት ቤት ማሸማቀቅ ነው። ካለፈው ስህተቱ መማር ያልፈጠረበት  ወያኔ በምርጫ 97 የንብ አርማ አልብሶ ለድጋፍ ሰልፍ መስቀል አደባባይ ያወጣው በሚሊዮን የሚቆጠር የአዲስ አበባ ህዝብ በማግሥቱ ካናቴራውን እንደለበሰ ለቅንጅት ሰልፍ ወጥቶ ጉድ እንዳደረገው ዘንግቶታል። ጮማና ውስኪ አዕምሮአቸውን ለሸፈናቸው ኋላ ቀር የህወሃት አመራሮች “አይደገምም” የሚል ካናቴራ በማልበስ ወደየቤታቸው ለሸኟቸው ታሳሪዎች ህዝባችን በነቂስ ወጥቶ ያሳየው ድጋፍና ደማቅ አቀባበል ሚያዚያ 30,1997 ቀንን የደገመ ትዕይንት መሆኑን እንዲረዱ አያስችላቸውም።
ህወሃት ህዝባችን ለነጸነቱ የሚያካሂደውን ትግል ለመቀልበስ የፈለገውን ያህል ጉልበት ለመጠቀም ቢፍጨረጨር ፤ እስር ግድያና የማሳደድ ተግባሩን አጠናክሮ ቢቀጥል ከህዝባችን ልብ የበለጠ እየራቀ፤ የጥላቻና የበቀል እርምጃ የሚቀሰቅስ ወኔ ለምናካሄደው ትግል ይፈጥር እንደሆነ እንጂ ከጀመርነው የነጻነት ትግል ወደ ኋላ እንደማይገታን አርበኞች ግንቦት 7 በጽናት ያምናል። ፍትህ እኩልነትና ነጻነት የሰፈነበት አገር ባለቤት ለመሆን የጀመርነው ትግል የፈለገውን ዋጋ ቢያስከፍለንም በድል ይጠናቀቃል። ለዕለት ጉርሳቸው ሲሉ በውትድርና ተቀጥረው ለህወሃት የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ውድ ህይወታቸውን እየገበሩ ያሉ ምስኪን ወገኖቻችን እየተካሄደ ያለው ትግል ለነርሱም ነጻነት መሆኑን ተረድተው የያዙትን መሣሪያ የደሃውን ልጅ እየገደሉና እያስገደሉ የማይጠረቃ የሃብት ዘረፋ ጥማታቸውን ለመወጣት በሚያዘምቷቸው አለቆቻቸው ላይ እንዲያዞሩና ትግሉንም እንዲቀላቀሉ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

No comments:

Post a Comment