እንዲሁም አገዛዙን ለማስወገድ ህዝቡ ማንኛውንም አይነት መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ያሳየበት ነው። ረሃብና ጥማቱን ችሎ ከውስጡ የተጣበቀውን አለቅት ለማስወገድ መወሰኑን አሳይቷል። “ሩጥ ስንለው የሚሮጥ፣ ተቀመጥ ስንለው የሚቀመጥ ህዝብ ፈጥረናል” በማለት ሲሳለቁበት በነበረቡት ገዢዎች ላይ እየጠራ ተሳልቆባቸዋል። ከእንግዲህም እሱ በፈለገው እንጅ እነሱ በፈለጉት መንገድ እንደማይገዛላቸው ነግሯቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ አድማው ከፍተኛ የህይወት መስዋትነት ሳያስከፍል በሌሎችም አካባቢዎች ሊተገበር የሚችል መሆኑን አሳይቷል። ህዝብ ቆርጦ ከወሰነ ምንም ነገር ለማድረግ የማይሳነው መሆኑንም እንዲሁ መስክረናል። ድርጅታችን አርበኞች ግንቦት 7 ህዝቡ ባደረገው ጠንካራ የስራ ማቆም አድማ የተሰማውን ኩራት ለመግለጽ ቃላት ያጥረዋል።
የህዝባቸውን ብሶት ብሶታቸው አድርገው፣ ህዝባቸውን በተሻለ ጎዳና ለመምራት የሚያስችል እውቀትና ክህሎት ያላቸው መምህራንም የትግሉ መሪ መሆን በመጀመራቸው በእጅጉ ኮርተናል። የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ካድሬዎችን እያሳፈሩ የሸኙበት መንገድ አኩሪና በሁሉም ቦታ ሊተገበር የሚገባው ምርጥ የትግል ስልት ነው። ምሁራን ለዲሞክራሲ፣ ፍትሃና ነጻነት የሚደረገውን ትግል በመምራት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽዎ እንዳላቸው ድርጅታችን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። ምሁራን ትግሉ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ እንደሚራ ብቻ ሳይሆን ከነጻነት በሁዋላ ለሚመሰረተው ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርዓት ዋስትና በመሆናቸው የጀመሩትን ትግል እስከመጨረሻው መርተው ዳር ያደርሱታል ብለን እናምናለን። በተለያዩ ምክንያቶች ትግሉን ያልተቀላቀላችሁ ምሁራን በፍጥነት ትግሉን ተቀላቅላችሁ ህዝባችሁን በመምራት አካባቢያችሁን ነጻ እንድታወጡ በድጋሜ ጥሪ እናቀርባለን።
ለህዝባዊ ጥሪው ፈጣን ምላሽ የሰጣችሁ ነጋዴዎች፣ የባጃጅና ታክሲ አሽከርካሪዎች እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞች፣ ድርጅታችን እየከፈላችሁ ላለው ወደር የለሽ መስዋትነት ከፍተኛ አክብሮት አለው። ግብር ባለመክፈል እንዲሁም የተለያዩ የትግል ስልቶችን እንደያካባቢያችሁ ሁኔታ በመጠቀም ትግላችሁን ከቀጠላችሁ፣ አገዛዙ እናንተን ለመግደል ለተሰለፉት ጥቂት የአገዛዙ ወታደሮች፣ የደህንነት እና የፖሊስ ተቋማት የሚከፍለው ገንዘብ ስለማያገኝ በመጨረሻ እጁን እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል። አሁንም ትግሉን ዳር የማድረስ ታሪካዊ አደራ ተጥሎባችሁዋል እና ትግላችሁን ቀጥሎ እንላለን።
ከንቱ ለሆነ አላማ የህዝባችሁ መጨፍጨፍ እረፍት ነስቷችሁ የጠመንጃችሁን አፈሙዝ በአፋኙ አገዛዝ ላይ ያዞራችሁ ፣ መሳሪያችሁን አስረክባችሁ ከህዝባችሁ ጋር የተቀላቀላችሁ ወይም በውስጥ ሆናችሁ በተለያዩ መንገዶች ለምትታገሉ የስራዊቱ አባላትም እንዲሁ ከፍ ያለ አክብሮታችን ይድረሳችሁ። ከህዝቡ ጎን ለመቆም ያልወሰናችሁ ዛሬውኑ ወስናችሁ ከነጻነት ትግሉ ጎን ተሰለፉ። ለህዝብ ያልሆነ አገዛዝ ለእናንተ ሊሆን አይችልም። እናንተ ምን አይነት ህይወት እንደምትገፉ እናውቃለንና ከዚህ የስቃይ ህይወት ለመውጣት ብቸኛው መንገድ የስቃዮች ሁሉ ምንጭ የሆነውን የወያኔን አገዛዝ ማስወገድ በመሆኑ ጥሪያችንን እንደሰማችሁ የነጻነት ሃይሎችን ለመቀላቀል ወስኑ።
አርበኞች ግንቦት 7 እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም ባለው አቅም ሁሉ ህዝባዊ ትግሉን እየደገፈ ይገኛል። የመጨረሻው የነጻነት ደወል እሰከሚደወል ድረስም ትግሉን ከህዝቡ ጋር ሆኖ ይቀጥላል።
No comments:
Post a Comment