በአይሲስ በግፍ በታረዱብን ወገኖቻችን የተሰማን ሀዘንና ቁጭት ከፍተኛ ቢሆንም እንኳን ከአዕምሮዓችን መውጣት የሌለበት ሀቅ አለ። ይህ ሀቅ “ያስጠቃን፣ ያሳረደን ወያኔ ነው” ከሚለውም ያለፈ ነው። መረሳት የሌለበት ሀቅ፣ ከአይሲስ የከፋ ጨካኝ በአገራችን የመንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረ መሆኑ ነው።
የህወሓት ፋሽስት ጦር በበደኖ፣ በአዋሳ፣ በሀረር፣ በጋምቤላ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በአዲስ አበባ፣ በሸካና መዠንገር፤ እንዲሁም በሚታወቁም በማይታወቁም የማሰቃያ እስር ቤቶች አይሲስ እየፈፀመ ካለው የባሱ ወንጀሎች በወገኖቻችን ላይ ፈጽሟል፤ አሁንም እየፈፀመ ነው። ባሳለፍነው ሣምንት እንኳን በሁመራ ወገኖቻችን የራሳቸውን መቀበሪያ ጉድጓድ ቆፍረው በጅምላ ተገድለዋል። በአይሲስና በህወሓት መካከል ያለው ልዩነት አይሲስ ነውረኛና አረመኔዓዊ ተግባሩን በቪዲዮ እየቀረፀ ለዓለም ሲበትን ህወሓት ግን እነዚሁኑ ነውረኛና አረመኔዓዊ ተግባሮችን እየፈፀመ መረጃዎች አፍኖ መያዙ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ህወሓት ሰዎችን ከነሕይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ የቀበረ አረመኔ፣ እኩይ ድርጅት ነው።
ስለሆነም ለዓለም ሰላም ስጋት የሆነውን አይሲስን ስንቃወም የራሳችንን አይሲስ – ህወሓትን – አለመርሳት እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ህወሓት፣ የአይሲስን እኩይ ተግባራት ከኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ጋር እና ከዲሞክራሲያዊያዊ ፓለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ጋር ለማገናኘት እያደረገ ያለው ጥረት ምን ያህል አደገኛ ተግባር እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረዳው ያስፈልጋል። ዓይን አውጣ ሌባ ንፁሁን ሰው “ሌባ” እንደሚለው ሁሉ የኛው አይሲስ ራሱን ንፁህ አስመስሎ ሌሎችን “አይሲስ” ማለቱ ሊነቃበት ይገባል።
ሌላው ተያያዥ ጉዳይ ደግሞ ስለስደተኝነት የሚሰጠው ገለፃ ነው። ህወሓት ለስደተኝነት ምክንያቱ ደላሎች እንደሆኑ ይናገራል። ይህ የጉዳዩን ግንድ ትቶ ቅርንጫፎች ላይ ማትኮር ነው። ህገወጥ ደላሎች ራሳቸው ሊኖሩ የቻሉት ገንዘብ ከፍለውና የሕይወት ሪስክ ወስደው ለመሰደድ የሚፈልጉ ዜጎች በመኖራቸው ነው። ችግሩን በቅንነት ለመመርመር የሚፈልግ “ይህን ያህል ሰው የሕይወት ሪስክ እየወሰደ ከአገር ለመሰደድ ምን አነሳሳው?” ብሎ መጠየቅ እና ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል። በሀገር ውስጥ በነፃነት ተረጋግቶ መኖር፣ ሠርቶ የማደግ ተስፋ ቢኖር ኖሮ ይኸን ያህል ሰው የአደጋውን ከፍተኛነት እያየ ለመሰደድ ይነሳሳ ነበርን? ኢትዮጵያዊው ከስደት ሊያገኝ የሚሻው ምንድነው? እንደ ወያኔ ካድሬዎች ገለፃ ከሆነ ከስደት ሊያገኝ የሚችለው አገሩ ውስጥ እያለለት ነው ኢትዮጵያዊ የሚሰደደው። ይህ ምን ዓይነት አመክኖ ነው? ከዚህ የባሰው ደግሞ ስደትንም የእድገት ውጤት አድርጎ የማቅረብ በሽታ ነው። ይህ እውነት ከሆነ፤ ህወሓት ለኢትዮጵያ አመጣሁላት የሚለው እድገት ውጤት ረሀብ፣ ስደት፣ መርዶ፣ እስር፣ ስቃይ፣ ሞት ከሆነ እንዴት “እድገት” ብለን እንጠራዋለን። ለስደተኝነት መብዛት ህገወጥ ደላሎችን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ፤ “እኔ ከደሙ ንፁህ ነኝ” የማለት ያህል ነው። በህጋዊዎቹም በህገወጦቹም ደላሎች ውስጥ የወያኔ ሰዎች በቀጥታም በተዘዋዋሪም እንዳሉበት መረጃዎች ያመለክታሉ። ገንዘብ ባላበት ሁሉ የወያኔ እጅ መኖሩ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው። የሰዎች ዝውውር የህወሓት አንዱ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ መሆኑ የማይታበል፤ በቀላሉ ማረጋገጥ የሚቻል ሀቅ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ በዓለም አቀፉ አይሲስ አረመኔያዊ ተግባሮች በደረሰብን የመጠቃት ስሜት ተውጠን የራሳችንን አይሲስ – አረመኔውን ህወሓት – እንዳንረሳ ያሳስባል። መቆሚያው ለማይታየው የዜጎቻችን መሰደድ መንስኤዎች የነፃነት እጦት እና የኑሮ እድሎች መጥበብ መሆናቸው እንዳንዘነጋ ይጠይቃል። ንቅናቂያችን እነዚህ ተያያዥ ችግሮች ሁሉ የሚቃለሉት ህወሓትን አስወግደን በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈኑባት ኢትዮጵያን ስንመሰረት ብቻ ነው ይላል። ለዚህም ደግሞ ሁላችንም በያለንበት የበኩላችንን ተሳትፎ ማድረግ ይገባናል። ሁለገብ ትግል ማለት፤ እያንዳንዱ ከሚመስለው ጋር እየተደራጀ በያለበት ወያኔ ማስጨነቅ፣ ማዋከብና ማዳከም፤ በመጨረሻም በጋራ ትግል ማስወገድ ማለት እንደሆነ ልብ እንበል። በሁለገብ ትግል ለውጥ የሚመጣው ሁሉም እንደ አቅሙ
በሚያደርገው ተሳትፎ በመሆኑ፣ የሚቻለንን በማድረግ የለውጥ ጠባቂ ሳንሆን፣ የለውጥ አምጭ አካል እንሁን ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
Category: Editorial
No comments:
Post a Comment