Wednesday, 11 February 2015

ለወያኔ ዉንብድና መልሱ ህዝባዊ እምቢተኝነትና ህዝባዊ አመጽ ነዉ!


pg7-logoዘረኞቹ የወያኔ መሪዎ የኢትዮጵያን በትረ ስልጣን ጨብጠዉ በኖሩባቸዉ ባለፉት ሃያ አራት አመታት የአገራችን የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እጅግ በጣም ከዘቀጠና ከረከሰ የወያኔ ድራማ ዉጭ ሌላ ምንም ነገር የማይታይበት አለባሌ መድረክ አድረገዉት ቆይተዋል አሁንም እያደረጉት ነዉ። አንድ ቋንቋ የሚናገሩትና ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸዉ የወያኔ መሪዎች ኢህአዴግ የሚባል አጋሰስ የሽፋን ድርጅት ፈጥረዉ በኢትዮጵያ ህዝብ ሰብዓዊ መብትና ነጻነትና ላይ ተነግሮም ተጽፎም የማያልቅ ግዙፍ ግፍና በደል ፈጽመዋል። ህጻን፤አዛዉንት፤ ወንድና ሴት ሳይለዩ መብቴን አትንኩ ያለቸዉን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያለምንም ርህራሄ በጥይት ጨፍጭፈዋል። ሴቶች እሀቶቻችንን እጅና እግራቸዉን አስረዉ ጡታቸዉን በመቆንጠጫ እየቆነጠጡ በሴትነታቸዉ ላይ የዉርደት ተግባር ፈጽመዋል። ወንዶች ወንድሞቻችንን ደግሞ ዉስጥ እግራቸዉን ገልብጠዉ እየገረፉ ጥፍራቸዉን አይናቸዉ እያየ በጉጠት እየሳቡ ነቅለዋል። ባጠቃላይ የወያኔ ዘረኞች በዛሬዉ ዘመን አንኳን ወገን በወገኑ ላይ የዉጭ ጠላትም በህዝብ ላይ የማይፈጽመዉ በደል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ፍጽመዋል።
ወያኔ ስልጣን እንደያዘ “አባይ ትግራይ” ወይም “ታላቋ ትግራይ” የሚለዉን ህልሙን ለማሳካት ወልቃይት ጠገዴን ከጎንደር ቆርሶ ከትግራይ ጋር ቀላቅሏል። ስልጣን ይዞ ከተደላደለ ከአመታት በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያን ገበሬ ከመሬቱ አፈናቅሎ ለምለም መሬቱን በርካሽ ዋጋ ለባዕዳን ሽጧል፤ ከዚህ አልፎ ተርፎም የአባቶቻችን አጽም ያረፈበትን የአገራችን ዳር ድንበር ቆርሶ ለጎረቤት አገር ገጸ በረከት አቅርቧል። ይህ አገራቸዉንና የሚመሩትን ህዝብ በሚጠሉ ጠባቦች የተሞላ ድርጀት ባለፈዉ ሳምንት የኢትዮጵያን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ደጋፊዎቹንና በአንቀልባ ታዝለዉ አስከዛሬ ያቆዩትን ምዕራባዉያን ጭምር ግራ ያጋባ ፀረ አገርና ፀረ ህዝብ እርምጃ ወስዷል። ድርጅት እያፈረሰና በፓርቲ ላይ የራሱን ተለጣፊ ፓርቲ እያቋቋመ ዛሬ ላይ የደረሰዉ ወያኔ ምርጫ የሚባል ድራማ በደረሰ ቁጥር የሚይዘዉ በሽታ ዘንድሮም ይዞት አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲንና መላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን አፍርሶ በምትካቸዉ የራሱን መኢአድና የራሱን አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ፈጥሯል። ይህ ወያኔ ከሰሞኑ የወሰደዉ የፖለቲካ እርምጃ በየትኛዉም አለም በተለይ የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዐትን እንከተላለን በሚሉ አገሮች ዉስጥ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ እጅግ በጣም ትልቅ የፖለቲካ ሸፍጥ ነዉ።
የወያኔን ታሪክ ተወልዶ ካደገበት ከደደቢት በረሃ እስከ ሚኒልክ ቤ/መንግስት ድረስ ያደረገዉን ጉዞ ስንመለከት ወለል ብሎ የሚታየን አንድ ሐቅ አለ፤ እሱም ወያኔ ሁሉንም ነገር በዘር መነጽር ብቻ የሚመለከትና ህዝብን በወዳጅና በጠላት ጎራ ለይቶ ወዳጅ አይደለም ያለዉን ሁሉ እንደ ሩሲያዊዉ ዮሴፍ ስታሊን እየገደለ የመጣ ድርጅት ነዉ። በእርግጥም ወያኔ ጫካ ዉስጥ እያለም ሆነ ዛሬ ከተማ ገብቶ የሚቃወመዉንና በሀሳብ የማይግባባዉን ድርጅትም ሆነ ግለሰብ እያፈረሰና እገደለ ባፈረሳቸዉ ድርጅቶች ምትክ ደግሞ የራሱን ተለጣፊ ድርጅት እየፈጠረ የመጣና ከዲሞክራሲያዊ አሠራርና ከስልጣኔ ጋር የማይተዋቅ ድርጅት ነዉ።
በመርፌ የተጠቃቀመ ቁምጣና ጥብቆ ለብሶ አስራ ሰባት አመት ጫካ ለጫካ የተጓዘዉ ወያኔ ጎንደር፤ ጎጃምና አምቦ እያለ ወደ አዲስ አበባ ሲጠጋ ከተገነዘባቸዉ ነገሮች አንዱ የለበሰዉ የተጠቃቀመ ቁምጣ የትም እንደማያደርሰዉና ለከተማ ኑሮ የሚስማማ አዲስ ልብስ እንደሚያሰፈልገዉ ማዉቁ ነዉ። በጥላቻ ተረግዞ በክፋት ላደገዉ ወያኔ ቢበቃዉም ባይበቃዉም ወይም ቢያምርበትም ባያምርበትም ይህንን ለከተማ ዉስጥ ኑሮ የሚያስፈልገዉን አዲስ ልብስ ለማዘጋጀት ብዙ ግዜ እልወሰደበትም። የሚሰርቅና የሚስቅ ምን ግዜም ተባባሪ አያጣም እንዲሉ ወያኔ የአዲስ አበባን መሬት የረገጠዉ ጦር ሜዳ ላይ የማረካቸዉን ወታደሮችና አገር ዉስጥ ያገኛቸዉን ደካማ ሰዎች ሰብስቦ በፈጠረዉ ኢህአዴግ በሚባል ፈረስ ጀርባ ላይ ተፈናጥጦ ነበር። ትግራይን ነጻ አወጣለሁ ብሎ ትግል የጀመረዉ ወያኔ ኢህአዴግን የፈጠረዉ ወያኔነቱን ለመተዉ ሳይሆን እራሱን በዚህ በኢትዮጵያ ስም በፈጠረዉ ድርጅት ዉስጥ ሸሽጎ እዉነተኛ ባህሪዩን ለመደበቅ ነበር።
ከግንቦት 1983 ዓም አስከ ግንቦት 1987 ዓም ድረስ የዘለቀዉንና በወያኔ የበላይነት ተጀምሮ ወያኔን በማንገስ የተጠናቀቀዉን የሽግግር መንግስት ወደ ኋላ መለስ ብሎ የቃኘ ማንም ሰዉ የወያኔን ሁለት ዋና ዋና መሠሪ ስራዎች በቀላሉ መመልከት ይችላል።
አንደኛ- ኦነግንና የደቡብ ህዝብ ንቅናቄን ጨምሮ አያሌ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ታዋቂ ግለሰቦችን አቅፎ ስራዉን የጀመረዉ የሽግግሩ መንግስት የስራ ዘመን የተገባደደዉ የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ያነሱ ግለሰቦችን በማሰርና ከወያኔ ቁጥጥር ዉጭ እራሳቸዉን ችለዉ ለመንቀሳቀስ የሞከሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ከሽግግሩ መንግስት በማባረር ነበር።
ሁለተኛ- ወያኔ የኋላ ኋላ እያደር ለመስራት ላቀዳቸዉ አገር የመበተንና ህዝብን የመለያየት ስራዎች እንዲያመቸዉ ከእያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት ጀርባ የኢትዮጵያ ህዝብ ተለጣፊ እያለ የሚጠራቸዉን ድርጅቶች በራሱ አምሳል እየፈጠረ ማሰማራቱ ነዉ።
ባጠቃላይ ወያኔ የፈጠረዉ የሽግግር መንግስት ኢትዮጵያዊ አጀንዳና አገራዊ ራዕይ ይዘዉ የተንቀሳቀሱ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን አጥፍቶ ወያኔን ዘለአለማዊ ንጉስ ለማደረግ ከመሞከሩ ዉጭ ሌላ ምንም ኢትዮጵያን የሚጠቅም ስራ አልሰራም።
ከሽግግሩ መንግስት በኋላ ወያኔ ተወዳዳሪዉም አሸናፊዉም እሱ ብቻ የሆነባቸዉን ሁለት ትርጉም የለሽ ምርጫዎችን አካሂዷል።እነዚህን ተወዳዳሪ የለለባቸዉን ሁለት ምርጫዎች በቀላሉ በማሸነፉ ህዝብ የወደደዉ መስሎት ልቡ ያበጠዉ ወያኔ ሦስተኛዉን አገራዊ ምርጫ ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ምርጫዎች በተለየ መልኩ ለቀቅ አድርጎ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ፤ መራጩን ህዝብ መቅረብ እንዲችሉና ወያኔን እራሱን ምርጫዉን አስመልክቶ ክርክር እንዲገጥሙት በሩን ከፈተላቸዉ። ነገሩ “የማይነጋ መስሏት” እንዲሉ ሆነና ሜዳዉም ፈረሱም ይሄዉና ብሎ የፊልሚያዉን ሜዳ የከፈተዉ ወያኔ የምርጫዉ ቀን ደርሶ በዝረራ መሸነፉን ሲሰማ በራሱ ሜዳና በራሱ ዳኞች ፍት ያሸነፉትን የህዝብ ተመራጮች ከየመኖሪያ ቤታቸዉ እያደነ አስሮ በአገር ክህደት ወንጀል ከሰሳቸዉ ። የሚገርመዉ ወያኔ በምርጫዉ ተወዳድረዉ በምስክር ፊት በአደባባይ ያሸነፉትን የህዝብ ተመራጮች በማሰር ብቻ አልተወሰነም። በወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ አይኑ ብሌን ይመለከተዉ የነበረዉን ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲን አፍርሶ እንደለመደዉ የራሱን ቅንጅት ፓርቲ ፈጥሮ ይበጃል ብሎ ላሰባቸዉ ደካማና ሆዳም ግለሰቦች አስረክቧል።
ይህ ቆየት ያለ በሽታዉ ዘንድሮም አገርሽቶበት አንድነትንና መኢአድን ለክፏቸዋል። ይህ ወያኔ ከሰሞኑ መኢአድና አንድነት ላይ የወሰደዉ እርምጃ እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች በመጪዉ ምርጫ ላይ ያሸንፉኛል ከሚል ፍራቻ አይደለም። ወያኔ ምርጫዉ የሚካሄድበት ሂደት ብቻ ሳይሆን ህዝብ የሰጠዉ ድምጽ የሚቆጠርበትና የምርጫዉ ዉጤት ለህዝብ የሚገለጽበት መንገድ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር እንደሆነና ይህንን ምርጫ ብቻ ሳይሆን የሚቀጥለዉንም ምርጫ ከሱ ዉጭ ሌላ ማንም እንደማያሸንፍ በሚገባ ያዉቃል። ወያኔ መኢአድንና አንድነትን የጥቃቱ ሰለባ ያደረጋቸዉ ህዝባዊ አላማቸዉንና አገራዊ ራዕያቸዉን በተለይ እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ፤ አንድነትና እኩልነት ጥያቄ ላይ ያላቸዉን የጠራና የማያወላዉል አቋም እጅግ በጣም ስሚጠላ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ ወያኔ እንዲህ በአጭር ግዜ ዉስጥ መኢአድንና አንድነትን የጨፈለቃቸዉ እነዚህ ሁለት አንጋፋ ፓርቲዎች አዲስ አበባን ጨምሮ በየክልሉ የዘረጉት መዋቅርና ከህዘብ ጋር የፈጠሩት የቅርብ ግኑኝነት እንቅልፍ ስለነሳዉ ነዉ። ሌላዉ በፍጹም መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር ይዋል ይደር እንጂ ወያኔ እኛ ቀድመን ካላጠፋነዉ በቀር “ኢትዮጵያዊነት” ፤ “አንድነት” ወይም ፍትህና ነጻነት ብሎ የተነሳን ማንንም ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ወይም ድርጅት ማጥፋቱ አይቀርም። በእርግጥም ከትናንት ወዲያ ቅንጀትን፤ ዛሬ ደግሞ መኢአድንና አንድነትን አፍርሶ የራሱን ተለጣፊ አሻንጉሊቶች የፈጠረዉ ወያኔ ነገ እነዚህ ፓርቲዎች የቆሙለትን አላማ የተሸከምነዉን ኢትዮጵያዉያን አንድና ሁለት እያለ ለቃቅሞ እንደሚያጠፋን ምንም ጥርጥር የለዉም።
ወያኔ አምስት አመት አየቆየ በሚመጣዉ የምርጫ ድርማ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጀርባ ላይ እንደማይወርድ በ1997 ዓም ሰኔ ወርና በ 1998 ዓም ህዳር ወር በአዲስ አበባ አደባባዮች ላይ በወሰደዉ ፋሺስታዊ እርምጃ በግልጽ አሳይቶናል።ከላይ ከፍ ሲል ለመግለጽ አንደተሞከረዉ ወያኔ ፊታችን ላይ ባለዉ በ2007ቱ ምርጫ ወይም በተከታታይ በሚመጡት ምርጫዎች ተሸንፌ ከስልጣን እወርዳለሁ የሚል ምንም አይት ስጋት የለበትም፤ ምክንያቱም በምርጫዉ ጨዋታ ዉስጥ ተጫዋቹም ፤ ሜዳዉም ዳኛዉም ወያኔ ብቻ ነዉ። ዛሬ የወያኔን መሪዎች ያንቀጠቀጣቸዉና እንዳበደ ዉሻ ያገኙትን ሁሉ እንዲነክሱ ያደረጋቸዉ አገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ በተግባራዊ ስራዎች ላይ መናበብ በመጀመሩና በህዝባዊ እምቢተኝነቱና በህዝባዊ አመጹ ዘርፍ የሚደረገዉ እንቅስቃሴ ህዝባዊ ሙቀት አግኝቶ እየተጋጋለ በመምጣቱ ነዉ። ወያኔዎች እነሱንና የገነቡትን ዘረኛ ስርዐት ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ የሚያጠፋዉ የህዝባዊ አመጹና የህዝባዊ እምቢተኝነቱ ጎርፍ መሆኑን ካወቁ ቆይተዋል። ይህ ከሰሞኑ በማሰር፤ በመደብደብና ድርጅት በማፍረስ የወሰዷቸዉ እርምጃዎች የሚያሳዩን ወያኔዎች ህዝባዊ ጎርፉን ቢቻል ለማጥፋት አለዚያም ጉዳት በማያደርስ መልኩ ለመገደብ ያሚያደርጉትን ከንቱ ሙከራ ነዉ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ የኢትዮጵያ ወጣት፤ ገበሬና ሰራተኛ ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ትናንት ቅንጅትን አፍርሶ የራሱን መናኛ ቅንጅት የፈጠረዉ ወያኔ ዛሬም እንደገና አሉ የሚባሉትንና አገራዊ ራዕይ ይዘዉ የሚንቀሳቀሱትን አንድነትንና መኢአድን አፍርሶ በምትካቸዉ እንደጌኛ ፈረስ የሚጋልብባቸዉን የራሱን ሁለት መናኛ ፓርቲዎች ፈጥሮ መኢአድና አንድነት ብሎ ሰይሟቸዋል። ይህ በዋና ዋናዎቹ ዘረኛ የወያኔ ባለስልጣኖች ተጠንቶ በጥንቃቄ የተወሰደዉ እርምጃ ፓርቲዎቹ ህግ ስላላከበሩ ነዉ የሚል ሽፋን ይሰጠዉ እንጂ የምርጫ ቦርዱ ሊ/መንበር ሳያስቡት ከአፋቸዉ አፈትልኮ የወጣዉ እዉነት በግልጽ እንዳስቀመጠዉ ከምርጫዉ ጨዋታ ወጥተዉ እንዲፈርሱ በተደረጉት አንድነትና መኢአድ ፓርቲና ወያኔ በተለጣፊነት ባስጠጋቸዉ ሁለቱ ተለጣፊ ፓርቲዎች መካከል ያለዉ ልዩነት አንዱ ቆሜለታለሁ ለሚለዉ ህዝብ የሚታዘዝ ህዝባዊ ሌላዉ ደግሞ ሆዱን ለሚሞላለት ወያኔ የሚታዘዝ ሆዳም መሆናቸዉ ብቻ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ወያኔ መብቴን ብለህ ስትጮህ በጥይት እየጨፈጨፈህ ነጻነት ስትለዉ በዱላ እየደበደበህና ሰላማዊ ሰልፍ ስትወጣ ደግሞ አፍሶ እያሰረህና ዉስጥ እግርህን ገልብጦ እየገረፈህ በሰላማዊ መንገድ የምታደርገዉን ትግል ምርጫ አሳጥቶሃል። ሆኖም ግልጽ በሆነ መንገድ እንነጋገር ከተባለ ወያኔ የትግል አማራጭ አያሳጣህም፤ ሊያሳጣህም አይችልም። ወያኔ እሱ እራሱ ህግ በሆነበት አገር ህጋዊ ወይም ሠላማዊ ትግል ብሎ ነገር ዋጋ ቢስ አንደሆነ ሁላችንም የተረዳን ይመስላል። ትግላችን ህዝባዊ እምቢተኝነት ነዉና ከዛሬ በኋላ ወያኔን ጥያቄ አንጠይቀዉም፤ አድርጉ የሚለንን አናደርግም፤ ሁኑ የሚለንንም አንሆንም። ትግላችን ህዝባዊ አመጽ ነዉና ከዛሬ በኋላ ወያኔ ሲገድለን እኛም እየገደልነዉ እንሞታለን እንጂ አንገታችንን ደፍተን የእሳት እራት አንሆንም። አዎ! ት ግላችን እምቢ ማለት ወይም ህዝባዊ እምቢተኝነት ነዉ፤ ትግላችን በወያኔ ላይ ማመጽ ወይም ህዝባዊ አመጽ ነዉ።

No comments:

Post a Comment