Monday, 12 January 2015

ትናንት ከዉጭ ወራሪዎች የታደገን መከላከያ ሠራዊታችን ዛሬም ከአገር ዉስጥ ወራሪዎች ይታደገናል


አስተዋዩ የኢትዮጵያ ህዝብ እድገቱን ለሚመኙ አስተዋይ መሪዎች እለታደለምና ደሃ ነዉ፤ ረሀብተኛ ነዉ አልተማረም ወይም ኋላ ቀር ህዝብ ነዉ ማለት ይቻል ይሆናል፤ ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝብ ያሰኘዉን ያክል ቢደኸይ ወይም ኋላ ቀር ቢሆን ለነፃነቱ፤ ለአንድነቱና ለግዛት አንድነቱ መከበር ያለስስት ደሙን የሚያፈስ ጀግና ህዝብ ነዉ። ይህ ጀግንነት ደግሞ አንደተረት በአፍ ተነግሮ የሚያበቃ ሳይሆን በመተማ፤ በአድዋ፤ በማይጮዉ፤ በወልወል፤ በፊልቱና በጎዴ የጦር ሜዳዎች ሊወጉትና ሊወሩት የመጡ ጠላቶቹ ጭምር የመሰክሩለት የታሪክ ሐቅ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከጀግንነቱ ጋር አርቆ አስተዋይና ታጋሽ ህዝብ ነዉ፤ ሆኖም ይህንን ህዝብ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በተከታታይ የገዙት የገዢ መደቦች ጀግንነቱን ለራሳቸዉ ክብርና ዝና ታጋሽነቱን ደግሞ ለስልጣን ዘመናቸዉ ማራዘሚያ አድርገዉ የመከራ ዘመን እያስቆጠሩ ኖረዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ታጋሽ ህዝብ ቢሆንም እርግጫዉና ጭቆናዉ በበዛበት ቁጥር አምርሮ የሚነሳ ለገዢ መደቦች የማይመች ቁጡና እልህኸኛ ህዝብ መሆኑንም በተከታታይ አሳይቷል። ይህንን ደግሞ በ1966 ዓም ከዳር ዳር ባቀጣጠለዉ ህዝባዊ አብዮት በ1983 ዓም ደግሞ በአራቱም ማዕዘናት ባካሄደዉ ህዝባዊ አመጽ አሳይቷል። ሆኖም አብዮቱንና ህዝባዊ አመጹን ከትግል ሜዳ እስከ ፖለቲካ ስልጣን አደባባዮች ድረስ አቀነባብሮ የሚመራ የተደራጀ ህዝባዊ ኃይል ባለመኖሩ የኢትዮጵያ ህዝብ የታገለላቸዉ የትግል ዉጤቶች ሁሉ የአምባገነኖች መጠቀሚያ ሆነዉ ቀርተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ጀግና ነዉ፤ ተጋሽ ነዉ፤ ወይም አርቆ አስተዋይ ነዉ ሲባል እንዚህ እሴቶች ወንዱን፤ ሴቱን፤ ምሁሩን፤ ገበሬዉን፤ ሰራተኛዉንና መለዮ ለባሹን ሁሉ የሚያጠቃልሉ ህዝባዊ እሴቶች ናቸዉ እንጂ የአንድ ህብረተሰብ ክፍል ልዩ ንብረቶች አይደሉም። በእርግጥም አብዛኛዉ የታሪካችን ክፍል በአገር አንድነት ግንባታና ይህንኑ አንድነት ከዉጭ ወራሪዎች በመከላከል ጦርነት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ጀግንነትን በቀጥታ የምናያይዘዉ ከዚሁ አገርንና የአገር አንድነትን ከማስከበር ስራ ጋር ነዉ። በእርግጥ አገርን ከጠላት መከላከል ጀግንነት ነዉ፤ ሆኖም መሳሪያ ተሸክሞ አገሩን ከጠላት የሚከላከል ሠራዊት ምን እለብሳለሁ፤ ምን እበላለሁ፤ በምንስ እዋጋለሁ ከሚለዉ ስጋት ተላቅቆ በሙሉ ኃይሉና አዕምሮዉ መዋጋት የሚችለዉ እንደነሱ ጀግና የሆነና በደጀንነት የተሰለፈ ህዝብ ሲኖር ብቻ ነዉ።
እስከ አድዋ ጦርነት ድረስ አገራችን ኢትዮጵያ የመሪዉን የክተት አዋጅ ጥሪ እየሰማ የሚዘምት ህዝብ እንጂ ቋሚ የመከላከያ ሠራዊት አልነበራትም። ባለፉት 60 አመታት ግን ኢትዮጵያ የምድር ጦር፤ አየር ኃይል፤ ብሔራዊ ጦርና እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ደግሞ የባሕር ኃይልን ጭምር ያካተተ ዘመናዊ የመከላከያ ሠራዊት ነበራት። ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የአገራችንን በትረ ስልጣን እስከጨበጠበት እስከ 1983 ዓም ድረስ የነበረዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሞላ ጎደል በመስኩ ልምድ፤ ችሎታና እዉቀት ባካበቱ ባለሙያዎች የተሞላና የአገረን ዳር ድንበር ከመጠበቅ ባሻገር ለወገናቸዉ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ደህንነት ቀና አመለካከት ባላቸዉ አገር ወዳዶች የተገነባ ሠራዊት ነበር። ወያኔ በ1983 ዓም አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ይህንን አገር ወዳድ የሆነ ፕሮፌሺናል ሠራዊት በትኖ ነዉ ለአንድ ድርጅት ጥቅምና ዝና በቆሙ፤ ፊደል ባልቆጠሩና ሙያዊ ብቃት በሌላቸዉ መሀይሞች የተሞላ መከላከያ ሠራዊት የተካዉ። እንደዚህ ስንል ግን ወያኔ በገነባዉ የአገር መከላከያ ሠራዊት ዉስጥ አገራቸዉ ኢትዮጵያን ከራሳቸዉ በላይ የሚወዱና ለአገራቸዉና ለወገናቸዉ ክብርና ጥቅም መስዋዕት ለመሆን የቆረጡ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፤ እንዲያዉም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚመራዉና የግዳጅ ትዕዛዝ የሚወስደዉ አገራቸዉን በሚጠሉ ዘረኞች መሆኑ ነዉ እንጂ ዛሬም ቢሆን አብዛኛዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል የእናት አገሩ ዳር ድንበር መደፈርና የወገኖቹ መረገጥ የሚያንገበግበዉ አገር ወዳድ ሠራዊት ነዉ።
የ1966ቱ ህዝባዊ አብዮት ሲፈነዳ የነበረዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፊዉዳሉ መንግስት የደሞዝ ጭማሪ አድርጎለት ከህዝባዊ ኃላፊነቱ ሊያዘናጋዉ ሲሞክር – “ሎሚ ተራ ተራ፤ “ሎሚ ተራ ተራ እኛስ አግኝተናል ሲቪሉን አደራ” ብሎ የህዝብ ወዳጅነቱን ያረጋገጠ አገር ወዳድ ሠራዊት ነበር። አመጸኛዉ ደርግ ይህንን ሠራዊት ተጠቅሞ ነዉ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሤን ስርዐት ያስወገደዉና የመሬት አዋጅን የመሳሰሉ ስር ነቀል አርምጃዊዎች መዉሰድ የጀመረዉ። አምባገነኑ ደርግ ቁልፍ በሆኑ የመከላከያ ሠራዊት ተቋሞች ዉስጥ ታማኝ የሆኑ የራሱን ሰዎች አስቀምጦ ለ17 አመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ቢረግጥም ጄኔራል ተፈሪ በንቲን፤ ኮሎኔል አጥናፉ አባተን፤ ተስፋዬ ትርፌን፤ ጄኔራል መርዕድ ንጉሴን፤ ቁምላቸዉ ደጄኔን፤ አምሀ ደስታንና ፋንታ በላይን የመሳሰሉ እስከመጨረሻዉ ትንፋሻቸዉ ድረስ ህዝባዊ አደራቸዉን የጠበቁ ታማኝ የህዝብ አገልጋዮች በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ነበሩ። በንጉሰ ነገስቱም ዘመን ቢሆን ገና ከጥዋቱ ከዝናና ጥቅም ይልቅ የአገራቸዉን ጥቅም ያሰቀደሙ እንደ ጀኔራል መንግስቱ ነዋይ አይነት የለዉጥ አርበኞች ነበሩ።
ወላድ በድባብ ትሂድ – ዛሬም ቢሆን እጅግ በጣም ጨለማ በሆነዉ ጨካኝና ዘረኛ ስርዐት ዉስጥ ጨለማዉን እየገለጡ በድፍረት የአገራቸዉን ህዝብ ጩኸትና ሰቀቃ አዳምጠዉ ዘረኝነት በቃ ያሉ ጀግኖች በመከላከያ ሠራዊቱ ዉስጥ አሉ። በአንድ ቋንቋና በዘር ሰንሰለት ተሳስረዉ የሚሰሩ የወያኔ ደህንነቶች መግቢያዉንና መዉጪያዉን ቆልፈዉ ለጌቶቻቸዉ ዘብ ቢቆሙም ጀግናና ጭስ መዉጪያ አያጣምና ከፍተኛ ልምድና ችሎታ ያላቸዉ የወያኔ መከላከያ ሠራዊት አባላት ከወያኔ ጎራ እየወጡ የህዝባዊ አመጹን ጎራ እየተቀላቀሉ ነዉ። ሁላችንም በየቀኑ በግልጽ እንደምናዉ ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁለት አይነት ዜግነት ፈጥረዋል። አንደኛዉ ዜግነት ወያኔና አገራቸዉን ከድተዉ የወያኔ ተላላኪ በሆኑ እንደነ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ፤ አዲሱ ለገሰና ሬድዋን ሁሴንን በመሳሰሉ ሆድ አደሮች የተሞላ ሲሆን፤ ሁለተኛዉ ዜግነት ደግሞ አገር ወዳዶችና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ያሉበት ነዉ። ከእንደዚህ አይነቱ በዘር ከተከፋፈለና እያንዳንዷ ኮሽ ያለች ነገር በወያኔ ደህንነት ሰራተኞች ተመዝግባ በምትመረመርበት አገር ዉስጥ ለህዝባዊ አላማ ጸንቶ መቆምና ስርዐቱን አልፈልግም ብሎ የነፃነት ኃይሎችን መቀላቀል ከፍተኛ ጀግንነትንና ቆራትነትን ይጠይቃል። ቆየት ባለዉ ግዜ እነ መቶ አለቃ ተሾመ ተንኮሉና ጄኔራል ከማል ገልቹ፤ አሁን በቅርቡ ደግሞ ሦስቱ የተዋጊ ሂሊኮፕተር አብራሪዎችና አራቱ ባለከፍተኛ ማዕረግ የአየር ኃይል ተዋጊ ጄት አብራሪዎች የወሰዱት ህዝባዊ እርምጃ ከሆነ በኋላ በሰበር ዜና ስንሰማዉ ቀላል ይመስላል እንጂ እርምጃዉ ጀግንነትን፤ ቆራጥነትንና በህይወት መወራረድን ይጠይቃል። እነዚህ ለፍትህ፤ ለነጻነትና ለእኩልነት የቆሙ ቆራጥ ዜጎች በወሰዱት እርምጃ አገር ዉስጥና ከአገሩ ዉጭ የሚኖረዉን ኢትዮጵያዊ እጅግ በጣም ደስ አሰኝቷል። በእርግጥም እነዚህ ጀግኖች የወሰዱት እርምጃ ህዝባዊ ትግሉን የሚያነቃቃና የሚያጠናክር ነዉና በልጆቻችን እርምጃ ልንኮራና ደስ ሊለን ይገባል። ሆኖም ይህ ቆራጥ እርምጃ የትግል ጥሪም ነዉና ሁላችንም ጥሪዉን አዳምጠን ዛሬ ነገ ሳንል አሁኑኑ አቤት ማለት አለብን።
ዛሬ ለአመታት በላይ ሲታመስና ሲብሰለሰል የቆየዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶት ገንፍሎ ወጥቶ ወደ ለየለት ህዝባዊ አመጽነት እየተቀየረ ነዉ። ይህንን ህዝባዊ አመጽ በትክክል መርቶ ከግቡ ለማድረስና ከዚህ በፊት በተከታታይ የተፈጠሩትን የስልጣን ከፍተቶችና ስህተቶች አርሞ ትግሉን በእስማማኝ መሰረት ላይ ለማቆም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ታሪካዊና አገራዊ ሃላፊነት አለበት። በቅርቡ ተዋጊ የጦር ሂሊከፕተራቸዉን እንደያዙ የወያኔ ስርዐት በቃን ብለዉ የነጻነት ሀይሎችን የተቀላቀሉት ጀግኖች ዜና ሲሰማ ወያኔ ከፍሎ ያሰማራቸዉ ተናካሽ ዉሾቹ ያንን የለመዱትንና የተካኑበትን እንቆርጣችኋለን እንፈልጣችኋለን የሚል ተራ ዛቻቸዉን አሰምተዉናል። ከዚህ አልፈዉም ወያኔ የታጠቀዉን መሳሪያ ዘመናዊነትና ያደራጀዉን ሠራዊት ብዛት ደጋግመዉ በመጥቀስ እነሱን መንካት ከእሳት ጋር መጫወት እንደሆነ ሊነግሩን ሞክረዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ በወቅቱ ስሙን እንኳን አጣርቶ የማይጠራዉ ህወሓት ከሰሃራ በታች ተወዳዳሪ የለዉም የተባለዉ ሠራዊት የገነባ ኃይል ለምን አንደሚዋጋ እንኳን በማያዉቅ ጀሌ ጦር ማሸነፍ ከቻለ ዛሬማ ፍጹም የሆነ ህዝባዊ መሠረት ያላቸዉና ለምንና ለማን እንደሚዋጉ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁ የነጻነት ኃይሎች ካሰቡበት ለመድረስ የሚያግዳቸዉ ምንም ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ወያኔና ሆድ አደር ደጋፊዎቹ ተንቅቀዉ ሊያዉቁ ይገባል። ወያኔ ልቡ ስላበጠ የተለቀ ይምሰለዉ እንጁ የትልቅነቱ መገለጫ አድርጎ የሚተማመንበት የመከላከያ ሠራዊት ያቺ የፍጥጫ ቀን ስትመጣ ወያኔን ለመደምሰስ ወገኖቹን የሚቀላቀል ሠራዊት ነዉ። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጀግኖቹ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት የወሰዱት ህዝባዊ እርምጃም በአየር ኃይሉ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ቀን፤ ግዜና ሁኔታ እየመረጠ እግረኛ ሠራዊቱም የሚወስደዉ እርምጃ እንደሆነ ያለ ጥርጥር እናምናለን።
ዉድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሆይ – አንተንና ወገኖችህን በዘር ከፋፍሎ እየገዛ አገርህን የሚያፈርሰዉ ወያኔ ለዚህ እኩይ ስራዉ የሚጠቀመዉ አንተኑ ከህዝብ አብራክ የወጣኸዉን የህዝብ ልጅ ነዉ። በቅርቡ ባህር ዳር ዉስጥ የቅዱስ ታቦት ማደሪያ የሆነዉን ቦታ ከቤ/ ክርሲቲያን ቀምቶ የሸቀጥ መሸጫ ለማድረግ ያደረገዉን ሙከራ የተቃወሙ ኢትዮጵያዉያን ወንድሞችህና ወንድሞችህ እንዲሁም አለም በቃኝ ያሉ መነኩሴ ጭምር በጥይት ጨፍጭፏል። በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ወልቃይት ጠገዴን ከጎንደር ቆርጦ ትግራይ ላይ የቀጠለዉ ወያኔ ይህ ፀረ ህዝብና ፀረ አገር ወንጀል አልበቃ ብሎት ለዘመናት አብሮ የኖረዉን የትግራይንና የጎንደርን ህዝብ ለማባላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነዉ። በታህሳስ ወር አጋማሽ ጎንደር ዉስጥ የትግራይና ክልልና የጎንደር ሚሊሺያዎች የተኩስ ልዉዉጥ ካደረጉ በኋላ ወያኔ አገርን ለመዉረር በሚመጣ ጠላት ላይ እንጂ በራሱ ወገን ላይ መዝመት የሌለባቸዉን ከ30 በላይ ታንኮችና ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች ወደ ጎንደር በማሰማራት አገሩንና ወገኑን መጠበቅ ያለበትን ሠራዊት ከገዛ ወገኖቹ ጋር እንዲፋጠጥ አድርገዋል።
በዚህ ፈታኝና እጅግ በጣም አስቸጋሪ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሂድና ግድል በተባለ ቁጥር መጠበቅና መንከባከብ የሚገባዉን የገዛ ወገኖቹን የማይገድል አስተዋይና ወገንተኛ ሠራዊት መሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት። አዎ! የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምንግዜም ቢሆን በአገሩ ጠላቶችና ወራሪዎች ላይ ብቻ እንጂ እያበለና እያጠጣ ባሳደገዉና እኔንና አገሬን ጠብቅ ብሎ ባስታጠቀዉ ህዝብ ላይ በምንም አይነት አፈሙዙን አያዞርም። ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ ከወያኔ በላይ ጠላት የላቸዉም። ህዝብና አገር እስከ ምድር ፍጻሜ ድረስ አብረዉ የሚዘልቁ ተከታታይ ክስተቶች ናቸዉ፤ ወያኔ ግን ትናንት በጠመንጃ ሀይል መጥቶብን እኛንና አገራችንን ለማጥፋት የሚታገል የለየለት ጠላት ነዉ። ከዛሬ ጀምሮ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ወያኔን ከዉስጥ ሆኖ መቦርቦር አለበት፡ ይህንን ማድርግ ካልቻለ ደግሞ ወያኔ ከወገኖቹ ጋር እንዲዋጋ ሲያሰማራዉ ወያኔን እየከዳ ከነጻነት ኃይሎች ጋር ተቀላቅሎ ወያኔን ለመደምሰስ በሚደረገዉ ትግል ዉስጥ ወሳኙን ሚና መጫወት ይኖርበታል። ግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከዚህ ቀደም እንዳደረገዉ ሁሉ አሁንም እንደገና ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት . . . ና ተቀላቀለንና አንድ ላይ ሆነን ወያኔንና ወያኔ የገነባዉን ዘረኛ ስርዐት ቀብረን የኢትዮጵያን ህዝብ ከዉርደት፤ ከእስር፤ ከድብደባ ከግድያና ከስደት እናድን የሚል አገራዊ ጥሪዉን ከአደራ ጋር ያስተላልፋል።

No comments:

Post a Comment