Tuesday, 9 December 2014

የህወሃት ምርጫ የህዝብ መከራ!

 


ህወሃቶች እኛ ከሌለን ይህችን አገር እንበትናታለን፤ ይህችን አገር የምንሰብር እኛ የምንጠግን እኛ እያሉ እንደሚያሟርቱ ሰምተናል። እኛ የቀረፅነው ፖሊስ ከሚቀየር ሞታችንን እንመርጣለን እያሉ ማቅራራታቸውም ከህዝብ የተሰወረ ነገር አይደለም። የህወሃት ፖሊሲ የሚቀየረው በመቃብርችን ላይ ነው የሚል የማይናወፅ አቋማቸው መቼም ቢሆን በሠለጠነ መንገድ በውይይትና በድርድር እንደማይቀየር ደጋግመው አሳይተውናል። ህወሃቶችን በሠለጠነ መንገድ ተደራድሮ እና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ለለውጥ አዘጋጃለሁ ማለት ከእባብ የእርግብ እንቁላል እንደመመኘት ያህል ነው። ከእባብ የእርግብን ዘር የሚጠብቅ ማን ነው?
እንግዲህ ህወሃቶች ይህን የመሰለ የከረረ አቋም ይዘው ምርጫ ለምን ያደርጋሉ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል። ይሄ ህወሃቶች ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ራዕይ የሌላቸው ከመሆን የሚመነጭ ነው። ድርጅቱ ራዕይ አልባ የሆነው ደግሞ በህወሃት ውስጥ የተሰባሰቡ ግለሰቦች ራዕይ አልባ በመሆናቸው ነው። ህወሃቶች የሚኖሩለትም ሆነ የሚሞቱለት ቁም ነገር ከመብልና መጠጥ የዘለለ አይደለም። ህወሃቶች ራዕይ ቢኖራቸው ኑሮ በታሪክ የሚያስወቅሳቸውንና የህዝቡን ፍቅር የሚያሳጣቸውን እኩይ ተግባራት ባልፈፀሙ ነበር። ራዕይ የሌላቸው በመሆኑ ለሚፈፅሙት ወንጀል ሁሉ ገደብ እንዳይኖራቸው ሆኑ። ራዕይ ያለው ሰውም ሆነ ድርጅት እኔ ብቻ አይልም። ራዕይ የሰነቀ ድርጅትም ሆነ ሰው ከራሱ ክበብ አልፎ ሌላው እንደምን ሁኖ በሠላም እና በደስታ እንደሚኖር ያስባል እንጂ ዕለት ዕለት ደም በማፍሰስ አይኖርም።
ህወሃት በምርጫ ስልጣኑን እንደማይለቅ ለራሱ የማለ ድርጅት ነው። እዚህ መሃላ ላይ ያደረሰው ደግሞ እስከ ዛሬ የፈፀማቸው ወንጀሎቹ ናቸው።የጨበጠውን ስልጣን በምርጫ ቢለቅ ነገ የሚከተለውን ጠንቅቆ ያውቃል። ትላንት ያፈሰሱት የንፁሃን ደም ከኢትዮጵያ ምድር ላይ እየጮኸ ነው። ዘርፈው የገነቡት ህንፃ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ቆመው ሌብነታቸውን እየመሰከሩባቸው ነው። በልማት ሥም ከኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ተዘርፎ የተደራጀው የንግድ ተቋም በኢትዮጵያ ህዝብ ወዝና ደም ታጥኖ እንዳማረበት አለ። ህወሃት የኢትዮጵያ የህዝብ ጠላት ሆኖ ራሱን ያቆመ ቡድን በመሆኑ በሰላማዊ እና በሰለጠን መንገድ የያዘውን ሥልጣን ለህዝብ አይለቅም።
እንግዲህ ምን ይሻላል ?
ህወሃቶች ኑና እንወዳደር ብለዋል። እነዚህ ቡድኖች ኑና እንወዳደር ሲሉ እነርሱ የብረት ቦክስ ጨብጠው፤ ሌሎቹ ደግሞ ሌጣቸውን ሁነው ያለ በቂ ታዛቢ እንዲፎካከሯቸው ወስነው ነው። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሁነንም ቢሆን የምንወዳደረው ለነፃነት መሆን ይኖርበታል። ከነፃነት በመለስ ያለው ማንኛውም ዓይነት የምርጫ ውጤት በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ዝሪፊያ፤ ዘረኝነት፤ እሥራት እና ግድያ ያስቆማል የሚል ዕምነት በማንም ዘንድ ያለ አይመስለንም። በምርጫ ውድድር የምናተርፈው የህግ የበላይነት፤ እኩልነት እና ነፃነት ካልሆነ ተጎጂው ሰፊው ህዝብ ይሆናል።
ህወሃት የብረት ቦክስ ጨብጦ እኛ ደግሞ ሌጣችንን ሁነን መወዳደር ፍትሃዊ አይደለም በማለት ድምፃቸውን እያሰሙ ያሉት ወገኖችም የህዝብን መሠረታዊ ፍላጎት ለሟሟላት አስፈላጊ የሆነው ነፃነት ዋነኛው ግባቸው መሆን ስለሚኖርበት ይመስለናል። ወደ ውድድር ከመግባታችን በፊት ህወሃት የብረት ቦክሱን ያውልቅ፤ የመወዳደሪያ መድረኩም እኩል ይሁን ማለታቸው የሚሰማ ቢኖር ፍትሃዊ ጥያቄ ነው።የህወሃትን የብረት ቦክስ ለማስወለቅ መሥዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውም ለነፃነት የሚከፈል ዋጋ ይሆናል። ከህወሃት ጭካኔና ድንቁርና ስንነሳ በዚህ መንገድ የሚሄዱት የሚከፍሉት መሥዋዕትነት ከባድ እንደሚሆን እንጠብቃለን። ግን ደግሞ ነፃነት ያለ መሥዋዕትነት እንደማይገኝ ሌላው ቀርቶ ነፃነትን የማያውቁት ህወሃቶች ያውቃሉ። በማንኛውም መልኩ ከህወሃቶች ጋር አገት ለአንገት ተናንቀው በአገር ቤት ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ድርጅቶች ልበ ሙሉነታቸውን እጅግ አድርገን እናደንቃለን። እምቢ ለነፃነቴ፤ እምቢ ለክብሬ፤ እምቢ ለህወሃቶች ቀይ መስመር ማለት ይሄ እንጂ ሌላ አይደለም። እንግዲህ ዘረኞቹና ዘራፊዎቹ ቡድኖች ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ ማሰብ ተገቢ ይሆናል። ህዝቡ በልዩ ልዩ ሰንሰለት የታሠረ በመሆኑም በሚፈለገው መጠን ወጥቶ የትግሉ አካል ካልሆነም ተስፋ መቁረጥ አይገባም።በተጀመረው ላይ ይበልጥ እያጠናከሩና እየጨመሩ እየተካሄደ ያለውን ትግል መቀጠል ምርጫ የሌለው ሥራ ነው።
ግንቦት ሰባት የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አገር ቤት ሁነው ከጭካኔ በቀር ሌላ ዕውቀት ከሌላቸው ህወሃቶች ጋር በትግል ላይ ያሉ ድርጅቶችን ያደንቃል። ያመስግንማል። በርቱ ከማለት በቀር የምንለው ሌላ የለንም።
እኛ የጀመርነውን ሁለ ግብ ትግል እያጠናከርነው ነው። የአገራችንን ውርደት፤ የወገኖቻችንን ጉስቁልና እያየን ዝም ብንል እርግማን ይሁንብን ያሉ ወጣቶች የአያቶቻቸውን ጋሻና ጦር አንስተዋል። እናቶችም ልጆቻቸውን መርቀው ፋኖ ተሠማራ ብለዋል። ሌሎች ደግሞ የኋላ ደጀን ሁነው ሳያቅማሙ ቁመዋል። ብዙ ባለሙያዎች ለአገራቸው የሚከፈልውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጀተዋል።
እንግዲህ የጀመርነውን ትግል የሚያስቆመን ምድራዊ ኃይል የለም። የህወሃት የመረጃ መረብ ይበጣጠሳል። የጦር ኃይሉ ከጥቂት ዘረኞችና ሌቦች ይልቅ ወገኑን እንደሚመርጥ በየቀኑ የሚደርሱን መረጃዎች ያሳዩናል። የከተማው ህዝብ ህወሃቶችን አክ እንትፍ ካላቸው ብዙ ዘመን ሁኖታል። የገጠሩም ህዝብ የህወሃት ዋሻ የመሆኑ ነገር አብቅቷል። ይሄ ሁሉ የእኛ አቅማችን ነው። ይሄን አቅም አደራጅተንና ሥራ አሲይዘን አገራችንን ነፃ የምናወጣበት ግዜ ሩቅ አይደለም።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

No comments:

Post a Comment