Thursday, 23 October 2014

“እኔ ብቻ” ቢያክሙት የማይሽር የወያኔ በሽታ

 

ዘረኝነት፤ ጎጠኝነትና ዕብሪት የወያኔ አዲሰ ባህሪያት ሳይሆኑ አስራ ሰባት አመት ጫካ ዉስጥ በቆየባቸዉ አመታትና ዛሬም ከጫካ ወጥቶ አገር እየመራ በቆየባቸዉ ሃያ ሦስት አመታት አብረዉት የኖሩ መታወቂያ ካርዶቹ ናቸዉ። ዘረኝነት፤ አማራ ጥላቻና የትግራይ ሪፓብሊክ ህልም ዋና ዋናዎቹን የወያኔ መሪዎች ደደቢት በረሃ ከገቡ በኋላ በድንገት የለከፋቸዉ በሽታ ሳይሆን ከና ከልጅነታቸዉ ተጠናዉቷቸዉ አብሯቸዉ ያደገ በሽታ ነዉ። ወያኔ ጨካኝ ነዉ፤ ወያኔ ዉሸታም ነዉ፤ወያኔ ከሃዲ ነዉ፤ ወያኔ ለኢትዮጵያ ዳርድንበርና የግዛት አንድነት ደንታ የሌለዉ ባዕድ አካል ነዉ። እነዚህ ሁሉ የወያኔን ማንነትና ምንነት በትክክል የሚገልጹ የወያኔ በሽታዎች ናቸዉ። በዛሬዉ ቆይታችን በልዩ መነጽር አብረን የምንመለከተዉ የወያኔ በሽታ ግን በአይነቱ ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት በሽታዎቸ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም በጠባይና በአገላለጽ ግን ለየት ያለ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለአመታት እንዳየዉም ሆነ ሀወሓትን መስረተዉ ለስልጣን ያበቁትና ህወሓት ለእነሱም አልበጅ ብሏቸዉ ጥለዉት የወጡት ግለሰቦች በቃልም በጽሁፍም እንደነገሩን ወያኔ የጫካ ዉስጥ ጠባዩን ዛሬም ያልለቀቀ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዛሬማ ጭራሽ ብሶበት ያየዉን ነገር ሁሉ ነጥቆ የራሱ ካላደረገዉ ወይም ሙሉ ለሙሉ ካልተቆጣጠረዉ አርፎ የማይተኛ ድርጅት ሆኗል። ብዙዎቻችን የወያኔ ስም በተነሳ ቁጥር ትዝ የሚለን ዘረኝነቱ ነዉ። በእርግጥም ወያኔ ግለሰብንና ግለሰቦችን ወይም የተለያዩ ቡድኖችን በዘር መነጽር ብቻ የሚመለከት ዘረኛ ድርጅት ነዉ። ሆኖም ወያኔንና ወያኔ የፈጠረዉን ዘረኛ ስርዐት ለመደምሰስ የሚደረገዉ ትግል የወያኔን ዘረኛ ገጽታ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የወያኔ ገጽታዎች ማጋለጥና መዋጋት አስፈላጊ ነዉ። ለምሳሌ ወያኔ በፕሮፓጋንዳዉ ይዋጋናል፤ በዲፕሎማሲ ዘርፍ ይዋጋናል፤ በማህበራዊ ሜዲያዉ ዘርፍ ለተሳዳቢዎች ገንዘብ እየከፈለ ይዋጋናል፤ ከዚህ በተጨማሪ በቁጥጥሩ ስር ባደረጋቸዉ ፍርድ ቤቶች፤ ፖሊስ፤ መከላከያና የደህንነት ተቋሞች አማካይነትም ይዋጋናል። አዎ ! ወያኔ በቁጥጥሩ ስር ባደረጋቸዉ ተቋሞች አማካይነት እንቅልፉን ትቶ ቀንና ማታ ይዋጋናል። ዉድ አድማጮቻችን እቺን ወያኔ በቁጥጥሩ ስር ባደረጋቸዉ ተቋሞች አማካይነት ይዋጋናል የምትለዋን አባባል ጠበቅ ያደረግነዉ አለምክንያት አይደለም። ዛሬ ብዙ የምናወራዉ ስለዚሁ “ሁሉን ነገር መቆጣጠር” ስለሚለዉ የወያኔ አባዜ ነዉ።
በወያኔ የበላይነት የተጻፈዉ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት – የኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረሰቦች፤ ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸዉ ይላል። ሆኖም የዚህ ሉዓላዊነት መገለጫ በሆነዉ ፓርላማ ዉስጥ 38 መቀመጫዎች ብቻ ያለዉ ህወሓት 509 መቀመጫዎች ያላቸዉን ከትግራይ ዉጭ ያሉትን ሌሎቹን የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች የፖለቲካ ህይወት ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል። የሚገርመዉ ወያኔ የሚቆጣጠረዉ የኢትዮጵያን ህዝብ የፖለቲካ ህይወት ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያን የኤኮኖሚና የማህበራዊ ዘርፎችም ሙሉ በሙሉ በወያኔ ቁጥጥር ስር የወደቁ ናቸዉ። በአጠቃላይ ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ በዬትኛዉም ዘርፍ ከላይ እስከታች እሱ የማይቆጣጠረዉ ምንም ነገር እንዲኖር አይፈለግም። ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ዉሰጥ በወያኔና በሁለቱ ግዙፍ የአገራችን ሐይማኖቶች መካከል ለአመታት የዘለቀዉ ንትርክ፤ አተካሮና ፍጥጫም የዚሁ የወያኔ ሁሉንም ነገር እኔ ብቻ ካልተቆጣጠርኩት የሚል ክፉ አባዜ ዉጤት ነዉ።
የወያኔ “እኔ ብቻ” አባዜ አዲስ አበባ ገብቶ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የተጀመረ አዲስ እብደት ሳይሆን ወያኔ ገና በረሃ ዉስጥ እያለም ሰፊዉን የትግራይ ጫካ እኔ ብቻ ካልተቆጣጠርኩት የሚል በሽተኛ ድርጅት ነበር። ይህ ደግሞ ወያኔን ስለምንቃወመዉ ብቻ የምንለዉ ተራ ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን ወያኔን ፈጥረዉ ለዛሬዉ ሥልጣን ካበቁትና ዛሬ የወያኔ አካሄድ አንገሽግሿቸዉ ይህንን ድርጀት በአይናችን አናይም ብለዉ ከማሉ የትግራይ ተወላጆች አንደበት የወጣ ሐቅ ነዉ። እነዚህ የወያኔን ታሪክ የተረኩልን ወይም በመጽሐፍ ጽፈዉ ያስነበቡን ግለሰቦች ወያኔ አንዳንድ እንደነሱ ጫካ ገብተዉ ትግል የጀመሩ የትግራይ ድርጅት መሪዎችን ለስብሰባ ጠርቶ ማታ በተኙበት ቦታ አንገታቸዉን እንዳረደ ሳይደብቁ ነግረዉናል። ወያኔ የትግራይን ጫካና በረሃ ብቻዬን ካልተቆጣጠርኩ በሚል ከኢዲህና ከኢህአፓ ጋር በተከታታይ ደም የተቃባ ድርጅት ነዉ። በተለይ ኢህአፓዎችን የትግራይ መሬት የናንተ አይደለምና ለቅቃችሁ ካልወጣችሁ እያለ ዛሬም ድረስ በየቦታዉ የሚጠቀምበትን “ክልሉን ለቅቃችሁ ዉጡ” የሚለዉን የዘረኝነት ፓሊሲዉን ገና ከጧቱ በረሃ ዉስጥ እያለ አሳይቶናል።
ወያኔ የትጥቅ ትግል ጀምሮ ጫካ ዉስጥ በቆየባቸዉ ግዜዎች ሁሉ ያሳየዉ ጠባይና አንዳንድ የወሰዳቸዉ እርምጃዎች ዛሬም ድረስ አብዛኛዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ ያጋቡና ዛሬም ድረስ መልስ ያልተኘላቸዉ እንቆቅልሾች ናቸዉ። ለምሳሌ ለህዝብ መብት፤ ነጻነትና እኩልነት እታገላለሁ ባዩ ወያኔ የሱን የመሰለ ተመሳሳይ አላማ የነበራቸዉን ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ህልዉናቸዉ እስኪጠፋ ድረስ በመሳሪያ ጭምር ተፋልሟቸዋል። በወቅቱ መሳሪያ አንግበዉ ለኤርትራ ህዝብ ነጻነት ይታገሉ የነበሩትን ጀብሃንና ከሻዕቢያን በተለይ ሻዕቢያን ግን ልክ እንደፈጣሪዉ ተመልክቶ ለፈጠሪ አምላክ ብቻ የሚሰጠዉን ስግደትና ማደግደግ ለሻዕቢያ ካለምንም ይሉኝታ ሰጥቷል። በትጥቅ ትግሉ ዘመን በነበረዉ የወያኔና የሻዕቢያ ግንኙነት የወያኔ መሪዎች ከሻዕቢያ ጋር ባልተስማሙባቸዉ ግዜዎቸም ቢሆን ወያኔ ሻዕቢያን እንደ ጌታዉ ማየቱንና ለሻዕቢያ መታዘዙን ያቆመበት አንድም ግዜ እንዳልነበረ ዛሬ በወቅቱ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የነበሩ ግለሰቦች በቁጭት የሚናገሩት ሐቅ ነዉ። የወያኔና የሻዕቢያ አላማ ተመሳሳይ እንዳልነበረ ለሁሉም ሰዉ ግልፅ ይመስለናል። ከሁለቱ የለየላቸዉ ከሀዲዎች ከመለስ ዜናዊና ከስብሀት ነጋ ዉጭ የአብዛኛዉ የህወሓት መሪና አባል አላማ የትግራይ ህዝብ መብትና ነጻነት በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ዉስጥ ተከብሮ እንዲኖር ነዉ። የጀብሀና የሻዕቢያ አላማ ግን ከዚህ ፍጹም የተለየ ነበር። ሆኖም ወያኔ ከሱ ጋር ተመሳሳይ አላማ ያላቸዉን ሌሎች ኢትዮጵያዉያን ድርጅቶች እየወጋ ለየት ያለ አላማ ላለዉ ሻዕቢያ ግን እጁን ሰጥቶ በወዶ ገባነት የኖረ ድርጅት ነዉ። ባጠቃላይ የአገራችን የክርስትና እምነት መሠረት በሆነችዉ ትግራይ ዉስጥ ተወልደዉ ያደጉት የወያኔ መሪዎች ሻዕቢያን እንዳምላካቸዉ ስለሚያዩ አጠጋባቸዉ ካለችዉ አክሱም ፅዮን ይልቅ ኤርትራ ድረስ እየሄዱ ለሻዕቢያ እንደ ታቦት ጎንበስ ብለዉ ሰግደዋል። ዛሬ እነዚህ የሻዕቢያ የእልፍኝ ዉስጥ ተላላኪዎችና ሻዕቢያ እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ማደጎ ልጅ ያሳደጋቸዉ ከሃዲዎቹ የወያኔ መሪዎች ናቸዉ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነጸነት፤ እከኩልነትና ሰላም የሚታገሉ ድርጅቶችን ከሻዕቢያ ጋር ይሰራሉ እያሉ ክስ የሚያቀርቡት። ደንቆሮዎቹ የወያኔ መሪዎች ምንም ነገር ስለማይገባቸዉ ነዉ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱ ሆን ብለዉ በቆፈሩት ጉድጓድ ዉስጥ ገብቶ ቁም ስቅሉን እያየ ነዉ። የዚህ ህዝብ ፍላጎት ከዚህ የምድር ላይ ገሀነም ከሆነ ጉድጓድ ዉስጥ መዉጣት ብቻ ነዉ። በሻዕቢያ በኩል ይዉጣ፤ በኬንያ ወይም በጂቡቲ በወያኔ እሳት የሚለበለበዉ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደዚህ አይነቱን የቅንጦት ምርጫ ለማስተናገድ ግዜም ትዕግስትም የለዉም።
ወያኔ በ1983 ዓም አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ የሽግግር መንግስት ሲያቋቁም ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ከሆነባቸዉ ነገሮች አንዱ የሽግግር መንግስቱን የማቋቋሚያ ሂደትም ሆነ በሚቋቋመዉ የሽግግር መንግስት ዉስጥ የሚወሰኑ ዉሳኔዎች ሁሉ በወያኔ ሙሉ ቁጥጥር ስር የሚወሰኑ ዉሳኔዎች መሆናቸዉን ማረጋገጥ ነበር። ለዚህ ነዉ የትግራይን ህዝብ ሰባትና ስምንት ግዜ እጥፍ የሚበልጠዉን የኦሮሞን ህዝብ እወክላለሁ የሚለዉ ኦነግ ገና ከጥዋቱ የሽግግር መንግስቱን ዘፈንና ጭፈራ ከተመለከተ በኋላ “ከዚህስ ጎመን በጤና” ብሎ ሁለተኛ ዙር የትጥቅ ትግሉን የጀመረዉ። በሽግግር መንግስቱ ዉስጥ ህገመንግቱን ማርቀቅን፤ የፌዴራል ስርዐት ማቋቋምንና የክልል አመሰራረትን ጨምሮ የሽግግር መንግስቱንና ከዚያም በኋላ የተፈጠረዉን የዉሸት መንግስት ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ሁሉንም ስራ የሰራዉ ህወሐት ብቻ ነዉ፤ ሌሎቹ ከአጃቢነት ዉጭ ሌላ ምንም አይነት የጎላ ሚና አልነበራቸዉም።
በኢትዮጵያ የሙያ ማህበራት ታሪክ ዉስጥ ረጂም ታሪክና ጉልህ የአስተባባሪነትና የህዝባዊ ትግል መሪነት ሚና የነበራቸዉ ሁለቱ አንጋፋ የሙያ ማህበራት የኢትዮያ ሰራተኞች ማህበር (ኢሰማ) እና የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር (ኢመማ) ነበሩ። እነዚህ ሁለት የሙያ ማህበራት ዛሬም መኖራቸዉ ጥርጥር ዉስጥ እስኪገባ ድረስ ደብዛቸዉ የጠፋዉ ወያኔ ሁለቱንም ማህበራት በቁጥጥሩ ስር በማድረጉ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በማቆጥቆጥ ላይ የነበሩ የሲቪክ ማህበራትና የዲሞክራሲ ግንባታ ተቋሞች ከዉጭ አገር ምንጮች እርዳታ እንዳያገኙ በማድረግ እነዚህ ተቋማት ወይ በወያኔ ቁጥጥር ስር እንዲደራጁ አለዚያም እንዲጠፉ አድርጓል። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ወያኔ እንቅስቃሴያቸዉን ብቻ ሳይሆን ህልዉናቸዉን ጭምር ሙሉ በሙሉ የማይቆጣጠር ምንም አይነት ህዝባዊ ተቋማት ወይም የሙያ ማህበራት የሉም።
ወያኔ ቄስ፤ ሼክ፤ መምህር፤ አሰልጣኝ፤ የአገር መሪ፤ ነጋዴ ወዘተ ሁሉንም ነገር መሆን የሚፈልግ ብቻ ሳይሆን መሆን የማይችለዉን ካልሆንኩ እያለ አገር የሚያበላሽ ችኮ ድርጅት ነዉ። ወያኔ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ከቤ/ክርስቲያን ህግና ደንብ ዉጭ የተሾመ ጳጳስ እያለ የራሱን ታጣቂ ጳጳስ የሾመ ዉግዝ ከመአሪዮስ የሆነ ድርጅት ነዉ። ወያኔ የክርስቲያን ተቋሞችን መቆጣጠሩ አልበቃ ብሎት ፊቱን ወደ መጂሊስ አዙሮ የእስላምና እምነት ተከታዮችንም ከእምነታቸዉ ዉጭ እምነት ካልሰጠኋችሁ ወይም ካልተቆጣጠርኳችሁ እያለ ያስቸገረ እኩይ ድርጅት ነዉ። ዛሬ ወያኔ ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር የገባዉ ከፍተኛ ቅራኔና በጥቁር ህዝብ ታሪክ ዉስጥ በጥንታዊነቷ የምትታወቀዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን ህጋዊዉ ሲኖዶስና የወያኔ ሲኖዶስ ተብላ ለሁለት የተከፈለችዉ ወያኔ የሙስሊሞቹን መጅሊስና እቺን ጥንታዊት ቤ/ክርስቲያን ለመቆጣጠር እጅግ በጣም ፀያፍ የሆነ እርምጃ በመዉሰዱ ነዉ።
ኢትዮጵያ ዉስጥ የሐይማኖት ነጻነት ተረጋገጠ ብሎ የነገረን ወያኔ ባጳጳስ ላይ ጳጳስ ሾሞ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን የተቆጣጠረዉ ገና በጧቱ ነበር። ወያኔ ጳጳስ ብሎ የሾማቸዉ የአድዋዉ ተወላጅ አባ ጳዉሎስ ጳጳስ ሆነዉ ባገለገሉባቸዉ አመታት ሁሉ ወገባቸዉን ባጭር ታጥቀዉ ያገለገሉት የሰማዩን አባታቸዉን ሳይሆን የአድዋዉን ወንድማቸዉን መለስ ዜናዊን ነዉ። ፍርድ የማይሳነዉ እግዚአብሄርም ይህንን ምህረት የማይገባዉ በደል ተመልክቶ ነዉ እነዚህን ሁለት አመጸኞች መንፈቅ በማይሞላ ግዜ ዉስጥ ተራ በተራ የወሰዳቸዉ። ወያኔ አይናቸዉ ገንዘብና ንብረት ካየ በፍጹም አርፈዉ የማይተኙ ስግብግቦች ስብሰብ ቢሆንም የኢተዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያንን ይቆጣጠራል ወይም ተቆጣጠረ ስንል ወያኔ የሚቆጣጠረዉ የቤ/ክርስቲያኒቱን ገንዘብና ንብረት አይደለም፤ ይልቁንም ወያኔ በቅርብ የሚቆጣጠረዉ የቤ/ክርስቲያኒቱን ዋና ዋና ዉሳኔዎችና ቤ/ክርስቲያንቱ በማህበረሰቡ ላይ ማድረስ የምትችለዉን ተፅዕኖ ነዉ። ዛሬ ወያኔ “ማህበረ ቅዱሳን” በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን ስር የተደራጁ የእምነታቸዉ ቀናተኞችን ዉስጣችሁ ካልገባሁ እያለ የሚያዉካቸዉ አብሯቸዉ ፈጣሪን ለማምለክ ሳይሆን ያንን ሁሉንም ነገር ካልተቆጣጠርኩ የሚለዉን አባዜዉንና ስስቱን ለማርካት ሲል ብቻ ነዉ።
የሚገርመዉ ወያኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ከሱ ቁጥጥር ዉጭ ሲተነፍስም ደስ ስለማይለዉ አንድ ለአምስት የሚባል የኮሚኒስቶች አደረጃጃት ይዞ መጥቶ ወጣቶችን፤ ሴቶችን፤ ሰራተኞችን፤ ገበሬዎችንና መምህራንን በአንድ ለአምስት አደራጅቶ አንዱ ስለሌላዉ በየቀኑ መረጃ እንዲሰበስብና ለበላይ አካላት እንዲያሳዉቅ አድርጓል። ስለሆንም ይህንን የወያኔን “እኔ ብቻ” የሚል አባዜ ከስሩ መንግሎ ለመጣል ብቸኛዉ መንገድ ወያኔን እራሱን በተባበረ ክንድ መንግሎ መጣል ነዉ እንጂ ዋልድባ፤ መጅሊስ፤ ወይም ማህበረ ቅዱሳን እያልን በተናጠል የምናደርገዉ ትግል ዋጋ የለዉም፤ ወይም ወያኔ ወደ እያንዳንዳችን አናት ላይ እስኪወጣ መጠበቅ የለብንም። ወያኔ ሌሎችን ሲያጠቃ “እኛ የለንበትም” ብለን ቁጭ ብለን እየተመለከትን የወያኔ ዱላ እኛጋ ሲደርስ የምናሰማዉ የድረሱልኝ ጩኸት ሰሚ አያገኝም – ማግኘትም የለበትም። የወያኔን ዘረኝነትና “እኔ ብቻ” የሚያሰኝ ክፉ በሽታ ለማጥፋት ብቸኛዉ መንገድ ወያኔንና ስርዐቱን በህዝባዊ ትግል ገርስሶ መጣል ብቻ ነዉ፤ ህዝባዊ ትግል ደግሞ መቀራረብን፤ መከባበርን፤ መተሳሰብን፤ አንድነትንና ትብብርን ይጠይቃል። እንግዲህ እንደ ትናንቱ ሁሉ የዛሬዉም ጥሪያችን ኑና ወያኔን በተባበረ ክንድ እንጣል የሚል ነዉ።

 
 
 
 
 
 
 

No comments:

Post a Comment