Friday, 26 February 2016

ጭፍጨፋውን ለማስቆም ሆ ብሎ መነሳት ብቸኛው መፍትሄ ነው !

 
February 26, 2016   
def-thumbየዛሬ 79 አመት ባህር አቋርጦ ድንበር ተሻግሮ የመጣው የጣሊያን ፋሽስት ሠራዊት በአዲስ አበባ ነዋሪ ወገኖቻችን ላይ ከፈጸመው ዘግናኝ የጭፍጨፋ እርምጃ የማይተናነስ እልቂት፣ ዛሬም በኦሮሞ ወገናችን ላይ በአገር በቀል የህወሃት አልሞ ተኳሽ የአጋዚ ጦር ሠራዊት እየተፈጸመ ይገኛል።
የካቲት 12 ቀን 1929፣ በሮዶልፎ ግራዚያኒ ትዕዛዝ የአዲስ አበባን ነዋሪ ሕዝብ በደም ጎርፍ ባጥለቀለቀው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ህጻናት፣ ጎልማሶች ፣ ሽማግሌዎች፣ አሮጊቶች፤ ነፍሰጡሮች፣ ለጋ ወጣቶች፣ በአጭሩ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሁሉ ዘራቸው ፣ ሃይማኖታቸውና ጾታቸው ሳይለይ በጅምላ በመታረዳቸው፣ ደማቸው በስድስት ኪሎ አደባባይ እንደ ወራጅ ወንዝ መፍሰሱን፣ ታሪክ ጊዜ በማያደበዝዘው ብዕሩ መዝግቦት ይገኛል። የግራዚያኒ ጦር በወገኖቻችን ላይ ያንን አሰቃቂ እልቂት የፈጸመው ለነጻነታቸው ቀናይ የሆኑት ሞገስ አስግዶምና አብረሃ ደቦጭን የመሳሰሉ ጀግኖች ኢትዮጵያኖች፣ የጣሊያንን ቅኝ አገዛዝ በመቃወም በጠላት ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ለመበቀልና በጠመንጃ ሃይል የአገሪቱን ህዝቦች በባርነት ቀንበር ሥር አውሎ ሃብትና ንብረት ለመዝረፍ በማለም ነበር።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነ የመጣው በፋሽስት ጣሊያንና ለጠባብ የቡድንና የግል ጥቅም የመንግሥትን ሥልጣን የሙጥኝ ባለው ህወሃት መካከል ያለው ልዩነት አንዱ ባዕድ ወራሪ ሌላኛው አገር በቀል ከመሆን ያለፈ አይደለም። ጣሊያን የኢትዮጵያን ማዕከላዊ ሥልጣን የፈለገው ለአገሩ ኢንዱስትሪ የሚሆን ጥሬ የተፈጥሮ ሃብት ፍለጋ ሲሆን፣ ህወሃት ደግሞ የአገሪቱን ለም መሬት በርካሽ ዋጋ ለባዕድ በመቸብቸብ ጭምር ባለሥልጣናቱና የጥቅም ተጋሪዎቹ ሃብት እንዲያካብቱ ከማድረግ የዘለለ ራዕይ ኖሮት እንዳልሆነ በበርካታ ተግባሮቹ አስመስክሯል።
ወያኔ አጋዚ የሚባል ልዩ ጦር አሰልጥኖና አስታጥቆ ከህዝብ የሚነሳን ተቃውሞና እሮሮ ለመጨፍለቅ የሚወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ፣ መነሻው ለዘረፋ መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀምበትን በትረ ስልጣን ለመከላከል እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ አካባቢ የተጀመረውን ህዝባዊ ተቃውሞ በሃይል ለመጨፍለቅ የህወሃት ልዩ ቅልብ ጦር በህዝባችን ላይ እየወሰደ ያለው ጭፍጨፋ የፋሺስት ግራዚያን ጦር አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ላይ የዛሬ 79 አመት ከፈጸመው የሚለየው በሟቹች ቁጥር እና በገዳዮቹ ማንነት ብቻ ነው። የአጋዚን ጦር አሰልጥኖና አስታጥቆ በገዛ ወገኑ ላይ ፣ እንደባዕድ ሠራዊት፣ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ እንዲፈጽም ያሰማራው ህወሃትም ሆነ ከአለቆቹ የተሰጠውን ትዕዛዝ በፍጹም ታማኝነት ተቀብሎ በገዛ ወገኖቹ ላይ ታሪክ ይቅር የማይል ወንጀል በመፈጸም ላይ የሚገኘው ይህ ሠራዊት፣ ላለፉት 25 አመታት ያልአግባብ ያፈሰሰው ደምና የቀጠፈው ወገኖቻችን ህይወት ቁጥር ለመቁጠር እያዳገተ መጥቷል።
በተለያዩ ጊዜዎች በኦጋዴን፤ በጋምቤላ፤ በቤኔሻንጉል፤ በአፋር፤ በአማራና ደቡብ አካባቢዎች ከደረሰው የግድያ ፍጅት በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመደፍጠጥ የአጋዚ ጦር ከአለቆቹ በተሰጠው ትዕዛዝ የጨፈጨፋቸው ዜጎች ቁጥር ከ300 በላይ ደርሷል:: ቁጥሩ ከዚህ በእጥፍ የሚበልጥ ቁስለኛና ከ8 ሺህ በላይ እስረኞችም እንዳሉ ገለልተኛ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየተናገሩ ነው። በአልሞ ተኳሾች ህይወታቸው ከተቀጠፉት መሃል ዕድሜያቸው ገና 8ና 9 አመት የልበለጣቸው ታዳጊዎች፤ አሮጊቶችና እርጉዝ ሴቶች ይገኛሉ። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአምቦ ከተማ በደረሰው ጥቃት የ9 አመት ታዳጊ ህጻንን ግንባር አነጣጥሮ የመታው የአጋዚ ጦር፣ ወንድሟን ከወደቀበት ለማንሳት ጎንበስ ያለቺውን እህቱን በሌላ ጥይት በመምታት ቤተሰቦቿንና የከተማውን ህዝብ የመረረ ሃዘን ውስጥ ጥሏል፤ ተመሳሳይ ግድያ በአሰላ ከተማ ውስጥ በምትኖር የ8 ዓመት ታዳጊ ላይም ተደግሟል።
በሴቶችና በህጻናት ላይ ጥይት የሚያስተኩስ የአውሬነት ባህሪ ከየትኛው ባህላችን የመጣ ነው? ይህንን አሰቃቂ ድርጊት የተመለከተ ወይም የሰማ ሰው እንዴት አድርጎ ነው ሠራዊቱንና አዛዦቹን ከአብራኩ የተገኘ የአገሩ ዜጋ አድርጎ ማሰብ የሚችለው? የዚህ አይነት አሰቃ ድርጊት ዛሬ የጀመረ ሳይሆን በድህረ ምርጫ 97 በአዲስ አበባና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥም ተፈጽሟል። በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ በወቅቱ ከተማዋን ወሮ የነበረው የአጋዚ ጦር ያገኘውን ሁሉ በጥይትና በቆመጥ ሲያዋክብ፣ ሠይድ የተባለ የ10 አመት ልጅ የጨርቅ ኳሱን ከመሬት አንስቶ ለመሮጥ ሲንደረደር አናቱን በጥይት ተመቶ እስከወዲያኛው አሸልቦአል። በስተርጅናቸው ይጦሩኛል ብለው መርካቶ ውስጥ ሽንኩርት በመቸረቸር ሁለት ልጆቻቸውን ተቸግረው ያሳደጉ የእነ ፍቃዱ እናት በአጋዚ ጥይት ሁለቱንም በአንድ ጀንበር ተነጥቀዋል:: ምንም ጥፋት እንዳላጠፋ እየመሰከሩ ባላቸውን ከእስር ለመታደግ የሞከሩ የልጆች እናት ወ/ሮ እቴነሽ ሴት ልጆቻቸው ፊት በጥይት ተገድለው ቤተሰብ የተገደሉበትን ጥይት ዋጋ ከፍሎ አስከሬን አንዲወስድ ተደርጓል። የ14 አመቱ ነብዩ አለማየሁም ባንክ ልትዘርፍ ነበር ተብሎ በግፍ ተገድሏል። ያ እሮሮ ያ ጩኸት ወያኔ ሥልጣን ላይ እስካለ ብቻ ሳይሆን እስከ ወዲያኛውም ከህሊናችን አይጠፋም። ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ የድህረ ምርጫ 97 አይነቱ ጭፍጨፋ አሁንም የኦሮሚያ ከተሞችንንና መንደሮችን እያዳረሰ ነው። “እናቴን ለምን ገደላችሁብኝ” ያለ ወጣት ደምቢዶሎ ውስጥ በጠራራ ጸሃይ ህዝብ ፊት ተረሽኗል፤ ምንም አይነት መሣሪያ ያልታጠቁ እናትና ልጅ በአንድ ቀን በአንድ ጀንበር በግፈኞች ጥይት ለህልፈት በቅተዋል፤ በደኖ ውስጥ ፍሮምሳ አብዲ የተባለ የ10 አመት ታዳጊና ወላጅ እናቱም እንዲሁ። ምስራቅ ሃራርጌ ውስጥ ደረታቸው ላይ በተተኮሰ ጥይት ህይወታቸውን ያጡት የ60 አመቷ አዛውንት አዴ ጁሃራ ሙሳንና የሌሎች ሰለባዎችን ፎቶግራፍ በማህበራዊ ድህረ ገጽ የተመለከትን ሁሉ ልባችን በሃዘን ተወግቶአል ፤ በቁጭትም በግኗል። በመቻራ፤ በነገሌ፤ በነቀምት፤ በኮፈሌ፤ በመንዲ፤ በሆሮ ጉዱሩ፡ በቦቆጂ፤ በአሰላ፤ በሮቤ፤ በጎባ፤ በመቱ ወዘተ በየቀኑ እየፈሰሰ ባለው ደም ምክንያት ተመሳሳይ ለቅሶ ተመሳሳይ ዋይታ የአገራችንን ምድር እያናወጠ ነው። ይህ አረሜኔያዊ ጭፍጨፋ የዕለት ተዕለት በሆነበት ሰሞን ባለፈው ሰኞ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የኦሮሚኛ ፕሮግራም ቃለመጠይቅ የሰጠው ጌታቸው ረዳ፡ በገዛ ወገኑ ላይ እንዲህ አይነት ዘግናኝ እርምጃ እየወሰደ ያለውን የአጋዚ ጦር “በመልካም ሥነምግባር የታነጸና ህዝባዊ ወገናዊነቱን ያረጋገጠ” በማለት ሲያሞካሸው ተሰምቷል። ከሶስት አራት ቀን ቆይታ ቦኋላ ደግሞ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በኦሮሚያ ያለው እንቅስቃሴ “የመንግሥትን ሥልጣን በሃይል ለመንጠቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ ስለሆነ የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል” ሲል በቴለቪዢን መስኮት ብቅ ብሎ ዝቷል። ታዳጊ ህጻናትንና እርጉዝ ሴቶችን ግንባር አልሞ የሚመታ ሃይል ከማሰማራትና ህዝብ ከማስጨፍጨፍ የበለጠ ምን አይነት የማይዳግም እርምጃ ለመውሰድ ህወሃት እንደተዘጋጀ ሃይለማሪያም ደሳለኝ እራሱ የሚያውቅ አይመስለንም። ህዝባዊ ተቃውሞ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ታንክና መትሬየስ እየተተራመሰ እየተመለከትን የማያዳግም እርምጃ የሚሉን እንደ ባህሪ አባታቸው ፋሽስት ጣሊያን የመርዝ ጭስ ከአየር የሚለቅ አይሮፕላን ለማሰማራት ፈልገው ይሆን ? ወቅቱ ፈቀደም አልፈቀደ ወያኔ ሥልጣኑን ለመከላከል ይጠቅማል ብሎ እስካመነ ድረስ የማይወስደው የጭካኔ እርምጃ ይኖራል ብሎ ማሰብ ቢያዳግትም፣ እንደ ሁለተኛው የአለም ጦርነት የመርዝ ጭስ በመጠቀም ሥልጣን ላይ ተደላድሎ መቀመጥ እንደማይቻል የመረዳት አቅም ያለው ወያኔ ውስጥ አለ ብሎ መዘናጋት አያስፈልግም።
በህዝብና በአገር ሃብት ጠንካራ ሠራዊት ገንብቶ ህዝብ እየገደለ፤ እያፈናቀለና እያሰደደ እስከወዲያኛው ሥልጣን መቆጣጠር የቻለ መንግሥት በታሪክ አይታወቅም። የወያኔም መንግስት የመጀመሪያው ሊሆን አይችልም:: የግራዚያኒ ቁራጭ የዛሬው ጥቁር ፋሽስት ወያኔ እራሱን የተለየ ጠንካራ አድርጎ የሚቆጥረው የአለም አምባገነኖችን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የአገራችንን የቀደምቶቹን አወዳደቅ ታሪክ እንኳ መለስ ብሎ ለመመልከት ባለመቻሉ ነው። በጠመንጃ ሃይል በአንድ ወቅት በአንድ ቦታ የሚነሳውን ወይም የተነሳውን ተቃውሞ ማዳከም ወይም መቆጣጠር ይቻል ይሆናል። አፍኖና ነጻነት ገፎ ሥልጣን ላይ ተደላድሎ ለረጅም ጊዜ መኖር ግን በፍጹም እንደማይቻል ወያኔ እራሱ ካካሄደው የጸረ ደርግ ትግል መማር ነበረበት:: ባለመማሩም የራሱን የወደፊት ዕጣ ከቀድሞው የዩጎዝላቪያ ፕሬዝደንት ስሎባዳን ሚሎሶቪችና የአይቬርኮስቱ ሎሬንት ባግቦ ተርታ እያሰለፈ ነው:: ሁለቱም በየአገራቸው ባደራጁትና በሚመሩት ሠራዊት ተማምነው በአገርና በህዝብ ላይ ለፈጸሙት ወንጀል በመጨረሻቸው አፍንጫቸውን ተሰንገው አለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተወረውረዋል:: የአገር መከላኪያ ጦር ዋና አላማና ተግባር የአገርን አንድነትና ሉአላዊነት ከባዕድ ወረራ መከላከል ነው። ወያኔ እየገዛት ባለችው አገራችን ግን እየሆነ ያለው በሠላም አስከባሪነት ሥም ለወያኔ መሪዎችና የጦር ጀነራሎች በውጪ ምንዛሪ ገቢ የሚያስገኝ ድንበር ዘለል ግዳጅ ተግባር ላይ መሠማራት ወይም የገዛ ወገንን መግደልና ማሠር ሆኗል:: ይህ አካሄድ በአስቸኳይ መቆም አለበት:: የወያኔን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ሲባል የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተቀብሎ ህዝብ መጨፍጨፍ፤ ማቁሰልና ማሰር የፍርድ ቀን ሲመጣ “ታዝዤ ነው” በሚል ከተጠያቂነት ነጻ የማያደርግ ወንጀል መሆኑን ሁሉም ሊያውቅ ይገባል:: አሁን በኦሮሚያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ ህዝብ በመፍጀት ለወያኔ ግዳይ ጥሎ የመሸለም አባዜ የተጠናወታቸው አዛዦች ካሉ ቆም ብለው
ማሰብና ከድርጊታቸው መታቀብ ያለባቸውም ከታሪክና ከህግ ፍርድ እራሳቸውን ለማዳን ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 በኦሮሚያ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ ለማስቆም ሁላችንም ሆ ብለን መነሳት፤ አምርረን በመታገል ይህን እጅግ ጨካኝ ዘረኛ ስርአት በማስወገድ ወንጀለኞቹን ለህግ ማቅረብ መቻል ይኖርብናል ብሎ ያምናል:: አባቶቻችን በፋሽስት ጣሊያን ጦር የተሰነዘረብንን ወረራና ጥቃት ለማክሸፍ ሆ ብለው በህብረት እንደዘመቱት ሁሉ፣ ይህ የኛ ትውልድም አገራችንንና ህዝባችንን ለከፋ መከራ የዳረገውን የወያኔ አገዛዝ ከላያችን አሽቀንጥሮ ለመጣል በህብረት መነሳትና መዝመት ያለብን ግዜው አሁን ነው።
በወያኔ ከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ምክንያት በፍርሃትና በጥርጣሬ መተያየታችን የአገዛዙን ጡንቻ አፈርጥሞታል። አንዱ ሲጠቃ ሌላው ዝም ማለቱን ከቀጠለ ሁላችንም በየተራ ተደቁሰን በባርነት ቀንበር ሥር ስንማቅቅ እንኖራለን። ይህ እንዳይሆን የፈለገ ሁሉ ዛሬውኑ በኦሮሚያ እየተቀጣጠለ ያለውን የነጻነት ትግል ይቀላቀል። ከአሁን ጀምሮ አንዱ ሲደማ የሌላው ከዳር ሆኖ ተመልካችነት ማብቃት ይኖርበታል። አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔን ጭፍጨፋ ለማስቆምና አገራችን ውስጥ ሠላም ፍትህና እኩልነት እንዲሰፍን የሚያካሂደውን ትግል ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለው ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲቀላቀሉት የትግል ጥሪውን በድጋሚ አጠናክሮ ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

Tuesday, 23 February 2016

የቆሰለው አውሬ አገራችንን ይበልጥ ሳያቆስል በጊዜ እንነሳ!

   
February 20, 2016 More
def-thumbየንቅናቄያችን ሊቀመንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ ተገኝተው ለኢትዮጵያውያን ባደረጉት ንግግር ወያኔ የቆሰለ አውሬ ሆኗል ብለው ነበር። ፕ/ር ብርሃኑ በንግግራቸው፣ የቆሰለ አውሬ በህይወት ለመቆየት ሲል ያለ የሌለውን ሃይል በመጠቀም ጥቃት በሰነዘረበት ግለሰብ ላይ የበቀል እርምጃ ከመውሰድ ወደ ሁዋላ የማይል በመሆኑ፣ ጥቃቱን ለመከላከል በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበው ነበር። አውሬነት የጭካኔ ደረጃንና ሁዋላቀርነትን የሚያሳይ ገላጭ ቃል ነው፤ አውሬነት ወያኔ በህዝባችን ላይ ለሚፈጽመው ግፍ ጥሩ ወካይ ቃል ነው፤ ነገር ግን ወያኔ ከአውሬ አልፎ የቆሰለ አውሬ ሆኗል፤ አደገኛነቱም ጨምሯል።
ፕ/ር ብርሃኑ በትክክል እንዳሉት የወያኔ የጥቃት ኢላማዎች ወያኔን የሚታገሉት የነጻነት ሃይሎች ብቻ አይሆኑም። መላው የአገራችን ህዝብ በቆሰለው አውሬ ከመጎዳት አያመልጥም። በነፍስ ግቢና ውጪ መካከል የሚገኘው የቆሰለው አውሬ አፈር ልሶ ከቁስለቱ አገግሞ እንዳይነሳ ጥፋቱን እየተከላከሉ፣ ሞቱ የሚፋጠንበትን መንገድ መቀየስ ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል። የቆሰለ አውሬ ወዳጅ ጠላት መለየት የማይችል፣ ፊት ለፊት ባገኘው ላይ ሁሉ እርምጃ ለመወሰድ የሚንደፋደፍ በመሆኑ፣ ሁሉም ዜጋ የጥቃት ጥፎሮቹ እሱም ላይ እንደሚያርፉ በመገንዘብ አውሬውን ለማጥፋት መረባረብ ይኖርበታል።
ሰሞኑን በኦሮሚያ አካባቢ እየተቀጣጠለ በመጣው ህዝባዊ እምቢተኝነት ወደ ከርሰ መቃብር እየተገፈተረ መሆኑ የገባውና የቆሰለ አውሬነት ባህሪውን በይፋ ማሳየት የጀመረው ይህ የወያኔ አገዛዝ አጥፍቶ ለመጥፋት አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት፡ አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር በማጋጨት የመፈራገጥ እርምጃውን ተያይዞታል:: ተጨማሪ ጊዜና እድል ከተሰጠውም ሌሎች ከዚህ የከፉ ድርጊቶችንም ሊፈጽም እንደሚችል ልብ ማለት ያሻል። ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ፍንዳታዎችን ሲያካሄድ የነበረ አገዛዝ ወደዚያ ልማዱ ተመልሶ ጉዳት ለማድረስ ወደኋላ የማይመለስ ብቻ ሳይሆን ተሰሚነት አላቸው የሚባሉትን ወይም ከሌላ ብሄረሰብ የሆኑትን በማስገደል በቀል ሊያስነሳ የሚችል ግጭት ሊቀሰቅስ እንደሚችል ይጠበቃል:: በኦሮምያና ተቃውሞ በሚያይልባቸው ሌሎች አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ህዝቡን በርሃብ ከመቅጣትም ወደ ኋላ የመለሳል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል:: ማምሻም እድሜ ነው እንደሚባለው ወያኔ ህዝባችንን በማጋጨት እስትንፋሱን ለአንድ ቀን የሚያረዝም እስከመሰለው ድረስ የሚችለውን ሰይጣናዊ መንገዶች ሁሉ ከመሞከር የማይታቀብ ፍጡር መሆኑ ጥርጣሬ ውስጥ የሚገባ አይደለም:: ይህ ሁሉ ሙከራ ከከሸፈበትና እንደማያዋጣው ከተረዳ በዘረፋና በሙስና የሰበሰበውን ሃብትና ንብረት ማሸሹን አጠናክሮ ይገፋበታል።
አርበኞች ግንቦት7 በ11ኛው ሰአት የሚገኘውን የቆሰለውን አውሬ ጥፋት ለመቀነስም ሆነ ግብዓተ መሬቱን ለማፋጠን ፣ በወታደራዊው እና በህዝባዊ እምቢተኝነቱ መስኮች ተግቶ እየሰራ ነው። ንቅናቄው ሁኔታዎችን ሁሉ አጥንቶ ተስማሚ ሆኖ ባገኘበት ሰዓት በቆሰለው አውሬ ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ ለኢትዮጵያ ህዝብ በተደጋጋሚ ገልጿል። ንቅናቄያችን አገራችንን ከቆሰለው አውሬ ቁጥጥር ሙሉ በሙሉ ካላቀቀ በሁዋላ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መክሮና ዘክሮ የሚገነባት የነጻነትና የእኩልነት አገር እንዲኖረን ለማስቻል አቅም የፈቀደለትን ሁሉ ከማድረግ ለአፍታም ቢሆን ወደ ኋላ እንደማይል ፣ የንቅናቄው ሊቀመንበር እና የመላው አባላቱ ተወካዮች በቅርቡ ባካሄዱዋቸው ጉባኤዎች በድጋሜ አረጋግጠዋል።
በአገር ቤትና በውጪ የሚኖረው ህዝባችንም በበኩሉ ይህ የቆሰለ አውሬ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ለማክሸፍ ከዚህ የሚከተሉትን እርምጃዎች እንደአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ መውሰድ ይኖርበታል።
1ኛ. በየቀኑ የሚካሄዱ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ትኩረት ሰጥቶ መከታተልና መረጃ መሰብሰብ:: ያገኛቸውንም መረጃዎች ወዲያውኑ ለመገናኛ ብዙሃን ማቀበል
2ኛ. የቆሰለው አውሬ አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት፣ አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር ለማጋጨት የሚያደርገውን ጥረት ማክሸፍንና ፣ ማጋለጥ።
3ኛ. ለዚህ እኩይ ስራ የሚሰለፉ ሃይሎችን ማስጠንቀቅ፣ ማጋለጥና እንደ አስፈላጊነቱ ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ።
4ኛ. በየአካባቢው የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ትንሽ ትልቅ ሳይባል መቀላቀል። በተለይ የወያኔ የነርቭ ማእከል ናቸው በሚባሉት ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰድ።
5ኛ. የወያኔን አገዛዝ ለመለወጥ በትግል ላይ ያሉ ድርጅቶችን በማቴሪያል፣ በገንዘብና በማንኛውም ነገር መርዳት።
6ኛ. በሁለገብ ትግሉ እየተሳተፉ ያሉ ሃይሎችን በአካል መቀላቀል፣ ካልተቻለም መረጃ በማቀበል ማገዝ።
7ኛ. ወያኔ በመካከላችን የዘረጋውን የልዩነት አጥር በማፍረስ ጥርጣሬና አለመተማመን እንዳይኖር ማድረግ፡ እያንዳንዱ ለሁሉም ሁሉም ለያንዳንዱ ወገናዊነቱን መግለጽ፤ የጎንዮሽ ሽኩቻዎችን ማቆምና የፖለቲካ መስመር ልዩነቶቻችንን ለማጥበብ ዝግጁ መሆን።
8ኛ. የእርስ በርስ ትብብርን ማጠናከር አንዱ ሲጎዳ ሌላው እያከመ፣ ሁሉም ተቃውሞውን በየአቅጣጫው መጀመር።
አርበኞች ግንቦት7 እንደቆሰለ አውሬ መፈራገጥ የጀመረው የወያኔ አገዛዝ በአገራችንና በህዝባችን ላይ ሊያደርስ የሚችለው አደጋ እንዲቀንስና ድህሬ ወያኔ የህዝቦቿን አንድነት በእኩልነት የምታረጋግጥ የተረጋጋች ፣ ሰላምና ብልጽግና የሰፈነባት አገር ለመመሥረት ከሚሹ የአገሪቱ ልጆች ሁሉ ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ የነጻነት ቀን እንደሚያቃርብ እርግጠኛ ነው ።
የወያኔን የሥልጣን እድሜ ለማሳጠር ሁላችንም ለተግባራዊ ትግል ዛሬውኑ ታጥቀን በቆራጥነት እንነሳ!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
አርበኞች ግንቦት7

በህወሓት አገዛዝ ቁጥጥር ስር የሚገኘው አየር ኃይል አብራሪ የነበረው አብዮት ማንጉዳይ ከ10 ዓመታት እስር በኋላ በረሃ ወርዶ አርበኞች ግንቦት 7ን ተቀላቀለ፡፡

February 1, 2016 
(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ)
በህወሓት አገዛዝ ቁጥጥር ስር የሚገኘው አየር ኃይል አብራሪ የነበረው አብዮት ማንጉዳይ ከ10 ዓመታት እስር በኋላ በረሃ ወርዶ አርበኞች ግንቦት 7ን ተቀላቀለ፡፡
በ1997 ዓ.ም የተደረገው ምርጫ ውጤት መጭበርበሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ አመፅ በኃይል ለመድፈቅ የህወሓት አገዛዝ አየር ኃይሉን ለመጠቀም በተጠንቀቅ እንዲቆም ማዘዙን በመቃወም ኤም.አይ-35 ተዋጊ ሄሊኮፕተር ይዞ ከአንድ ሌላ ጓደኛው ጋር ወደ ጅቡቲ የኮበለለው አብዮት ማንጉዳይ በጅቡቲ መንግስት አማካኝነት ተላልፎ በመሰጠቱ ነበር ለእስር የበቃው፡፡
አብዮት በህወሓት ደህንነቶች እጅ እንደወደቀ ክስ ተመስርቶበት ለፍርድ ሳይቀርብ በድሬ ደዋና በሌሎች ስውር ማሰቃያ ስፍራዎች እጅግ በጣም ዘግናኝና አስከፊ የሆነ ሰቆቃ ተፈፅሞበታል፡፡
አብዮት ማንጉዳይ በረሃ ወርዶ አርበኞች ግንቦት 7 እያፋፋመው የሚገኘውን የአርበኝነት ጎራ ነፍጥ ጨብጦ ለመቀላቀል አሁን በስልጠና ላይ ይገኛል፡፡

Tuesday, 9 February 2016

የህዝባችን እንባ ለማቆም ሁላችንም አምርረን እንታገል !


January 29, 2016  
def-thumbኢትዮጵያ አገራችን ከፍተኛ የሆነ የህልውና ስጋት ተደቅኖባታል። ልጆቿ በያቅጣጫው ዋይታቸውን እያሰሙ ነው። የወያኔ የተበላሸ ስርዓት እና የስግብግብነት ተፈጥሮ ተደማምረው ህዝባችንን በቃላት ሊገለጽ በማይቻል ሰቆቃ ውስጥ ከተውታል። ህሊና ይዘው መፈጠራቸው ጥያቄ ውስጥ እስከሚገባ ድረስ፣ ቅልብ የወያኔ ገዳይ ወታደሮች በኦሮሞ እናቶችና ህጻናት ላይ የፈጸሙት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በረጅሙ ታሪካችን ያላየነውና ያልሰማነው ነው። ባለፉት መንግስታት ለነጻነታቸው የጮሁ ወጣቶች በስርዓቱ የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው ታሪክ የመዘገበው ሃቅ ነው፣ ነገር ግን ህጻናትና ታዳጊዎች እጅግ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ግንባራቸውንና ደረታቸውን በጥይት እየተመቱ ሲወድቁ ስንመለከት ይህ በታሪካችን የመጀመሪያ ነው። አለም በፍጥነት እየተለወጠ ባለበት በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መወሰዱ ደግሞ የአገዛዙ ቁንጮዎችንና እነሱን ተከትለው ወደ ጥፋት አረንቋ የሚተሙትን ሁሉ ከሰው መፈጠራቸውን እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው። የኦሮሞ ህዝብ በአጋዚ ወታደሮችና በፌደራል ፖሊሶች በግፍ ለተነጠቀው ልጆቹ ድምጹን ከፍ አድርጎ አልቅሷል፤ ቁጭቱን በቻለው መንገድ ሁሉ ሊገልጸው ሞክሯል። ነገር ግን እስካሁኗ ሰአት ድረስ መገደሉ፣ መታሰሩ፣ መሰደዱ፣ መዋረዱ አለቆመም። አገዛዙ ለአንድ ቀን በስልጣን ላይ ውሎ እስካደረ ድረስ ይኸው ግፍ ይቀጥላል።
የወልቃይት ህዝብ እኛ እንደፈለግን እንጅ አንተ እንደፈለክ አትኖርም ተብሎ ተፈርዶበት ያለፉትን 25 ዓመታት በስቃይ አሳልፏል። አሁንም እንደገና ” እኛ እናውቅልሃለን እየተባለ” መከራውን እየበላ ነው። በአካባቢው ያንዣበበው የሞት ደመና እጅግ አደገኛ ነው። እየተረጨ ያለው መርዝ ካልቆመ፣ አካባቢው በአጭር ጊዜ የግጭት አውድማ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ዘራፊው የህወሃት ቡድን ግጭትን ከማባበስ በተረፈ ችግሩን የማስቆም ፍላጎት አላሳዬም።
በዚሁ አካባቢ የአንድ አገር ሎጆችን ቅማንትና አማራ እያሉ እርስ በርስ ለመከፋፈልና ለማጋጨት ወያኔ እየዘራው ያለው ይጥፋት ዘር እስካሁን ከደረሰው እልቂት በላይ ሌላ እልቂት ይዞ እየመጣ ነው። የአገር ሰላምና ጸጥታ እናስከብራለን ብለው መሳሪያ የታጠቁ ሃይሎች በሁለቱም ወገን ግጭት ለመቀስቀስ ሲዶልቱ፣ ሲያቅራሩና ሲሸልሉ ውለው እያደሩ ነው። ከዚህ ሁሉ የእልቂት ጀርባ ያሉት ዜጎችን ካላጋጩ ውለው ማደር የማይችሉት የወያኔ መሪዎችና ግብረአበሮቹ ናቸው።
የደቡብ ህዝብም ልጆቹን በሞት እየተነጠቀ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቹም በየእስር ቤቱ ታጉረዋል፡፡ ዛሬ ወደ ኮንሶ፣ አርባምንጭ፣ ቁጫ፣ ሃመር ወዘተ ብንሄድ የምንሰማው ዋይታና ለቅሶ ነው።
የሶማሌው ወገናችን በልዩ ሃይል አባላት የዘረ ፍጅት እየተፈጸመበት ነው፤ አፋሩ ፣ ጋምቤላውና ቤንሻንጉሉ ከቀየው እየተፈናቀለ፣ መሬቱን እየተነጠቀ ለሞትና ለዘላለማዊ ድህነት ተዳርጓል።
ይሄ ሁሉ መከራና ግፍ ሳያንስ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ህዝባችን በረሃብ እየተጠቃ መሆኑ በሰፊው እየተነገረ ነው። በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በተፈጥሮ በሚሳበብ የአየር መዛባት ችግር ምክንያት ባለፈው የምርት ዘመን የተዘራው ሰብል እንዳለ ወድሞአል:: በዚህም የተነሳ በህዝባችን ላይ ያንዣበበው የረሃብ አደጋ እስከዛሬ ካየነው ሁሉ የከፋ እንደሚሆን አለማቀፍ ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ነው። ላለፉት 10 አመታት በእጥፍ አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቤያለሁ እያለ ህዝብ ሲያደነቁርና የለጋሽ አገሮችን ቀልብ ለመሳብ ሲባዝን የኖረው ወያኔ ግን በፈጠራ ታሪክ የገነባው ገጽታ እንዳይበላሽበት ረሀቡን ለመደበቅና የጉዳት መጠኑን ለማሳነስ ብዙ ርቀት ተጉዟል። ያም ሆኖ የችግሩ ግዝፈት እያየለ ሲመጣና ተጎጂዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደየ አጎራባች ከተሞች መሸሽ ሲጀምሩ ሳይወድ በግድ ለማመን ተገዷል። ። በሰሜን ወሎ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በደቡብና በኦሮምያ በድርቁ ምክንያት በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ የሚገኙ እናቶችና ህጻናት ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም፣ ወያኔ ግን እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ እዚህም ላይ የቁጥር ጨዋታ በመያዙ አሁንም ተገቢው እርዳታ ለህዝባችን በጊዜ እንዳይደርስ እየተከላከለ ለህዝብ መከራ ደንትቢስነቱንና ጨካኝነቱን እያሳየ ይገኛል።
ወያኔ በህዝባችን ላይ የደገሰው የሞት ድግስ በዚህ ብቻ አያበቃም። የኑሮ ውድነቱ ጣሪያ በመንካቱ ህዝቡ እያንዳንዷን ቀን የሚያሳልፈው በጣርና በጭንቅ ነው፤ ከጥቂት የወያኔ ባለስልጣናትና ሸሪኮቻቸው ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ኑሮው ሲኦል ሆኖበታል። ችግሩና መከራው እየከፋ ሲሄድ እንጅ እየቀነሰ ሲሄድ አይታይም። በሚብለጨለጩና የህዝቡን መሰረታዊ የፍጆታ ችግር በማይቀርፉ ስራዎች ላይ በማትኮር ህዝብን በልማት ስም ለመሸንገል ሙከራ ቢደረግም፣ አልተሳካም። ከኑሮ ውድነት በተጨማሪ ስራ አጥነቱ፣ አፈናው ፣ ስደቱ እስርና እንግልቱ፤ ሙስናው፣ የፍትህ እጦቱ ወዘተ የአገራችን ህዝብ ኑሮውን በጉስቁል እንዲገፋ አድርጎታል።
አርበኞች ግንቦት 7 አገራችንና ህዝባችን ከዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ መውጣት የሚችለው አገዛዙ የዘረጋው የተበላሸ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎች ሲለወጡና ከህዝብ፡በህዝብ ለህዝብ የሚቆም የመንግሥት ሥርዓት በአገራችን እውን መሆን ሲችል ብቻ ነው ብሎ ያምናል:: የወያኔ የሥልጣን ዕድሜ በተራዘመ ቁጥር በህዝባችን ላይ የሚደርሰው በደልና ሰቆቃም እንዲሁ እየተራዘመ ይሄዳል:: ህዝባችን ከሚደርስበት ለቅሶና መከራ እንዲገላገል ሁላችንም በያለንበት አምርረን እንታገል::

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
አርበኞች ግንቦት7