Wednesday, 27 January 2016

የሰላምን በር ጠርቅሞ የዘጋው ወያኔ ነው


January 23, 2016   
def-thumbየወያኔ አረመኔያዊ ያገዛዝ ስርዓት በህዝባችን ላይ የሚፈጽመው አፈና ግድያና ዝርፊያ በመጠኑም በዘግናኝነቱም ይበልጥ እያገጠጠ ስለመጣ ለወትሮው እንዳላዩ አይተው የሚያልፉትን ምዕራባውያን ለጋሾቹንና ወዳጆቹን ሳይቀር በእጅጉ ማሳስብ ጀምረዋል። ወያኔ ለምዕራባውያን ደህና ሎሌ በመሆን ወንጀሌን እንዳላዩ እንዲያዩልኝ ማድረግ እችላለሁ የሚለው አካሔዱ በውንብድና ተግባሩ ለከት የለሽነትና ዘግናኝነት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ እየተሸረሸረበት ነው። ብዙዎቹ ምዕራባውያን ላለፉት ሁለት ወራት በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ የሚካሄደውን ጭፍጨፋና አፈና ለማውገዝ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
አሜሪካንን ጨምሮ የወያኔ ለጋሽ ሀገራት የሆኑት ምዕራባውያን ሰሞኑን በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ ወያኔ የከፈተውን የዕብሪት ጭፍጨፋ፣ እስራትና አፈና አስመልክቶ ችግሩን በውይይትና በስልጡን መንገድ ይፈታ ዘንድ የሚያሳስቡ ግልጽና ባንጻራዊ ደረጃ ሲታዩ ጠንከር ያሉ መግለጫዎችን አውጥተዋል። የደረሰውም ጥፋት ተመርምሮ ጥፋተኛ ወገን እንዲጠየቅ የሚጠይቁና ችግሩም በሰላምና በውይይት እንዲፈታ እየጎተጎቱ ይገኛሉ። ባለፉት በርካታ ዐመታት ምዕብራባውያኑ የወያኔ ጉጅሌ ይህንን አቅጣጫ እንዲከተል ተጽዕኖ የመፍጠር አቅማቸውን ተጠቅመው ያደረጉት በቂ ግፊት እንደሌለ ይታወቃል። የአሜሪካ መንግስትና የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገሮች ዘግይተውም ቢሆን ሀገራችን ውስጥ የተካሄደውንና እየተካሔደ ያለውን ጭፍጨፋ ማውገዛቸውና ወደፊትም በዝርዝር ተመርምሮ ተጠያቂው እንዲታወቅ ያቀረቡትን ሀሳብ እንደ በጎ ጅምር እንመለከተዋለን።
ለሀገራችንና ለህዝባችን እጣ ፋንታ የምንጨነቅና የህዝቡ ጥቃት ያንገፈገፈን የሀገሪቱ ልጆች የችግሩ የመፍትሔ መጀመሪያ ይህ በጉልበቱ ህዝባችን ላይ የተጫነ መንግስት ነኝ ባይ የግፈኞች ጥርቅም በሃይል በሚደረግ ትግል ጭምር መወገድ አለበት ወደሚለው ውሳኔ የደረስነው የሰላም በርና ጭላንጭል ሁሉ በመዘጋቱ እንደሆነ ስንገልጽ ቆይተናል ። ላለፉት ሁለት ወራት በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውና ከመቶ ሀምሳ በላይ ወገኖቻችን ያለቁበት ጭፍጨፋ እንዲሁም በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ተመሳሳይ ግድያ፣ እስራትና የተቀናቃኝን አድራሻ ደብዛ ማጥፋት እርምጃ የሚያሳየው ይህ ስርዓት የበለጠ ጥፋት ከማድረሱ በፊት በፍጥነት መወገድ ያለበት መሆኑ ላይ ያለን አቋም ለሁሉም ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መምጣቱን ነው። እንደ ወያኔ ያለ ከህዝብ የተጣላ የፖለቲካ ሀይል የፖለቲካ ጥቅምን የሚያየው ከራሱ ህልውናና ደህንነት አንጻር እንጂ ከህዝቡ ሰላም ብልጽግናና ነጻነት ወይም ከሀገሪቱ የረጅም ጊዜ እጣ ፋንታ አንጻር አይደለም። የወያኔን ገዥዎች የሚያስጨንቃቸው የህዝቡ ኑሮ ሳይሆን የራሳቸው የዝርፊያ ስርዓት ባግባቡ መጠበቅ አለመጠበቁ ነው። ለዚህ ነው ስርዓታቸውን ለመጠበቅ የነጻነት ጥያቄ ኮሽታ በሰሙ ቁጥር የሚባንኑት። ለዚህ ነው በሰላም መብቱን የጠየቃቸውን ሁሉ መደዳውንና በጭካኔ በጥይት የሚረፈርፉትና የተረፋቸውን እንደ እንስሳ ወህኒ በረት ውስጥ የሚያጉሩት።
አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔ ጸረ ህዛብና ጸረ አገር እርምጃ ሊቆም የሚችለው ላለፉት 25 አመታት ወያኔ በመካከላችን የገነባው የመከፋፈልና የልዩነት ግድግዳ ለመናድ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንዳችን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በሁላችንም ላይ እንደ ተፈጸመ ቆጥረን በጋራ ስንንቀሳቀስ ብቻ ነው ብሎ ያምናል:: ዛሬ በኦሮሚያ ወገኖቻ ላይ እየተፈጸመ ያለው ሰቆቃና ግዲያ ትናንት በጋምቤላ ፤ በኦጋዴን ፤ በአፋር፤ በቤኔሻንጉል ፤ በደቡብና በአማራ ወገኖቻችን ላይ በፈረቃ ሲፈጸም የቆየና እየተፈጸመ ያለ መከራ መሆኑን የማይገነዘብ የለም:: በፈረቃ መገደል፤ በፈረቃ ወህኒ መወርወር ፤ በፈረቃ መፈናቀል፤ በፈረቃ ለስደት መዳረግ የሁላችንም ዕድል ፈንታ ሆኖአል:: ይህንን ስቃይና መከራ ማስቆም ለፍትህና ለነጻነት የቆመ ዜጋ ሁሉ ግዴታ ነው::
ወያኔ የሰላም በሮችን በሙሉ ጠርቅሞ ሲዘጋ ለአገራቸው ጥቅም ሲሉ ዝምታን የመረጡ ምዕራባዊያን የህዝብ ብሶት ገንፍሎ አደባባይ ከወጣና ብዙዎች በአጋዚ ጦር ጨካኝ ግዲያ ህይወታቸውን ከገበሩ ቦኋላ ዘግይተውም ቢሆን መናገር መጀመራቸው መልካም ጅምር ነው:: ነገር ግን በእብሪት የተወጠሩ የወያኔ መሪዎች በባዕዳን አለቆቻቸው ቁጣ ከአቋማቸው ፍንክች ይላሉ ብሎ መጠበቅ መዘናጋት እንዳያስከትል መጠንቀቅ ተገቢ ነው::  ችግሮችን ተነጋግሮ መፍታት ትልቅ አቅምና ችሎታን የሚጠይቅ የዘመናችን ሥልጣኔ ውጤት ነው:: በጠመንጃ ተጸንሶ በጠመንጃ የተወለደው ወያኔ ለእንዲህ አይነት ዕድገትና ሥልጣኔ አልታደለም::
አርበኞች ግንቦት 7 የወያኔ ስርዓት ሊወገድ እንጂ ሊጠገን የማይችል የተበላሸ ስርዐት መሆኑን ይገነዘባል:: በመሆኑም በህዝባችንና በአገራችን ላይ የሚፈጸመውን ወንጀል ለማስቆም የጀመረውን ሁለገብ ትግል የወያኔ አገዛዝ እስኪወገድና ሠላምና ዲሞክራሲ በአገራችን እስኪሰፍን ድረስ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ለወዳጅም ለጠላትም ያረጋግጣል ::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

ኢትዮጵያ አምባገነንነትን እንቢ ትበል!!!


January 13, 2016 More
def-thumbሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ውስጥ ብቻ ከ150 በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በአማራ፣ በጋምቤላና በሶማሌ ቁጥራቸው የማይታወቅ በርካታ ወገኖቻችን ተገድለዋል፤ በሌሎችም ክልሎች ወገኖቻችን እየተገደሉ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተደብድበዋል፤ ታስረዋል። የህወሓት አገዛዝ ዜጎች መግደል፣ መደብደብና ማሰር መደበኛ ሥራው አድርጎታል።
በተለይ በኦሮሚያ ክልል እየቀጠለ ያለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት እና ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የሁላችንም ተሳትፎ የሚሻ ነው። ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ትናንሽ የገጠር ከተሞችን ሳይቀር ያዳረሰ መሆኑ የበርካታ ሕዝብ ስሜትንና ጥቅምን የሚነካ አጀንዳ በፍጥነት እንደሚሰራጭና ሕዝብን እንደሚያደራጅ አመላካች ነው። ከዚህ ሕዝባዊ ትግል በርካታ ድሎች የተገኙ ቢሆኑም ሁለቱ መሠረታዊ በመሆናቸው አጽንዖት ሊሰጣቸው ይገባል።
አንደኛ
በአለፉት ሁለት ወራት በኦሮሚያ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ አቀራርቧል። ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ሕዝብ ያልመከረበት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መቃወም ፍትሃዊ መሆኑ በሰላማዊም ሆነ በአመፅ መንገድ የህወሓትን አገዛዝ መታገል የመረጡ የዲሞክራሲ ኃይሎችን በሙሉ ያስማማ፤ በኦሮሞና በአማራ ማኅበረሰብ መካከል መልካም የሆነ መግባባትን የፈጠረ መሆኑ ትልቅ ድል ነው። ይህ ማለት ግን አፍራሽ ጽንፈኛ አስተያየቶች ከወዲህም ከወዲያም መወርወራቸው ቀረ ማለት አይደለም፤ ያም ሆኖ ግን በሕዝቡና በፓለቲካ ልሂቃኑ መካከል ያለው መናበብ ከቀድሞው በጣም በተሻለ ሁኔታ መገኘቱ ተስፋ ሰጪ ነው። ይህንን ድል ማስከንና አድማሱን ማስፋት ያስፈልጋል። በተለይም የነፃነት ትግሉ አካል የሆኑትን የትግራይ ወገኖቻችንን ማቀፍ እና ህወሓትን ከትግራይ ሕዝብ መነጠል ያስፈልጋል። ወደ ህወሓት የሚወረወሩ ፍላፃዎች ወደ ትግራይ ሕዝብ የተወረወሩ መስለው እንዳይታዩ በንግግሮቻችንና ጽሁፎቻችን ሁሉ ግልጽ ማድረግ ይኖርብናል። ሶማሌን፣ አፋርን፣ ሲዳማን እና ሌሎችን ማኅበረሰቦችን በተመለከተ ተመሳሳይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ወሳኝ ወቅት በማኅበረሰቦች መካከል እየተፈጠረ ያለው መግባባትን የሚቀለብስ ወይም ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገባ አንዳችም ተግባር እንዳይፈፀም ነቅቶ መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው። ይህ ትግል፣ እስካዛሬ አጥተነው የነበረው የኢትዮጵያውያንን ማኅበረሰብ መቀራረብን አምጥቶልናል፤ በሚገባ ከተጠቀምንበት ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን የመገንባት አቅማችንን በከፍተኛ ሁኔታ ያጠነክርልናል። ስለሆነም፣ ከግራ እና ቀኝ በሚወረወሩ ዘረኛ አስተያየቶች እና ተግባራት ይህንን ስሜት ለማደፍረስ የሚጥሩትን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል።
ሁለተኛ
ከእንግዲህ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተፈፃሚ ማድረግ አይቻልም፤ አስፈፃሚም የለውም። ይህ አንድ ትልቅ ድል ነው፤ ሆኖም ህወሓት የአገዛዙ ወንበር ላይ እስካለ ድረስ ይህ ድል መሠረታዊ የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ አያመጣም። እስከ አሁን ከአንድ መቶ አምሳ በላይ ዜጎች ተገለውብናል፤ የሟቾች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረም ነው። ገዳዮች በመግደላቸው ሲሸለሙ እንጂ ሲጠየቁ አላየንም። በግልባጩ የሟች ቤተሰቦች የጥይት ወጪ ካልከፈላችሁ አስከሬን አንሰጥም እየተባሉ ነው።
ገዳይን እየሸለመ፤ ሟችን የሚቀጣ ኋላ-ቀር ፍርደ-ገምድል ሥርዓት ማብቃት ይኖርበታል። ስለሆነም የወቅቱ ጥያቄ መላዋን ኢትዮጵያ ከህወሓት አገዛዝ ነፃ ማውጣትን ዓላማው ያደረገ መሆን ይኖርበታል። “ኦሮሚያ አምባገነንነትን እንቢኝ ብላለች!” ከሚለው መሪ መፈክር “ኢትዮጵያ አምባገነንነትን እንቢኝ ብላለች!” ወደሚለው መሪ መፈክር መሸጋገር ድላችንን ያቀርባል።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የወገኖቻችን ደም በከንቱ ፈሶ መቅረት የለበትም፤ ገዳዮች በህግ ሊጠየቁና ሊቀጡ፣ ተበዳዮች ደግሞ ሊካሱ ይገባል ብሎ ያምናል። ሆኖም ህወሓት ስልጣን ላይ ሆኖ እያለ እነዚህ ነገሮች ሊፈፀሙ ይችላሉ ብሎ አያምንም። በአርበኞች ግንቦት 7 እምነት ኢትዮጵያ አምባገነንነትን አሻፈረኝ ብላለች፤ ይህም በሕዝባዊ እምቢተኝነት እና በሕዝባዊ አመፅ እየታየ ነው። ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ሕዝባዊ አመፅ ሲደጋገፉ ባነሰ ኪሳራ አምባገነኑን አገዛዝ ከጫንቃችን ለማውረድ ያስችለናል ብሎ ያምናል። ስለሆነም ኢትዮጵያ አምባገነንነትን እምቢ ትበል!
አንድነት ኃይል ነው!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!