July 18, 2015
ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር)
ለግንቦት 9 (May 9th 2015) ስብሰባ ለውይይት የቀረበ
መግቢያ:
የወያኔ ሥርዓት ለሀገሪቱ የማይበጅ፤ አገሪቱን አደገኛ ችግር ውስጥ የከተተና የበለጠ ጊዜ እስካገኘ ድረስ የሚያመጣው መዘዝ ዘላቂና መውጫ የሌለው ምስቅልቅል ውስጥ አገሪቱን የሚከታት መሆኑን ብዙው ህዝብ ይገነዘባል ማለት ይቻላል:: ስለ ሕዝቡ በጥቅል እንኳን መናገር ባይቻል የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉና በተለይም በተቃዋሚ ድርጅቶች አካባቢ የሚገኙ ያገሪቱ ዜጎች በግልጽ የተረዱት ጉዳይ ነው:: በተለይ በቅርብ ጊዜ የወያኔ መንግሥት በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚወሰደው የጭካኔ እርምጃ (ኦሮምያ፤ አማራ፤ አፋር፤ ሶማሊ፤ ጋምቤላ፤ ሲዳማ፤ሐረሪ፤…ወዘተ) እንዲሁም ሆን ብሎ ማህበረሰቡን በዘውግ ከፋፍሎ ለማባላት የሚያደርገውን መሰሪ እንቅስቃሴ በቅርብ የሚመለከቱ በዘውግ የተደራጁ የፖለቲካ ሀይሎች ሳይቀር የወያኔ አካሄድ ለነሱም የማይበጃቸው መሆኑን በመገንዘብ የስርዓቱ እድሜ ማጠር እንዳለበት ያምናሉ፤ ምንም እንኳን ይህንን ችግር በዘውግ መሰረት ላይ የቆመ ፖለቲካ የፈጠረው መዋቅራዊ ችግር አድርገው ሳይሆን የወያኔ የተለየ አምባገነናዊ ባህርይ የፈጠረው ችግር አድርገው የሚመለከቱት ቢሆንም:: በዚህ ጉዳይ ላይ በርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አደረጃጀትና እንቅስቃሴን በሚመርጡና የሀገሪቱን ፖለቲካ በዘውግ መነጽር በሚያዩ ኃይሎች መሀከል ያለው ሰፊና መትከላዊ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ የወያኔ ሥርዓት በቶሎ መቀየር እንዳለበት ሰፊ ሀገራዊ ስምምነት አለ ማለት ይቻላል::
ሌላው ሰፊ ስምምነት ያለ የሚመስለው ደግሞ በጥቅሉ የወያኔን ሥርዓት የሚተካው ምን አይነት ሥርዓት መሆን አለበት? የሚለው ላይ ነው:: ይህ ስምምነት “ጥቅል” ነው የሚባለው ሁሉም ምትኩ ሥርዓት “ዴሞክራሲያዊ” መሆን አለበት በሚለው ላይ ከመስማማቱ ባሻገር ይህ “ዴሞክራሲያዊ” ሥርዓት በኢትዮጵያ ሁኔታ ዘላቂና የተረጋጋ ማህበረሰብን ለመፍጠር ምን ተጨባጭ መልክ ይይዛል? በሚለው ዝርዝር ላይ ስምምነት አለመኖሩን ለማመላከትና ይህ ዝርዝር ጉዳይ ደግሞ በተግባራዊ ሂደት ላይ ወሳኝ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ለማሳየት ነው:: ለምሳሌ ያክል ከላይ የተጠቀሰው: ፖለቲካው ዘውጌ መሰረት እንዲኖረው በሚፈልጉ ኃይሎችና ከዚያ ይልቅ በርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ እንዲኖር በሚፈልጉት መሀከል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚይዘውን ተጨባጭ ቅርጽ በሚመለከት ያላቸው ልዩነት ትልቅ ትርጉም ያለውና በጥንቃቄ ካልተያዘ በጣም አወዛጋቢ ሊሆን የሚችል ልዩነት ነው:: ከስሜት የጸዳ፤እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለዘላቂው መመስረትን ማዕከል ያደረገ ጠንካራ ውይይት የሚፈልግ ጉዳይ ነው:: ያም ሆኖ ግን የሚፈጠረው ሥርዓት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እነኝህን ኃይሎች አቻችሎ ይዞ መሄድ ሊኖርበት እንደሚችል መገመትና ይህም አይነት ማቻቻል በተጨባጭ ምን መልክ ይይዛል የሚለውን በጥንቃቄ ማሰብ ብልህነት ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ፖለቲካ ውስጥ ከሚሳተፉ ኃይሎች የሚጠበቅ ነው:: ይህ ጉዳይ እራሱን የቻለ ውይይት የሚፈልግ ስለሆነ ወደፊት በሰፊውና ዝርዝር ተግባራዊ እንድምታው ላይ በማተኮር እንመለስበታለን:: ለዚህ ውይይት ያክል ግን ከሽግግሩ ጋር በተያያዘ አንድ አስፈላጊ ጉዳይ ላይ ብቻ እናተኩራለን:: የሽግግሩ ተዓማኒነት ጉዳይ ላይ::
የወያኔ ሥርዓት በቶሎ መወገድ አለበት፤ ይህንንም ሥርዓት መተካት ያለበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሆን አለበት በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ስምምነት ካለ (በዝርዝሩ ላይ የሚኖሩት ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው)፤ ወዲያውኑ የሚነሳው ጥያቄ ደግሞ ታዲያ ይህን ሰፊ ስምምነት የሚያንጸባርቅ፤ ቢያንስ ይህን እምነት በኦፊሴል በሚያንጸባርቁ የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ ሰፊ ሀገራዊ የትግል መድረክ ለማዘጋጀትና በጋራ ለመታገል ለምን አስቸጋሪ ሆነ? በጋራ መታገል ባይቻል እንኳን እርስ በርስ መጠላለፉን ማስቆም ለምን አልተቻለም? የሚለው ጥያቄ ነው:: እዚህ ጉዳይ ላይ በሰፊው ሳንገባ ብዙ ጊዜ የሚቀርቡት ምክንያቶች የሚከተሉትን ይመስላሉ፤
በዘውጌ ፖለቲካ ዙሪያ በተደራጁና በሀገራዊ (ርእዮተ አለማዊ) አመለካከት ዙሪያ በተደረጁት መሀከል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመፍጠር ዙሪያ ያሉ የተለያዩ አመለካከቶች የፈጠሯቸው ያለመተማመን (አንዱ ሌላውን በእውነት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፈጠር የሚታገል መሆኑን መጠራጠር)፤
የሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ሁሌም በጉልበት ያሸነፈው አካል ፖለቲካውን በኃይል የሚቆጣጠርበት ታሪክ መሆኑና ይህም ያመጣው ያለመተማመንና የመሽቀዳደም ስሜት: (በምንም መልክ የፖለቲካ ሥልጣንን የያዘው ኃይል ከዚያ በኋላ ለሁሉም የተደላደለ የመወዳደሪያ ሜዳ ይፈጥራል ብሎ ባለማመን) ሥርዓቱ በዘላቂነት የሚመሰረትበትን መንገድ ከማሰብ ይልቅ መጀመሪያ ሥልጣን ላይ ማን ይወጣል በሚለው ላይ ያጠነጠነ መሆኑ::
የፖለቲካ ሥልጣን እያንዳንዱ ድርጅት በሕዝብ ዘንድ ባለው ተቀባይነት ወይንም ትግሉን ከዳር ለማድረስ በሚያደርገው አስተዋጽኦ መሰረት የሚደላደል (ስለዚህም በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወይንም የስራ አስተዋጽኦንና ክህሎትን ባማከለ ፍትሀዊ ክፍፍል) ሳይሆን ቢበዛ የፖለቲካ ኃይሎች የድርድር ውጤት ወይንም የጊዜው የኃይል አሰላለፍ ውጤት ነው ብሎ ከማመን የመጣ ሁሉም የራሱን ድርጅት አቁሞ ከሌሎች ጋር “በእኩልነት” ተደራድሮ እኩል የሚደለደል አድርጎ መገመት ያመጣው የድርጅቶች እንደአሸን መፍላት፤ይህ ደግሞ በበኩሉ የፈጠረው ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሌላውን አልፎ እንዳይወጣ በተቻለ መጠን የመከላከልና የማሰናከል አባዜ…ወዘተ
እነኝህንና ሌሎች መሰል ምክንያቶችን ደምረንና ቀንሰን ስናያቸው የሚያጠነጥኑት በሁለት አይነት አለመተማመኖች ላይ ነው:: የመጀመሪያው አለመተማመን ድርጅቶቹ (ከራስ ድርጅት በስተቀር) በእርግጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር ይፈልጋሉ ወይ? የሚለው መጠራጠር ሲሆን ሁለተኛውና የተያያዘው ደግሞ ባመለካከት ደረጃ ይህ ፍላጎት ቢኖራቸው እንኳን ባንድ አጋጣሚ የፖለቲካ ሥልጣንን ካገኙት በኋላ ለሁሉም እኩልና የተደላደለ ሜዳ የመፍጠር ፍላጎት ይኖራቸዋል ወይ? ያገኙትን ሥልጣን ውድድሩን አላግባብ ለማሸነፍ እንዲያስችላቸው ለራሳቸው በሚያደላ መልኩ ይጠቀሙበታል የሚለው ፍርሀት ነው:: እነኝህ ፍርሀቶች ምንም መሰረት የሌላቸው አይደሉም:: ከላይ እንደተጠቀሰው በታሪካችን የታየው ይህ ብቻ መሆኑ፤ በከፍተኛ ጥርጣሬ የተተበተበው ባህላችንና እያደር ያገዛዝ ስርዓቶች እያኮሰመኑት የሄዱት ማህበራዊ እሴታችን ሲታከልበት እንዲህ አይነት መጠራጠርና ፍርሃት ባይኖር ነበር የሚገርመው:: ስለዚህ ሂደቱ ያንን ፍርሃት በተጨባጭና አሳማኝ በሆነ መልኩ የሚቀርፍ መሆን ይገባዋል:: ከዚያም ባሻገር ግን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፈጠሩን ዋና አላማቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱና እነኝህ ፍርሀቶቻቸው ይህ ሥርዓት እንዳይፈጠር እንቅፋት ይሆናል ብለው ከልብ የሚያምኑ የዴሞክራሲ ወገንተኞች ያሉትን ያክል፤ እነሱ ሥልጣኑን እስካልያዙ ድረስ የሚኖረውን ምንም አይነት ውጤት (ሂደቱ ምንም ያክል አመርቂ ቢሆን) ኢዴሞክራሲያዊ ነው ብለው ከማጣጣል የማይመለሱ፤ ዴሞክራሲን ላፋቸው ያክል የሚናገሩት እንጂ ከልባቸው የማያምኑበት፤ የዴሞክራሲ ሳይሆን የስልጣን ወገንተኞችም በሰፊው የሚርመሰመሱበት የፖለቲካ ምህዳር ስለሆነ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱ ጠንካራ መሰረት እስከሚይዝ ድረስ እነኝህን ጥርጣሬዎች የሚቀርፍ፤ የሀገራችንን የተወሳሰበ የፖለቲካ ትርምስ ከግምት ያስገባ የሽግግር ሂደት ማሰብ በጣም አስፈላጊ ነው:: ይህን ስናስብ ግን ሁሉም ሰው የሚስማማበት ሂደት ይኖራል ከሚል የዋህነት አይደለም:: ከላይ እንደተጠቀሰው የስልጣን ተካፋይ አልሆንንም ብለው እስካሰቡ ድረስ (ለምሳሌ በምርጫ ማሸነፍ ስለማይችሉ) ምንም አይነት ሂደትን የሚያጣጥሉ ይኖራሉ:: የዚህ ሂደት ተዓማኒነት በጣም የሚያስፈልገው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ወገንተኞችን (ማለትም በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የህዝብ ውክልና ያገኘን የፖለቲካ ቡድን ማህበራዊ ተቀባይነት ወይንም ሌጂትመሲ ለመቀበል የማያቅማሙ) የሚያስማማ ሂደት እስከሆነ ድረስና ይህም በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እስከሆነ ድረስ አመርቂ ሂደት ነው ብለን ልንወስደው እንችላለን::
ስለዚህ ሽግግሩን በተመለከተ እነኝህን ጥርጣሬዎች ሊቀርፍ የሚችልና ከሽግግሩ በኋላ በምርጫ የሚፈጠረውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሙሉ ተዓማኒነት የሚያጎናጽፍ ሂደት ማሰብ ይገባናል:: ይህ ደግሞ ሶስት ደረጃዎች ያሉት ሂደት ነው:: የመጀመሪያው በሽግግሩ ወቅት የሚመሰረተውን “የሽግግር መንግሥት” ምንነት የሚወስነውና ይህ መንግሥት የህዝብ ውክልና ያለው መንግሥት እስከሚመሰረት ድረስ የሚሰራቸውን ስራዎች የሚመለከተው ነው:: ሁለተኛውና በጣም ወሳኙ ጉዳይ ደግሞ ከሽግግሩ ወቅት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሻግረውን የመጀመሪያውን ምርጫ ተዓማኒነት የሚመለከተው ነው:: ሶስተኛው ደግሞ ከሽግግሩ በኋላ የሚኖረው ሥርዓት ቅርጽን የሚመለከት ነው:: በነኝህ ጉዳዮች ላይ ግልጽ አመለካከትና አልፎም ሰፋ ያለ የፖለቲካ ሀይሎች ስምምነት መፍጠር ከተቻለ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ረጅም ጉዞና በዚህም መሰረት ዘላቂና የተረጋጋ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያለንን እድል በእጅጉ ያሰፋልናል:: እነኝህ ሶስቱም የሽግግሩ አካሎች በጣም አስፈላጊ ቢሆኑም ለዚህ ውይይት የመጀመሪያውን ክፍል በሚመለከት ያሉትን ሥራዎች (የሽግግሩ ሥርዓት እንዴት ይቋቋማልና ምን ምን ሥራዎችን ያከናውናል የሚለውን) ለግንዛቤ ያክል ብቻ አስቀምጠን ለዚህ ውይይት በሁለተኛው ጉዳይ (የመጀመሪያውን ምርጫ በሚመለከት) እና በሶስተኛው ጉዳይ ማለትም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ቅርጽ በእኔ እምነት ለምን ፕሬዜዳንታዊ መሆኑ እንደሚያስፈልግ ላይ በማተኮር አንዳንድ ለውይይት መተንኮሻ የሚሆን የመፍትሄ ሀሳብ እጠቁማለሁ:: ይህን የመፍትሄ ሀሳብ የማቀርበው በግሌ እንጂ በድርጅቱ የጸደቀ አመለካከት አይደለም:: ሀሳቡ ግን ሰፋ ያለ ማህበራዊ ተቀባይነት፤ በተለይም ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ምሁራንና የፖለቲካ ሀይሎች ዘንድ ተቀባይነት ካገኘ ድርጅቱ ባለው አሰራር መሰረት ወደፊት የድርጅቱ ቋሚ ፖሊሲ አድርጎ ሊወስደው፤ ከዚያም ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችና ከመላው ማህበረሰቡ ጋር ሊወያይበትና የጋራ አቋም እንዲሆን ሊሰራበት ይችላል:: ለአሁኑ ግን እንደ አንድ “የህዝባዊ ምሁር” ሀሳብ ብቻ ተደርጎ ይወሰድ::
የሽግግር ሥርዓቱ አፈጣጠርና የሚሰራቸው ሥራዎች
የሽግግር ሥርዓት የሚባለው አሁን ያለው ሥርዓት ወድቆ የህዝብ ሙሉ ውክልና ያገኘ፤ በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት እስከሚመሰረት ድረስ ያለውን አጭር ጊዜ የሚመለከት ነው:: ይህ ጊዜ በመሰረቱ አዲሱን ሥርዓት ለመፍጠር ዝግጅት የሚደረግበት ጊዜ ነው:: የሽግግሩ ሥርዓት በራሱ ምንም የሕዝብ ውክልና የለውም:: አፈጣጠሩም በአብዛኛው ያለፈው ሥርዓት የወደቀበት ሂደት የሚወስነው ነው:: ለምሳሌ የወያኔ ሥርዓት የሚሄድበት አካሄድ እንደማያዋጣው አውቆና በጉልበት ተገፍቶ ከወደቀ የሚደርስበትን ኪሳራ በመፍራት ይህንን ክፍያ ለመቀነስ በሚል በሀገሪቱ ካሉ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በመደራደር የሚፈጠር የሽግግር ሂደት ከሆነ የሚይዘው ቅርጽና በሂደቱም የሚሳተፉ ሃይሎች አይነት፤ ወያኔ በጉልበት በሚፋለሙት ሀይሎች ተሸንፎ ወይንም በጠንካራ ህዝባዊ እምቢተኛነት ተገፍቶ ቢወድቅ ከሚፈጠረው የሽግግር ቅርጽና የሚሳተፉት ሃይሎች አይነት ይለያል:: ይህም ሆኖ ግን ሽግግሩ በርግጥም ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግር ከሆነ በዚያ አጭር ጊዜ መሰራት ያለባቸው ቁምነገሮች በደንብ የታወቁ ናቸው:: በዚህም ምክንያት የሽግግሩ ሥርዓት ስኬት ባብዛኛው የሚለካው በሽግግሩ ውስጥ ምን አይነት ሃይሎች ናቸው የተሳተፉት በሚለው ሳይሆን (በምንም መልኩ ቢሰላ በዚህ የሽግግር ሂደት ውስጥ አልተሳተፍኩም ወይንም የሚገባኘን ሚና አልተጫወትኩም ብሎ የሚያምን የፖለቲካ ወይንም ማህበራዊ ሀይል መኖሩ የማይቀር በመሆኑ) እነኝህን ስራዎች በብቃትና የአዲስ ሥርዓት ምስረታ ዝግጅቱን ተአማኒና ሰፊ ማህበራዊ ተቀባይነት ባለው መልኩ በመስራቱ ላይ ነው:: ስለዚህ በዚህ ጽሁፍ ትኩረት የምናደርገው የሚሰሩት ስራዎች ላይ ነው:: ይህ ማለት ግን በሽግግሩ ሂደት ባሉት የሥልጣን እርከኖች የሚሳተፉት ሃይሎች ማንነትና አወቃቀሩ ምንም ትርጉም የለውም ለማለት አይደለም:: በተቻለ መጠን በሽግግሩ ወቅት የሥልጣን አወቃቀር ላይ ሰፊ የፖለቲካ ሃይሎችና ማህበራዊ ስብስቦች የሚሳተፉበት መሆኑ የሽግግሩን ወቅት ስራ የበለጠ ተዓማኒ የማድረግ እድል አለው:: ሽግግሩን የማቆም ታሪካዊ እድል ያገኙ ኃይሎች ይህን አጥብቀው ሊያስቡበት ይገባል:: ዋናው ትኩረት መሰጠት ያለበት ግን የሚሰሩትን ሥራዎችና የሚፈጠሩትን ተቋማት በርግጥም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር ሁኔታውን የሚያመቻቹ መሆኑን ማስረገጡ ላይ ነው::
1) በሽግግሩ ወቅት (ሙሉውን ጊዜ) በጊዜያዊው መንግሥት የሚሰሩ ሥራዎች
ከላይ በጥቅሉ እንደተጠቀሰው በሽግግሩ ጊዜ በዋናነት የሚሰራው አዲሱን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማዋለድ የሚሰራው ስራ ነው:: ይህ ማለት በዚህ ወቅት ምንም አዘቦታዊ (routine) የመንግሥት ሥራዎች አይሰሩም ማለት አይደለም:: በጉዳዩ ላይ ብዙ ያሰቡበት ተመራማሪዎች እንደሚስማሙበት በዚህ ወቅት በማህበረሰቡ ላይ ዘላቂ ውጤት ያለው የመንግሥት ፖሊሲ ነክ ስራ ሳይሆን በተቻለ መጠን ውጤታቸው ከሽግግሩ ጊዜ የማያልፍ ስራዎች ይሰራሉ:: በዚህ ዝርዝር ላይ ክርክር ሊኖር ቢችልም ይህ እጅግ አወዛጋቢ ስላልሆነ ብዙ ትኩረት የሚያሻው ስራ አይደለም:: ይልቁንም ትኩረት የሚያሻው አዲሱን ሥርዓት በማዋለድ ሂደት ላይ ዘላቂ እንድምታ የሚኖራቸው ጉዳዮች ላይ ስለሆነ እነሱ ላይ እናተኩር:: እነኝህ ስራዎችም በራሳቸው እርስ በርስ የተገናኙ ግን ለመረዳት እንዲመች በሁለት ከፍለን ልናያቸው የሚገቡ ስራዎች አሉ:: እነኝህም የመጀመሪያው በሽግግሩ ወቅት መሰራት ያለባቸው ለቋሚው ሥርዓት መሰረት የሚሆኑ መሰረታዊ ስምምነቶችና ተቋማት ናቸው:: ሁለተኛው ደግሞ በሽግግሩ ወቅት ማህበረሰቡን ለቋሚው ሥርዓት የሚያዘጋጁና የማህበረሰቡን ስነልቦና የሚቀርጹ ተቋማትና ስነልቦናዊ ድባብ የመፍጠሩ ስራ ነው:: እነኝህ ሁሉም ስራዎች ግን ባንድ መልኩ ወይንም በሌላ ከላይ የጠቀስኳቸውን የጥርጣሬና ያለመተማመን መንፈስ የሚሰብሩ መሆን ይገባቸዋል::
ሀ) ለቋሚው ሥርዓት የማእዘን ድንጋይ የሚሆኑ መሰረታዊ ስምምነቶችና ተቋማት
እዚህ ላይ በመጀመሪያና በዋናነት የሚጠቀሰው የቋሚውን ሥርዓት የጫወታ ሕግ የሚያስቀምጠው የሕጎቹ ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ነው:: ይህ ሰነድ ወሳኝ የሆነውን ያክል በተለይ አሁን በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎችን ሁሉ በሚያስማማ መልኩ መቅረጹ (ወይንም ያለውን ማሻሻሉ) በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው:: ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜት፤ የዛሬንና የነገን ከማሰብ ይልቅ ባለፈው ታሪክ ላይ በመንጠልጠል ደጋፊዎችን በሲቃ ስሜት (passion) ማሰባሰብን መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ልሂቃን በሚርመሰመሱበት የፖለቲካ ምህዳር፤ በረጅሙ አማትሮ የሚያይ፤ ሰፋ ያለ ማህበራዊ ስምምነት ያዘለ ሕገ መንግሥት ማዘጋጀት እጅግ ከባድና የረጅም ጊዜ ራዕይን መሬት ከረገጠ የሰጥቶ መቀበል ፖለቲካ ጋር አዋህደው መጓዝ የሚችሉ አዲስ ስርዓት አዋላጅ ዜጎችን የሚፈልግ አስቸጋሪ ስራ ነው:: ይህ ሕገ መንግሥት ምን መምሰል አለበት የሚለው ጉዳይ ላይ እዚህ ጽሁፍ ውስጥ በሰፊው አልገባበትም ግን በጥንቃቄ መሰራት ያለበት፤ በፍጹም ልንተወው የማንችለው የሽግግሩ ዋና የቤት ስራ መሆኑን ጠቅሶ ማለፍ ይበቃል:::: ከዚህ ጋር በተያያዘ በአንድ ወሳኝና የሚያስፈልገውን የመተማመን ስሜት በመፍጠር በኩል ጠቃሚ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ግን ያለኝን አመለካከት ባጭሩ እሄድበታለሁ:: ባጠቃላይ በአካሄድ ደረጃ ሊባል የሚችለው ግን ይህ ውይይት የሽግግሩ ጽንስ ከመጀመሩ በፊት ጀምሮ በሕገ መንግሥቱ ላይ ያለመስማማት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ በሚባሉት ጉዳዮች ላይ ምሁራንና የፖለቲካ ልሂቃን ካሁኑ ውይይት ቢጀምሩበት ጠቃሚ መሆኑን ነው:: ሌላው በሂደት ደረጃ የሚነሳውና እጅግ አስፈላጊ የሆነው፤ ሕገ መንግሥቱን የማዘጋጀት ሂደት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማህበረሰቡን በሙሉ በስፋት ማሳተፍ የሚችልና ቀጣይነት ያለው ነጻ ውይይት በማህበረሰቡ ውስጥ በመገናኛ ብዙሀን አማካኝነትም ሆነ በስብሰባዎች መካሄድ እንዳለበት አጽንኦት መስጠቱ ተገቢ ነው:: የዚህን ሂደት ከባድነት ስንገልጽ ግን የሚኖሩት ልዩነቶች ጠንካራ ስሜቶች የሚንጸባረቁባቸው ቢሆኑም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረትን ማዕከል እስካደረጉ ድረስ ከሚያለያዩት ጉዳዮች የሚያስማሙት የሚበልጡ መሆናቸውን ማወቅና ማመንም ተገቢ ነው::
ከተለያዩ የአህጉራችን ተመክሮዎች እንዳየነውና የወያኔ ዘመን ፖለቲካ ማንንም በማያሞኝ መልኩ ግልጽ ያደረገው አንድ ነገር ቢኖር ሕገ መንግሥት በጹሁፍ ደረጃ መኖሩና ተግባራዊ መሆኑ ፍጹም የማይገናኙ ክስተቶች መሆናቸውን ነው:: ከዚህ አንጻር ጥሩ ሕገ መንግሥት መጻፍ በጣም ቀላሉ ነገር ነው::[1] ከላይ ሕገ መንግሥትን በማርቀቅና የማሕበረሰቡን ስምምነት እንዲያገኝ ማድረግ አስቸጋሪ ነው ያልነው በእርግጥ በተግባር የመተርጎም ፍላጎቱ አለ ብለን እስካመንን ድረስ ብቻ ነው:: ይህንን ካመንን ከባዱ የሽግግር ዘመን ሥራ የሚዘጋጀውን ሕገ መንግሥት በእውነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉትን የመንግሥት ተቋማት የመፍጠርና እነኝህ ተቋማት በሕገመንግሥቱ የተሰጣቸውን ስራ ለመስራታቸው በቀናኢነት የሚጠብቁ ባለሟሎችንና ዜጎችን በመንግሥት ውስጥም ሆነ ከመንግሥት ውጭ በብዛት ማፍራት ነው:: ከዚህ አንጻር ሕገ መንግሥቱ የሚይዘው ቅርጽ ላይ ያሉ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የግድ የሚላቸውና በትክክል እንዲሰራ በጣም አስፈላጊ የሆነው የሥልጣን ክፍፍል ላይ በማተኮር በነጻነት እንዲሰሩ በጠንካራ መሰረት ላይ መቆም ያለባቸውን ዋና ዋና ተቋማት መዘርዘር እንችላለን:: ከነኝህም ውስጥ ዋናዋናዎቹ:
ፍርድ ቤቶችና ከዚያ ጋር የተያያዙ የፍትህ ተቋማት (ፖሊስ፤ የአቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት…ወዘተ)
የመከላከያና የደሕንነት አካላት ከፖለቲካ ወገንተኛነት ተላቀው ሙያዊ ስራቸውን ብቻ እንዲሰሩ ማድረግ
ከምርጫ ጋር የተያያዘ ስራ የሚሰሩ መስሪያቤቶችን ሁሉ በተግባር ገለልተኛ ማድረግ (ይህ ጉዳይ በተለይ ከሽግግሩ ጋር የተያያዘ ስለሆነ በመፍትሄ ሀሳቡ ላይ በድጋሚ እንመለስበታለን)
በመንግሥት ባጀት የሚተዳደሩ የመገናኛ ብዙሀን ከስራ አስፈጻሚ አካሉ ነጻ በሆነ አካል ስር እንዲተዳደሩ ማድረግ
በመንግሥት ባጀት የሚተዳደሩ የትምህርት ተቋማት፤ በተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአካዳሚ ነጻነታቸው በተጠበቀ መልኩ እንዲሰሩ ከስራ አስፈጻሚ አካሉ ነጻ ሆነው በቻርተር እንዲተዳደሩ ማድረግ…ወዘተ.
እነኝህና መሰል ተቋማት አዲስ የሚፈጠሩ ሳይሆኑ አሁንም ያሉ ናቸው:: አሁን የሚሰራበትንም ሕገ መንግሥት በመርገጥ ሁሉም የገዢው ፓርቲ እንደፈለገ የሚጫወትባቸው ያገዛዝ መሳሪያ ሆኑ እንጂ:: መሰረታዊ አወቃቀራቸው በሚቀረጸው ሕገ መንግሥት የሚገለጽ ቢሆንም በሽግግሩ ወቅትም የሚሰሩ ናቸው:: ስለዚህ በሽግግሩ ጊዜ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚመጥን መልኩ በተግባር እንዲሰሩ የማድረጉ ሀላፊነት የሽግግር መንግሥቱ ነው:: የሽግግር ሂደቱ ተዓማኒነት ከሚለካባቸው መስፈርቶች አንዱና ምናልባትም ዋናው በነኝህ ተቋማት ላይ በሚያደርገው ማሻሻል ስለሆነ የሽግግር መንግሥቱ ትልቅ ስራው አድርጎ የሚወስደው ነው::
በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሊነሱ የሚችሉ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሳልገባ ግን ከሚፈጠረው ሥርዓት ቅርጽ ጋር በተያያዘ (ይዘቱ ዴሞክራሲያዊ መሆኑ ላይ ስምምነት እንዳለ ተቀብዬ) በተለይ ደግሞ እንዲፈጠር አስፈላጊ ነው ያልኩት በዴሞክራሲያዊ ሀይሎች መሀል የሚኖርን መተማመን ለማጠናከርና የሚፈጠረው ሥርዓት በሂደት ጠንካራ ሀገራዊ መሰረት አንዲኖረው ስለሚረዳ ብቻ የሚፈጠረው ስርዓት ቅርጽ አሁን ካለው ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ይልቅ ፕሬዜዳንታዊ ለምን ቢሆን እንደሚመረጥ አንድ ሁለት ሀሳቦችን ላቅርብ::
ሀ_1) ፕሬዜዳንታዊ ስርዓት በኢትዮጵያ ሁኔታ ለምን ይመረጣል?
በዚህ ጉዳይ ላይ የማቀርበው አጭር አስተያየት ንድፈ ሀሳባዊ አይደለም:: ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተለያዩ ቅርጾች ቢይዝም ዴሞክራሲያዊነቱን የሚያረጋግጡት መሰረታዊ ምንነቶች ተግባራዊ እስከሆኑ ድረስ ቅርጹ በራሱ ዴሞክራሲያዊነቱን ጥያቄ ውስጥ አይከተውም:: ቅርጹን የሚወስነው ደግሞ እያንዳንዱ ሀገር ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር በሚያደርግበት ጊዜ ያለበት የራሱ ታሪካዊ፤ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ነው:: የንድፈ ሀሳብ ጉዳይ አይደለም:: በኢትዮጵያም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በምናደርገው ሽግግር ወቅት የምንመርጠው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቅርጽ አሁን ሀገራችን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ በጥንቃቄ በመገምገም የትኛው ቅርጽ ነው ልንፈጥር የምንፈልገውን ሥርዓት በተሻለ መደላደል ላይ ሊያስቀምጥልን የሚችለው የሚለውን ጥያቄ በመመለስ ነው:: ምንም እንኳን የዚህ የመጨረሻ ውሳኔ በሽግግሩ ወቅት የሚረቀቀውን ሕገ መንግሥት የሚያጸድቀው ህዝብ ቢሆንም፤ በዚያ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሀይሎችና በእውቀታቸው የማህበረሰቡን ግንዛቤ መቅረጽ የሚችሉ ምሁራን ቢያንስ የሚቀርቡትን አማራጮች ጥቅምና ጉዳት በማሳየት በኩል ትልቅ ሚና ስለሚኖራቸው ይህንን ውይይት ካሁኑ መጀመሩ ጥቅም አለው ብዬ ስለማምን ነው እዚህ ጽሁፍ ላይ ባጭሩ የማቀርበው::
ያለፉት 24 አመታት የወያኔ “የውሸት ፓርላሜንታሪ ስርዓት” ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመስረት ከምር የሚፈልጉ ሀይሎችን ሊያስተምሩ የሚገባቸው ሁለት ወሳኝ ተመክሮዎች ያሉ ይመስለኛል:: አንደኛው ሁሉም የሚያውቀው በተግባርና በንድፈ ሀሳብ መሀከል ያለው ከውቅያኖስ የሰፋ ልዩነት ነው:: ስለዴሞክራሲ መለፈፍና በተግባር ዴሞክራሲያዊ መሆን ለየቅል መሆናቸውን ያለምንም ጥርጥር በአይናችንና በኑሯችን አይተነዋል:: ሁለተኛው ትምህርት ደግሞ በንድፈ ሀሳብና በኦፊሴላዊ መዋቅር የተቀመጠን አካሄድ በተግባር ለመገርሰስ ምን ያክል ቀላል እንደሚሆንና የቅለቱ መጠን ደግሞ በስርዓቱ ቅርጽ ላይ ያሉትን ቀዳዳዎች በግልጽ ላልወጣውና ለተደበቀው እውነተኛ የፖለቲካ ሃይሎች ፍላጎት ማስፈጸሚያ ማዋል እንደሚቻል ነው:: በዚህ ሂደትም የአንድን ሥርዓት እውነተኛ ምንነት ሳይሆን ከላይ የለበሰውን የማስመሰያ ልብስ ብቻ ለማየት ለሚፈልጉ አገራዊም ሆነ ውጫዊ ሀይሎች ማማለያነት እንዴት ሊውል እንደሚችል በበቂ አይተናል:: የዚህ ክፍል ውይይት በኢትዮጵያ ሁኔታ በስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች የሚፈጠረውን መዋቅር ለጠባብ ጥቅማቸው እንዳያውሉት በትንሹም ቢሆን ለመከላከል የሥርዓቱን ቅርጽ ብዙ ቀዳዳ የሌለው እንዲሆን ለመሞከር ነው::
በተግባር በኢትዮጵያ እንደምናየው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር የማይፈልጉ ኃይሎች የፓርላሜንታዊ ሥርዓትን ለማዋከብ (abuse) ከሚያስችላቸው ቀዳዳ አንዱ በቂ የሆነና የተለያዩ የሥልጣን አካሎችን መዋቅራዊ በሆነ መልክ መለያየት የሚችል የሥልጣን ክፍፍል ያለመኖሩ ነው:: በዚህ ሁኔታ የፓርላማው አባሎች ሥልጣናቸውንም ሆነ ተግባራቸውን የሚያዩትና የሚለኩት ለሥልጣን ካበቃቸው ፓርቲ ጥቅም አንጻር ብቻ ስለሚሆንና ጠንካራ የሆነ ተቋማዊ ተአማኒነት (institutional loyalty) ስለማይኖራቸው ፓርቲው ለመረጠው (በቀጥታ በህዝብ ያልተመረጠ) ስራ አስፈጻሚ አካል ተገዢ የሚሆኑበትን ሁኔታ ይፈጥራል:: ይህ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ከስልጣን ክፍፍል ጋር የሚመጣውን የጎንዮሽ ተጠሪነት (horizontal accountability) ያዳክመዋል:: በፕሬዜዳንታዊው ቅርጽ ግን የስራ አስፈጻሚው አካል በመላው ህዝብ (ስለዚህም የመላውን ህዝብ ጥቅም ወደ ማስጠበቅ)፤ የህግ አውጭው አካል ደግሞ በያካባቢው ህዝብ ምርጫ ለየብቻቸው የሚሰየሙ መሆናቸውና (ስለዚህም ተጠሪነታቸው ለመረጣቸው አካባቢ ህዝብ) በዚህም ምክንያት የሚኖረው የተጠሪነት ልዩነት ተዓማኒነቱን ይበልጥ ወደ ተቋማዊ ተዓማኒነት እንዲያደላ ያደርገዋል የሚል እምነት አለኝ:: በዚህ ሁኔታ የሥራ አስፈጻሚውን ምርጫ ያሸነፈውና የሕግ አውጭውን ምርጫ ያሸነፈው አካል የተለያዩ ሊሆኑ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ:: ይህ ሁኔታ በስራ አስፈጻሚውና በህግ አውጭው መሀከል ብዙ ንትርክ ሊያመጣና አስተዳደሩንም ሊያዳክመው ይችላል:: ይህ ግን በራሱ መጥፎ ነገር አይደለም:: ይበልጡንም በጀማሪ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሰጥቶ መቀበል ፖለቲካ እንዲዳብር ይረዳል የሚል እምነት አለኝ::
ሁለተኛውና በተለይ በሀገራችን ሁኔታ ይህንን ቅርጽ እጅግ አስፈላጊ የሚያደርገው ባለንበት የታሪክ ሁኔታ የተፈጠረውን በዘውጌ ማንነትና በሀገራዊ ማንነት መሀከል ያለውን በቅጡ ያልተፈታ ግጭት በሂደት አገራዊ ማንነት እያደር እየተጠናከረ እንዲሄድ ያደርገዋል የሚል እምነት አለኝ:: የሀገራዊ ማንነት መጠናከር ደግሞ ለማንኛውም የሚሰራ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጣም አስፈላጊ ነው:: በፓርላሜንታዊ ሥርዓት መራጮች የሚመርጡት ያካባቢያቸውን ወኪል ብቻ ነው:: ያ ወኪል ላጠቃላይ ማህበረሰቡ የሚጠቅም መሪ ነው አይደለም በሚለው ላይ መራጩ ድምጽ የለውም:: በዋናነት ተዓማኒነቱ ለመረጠው አካባቢ ማህበረሰብ ነው:: በፓርላማው የተመረጡ ሰዎች (ብዙሀኑን መቀመጫ ያገኘው ፓርቲ ወኪሎች) በሚያደርጉት የስልጣን ድርድር ወይንም ፓርቲው በሚወስነው ውሳኔ ብቻ ነው የስራ አስፈጻሚውን ስልጣን የምትረከበው:: ስለዚህም ተዓማኒነቷ ለፓርቲዋ ወይንም ፓርላማው ውስጥ ላሉት ወኪሎች ብቻ ነው:: አጠቃላይ ማህበረሰቡን በእኩልነት ለማገልገል የገባችው ቃል ወይንም እንዴት ሁሉንም ማህበረሰብ እንደምታገለግል በዝርዝር ያስቀመጠችው ፕሮግራም (ካጠቃላይ የፓርቲው ፕሮግራም ውጭ) የላትም:: የስልጣኗ መሰረትም መላው (ወይንም አብዛኛው) ህዝብ አይደለም:: ይህ ሁኔታ እንደኛ አገር የዘውጌ ማንነት በበረታበት ሁኔታ ሀገራዊ ማንነትን የሚያጠናክርበት መንገድ የለውም:: በመላው ህዝብ የተመረጠች ፕሬዜዳንት በምትኖርበት ሁኔታ ግን በመጀመሪያ ተመራጯ ለምን ሥልጣን እየተወዳደረች እንደሆነ መላው ማህበረሰብ ያውቃል:: ህዝቡ የሚመርጠውም ለዚያ ሥልጣን ብቁ ነች አይደለችም ብሎና በዚያ መስፈርት መዝኖ ነው::[2] ሁለተኛ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር በብዙሀኑ ህዝብ ለመመረጥ የተለያዩ ዘውጌ ማህበረሰቦችን ድጋፍ ይፈልጋል:: የአንድ ዘውጌ ማህበረሰብን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ ነው ከተባለ ብዙሀኑ ሊመርጠው አይችልም:: ስለዚህም ፕሬዜዳንት የመሆን ፍላጎት ያለው ሰው ሀገሪቱን ከዘውጌዎች በላይ በሆነ ማንነት የማሰባሰብ ወይም ቢያንስ ለአንድ ዘውግ የሚያደላ አይደለም ተብሎ መታመን አለበት:: የፕሬዜዳንቱን ዕጩ የሚያቀርበው ፓርቲው እንኳን ቢሆን ፓርቲው ለፕሬዜዳንትነት የሚያቀርበው ዕጩ በመላው ሕዝብ ዘንድ ኢአድሏዊ በመሆኑ የሚታወቅ መሆኑን ከግምት ማስገባት አለበት:: ይህም በፓርቲው ውስጥም እንኳን የፖለቲካ ሥልጣን ይገባኛል የሚል ታታሪነት (ambition) ያላቸው ግለሰቦች ዘውጌያዊ ስሜታቸውን እንዲሞርዱ፤ ብሎም በሀገር ደረጃ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል:: ይህ ደግሞ ባንዴም ባይሆን በሂደት የፖለቲካ ፍላጎትና ታታሪነት ያላቸውን ሰዎች ገና ከመነሻው ከዘውግ ባሻገር እንዲያስቡ ያበረታታቸዋል የሚል እምነት አለኝ:: ይህ ደግሞ እየተጠናከረ ሲሄድ ሀገራዊ ማንነትንም እያጠናከረ ይሄዳል የሚል እምነት አለኝ::
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚነሳው አንድ አስፈላጊ ጉዳይና የሥርዓቱን ቅርጽ የሚወስነው ጉዳይ ለሥራ አስፈጻሚነት የሚመረጠው ፕሬዜዳንት በምንም ሁኔታ ከ50% በላይ የሆነውን ህዝብ ይሁንታ ያገኘ መሆኑን ማረጋገጥ ነው:: እንደሚታወቀው በጀማሪ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች የሚታወቀው አንድ ነገር ቢኖር ሥልጣን ላይ ለመውጣት ፍላጎቱና ታታሪነቱ ያላቸው ሰዎች እጥረት አለመኖሩ ነው:: በዚህ ሁኔታ ለምርጫ በእጩነት የሚቀርቡት ሰዎች ቁጥራቸው የበዛ ሊሆን ይችላል:: የዘውግ ክፍፍሉ መስመር ይዞ ጠንካራ አገራዊ ማንነት እስከሚገነባ ድረስም ለእጩነት የሚቀርቡት ሰዎች የተወሰነ የዘውግ ድጋፍ የሚያገኙ ሊሆኑ ይችላሉ:: በዚህ ጊዜ በአንድ ዙር ምርጫ ከሌላው በዛ ያለ ድምጽ ያገኘ እጩ የሚመረጥበት ሁኔታ ካለ የብዙሀኑ ድምጽ ሳያስፈልገው ምርጫውን ባብላጫ ድምጽ ብቻ የሚያሸንፍ ሊኖር ይችላል:: ይህ ደግሞ ከላይ የጠቀስኩትን የፕሬዜዳንቱን የሀገር መሪ የመሆን ተቀባይነት በእጅጉ ያዳክመዋል፤ የዘውጌ ክፍፍሉንም የበለጠ ሊያጠናክረው ይችላል:: ስለዚህ አንዱ በግልጽ መቀመጥ ያለበት ነገር በመጀመሪያ ዙር ምርጫ 50% በላይ ያገኘ እጩ ከሌለ ከፍተኛውን ድምጽ ያገኙት ሁለት እጩዎች እንደገና ለውድድር ቀርበው ከሁለቱ ከ50% በላይ ያገኘው እጩ የሚያሸንፍበትን ሂደት መከተል ያለብን ይመስለኛል:: ይህ ባንድ በኩል ከስልጣን ፍላጎት ባሻገር ለቢሮው የሚመጥን ምንም ይህ ነው የሚባል ችሎታም ሆነ ህዝባዊ ተቀባይነት የሌላቸውን ሰዎች በምርጫው ውስጥ ገብተው የውድድሩን ሂደት መጫወቻ እንዳያደርጉት ከወዲሁ ተስፋ የሚያስቆርጣቸው ሲሆን በዋናነት ግን ከላይ እንደጠቀስኩት ያለ ብዙሀኑ ድምጽ ይሁንታ በጎንዮሽ ድርድርና አሻጥር የሚገኝ ሥልጣን እንደማይኖር ምልክት ይሰጣል::
ይህን ጉዳይ በመጠኑ ያነሳሁበት ምክንያት ግልጽ ከሆነ ይበልጥ አከራካሪ ሊሆን ስለሚችለው የመጀመሪያውን ምርጫ በሚመለከት ያለኝን ሀሳብ አቅርቤ ላጠቃልል::
ለ) በሽግግሩ ወቅት ማህበረሰቡን ለቋሚው ሥርዓት የሚያዘጋጁና የማህበረሰቡን ስነልቦናዊ ድባብ የሚያዘጋጁ ሥራዎች
ሌላውና ከመጀመሪያው ባልተናነሰ አጽንኦት ተሰጥቶት የሚሰራበት የሽግግር ወቅት ስራ በሽግግሩ ሙሉ ዘመን በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲፈጠር የሚፈለገውን የስነ ልቦና ድባብ የሚቀርጹ ስራዎች ናቸው:: እነኝህ ስራዎች ገሚሶቹ ከላይ በተጠቀሱት ተቋማት የሚሰሩ ሲሆኑ ሌሎቹ መንግሥት በሚሰራቸው ሳይሆን በማይሰራቸው፤ ማህበረሰቡ ውስጥ በሚኖሩ ወይንም ሽግግሩን ተከትሎ እንደ አዲስ በሚፈጠሩ የማህበረሰቡ ተቋማት የሚሰሩ ናቸው:: እነኝህን ተቋማት አንድ ሁለት ብሎ ከመጥቀስ ይልቅ በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲፈጠር የሚፈለገውን ስነ ልቦናዊ ድባብ መግለጹና ለዚህም የሚያስፈልጉትን ሁኔታዎች ማስቀመጡ ይቀላል:: ባለፉት አርባ ግድም አመታት በኢትዮጵያ ሥልጣን የጨበጡ መንግሥታት በማህበረሰቡ ላይ ከፈጠሩት አስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱና ዋናው የማህበረሰቡን ስነ ልቦና ማኮላሸትና የሞራል መሰረቱን መናድ ነው:: ይህንን የመጠገን ሂደት መጀመር የሽግግር ወቅቱ አንድ ሥራ ነው::
ያገዛዝ ስርዓቶች ለመግዛት ከሚያስፈልጋቸው ነገር አንዱ ህብረተሰቡን በፍርሀት ቆፈን ውስጥ መክተት ነው:: እየፈሩ ስለ ሀገር የልብን መናገርና መከራከር አይቻልም:: እየፈሩ በነጻነት መምረጥ አይቻልም:: እየፈሩ የመንግሥትንና የመንግሥት ባለሟላትን ስህተቶችና ጥፋቶች ማጋለጥ አይቻልም:: በፍርሀት ማህበረሰብ ውስጥ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መሰረቶች መገንባት አይቻልም:: ስለዚህ በሽግግሩ ወቅት የመንግሥት (እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት) አንዱ ስራው ማህበረሰቡን ከዚህ የፍርሀት ቆፈን ማላቀቅ ነው:: እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት በአብዛኛው የፍርሀት ምንጭ መንግሥት ራሱ ነው:: ማህበረሰቡን ከፍርሀት ለማላቀቅ ቆርጦና አስቦ የሚሰራ መንግሥት፤ ማህበረሰቡ መንግሥትን እንዲፈራ ለረጅም ጊዜ የደረሰበትን የስነልቦና ተጽእኖ ገፍፎ በምትኩ መንግሥት የሚፈራ ሳይሆን በስራው የሚከበርበትን ሁኔታ መፍጠር አለበት:: በዚህ ዙሪያ መንግሥት ነጻ ውይይትን የሚያበረታታበት (የመንግሥት ሚዲያን በነጻነት እንዲሰራ በማድረግ)፤ ከመንግሥት ውጪ ሀላፊነት የሚሰማቸው ነጻ የህትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች በስፋት የሚሰራጩበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በነጻነት ምሁራዊ ውይይቶችን እንዲያዘጋጁ ማበረታታት፤ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ሰዎችም ሆኑ ምሁራን እነኝህን ሚዲያዎች ተጠቅመው በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ በድፍረት እንዲሳተፉ ማበረታታት፤ ማህበረሰቡ በያካባቢው በሀገሩ ጉዳይ ላይ ያለምንም ፍርሀት የሚሳተፍበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት…ወዘተ በጣም አስፈላጊ ነው::
ከዚህ ጋር የተያያዘና የማህበረሰቡን ስነ ልቡና ሊያረጋጋ የሚችል ሌላ ሥራ የብሄራዊ እርቅ ሂደት ነው:: በደርግ ሥርዓትም ሆነ በወያኔ ያገዛዝ ዘመን ብዙ በጣም ብዙ ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችና ግፎች ተፈጽመዋል:: ብዙ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል፤ አካለ ስንኩላን ሆነዋል፤ ተሰደዋል ከኑሮ ተፈናቅለዋል:: እንደ ማህበረሰብ እነኝህ ኩነቶች የስነ ልቡና ጠባሳ ፈጥረዋል:: ብዙዎቹ በደሎች ገና ቁስላቸው ያላሻረ ነው:: ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጀመር ከተፈለገና ሥርዓቱ የሚፈልገው ቀና ማህበራዊ ውይይትና ክርክር እንዲኖር ካስፈለገ ይህ ያልደረቀ ቁስል የሚያሽርበት መንገድ መፈለግ አለበት:: ይህ በተበዳዮች በኩል ትልቅ ትዕግሥት፤ ሆደ ሰፊነት፤ ይቅር ባይነት፤ በበዳዮች በኩል ደግሞ እውነተኛ ጸጸት የሚጠይቅ አስቸጋሪ ስራ ነው:: ባንድ በኩል ላለፈው ፍትህ ፍለጋ: በሌላ በኩል የወደፊቱ የመረጋጋት ፍላጎት ማህበረሰቡን ወጥረው የሚይዙት አስቸጋሪና አስጨናቂ ተግባር ነው:: ይህ በምን መልክ ይደረጋል የሚለው በራሱ የሰከነ ውይይት የሚፈልግ ነው:: ግን በሽግግሩ ወቅት መተግበር ያለበት ሥራ ነው:: ማህበረሰቡን ከፍርሃት የማላቀቅና ባዲስ መንፈስ የማስጀመሩ ስራ አንድ አካል ነው::
ማህበረሰቡን የፍርሃት ቆፈን ውስጥ የሚከተው ግን መንግሥት የሚያደርገው ድርጊት ብቻ አይደለም:: የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ሀይሎችም ካሉ በማህብረሰቡ ስነልቦና ላይ ተመሳሳይ ተጽእኖ አላቸው:: ስለዚህ ማህበረሰቡን ከፍርሀት ቆፈን የማላቀቅ አንዱ የሽግግሩ መንግሥት ስራ በሀገሪቱ ሰላምን ማስፈን ነው:: በሃሳብ ደረጃ የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ያለምንም ተጽእኖ እንዲስተናገዱ እያበረታቱ እነኝህ ክርክሮች በምንም አይነት ወደ ሀይልና “የማይስማማን አመለካከት በጉልበት የሚያፍን” ወይንም ምናልባት ለምርጫው ጊዜ ለመዘጋጀት ካሁኑ ተቀናቃኞችን የማኮላሸት አይነት አካሄድ እንዳይሻገሩ መጠበቅ በጣም ያስፈልጋል:: ይህ ብዙ ጊዜ የሚሆነው በፖለቲካ ድርጅቶችና ደጋፊዎቻቸው አካባቢ፤ በተለያዩ የሃይማኖት አክራሪ መሪዎችና ተከታዮች አካባቢ፤ የመንግሥትና የሚዲያ አይን በበቂ በሌለባቸው ቦታዎች፤ ባጠቃላይ ስሱ ስሜቶች በሚንጸባረቁባቸው ጉዳዮችና የመንግሥትን ሥልጣን ሀብት ለማካበት እንጠቀምበታለን ብለው የሚያስቡ የፖለቲካ ድዊዎች አካባቢ ስለሆነ የሽግግር መንግሥቱ የጫወታውን ሕግ ለሁሉም እኩልና ግልጽ አድርጎ ካስቀመጠና ለሕጉ ተዓማኒነቱን እራሱ በተግባር እያሳየ ለእንዲህ አይነት ግጭቶች ምንም ትዕግስት እንደሌለውና ፍጹም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ማሳየት አለበት:: በተቻለ መጠን የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ከውሸት የጸዱ፤ ምክንያታዊና የሰለጠኑ እንዲሆኑ በምሳሌነት ማሳየትና መምራት አለበት::
ፍርሃትን ከማስወገድ በተጨማሪ የማህበረሰቡን የሞራል መሰረት የመገንባት ጅማሮ (ይህ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሥራ መሆኑን ባለመርሳት) ታስቦበት መሰራት የሚጀምረውም በዚህ የሽግግር ወቅት ነው:: እንደሚታወቀው በተለይ በወያኔ ሥርዓት እጅጉን የተጎዳው የማህበረሰቡ የሞራል መሰረት ነው:: ሥርዓቱ የህብረተሰቡን ግብረገብነት የሚቀርጹትን የሃይማኖት ተቋማት ከማራከሱ ባሻገር፤ የማንኛውም ህብረተሰብ ሰላምና ዘላቂነት ዋስትና የሆኑትን ማህበራዊ እሴቶች ሆን ብሎ ንዷቸዋል:: ለዓብነት ያክል ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ እንጥቀስ:: ውሸትና ሙስና:: እነኝህ ሁለት ማህበራዊ ደዌዎች በማህበረሰባችን ዘንድ ቤታቸውን ሰርተዋል ማለት ይቻላል:: ያገዛዝ ስርዓቶች አይነተኛ መገለጫ የሆኑ፤ ውጤታቸው ግን ካገዛዝ ስርዓቱ ተጠቃሚዎችም ባለፈ የማህበረሰቡን ስነልቦና ሁሉ የሚበክልና የበከለ መሆኑን መካድ አይቻልም:: ስለዚህም እነኝህን ደዌዎች ለማከም ሰፋ ያለ የህብረተሰብ ተሳትፎን የሚጠይቅ ነው:: ይህንን ስራ ግን በተግባር በማሳየት ቀዳሚውን ሚና የሚጫወተው የሽግግሩ መንግሥት ነው:: ለምሳሌ የሽግግሩ መንግሥት ማህበረሰቡን ላለመዋሸት፤ የመንግሥት ባለሟላት በምንም አይነት አውቀው ውሸት እንዳይናገሩ፤ እንዲህ አይነት አስነዋሪ ምግባር በአድራጊዎቹ ላይ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል ማሳየት ይችላል:: የስነ ጥበብ ባለሙያዎች የውሸትን ማህበራዊ ጉዳት በሚመለከት ማህበረሰቡን የሚያስተምሩ ብዙ የኪነት ስራዎች ሊሰሩ ይችላሉ:: ትምህርት ቤቶች ወጣቶችን በዚህ ዙሪያ ማስተማር ይችላሉ…ወዘተ. ሙስናንም በተመለከተ እንደዚሁ:: የሽግግሩ መንግሥት ከሙስና የጸዳ እንዲሆን፤ ማህበረሰቡን ሙስና “ተጎጂ የሌለበት በሽታ” (victimless) ሳይሆን ጠቅላላ ማህበረሰቡን በተለይ ግን ድሆች ዜጎችን የበለጠ የሚያጠቃ፤ የማህበረሰቡን የሞራል ህልውና፤ የፖለቲካ መረጋጋትና የሚፈጠረውን ሥርዓት ይዘት ለዘላቂው የሚበክልና ያለይቅርታና ርህራሄ መዋጋት ያለብን ተውሳክ መሆኑን ማስረዳት፤ በሙሰኞች ላይ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ እየተከታተሉ ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ በምንም አይነት በሙስና መክበር እንደማይቻል ማሳየት ይገባል:: መንግሥት እንዲህ አይነት ቆራጥ አቋም መያዙ ሲታይ በመንግሥት ባለሟሎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚፈጠረው ስነልቦና ይህንን ነቀርሳ ለዘላቂው ለማስወገድ ትልቅ እርዳታ ይሰጣል:: በተለይ ከፖለቲካ ሥልጣን የሚገኝ የኢኮኖሚ ጥቅም አለ ብለው ፖለቲካውን ራሱን ለማቆሸሽ ወደኋላ የማይሉ አድርባዮችን ለመጥረግ፤ ስለዚህም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን በተሻለ የሞራል መደላደል ላይ ለማስቀመጥም ተጨማሪ እገዛ ያደርጋል:: እነኝህ በሽታዎች ባንድ ጊዜ ይነቀላሉ የሚል የዋህነት አይኖረንም:: ግን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲመሰረት የሚያስከፍሉት ኪሳራ ከፍተኛ መሆኑን በማሳየት በሽግግሩ ጊዜ የሚወሰዱት እርምጃዎች ለዘላቂ መፍትሄ መንገድ ይጠርጋሉ::
በሽግግሩ መንግሥት የስራ ዘመን የሚሰሩትን ስራዎች ለናሙና ያክል ካስቀመጥን የዚህ ውይይት ዋና ክፍል የሆነውንና የሽግግሩ ዘመን ማለቁንና ወደ ዘላቂው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሻግረንን፤ የመጀመሪያውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሚመለከት ያለኝን አመለካከት ከነመፍትሄው ወደሚገልጸው ክፍል እንሻገር::
የሽግግሩ ወቅት የመጨረሻና ወሳኝ ስራ፤ የመጀመሪያው ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ
የሽግግሩ መንግሥት እነኝህን ሰፋፊ ስራዎች በብቃት መስራቱ ሳያንሰው ከምንም ነገር በላይ የብቃቱና የትክክለኛነቱ መለኪያ ስራውና በርግጥም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመሸጋገሩን እውነታ የሚያበስረው ወይንም የሚሰብረው የመጀመሪያው ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ፤ባገሪቱ ህዝብም ሆነ ባለማቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማድረጉና ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ ለተመራጩ ማስተላለፉ ላይ ነው:: ይህ ምርጫ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ካለው ፋይዳ አኳያ ምናልባትም ሁሌም ከሚቀርቡት መፍትሄዎች ወጣ ያለና ደፋር (bold) መፍትሄ የሚፈልግ ሊሆን ይችላል:: መታወቅ ያለበት ዋናው ቁም ነገር ይህ ምርጫ እውነትም ነጻና ፍትሃዊ መሆኑ ላይ ብቻ አይደለም:: እውነተኛ የህዝብ ፍላጎት የተገለጸበት መሆኑን ምንም አይነት ጥርጣሬ እንዳይኖረው ማድረጉ ላይ ነው:: ነገሩን አስቸጋሪ የሚያደርገውም ይኸው ነው:: ከላይ እንዳልነው ማህበረሰባችን ባጠቃላይ፤ በተለይም የፖለቲካ ድርጅቶች አካባቢ ያለው ስር የሰደደ ጥርጣሬና አለመተማመን እስካለ ድረስ ሂደቱ ትክክል እንኳን ቢሆን በምርጫ በተሸነፉ ኃይሎች አካባቢ “ያላግባብ ነው የተሸነፍኩት” የሚል ስሜት (perception) መፈጠሩ የሚቀር አይመስልም:: በተለይ ደግሞ በሽግግሩ ወቅት የመንግሥት ሥልጣንን የያዘው ኃይል ምርጫውን እስካካሄደው ድረስና ይኸው ኃይል ምርጫውን ካሸነፈ የምርጫውን ሂደት ስለዚህም የሚፈጠረውን አዲስ ሥርዓት በጥርጣሬ ውስጥ ይጥለዋል:: ይህ ደግሞ ዘላቂ አደጋ ነው የሚሆነው:: ስለዚህ ይህን ምርጫ ከምንም አይነት ጥርጣሬ ነጻ ላማድረግ ምን መደረግ አለበት የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ይሆናል::
ይህን ጥርጣሬ ፈጽሞ ለማስወገድ የሚቻለው ምርጫውን የሚያካሂደውን አካል በጊዜው ሥልጣን ላይ ካለው ኃይል ሙሉ ለሙሉ መለየት ነው:: ከዚያም በተጨማሪ ምርጫውን የሚያካሂደው ኃይል ይህን ምርጫ ለማካሄድ ብቃቱ ያለውና በሃገሪቱ ካሉት የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ ምንም ወገንተኛነት የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ይህንንው ለሁሉም የፖለቲካ ተቀናቃኞችና ነጻ ተመልካቾች ሁሉ ማሳመን ይጠበቅበታል:: የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብ ለሚከታተል ማንም ሰው ይህ ምን ያክል ከባድና ምስጋና የሌለው ሥራ እንደሆነ መገመት አያቅትም:: ታዲያ ይህንን ስራ ማን ቢሰራው ነው የተሻለ ተዓማኒነት የሚኖረው?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ መመልከትና ካሉት አማራጮች ውስጥ የበለጠ ከጥርጣሬ የጸዳ ነው የሚባለውን መምረጡ ተገቢነው:: ምርጫን ነጻና ፍትሃዊ ለማድረግ እስከዛሬ ከነበሩት ተመክሮዎች ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ:
ሀ) በመንግሥት በተቋቋመ ነጻ የምርጫ ኮሚሽን ዋና አስፈጻሚነት የሚካሄድ (በተጨማሪ የውጭ ታዛቢዎች ትዝብታቸውን የሚገልጹበት)
ለ) የሚቋቋመው የምርጫ ኮሚሽን በሃገሪቱ ከሚገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች በእኩል ተዋጽኦ ማቋቋምና ኮሚሽኑ በምልዓተ ድምጽ የሚያሳልፈው ውሳኔ ትክክለኛ ነው ብሎ መቀበል
የመጀመሪያው አካሄድ ከሞላ ጎደል አብዛኛው ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር ተግባራዊ ያደረገው አካሄድና በኢትዮጵያም የተተገበረው ነው:: ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሰረት ያልጣለባቸው ሀገሮች ውስጥ ሁሌም ይህ አካሄድ በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል የሚመርጠውና በብዙ ሃገሮች ተመክሮ እንደታየው በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል እራሱን በሚጠቅም አኳኋን ሂደቱን ያጨናገፈበት ሁኔታ ነው የሚታየው:: ለዚህ ምሳሌ ከኢትዮጵያችን ውጪ ሌላ አገር መጥቀስ አያስፈልገንም:: በጣም በቅርብ የሆነ የሌላ ሃገር ምሳሌ ካስፈለገ ከሰሞኑ በግብጽ የሆነውንና በአፍጋኒስታን ባለፈው ዓመት የሆነውን ማየት ብቻ ይበቃል:: ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል የምርጫ አስፈጻሚውን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር በማድረጉ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚታየው የምርጫ አስፈጻሚው ኃይል ተቋማዊ ደካማነት ነው:: እንዲህ አይነት ተቋም በሕግ የተሰጠውን ነጻነት ተግባራዊ ለማድረግ ሶስት ተያያዥ ሁኔታዎች ተሟልተው መገኘት አለባቸው:: በመጀመሪያ የሕግ ተቋማቱ በራሳቸው ነጻ የሆኑና የመንግሥት ስልጣን የያዘውን አካል ከሕግ በታች መሆኑን ማስረገጥ የሚችሉ መሆን አለበት:: ይህ በራሱ ትልቅ ስራ ነው:: ቀጥሎ የምርጫ አስፈጻሚው ተቋም ራሱ ለነጻነቱ ቀናኢ የሆነ፤ ከምንም ነገር በላይ ለተቋሙ ነጻነት የቆመ፤ ሥራውንም በተገቢው ለመስራት የሚችል ተቋማዊ ብቃት ያለው መሆን አለበት:: ሶስተኛው ደግሞ በተቋሙ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች፤ በተለይ በሃላፊነት ላይ ያሉት ሰዎች፤ ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ያላቸው ብቻ ሳይሆን ሙያው የሚጠይቀው ጠንካራ መንፈስና የሞራል ልዕልና ያላቸው ሰዎች መሆን አለባቸው:: እንዲህ አይነት ተቋም እንዲኖር ደግሞ በሽግግር ወቅት ሥልጣን ላይ ያለው ኃይል የምር ፍላጎቱ ቢኖረው እንኳን፤ እንደ ኢትዮጵያ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ለረጅም ጊዜ ከቆየ ማህበረሰብ፤ ለዚህ የሚመጥን ክህሎትና ድፍረቱ ያላቸው ባለሙያዎች በአጭር የሽግግር ወቅት ይገኛሉ ማለት አስቸጋሪ ነው:: በሽግግሩ ባለስልጣናት የሚሾሙት የምርጫ ኮሚሽን አባላት ገና በቂ የሥራ ልምድና ተቋማዊ ነጻነት ባላዳበሩበት ሁኔታ የውጭ ታዛቢዎች መኖራቸው ይህንን ሁኔታ ሊቀይረው አይችልም:: የምርጫ ታዛቢዎች ምርጫው እንከን የለሽ ነው ቢሉ እንኳን ይህንን ውጤት ተሸናፊ ፖለቲከኞች በጸጋ ይቀበሉታል ማለት አይደለም:: ስለሆነም ይህ አማራጭ ከምንም አይነት ጥርጣሬ ውጪ የሆነና ፍጹም ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ያካሂዳል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው:: በተለይ በስልጣን ላይ ያለው ኃይል ይህን ምርጫ እስካሸነፈ ድረስ ጥርጣሬው በፍጹም የሚጠፋ አይሆንም::
ሁለተኛው አማራጭ በተለይ በምርጫ 97 ወቅት በምርጫው የተሳተፉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች በአማራጭነት ያቀረቡት አካሄድ ነበር:: በምክንያትነት የቀረበው በምርጫ ቦርዱ የሚሳተፉት ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች እስከሆኑ ድረስ ሂደቱ ለማንም የፖለቲካ ኃይል በማያደላ መልኩ እንዲካሄድ ያደርጋሉ፤ ውጤቱንም ለመቀበል ያስችላቸዋል የሚል መከራከሪያ ነበር:: ይህ መከራከሪያ መሰረት ያደረገው ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ነጻና ፍትሃዊ ምርጫን ይፈልጋሉ፤ ከዚህም ተጠቃሚ ናቸው የሚለው እሳቤ ነው:: ይህ ግን ሁሌም እውነት ነው ማለት አይቻልም:: ለውሳኔ በሚቀርብላቸው ጉዳዮች ላይ በቀረቡት ማስረጃዎች ፋይዳ ሁሉም ባይስማሙስ? በድምጽ ብልጫ ይወስኑ ካልን በድምጽ የተሸነፉት የፖለቲካ ሃይሎች ተወካዮች ያሸነፉትን ሁሉ “ምርጫውን አጭበረበሩ” ብለው ላለመክሰስ ምን ይከለክላቸዋል? ይህንንስ የሚያደርጉ ከሆነ (ምንም እንኳን ክሳቸው ውኃ የማይቋጥር ቢሆን) ደጋፊዎቻቸውንና በምርጫው ውጤት ያልተደሰተውን ሁሉ በምርጫው ተዓማኒነት ላይ ጥርጣሬ እንዲኖር ስለዚህም ስሜት በማነሳሳት ወደ ግጭት እንዲሄድ አያደርጉም ወይ? ለዚህ ምንም ማረጋገጫ የለም:: የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሃይሎች ስብጥር በደንብ ለሚያውቅ ግን ይህ አይሆንም ብሎ ሊምል አይችልም:: ይህ ሞዴል ግን ከዚህም ያለፈ ያሰራር ችግር ሊገጥመው ይችላል:: የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው በመሰረታዊ መንገድ የማይተማመኑ ኃይሎች ባንድ ላይ ሆነው በየጊዜው በሚያደርጉት መጓተት የምርጫ አስፈጻሚው አካል በእርግጥም የተቀላጠፈና ብቃት ያለው ሥራ መስራት ይችላል ወይ የሚለውን ጥያቄ በአወንታዊነት መመለስ አይቻልም:: ይልቁንም ኮሚሽኑ ራሱ የግጭት አመንጪ ሊሆን የሚችልበት እድሉ የሰፋ ነው::
በነኝህና ተመሳሳይ ምክንያቶች እነኝህ ሁለቱም የተለመዱ ሞዴሎች በተለይ አሁን ባገራችን የፖለቲካ ሃይሎች ዘንድ ያለውን አለመተማመን ሊያከስም የሚችል ተቀባይነት ያለው ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሻግር ምርጫ ሊደረግ ይችላል የሚል እምነት የለኘም:: ስለዚህ ከነኝህ ከተለመዱ አካሄዶች ወጣ ያሉና ያልተለመዱ ደፋር አካሄዶችን መቃኘቱ ይጠቅማል:: ከዚህ አንጻር ሁለት አማራጮችን በጥንቃቄ መመልከቱ ይበጃል እነኝህም:
በሽግግሩ ወቅት በሥልጣን ላይ ያሉ ኃይሎች ወይንም በሽግግሩ መንግሥት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ኃይሎች በመጀመሪያው ምርጫ ላይ እንዳይሳተፉ ማድረግ
የመጀመሪያውን ምርጫ ምንም ኢትዮጵያዊ ኃይል ሳይኖርበት ምርጫ የማካሄድ ልምድ፤ ክህሎትና፤ ገለልተኛነት ያለው የውጭ ሀገር መንግሥት ወይንም መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም በሙሉ ሥልጣን እንዲያካሂደው መስማማት::
እነኝህን ሁለት ያልተለመዱ አማራጮች ከነ አወንታዊና አሉታዊ መከራከሪያቸው አቅርቤ በእኔ እምነት የተሻለውን በመምረጥ ይህንን ውይይት ላጠቃል::
የመጀመሪያው አማራጭ ጠንካራ ጎኖች ያሉትን ያክል ተግባራዊነቱን የሚያሰናክሉ ደካማ ጎኖች አሉት:: ከጠንካራ ጎኖቹ ውስጥ ምናልባት ዋናው በሽግግሩ ወቅት ስልጣን ላይ ያሉ ኃይሎች በመጀመሪያው ምርጫ ላይ ምንም ቀጥተኛ የሆነ የራስ ጥቅም ከሌላቸው (በምርጫው ስለማይሳተፉ) ምርጫውን ያለምንም ወገንተኛነት ለማካሄድ ይችላሉ የሚለው ነው:: በዚህ ሁኔታ የሽግግሩን ስልጣን የያዙ ሰዎችን ወይንም የፖለቲካ ቡድኖችን የሚገፋፋቸው ወይንም የሚያገኙት ጥቅም (incentive) የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲፈጠር የማየት ፍላጎት ነው ማለት ነው:: ይህ ከሆነ ደግሞ ምርጫውን ያለወገንተኛነት ከማካሄድም በላይ በሽግግሩ ወቅት መሰራት ያለባቸውን ከላይ የዘረዘርናቸውን ስራዎች በብቃትና በንጽህና የመስራት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ይቻላል:: ሌላው የዚህ አማራጭ በጎ ጎን በሽግግሩ ሂደት ማን ይሳተፍ የሚለውና የብዙ መጓተት ምክንያት የሆነውን የውስጥ ፍላጎትና ግፊት፤ ስለዚህም በፖለቲካ ኃይሎች መሀከል ያለውን ጥርጣሬና አለመተማመን፤ ይቀንሰዋል የሚል ነው:: ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት በሽግግሩ ላይ መሳተፍ ለዘላቂው ስልጣን መወጣጫ ይሆናል ብለው የሚያስቡና የሚጓጉ ኃይሎች በሽግግር መንግሥቱ መሳተፍ እንዲያውም ከዘላቂው ሥልጣን የሚያቅብ መሆኑን ሲያውቁ በሽግግሩ ወቅት ባለ ስልጣን የመሳተፍ ፍላጎታቸውን ያቆሽበዋል[3]፤ ይህ ደግሞ የሽግግሩ ሥራ ንጹህ የመሆኑን እድል በዚያው ልክ ያሰፋዋል:: ከዚህ ጋር የተያያዘው ሌላው ጥቅም ደግሞ ከሽግግሩ በኋላ በምርጫ በስልጣን ላይ የሚወጣው መንግሥት የሽግግሩን ሥልጣን ከያዘው የተለየ እንደሚሆን ከወዲሁ ከታወቀ፤ የሽግግሩን ስልጣን የያዙት ኃይሎች ወደፊት ከሚመጣ ተጠያቂነት ራሳቸውን ነጻ ለማድረግ ጠንክረው ይሰራሉ፤ ስለዚህም ሽግግሩን ተአማኒ ብቻ ሳይሆን በሽግግሩ ወቅት የሚፈጠሩት ተቋማት በእርግጥም ከመጪው መንግሥት ስራ አስፈጻሚ ኃይል ነጻ ሆነው እንዲሰሩ የማድረግ እድላቸው የሰፋ ይሆናል የሚል ነው::
ባንጻሩ ይህ አካሄድ የራሱ የሆኑ ችግሮች አሉበት:: የመጀመሪያው የወያኔን መውደቅ እውን ያደረጉት ሃይሎችና የወደቀበት መንገድ ሳይታወቅ በጥቅሉ ይህን አማራጭ ለውጡን ያመጡት ሃይሎች በሙሉ ልብ ይቀበሉታል ለማለት አይቻልም:: ከዚያም በላይ ግን ወያኔን በመጣል ሂደት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ጠንካራ ፍላጎትና ራዕይ አለን ብለው የታገሉ ኃይሎችን ሥርዓቱን ለመፍጠር በሚደረግ ምርጫ መሳተፍ አትችሉም የሚል ስምምነት ማስቀመጥ የነሱን መብት መጋፋት ብቻ ሳይሆን ሃገሪቱንም ጠንካራና የዴሞክራሲ ወገንተኛ የሆኑ መሪዎች ሊያሳጣት ይችላል:: ህዝቡንም የሚፈልገውን እንዳይመርጥ ማእቀብ ያደርግበታል:: ከዚህ በተጨማሪ ግን በሽግግሩ ወቅት የመንግሥት ስልጣን የያዙ ኃይሎች እራሳቸው እንኳን በምርጫው ባይወዳደሩ ከሚወዳደሩት መሀከል በአንድ ምክንያት ወይንም በሌላ ለሚመርጡት ኃይል አያደሉም ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር ይከብዳል:: የምርጫ ኮሚሽኑ ጠንካራና በእውነትም ነጻ እስካልሆነ ድረስ በጊዜው በስልጣን ላይ ያለው ኃይል ስለማይወዳደር ብቻ ምርጫው ተዓማኒ ይሆናል ማለት አይቻልም::[4] ስለዚህ ይህ አማራጭ ቀደም ብለው ከተቀመጡትና በተለምዶ ከሚሰራባቸው ሞዴሎች የተሻለ ተዓማኒ የመሆን እድል ያለው ቢሆንም በውስጡ ያዘላቸው ድክመቶች በቀላሉ የሚታለፉ አይደሉም:: ተግባራዊነቱም ለውጡን ባመጡት ኃይሎች መልካም ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሰረተ ይሆናል::
የመጨረሻውና በእኔ እይታ ከሁሉም የተሻለ አማራጭ ነው ብዬ የማምነው የመጀመሪያውን ምናልባትም ሁለተኛውን ጨምሮ (ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እስከሚደረግ ድረስ) ምርጫውን ከሁሉም በሃገሪቱ ካሉ የፖለቲካ ኃይሎች ፍጹም ገለልተኛ በሆነ ሶስተኛ ሀገር ወይንም የሶስተኛ ሀገር ነጻ ተቋም እንዲደረግ ማድረግ ነው:: ይህ ሶስተኛ ሀገር በተቻለ መጠን እንደሀገር የተለየ ጥቅም (ጂኦ ፖለቲካዊ) ያለው መሆን የለበትም:: በገለልተኛነቱና በለዘብተኛነቱ የታወቀ፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ወገንተኛ መሆኑ ባለማቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ከኢትዮጵያ ጋር ባለው ግንኙነት ያስመሰከረ፤ በሀገሪቱ ያሉትን የፖለቲካ ኃይሎች የማይጎረብጥ ሀገር መሆን ይኖርበታል[5]:: ይህ አማራጭ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በጥሩ ምሶሶ ላይ ለማቆም ብዙ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን ምናልባት ሊያከራክር የሚችሉ አንድ ሁለት ድክመቶች ይኖሩታል:: ከድክመቶቹ እንጀምር:: እንዲህ አይነቱን አማራጭ የሚቃወሙ ሰዎች ሊያነሱ የሚችሉት አንድ መከራከሪያ እንዲህ አይነቱን ወሳኝ ሀገራዊ ስራ ለውጭ ኃይሎች መስጠት የሀገሪቱን ሉአላዊነት የሚነካ ምናልባትም የሀገሪቱን ክብር የሚያጎድፍ ሊሆን ይችላል የሚል መከራከሪያ ነው:: ይህ ግን በእርግጥም ክብረ ነክ ነው ቢባል እንኳን (እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለመፈጠሩ በሀገሪቱ ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው ውርደት ከዚህ በጣም የከፋ ነው) ከሚሰጠው ጥቅም ጋር አብሮ ቢመዘን ያን ያክል ጠንካራ መከራከሪያ ነው ለማለት ያስቸግራል:: ሌላውና ምናልባትም የበለጠ ሊታሰብበት የሚገባው (ከዚህ በፊትም እኛ እስከምናውቀው ድረስ በተግባር ታይቶ ስለማይታወቅ) እንዲህ አይነቱን ሀላፊነት ለመውሰድ የሚፈልግ ገለልተኛ ሀገር ወይንም ተቋም ይኖራል ወይ? ከተገኘስ ወጪውን ማን ይችለዋል? የሚለው ነው:: ይህ ግን በሀገሪቱ ያሉት ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች (በሽግግር መንግሥት ስልጣን ላይ ያለው ኃይል ተጨምሮ) እስከተስማሙበት ድረስ እንዲህ አይነት የዴሞክራሲ ወገንተኛ መንግሥት ማግኘትና ይህም መንግሥት ወጪውን በእርዳታ መልክ ለመሸፈን ያስቸግረዋል ለማለት አይቻልም:: ይህን ውይይት ከዳር ለማድረስ ግን እንዲህ አይነት አካል ይገኛል በሚል እሳቤ የአማራጩን ጠንካራ ጎኖች እንመልከት::
በመጀመሪያ ብዙም ጥያቄ ውስጥ የማይገባው የእንዲህ አይነት ሃይል ገለልተኛነት ነው:: በሃገሪቱ ካሉት ኃይሎች ውስጥ አንዱ ወይንም ሌላው ቢያሸንፍ የሚያገኘው የተለየ ጥቅም ወይንም ጉዳት አይኖርም:: ይልቁንም የሃገሩ ወይንም የተቋሙ ታዋቂነትና ክህሎት (reputation) የሚመዘነው ምርጫውን በብቃትና በፍጹም ገለልተኛነት ማድረጉ ላይ ስለሆነ ለዚህ ጉዳይ አጽንኦት ሰጥቶ ይሰራል ተብሎ ይታሰባል:: ይህን ሃላፊነት የወሰደው ሃገር ይህ ስራ በብቃት መሰራቱን ማረጋገጥ ስላለበት (በምሳሌነትም በሌሎች ሃገሮች በአትኩሮት ስለሚታይ) በስራው ሰፊ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ለስራው ያሰማራል ተብሎ ይጠበቃል:: በዚህ ሂደት ላይ እንዲህ አይነቱ ኃይል ወደፊት የሚካሄዱትን ምርጫዎች የሚመራውን ቋሚ የምርጫ ተቋም የመገንባትም ሃላፊነት አብሮ ከወሰደ ለወደፊቱም ጠንካራና ነጻ ተቋም የመገንባቱን ስራ በጣም ያግዘዋል:: በእንዲህ አይነት ፍጹም ገለልተኛ ሃይል የተካሄደ ምርጫ ተአማኒነት በሃገር ውስጥም ሆነ ባለማቀፍ ደረጃ ጠንካራ ነው የሚሆነው:: እንዲህ አይነት ጠንካራና ተዓማኒ ኃይል ይህን አስቸጋሪ ሥራ ከሽግግር መንግስቱ ጫንቃ ላይ ካነሳለት የሽግግር መንግስቱ ከላይ የጠቀስናቸውን እጅግ አስፈላጊና አድካሚ ስራዎች ላይ ሙሉ ኃይሉን ስለሚያሳርፍ እነኝህን የሽግግር ጊዜ ስራዎች በተሻለ ብቃት የመወጣት እድሉም ከፍተኛ ይሆናል:: የሽግግር መንግሥቱም ለዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት ያለውን ቁርጠኛነት በዚህ ፍላጎቱ ብቻ በሀገሪቱ ላሉት የፖለቲካ ኃይሎችም ሆነ ለመላው ማህበረሰብ ግልጽ ያደርጋል:: ይህ ደግሞ በማህበረሰቡ ስነልቦና ላይ የሚኖረው አወንታዊ እንድምታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም::
የዚህ አማራጭ ጥቅም ግን ከዚህም በላይ አሁን እየተካሄደ ያለውንም የዴሞክራሲ ትግል በማገዝ ላይም ነው:: ይህንን ውይይት ስጀምር በተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች መሀከል ይህንን ሥርዓት ለማስወገድ ፍላጎት እያለም ለምን መተባበር አልተቻለም? የሚለውን ጥያቄ በጥቅሉ የመለስኩት በተለይ ሽግግሩን በሚመለከት ባለው የመተማመን እጦት እንደሆነ ጠቁሜ ነበር:: ይህንን አማራጭ በሃገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ቢወያዩበትና ቢቀበሉት፤ በውስጣቸው ያለውን ከፍተኛ የጥርጣሬ ዳመና ምን ያክል ሊገፈው እንደሚችል ለመገመት አያስቸግርም:: ከዚህም በላይ ግን የፖለቲካ ሥልጣን በህዝብ ፍላጎትና ውክልና ሳይሆን ባቋራጭ በሚደረግ መደራደር ይገኛል ብለው የሚያምኑ የፖለቲካ ደካሞችን ከመድረኩ በማጥራት በኩልም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ:: በተለይም ደግሞ ወያኔ በጉልበት እንጂ በፍላጎቱ ስልጣን አይለቅም ብለው ነፍጥ አንስተው የሚታገሉ ኃይሎች እንዲህ አይነቱን አማራጭ በግልጽ ቢቀበሉት በትግሉ ሂደት እነሱ ስልጣን ከያዙ አይለቁም በሚል ፍርሃት በጥርጣሬ የሚያዩዋቸውንና በዚህም ምክንያት ትግላቸውን ከመደገፍ የሚታቀቡ ኃይሎችን ትግሉን እንዲደግፉ ማበረታታት ይችላል:: በሀገር ውስጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ ከወያኔ ጋር በሚደረግ የምርጫ ሂደት ወያኔን ማባረር እንደማይቻል እያወቁም በሂደቱ የሚሳተፉ ሀይሎችም ከወያኔ የውሸት ምርጫ የተለየ ሰላማዊ አማራጭ በማቅረብ ማህበረሰቡን ለትግል ለማሰባሰብ፤ በወያኔ ላይም ከፍተኛ የሞራል ድል እንዲያገኙ ይረዳቸዋል:: ከሁሉም በላይ ግን ሰላማዊም ሆነ የአመጽ ትግል ለማድረግ የሚያስችል ከፍተኛ የሆነ የህዝብ የትግል መንፈስ ለማዳበር ይጠቅማል::
ማጠቃለያ: ወያኔን ለመጣል ጉልበት ያስፈልጋል የሚሉ ኃይሎች ይህን ሀሳብ ለምን እንዲደግፉት ይጠበቃል?
በዛሬ ጊዜ የሚደረግ፤ ከጉልበት ጋር የተያያዘ ትግል እንደቀድሞው የሚምል የሚገዘትበትና ለትክክለኛነቱ ምንም ጥርጣሬ የሌለው የኢኮኖሚ ወይንም ማህበራዊ ርዕዮተ አለም ይዞ የሚደረግ ትግል አይደለም:: ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ወደዚያ የተገፉት ሌላ አማራጭ በማጣት ነው:: ሁሉም የሚስማሙበት አንድ ዋና አላማ ቢኖር (ቢያንስ በፕሮግራማቸው ላይ ያስቀመጡት) ከምንም ነገር በላይ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተመስርቶ ማየትን ነው:: ከዚህ አላማ ጋር የተያያዘውና የዚህ ትግል ስኬት አንዱ ወሳኝ ጉዳይ በማህበረሰባችን ዘንድ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደትን በሚመለከት የጠራ አመለካከት እንዲያዝ፤ በትግሉ ሂደት ደግሞ በሚፈጠረው ሥርዓት ዙሪያ ሰፋ ያለ ማህበራዊ መሰባሰብንና ፍላጎትን መፍጠር ነው:: ይህን ለማድርግ ለእንዲህ አይነቱ ሰፊ ማህበራዊ መሰባሰብ እንቅፋት ይሆናሉ ተብሎ የሚታሰቡ እክሎች እየተጠኑ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ፤ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን በነዚህ መፍትሄዎች ዙሪያ ማወያየትና ይህን አመለካከት እንዲጋሩ በዚህም የትግሉ አካል እንዲሆኑ ማድረግ የታሰበው ውጤት ላይ ለመድረስ እጅግ አስፈላጊ ነው:: በዚህ የውይይት ሃሳብ ላይ የቀረበውን የመፍትሄ ሃሳብ በፖለቲካ ኃይሎችና በምሁራን ዘንድ መሸጥ ከተቻለ ትግሉን በማሳጠርም ሆነ በሚፈጠረው ሥርዓት ላይ የጠራ አመለካከት እንዲሁም ሰፋ ያለ የማህበረሰብ ድጋፍ (constituency for democracy) በመፍጠር ብሎም ሥርዓቱን እውን ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ ያሳካል የሚል እምነት አለኝ::
[1] ለዚህ ታሪካዊ ማስረጃ ካስፈለገ በአሁኑ ጊዜ በኢሕአዴግ ተቀርጾ የጸደቀውን ሕገ መንግስት በብዙ መልኩ የሚመስለውን በሶቭየት ሕብረት በእስታሊን አጋፋሪነት የጸደቀውን የ1936 ሕገ መንግሥት መመልከት ብቻ ይበቃል:: ይህ ሕገ መንግስት ብንመለከት በአንቀጽ 125 ላይ ያለምንም ሳንሱር የመጻፍ፤ የመናገር፤ የመሰብሰብ፤ የመደራጀት፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶችን ያለምንም ገደብ ይፈቅዳል:: በአንቀጽ 134 ደግሞ ለሁሉም ላቅመ አዳም ለደረሰ ዜጋ በሚስጥር ድምጽ አሰጣጥ መሪዎቹን የመምረጥ መብት አልፎም በአንቀጽ 17 ደግሞ ማንኛውም የፌደሬሽኑ አካል የሆነ ክልል እራሱን የማስተዳደርና በሕዝብ ውሳኔ እስከመገንጠልና የራስን ሀገር እስከማቋቋም የደረሰ መብት ይሰጣል:: በተግባር የሆነውን ግን ሁላችንም የምናውቀው ነው::
[2] እንደሚታወቀው አንድ ሰው የመረጠውን አካባቢ ህዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ፤ ጥሩ ሕግ አውጪ ሊሆን ይችላል:: ይህ ማለት ግን ጥሩ ሀገራዊ መሪ ይሆናል ማለት አይደለም::
[3] ቆሸበ ማለት በእንግሊዘኛው supress the appetite የሚለውን ትርጉም የያዘ ነው::
[4] ባለፈው አመት በአፍጋኒስታን የታየው የምርጫ ቀውስ የቀድሞው ፕሬዜዳንት ካርዛይ በምርጫው ባይወዳደሩም እሳቸው የሚፈልጉትን ሰው ለማስመረጥ የምርጫ ኮሚሽኑን በመጠምዘዝ ኮሮጆ አስገልብጠዋል በሚል ነው:: በዚህም ምክንያት የምርጫ ኮሚሽኑ ሃላፊ ከስልጣናቸው ተነስተዋል::
[5] ከዚህ አንጻር የእስካንዲኔቪያ ሃገሮች ተመራጭ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ::